>
5:13 pm - Thursday April 19, 5523

አሜሪካውያን/ምዕራባውያኑ ‘ኢትዮጵያን አንድነት እና የኢትዮጵያኒዝምን' እንቅስቃሴ ስለምን ይፈሩታል?! (በዲ/ን ተረፈ ወርቁ)

አሜሪካውያን/ምዕራባውያኑ ‘ኢትዮጵያን አንድነት እና የኢትዮጵያኒዝምን’ እንቅስቃሴ ስለምን ይፈሩታል?!

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ


‘‘እንደ ቅድመ 21ኛው ክፍለ ዘመን ትግሎች ሁሉ ዛሬም በ21ኛው ክፍለ ዘመንም አፍሪካን ከዘረኝነትና ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሙሉ በሙሉ ነፃ ለማድረግ፤ ኢትዮጵያኒዝምን (የኢትዮጵኒዝምን ፍልስፍና/እንቅስቃሴ) በግድ መሠረት ማድረግ አለብን፤’’

(የቀድሞ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት፣ ታቦ እምቤኪ) 

እንደ መንደርደሪያ

የአፍሪቃን ገዢዎች የተካቸው አሜሪካ በቀዝቃዛ ጦርነትና በዐረብ-እስራኤል ግጭት ሰበብ ከ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ ጀምሮ በአፍሪቃ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ ላይ የነበራት መመሪያ ከቅኝ ገዢዎቹ ከአውሮጳያንን መርሕ ብዙም የማይለይ እንደነበር ዶ/ር ኪሲንጀር በ1960ዎቹ ለአሜሪካ መንግሥት ያቀረበው ምክረ ሐሳብ/ዘገባ የተወሰነ ቢሆን ጠቃሚ ፍንጭ ይሰጣል፡፡ ይህ ከዚህ በታች ተቀንጭቦ የቀረበው የታሪክ ሰነድ ዛሬ ሀገራችን ከአሜሪካና ከምዕራባውያን መንግሥታት እየደረሰባት ያለውን ‘ጫና እና እጅ የመጠምዘዝ’ ሙከራዎች ዛሬ የተጀመሩ ሳይሆን የትናንትና ቅጥያዎች መሆናቸውን የሚያስገነዝበን ነው፡፡ 

ዶ/ር ኪሲንጀር ለሀገሩ ለአሜሪካ መንግሥት- ‘‘ቀይ ባሕር ለጦር ስልት ያለው ጥቅም’’ በማለት ለሀገሩ ለአሜሪካ መንግሥት ያቀረበው ምክረ-ሐሳብ ነው፡፡ ከዚሁ ሰነድ ላይ በጥቂቱ ቀንጭብን ለማየት እንሞከር እስቲ፡፡

የኢትዮጵያ ሰላም ካገኘች ሕዝቧ ሠራተኛና ታታሪ ስለሆነ፣ በዓለም ብድር ዕዳም እንደሌሎቹ የሦስተኛ ዓለም አገሮች ተዘፍቃ የማታውቅና የኮራች አገር በመሆኗ አንድ ቀን ራሷን የቻለች አገር ትሆናለች፡፡ ዕድል አግኝታ በዘመናዊ ሥልጣኔ ብትገፋ ደግሞ የምትቻል አገር አይደለችም፡፡ ስለዚህ ከንጉሥ ኃይለ ሥላሴ በኋላ ኢትዮጵያን የሚመራ መንግሥት ሰላም እንዳያገኝና፣ አገሪቷም እንደ ዐረብ አገሮች ተከፋፍላና ተነጣጥላ ካልተበታተነች በስተቀር ለወደፊቱ በቀይ ባሕር ላይ አሜሪካ የምትጫወተው ሚና እንዳይመነምን እንዳያድጉ ማደናቀፍ ከሚገባቸው በቀይ ባሕር አዋሳኝ ታዳጊ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ መሆን አለባት፡፡

የቀይ ባሕር ወተት’’ የሆነውን የዐረብን ነዳጅ በነጻ አለቀረጥ ማለብ የምንችለው መንግሥታችን ኢትዮጵያን ከጎረቤቷ ከሱማሌ ጋር ብቻ ሳይሆን ክፍለ ሀገሮቿን ራሳቸውን በሰሜንና በደቡብ ከፋፍሎ፣ የደከመውን ወገን በመርዳት ያላመፀውን ጎሳ በመነሳሳት ከዳር ድንበሯ ዘላለም ሁከትና ጦርነት እንዳይለያት በማድረግ ፀረ-መንግሥት ተዋጊዎችን በሲ.አይ.ኤ በማደራጀት በአገሪቷ ሰላም በመንሳት ብቻ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥንካራና ብርቱ ቢሆንም ቅሉ፣ በሥልጣን ፍላጎቱ ደካማ ጎን አለው፡፡ አንዱ በሌላው ላይ መንገሥ ዋና ምኞቱ ነው፡፡ በታሪካቸው ዲሞክራሲያዊ መንግሥት መስርተው አያውቁም፡፡ ከጥንት ጀምሮ ቢሆን አንዱ ንጉሥ ሌላውን በመግደል ሥልጣን መቀማትና ማመፅ ባህላቸው፣ ልማዳቸውና ታሪካቸውም ነውና፡፡ እኛ ያሳደግነው ውሻም ቢሆን ሊነክሰን ቢሞክር የመንግሥት ግልበጣ በማካሄድ፣ ላንዲት ዘመን እንኳ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ሰላም ሳይኖር፣ ሰሜናዊና ደቡባዊ፣ እንዲሁም ኤርትራ፣ ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ እየተባባሉ እርስ በርሳቸው ሳይስማሙ ለረጅም ጊዜ ከኖሩ፣ ቀይ ባሕር ለአሜሪካ መንግሥት ጠቃሚ በር ሆኖ ይኖራል፡፡

ኪሲንጀር ምክረ-ሐሳቡን በመቀጠል- ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉርና በተለይም ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ ካላት ወሳኝ የሆነ ጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ፣ ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትእምርት፣ የፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ እምብርት ሀገር ከመሆኗ የታሪክ እውነታ ጋር በተያያዘ- ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናን በማስተባበርና አህጉራዊ ትስስርን ለመፍጠር የምታደርገው እንቅስቃሴ፣ ለአሜሪካ አደጋ ሊሆን ስለሚችል በጥንቃቄ መቃኘት የሚገባው መሆኑን እንደሚከተለው ይገልጻል፡፡    

ሱማሌና ኢትዮጵያ አንድ ቀን ከተባበሩ፣ የአሜሪካ ታላቅነትና ብልፅግና በቀይ ባሕርና በዓለም ላይ አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያና ሱማሌ ማዶ ካሉት የዐረብ አገራት ጋር በቀይ ባሕር ጥቅም ላይ ተስማምተው ቢዋዋሉ፣ የአሜሪካና የአውሮፓ ሕዝብ ‘ቡፋሎ’ ፍለጋ ወደ ጫካ መሄድ ካልሆነ በስተቀር፣ ጥበባችንን እንኳን ሽጠንና ለውጠን መኖር እንችልም፡፡ ሊቃውንቶቻችን ወደ አፍሪቃ ሲፈልሱ ከሩቅ ማየትና መገንዘብ የእኛ ተራ እንደሚሆን እንርሳ፡፡ በማለት ምክረ-ሐሳቡን አቅርቧል፡፡

ለመሆኑ የሆነስ ሆነና አሜሪካውያኑና ምዕራባውያኑ ለቅኝ ግዛት መስፋፋትና ሀብት ቅርምት ሥጋት ይሆንብናል ያሉት የኢትዮጵያ አንድነት፣ የኢትዮጵያኒዝም እንቅስቃሴ በአፍሪካና በዓለም ታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ምን ምልክ ነበረው የሚለውን በአጭሩ ለማሳየት ልሞክር፡፡

ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያኒዝም እንቅስቃሴ

‘‘የፓን-አፍሪካኒዝም አባት’’ ተብሎ የሚጠራው አፍሪቃ አሜሪካዊው ዊልያም ዱ-ቦይስ እ.ኤ.አ. በ1913 የኢትዮጵያ ኮኮብ (The Star of Ethiopia) የሚል ተውኔት ደርሶ ለሕዝብ እንዲታይ አድርጎ ነበር፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያን “የሰውልጆች ሁሉ እናት (መፈጠሪያ)” ብሎ ይጠራት እና አስተምሯል፡፡ የዓለም ስልጣኔ ሁሉ ከናይል ሸለቆ (ግብጽና ኢትዮጵያ) እንደተጀመረም ያቀነቅን የነበረ አፍሪካዊ ምሁር ነበር፡፡

ኢትዮጵያኒዝም- እንደ ጽንሰ ሐሳብ ሲተነተን በመላ ዓለም የሚኖሩ አፍሪካዊያን/ጥቁር ሕዝቦች ንቅናቄና ጥምረት መገለጫ ነው፡፡ የጥቁሮች አንድነት የፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የማኅበራዊ ዕድገት መሠረት ነው በሚል እምነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ኢትዮጵያኒዚም መንፈሳዊ ነፃነት፣ በራስ መተማመን፣ ለራስ ክብር መስጠት፣ ራስን መቻል፣ የዉጭ ጭቆናን መቋቋም፣ ዓለማዊ ሕይወት በመንፈሳዊ ሕይወት ማነጽን፣ የተጨቆኑ ሰዎች በጋራ እንዲተባበሩ፣ የሰብአዊ መረዳዳትና እርስ በርስ መተሳሰብን ያጨቀ ሰፊ አስተምሮት ነው፡፡

የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና የአፍሪካዊያን/የጥቁር ሕዝቦችን ታሪክ፣ ባህል፣ መንፈሳዊና ሳይንሳዊ ግኝቶችን ለማጣመር ያለመ በመሆኑ በፀረ ቅኝ አገዛዝ፣ በፀረ ባርነትና በፀረ ዘረኝነት ላይ የተደረጉ ተጋድሎዎችም የዚሁ አስተሳሰብ ፍሬ ተደርገው ይታያሉ፡፡

ኢትዮጵያኒዝም ከአፍሪካውያን፣ ከአፍሪካ አሜሪካውያንና ከመላው የጥቁር ሕዝቦች የነጻትና የመብት ትግል እንስቃሴ ታሪክ ጋር ጥብቅ የሆነ ቁርኝት እንዳለው የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ፡፡ የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና የተፈጠረው፤ በሃይማኖትና በፖለቲካ የጭቆና ቀንበር ውስጥ ወድቀው፤ እንዴት ነፃነታቸውን ለመቀዳጀት እንደሚችሉ ሲያስቡና ሲያሰላስሉ በነበሩ፤ ከአፍሪካ በባርነት የተጋዙ ጥቁር/አፍሪካ-አሜሪካውያን ነው፡፡

የፍልስፍናው ንድፈ-ሐሳብ፤ መንፈሳዊነትን ከሰው ልጆች ነፃነት ጋር ያጣመረ፣ ያቀናጀና ያስተሳሰረ ነው፡፡ ኢትዮጵያኒዝም የተጀመረው በ16ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ገደማ አካባቢ ቢሆንም፤ ከ1776 የአሜሪካ የነፃነት ትግልን ተከትሎ እያየለና እየተስፋፋ የመጣ ነው፡፡

በ19ኛው ክፍለ ዘመን በተለይም ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ዜናው ከተሰማው የዓድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያኒዝም በዓለም ዙሪያ እየተስፋፋ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ተጠናክሮ ዘልቆአል፡፡ በመንፈሳዊ ዓለም የተሰማሩ በአሜሪካና በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ቄሶችም ፍልስፍናው እንዲስፋፋ ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ የነፃነት አፍቃሪዎችም፤ ‘‘አፍሪካ ለአፍሪካውያን ትገባለች!’’ የሚለውን የፓን-አፍሪካን መሪ መፈክር ያስተጋቡት የኢትዮጵያኒዝም የነጻነት መንፈስ በፈጠረባቸው ወኔና ቅንአት ነው፡፡

ይህ ኢትዮጵያኒዚም የፈጠረው የነጻነት መንፈስና መነቃቃትም አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ቀንበር አላቆ ልጆችዋ በነጻነትና በእድገት ጎዳና እንዲገስግሱ የሚያልመውን የፓን-አፍሪካኒዝምን ፍልስፍና ወለደ፡፡ የታሪክ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ የጋናው ፕሬዚዳንት ኩዋሜ ንኩሩማህ ከአፍሪካ መሪዎች መካከል ግንባር ቀደም ፓን አፍሪካኒስት የነበሩ ሲሆን፣ ማርከስ ጋርቬይ፣ ጥቁር አሜሪካዊው ማልኮም ኤክስ፣ እንዲሁም ደግሞ ዊሊያም ኤድዋርድ ቡርግሃርድ ዱ ቦይስ ከአፍሪካ ውጭ የሚኖሩ የንቅናቄው አመንጪዎች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡

የፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ አቀንቃኞቹ አንዲት አፍሪካን የመፍጠር ዓላማ ነበራቸው፡፡ በመላው ዓለም በነጮችና በጥቁሮች መካከል ያለውን ልዩነት ለማስተካከል፣ ፍትሐዊ ያልሆነው የሀብት ክፍፍል እንዲቀርና አፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ ተወዳዳሪነቷ አድጎ በቂ ተፅዕኖ ለማድረግ የምትችልበት ዕድል እንዲፈጠር ያለመ ዓላማ ነበራቸው፡፡

የኢትዮጵያኒዚምና የፓን-አፍሪካን ቅደመ ተከተልና ትሥሥርን ለአሁኑና ለመጪው ትውልዶች ለማስተላለፍ ሲባልም ዛሬ በአዲስ አበባ፣ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቅጥር ግቢ ውስጥ የታላቁ ፓን አፍሪካኒስት ዶክትር ኩዋሜ ንክሩማህ ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡ በንኩርማ ሐውልት ስርም፤ “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፤ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ተቀርጾ ይገኛል፡፡ ይህ መንፈሳዊ ጥቅስም ለአፍሪካና ለአፍሪካ አሜሪካውያን ኢትዮጵያዊነት- የመንፈሳዊ ነፃነት፣ የራስን ፖለቲካዊናና ኢኮኖሚያዊ ተፈጥሮአዊ አቅምን የሚገልጽ መንፈሳዊ እውነት አድርገው ተጠቅመውበታልም፡፡

በመሠረቱ የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ብዙ መሥዋዕትነት ተከፍሎበት የተገነባ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ እ.አ.አ. በ1896 በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ አመራር ኢትዮጵያ በዐድዋ ጦርነት በተስፋፊ ኢጣሊያ ላይ የተቀዳጀችው ድል በአፍሪካና በደቡብ አሜሪካ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ይማቅቁ ለነበሩ ሕዝቦች በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ጥላ ሥር ሆነው የማይቀረውን የነፃነት ብርሃናቸውን ያዩበት ሕያው ተስፋቸው ነበር፡፡

ይህንን ድል ተከትሎም የደቡቡ አፍሪካ ዘረኛ ነጮች በ1906 የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና እንደ አደገኛ የኢትዮጵያ ፕሮፖጋንዳ አድርገው ስለቆጠሩት፣ ሕግ አውጥተውና ፍልስፍናውን አንቋሽሸው ‘ኢትዮጵያኒስቶችን’ ማሰርና አልፎ አልፎም መግደል ጀመሩ፡፡ ቀጥለውም የኢትዮጵያኒዝምን እንቅስቃሴ እንደ አደጋና እንደ ሽብር አሰፋፊ ቆጥረው የወታደር ኃይላቸውን አጠናከሩ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ርምጃቸው፤ በ1906 የዙሉ እንቅስቃሴን ቀጥሎም የባንባታና በኒያሳላንድና በሌሎችም አካባቢዎች የፀረ- አፓርታይድን ተቃውሞን ፈጽሞ ሊገታው አልቻለም፡፡

ኢትዮጵያኒዝም በዓለም መድረክ ያስገኛቸው ለውጦች ብዙ ናቸው፡፡ በደቡብ አፍሪካ፤ የአፍሪካን ናሽናል ኮንግሬስ ያቋቋሙት በኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና ጥልቅ እውቀት የገበዩ የደቡብ አፍሪካ ቄሶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያው የአፍሪካ ናሽናል ኮንግሬስ ፕሬዝዳንት ጆን ላንጋቢሌሌ ዱቤ፤ በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍናቸውና አቁዋማቸው ታስረው ከተፈቱ በሁዋላ የአፍሪካ ናሽናል ኮንግሬስ ፕሬዝዳንት ሁነዋል፡፡  የስማቸው ቅፅል ስምም፤ ‘‘ግልፅ ኢትዮጵያዊ’’ ማለትም ሁልጊዜ ለአደጋ የተጋለጠ ይባል ነበር፡፡

ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ፤ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ፤ እንደ ናይጀሪያ እና ጋና፤ በፈረንሳይ ስር የነበሩ እንደ ካሜሮን ያሉ ሀገሮች የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና በመጠቀም ሃይማኖትን ከፖለቲካ ጋር አገናኝተው ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ኢትዮጵያኒዝም ሁነኛ ስልት አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡

በኬንያ እነ ፕሬዝዳንት ጆሞ ኬኒያታ ሳይቀሩ ‘‘አፍሪካ ለአፍሪካዊያን’’ የሚለውን የፓን አፍሪካ ፅንሰ ሐሳብ ተከትለው እሰከ 1960 ዓ.ም. ድረስ ተጠቅመውበታል፡፡ የራስ ተፈሪያኒዝም ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴም በካሪቢያን ሀገሮች የመነጨውና የተስፋፋውም ከዚሁ ከኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ጋር ተያይዞ ነው፡፡

ባጠቃላይ ሲታይ፤ ኢትዮጵያኒዝም በተለያየ መንገድ ቢገለፅምና የተለያዩ ሰዎችና ሀገሮች ቢጠቀሙበትም ዓላማው አፍሪካንና የጥቁር ዘርን ሙሉ በሙሉ ከቅኝ ግዛትና ከዘረኝነት ለማውጣት እንደ ችቦ መብራት ሆኖ እንዳገለገለና ግልጋሎቱን እንደቀጠለ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የዛሬውን ጽሑፌን የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት የነበሩት ታቦ እምቤኪ፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የክብር ዶክትሬት ባበረከተላቸው ጊዜ የኢትዮጵያኒዝም መርሕ/ፍልስፍና መሠረት አድርገው ለእኛ ኢትዮጵያና ለአፍሪካውያን ካስተላለፉት ንግግራቸው በአጭሩ በመጥቀስ ላጠቃልል፡፡

‘‘እንደ ቅድመ 21ኛው ክፍለ ዘመን ትግሎች ሁሉ ዛሬም በ21ኛው ክፍለ ዘመንም አፍሪካን ከዘረኝነትና ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሙሉ በሙሉ ነፃ ለማድረግ፤ ኢትዮጵያኒዝምን (የኢትዮጵኒዝምን ፍልስፍና/እንቅስቃሴ) በግድ መሠረት ማድረግ አለብን፤’’

ሰላም ለኢትዮጵያ!

Filed in: Amharic