>

የአማራ ህልውናዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ መብቱ መከበር የሚችለው.... (ወንድወሰን ተክሉ)

የአማራ ህልውናዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ መብቱ መከበር የሚችለው በራሱ አማራዊ ኋይል እንጂ በመከላከያና በሌላ አካል አይደለም!!!
 ወንድወሰን ተክሉ

♦  የአማራን ብሄርተኝነትና አማራዊ አደረጃጀትን በአንድ አማራዊ ሕዝባዊ ኋይል/ፋኖ የተደገፈ ካላደረግን በአማራ ሕዝብ ህልውና መክሰምና ለዘላለማዊ ባርነት የተስማማን መሆን እንሆናለን!!!
በዛሬይቱ ኢትዮጲያ ጎሳ ተኮር ፌዴራላዊ አወቃቀርን መሰረት ባደረገ ሕገ መንግስት መገዛት ከጀመረችበት 1991 ጊዜ ጀምሮ ሁለት ክልሎች ማለትም ትግራይና ኦሮሚያ  ወደ ሉዓላዊ ሀገርነት ደረጃ በሚያደርሳቸው መጠን እጅግ የተደራጀ ኋይል መገንባት የቻሉበትን ሁኔታና በአንጻሩም በሁለቱም ክልል ፖለቲካዊ አደረጃጀት ፍልስፍና ውስጥ በጠላትነት የተፈረጀው አማራ እጅግ በሚደንቅ ሁኔታ ምንም ሳይደራጅ ባዶ እጁን አፉን ከፍቶ የተቀመጠበትን ሀገር እናያለን።
ብሔር ወይም ቌንቌ ተኮር አደረጃጀትን በ1991 ላይ መንግስታዊ ሕግ ያደረጉት ህወሃትና ኦነግ ቀደም ብሎ ለሰላሳ ዓመታት የመደራጃ መሰረታቸውን/አስኴሉን/  በጸረ አማራ፣ጸረ ኦርቶዶክስና ጸረ ኢትዮጲያ ላይ አድርገው በመደራጀት የመጨረሻ ግባቸውንም ኢትዮጲያን ከፋፍሎና አዳክሞ በመገነጣጠል ታላቂቷን ትግራይ፣ታላቂቷን ኦሮሚያ መንግስት ለመመስረት ሲታገሉ አማራው ይህንን በማንነቱ ላይ አነጣጥሮ እየታገለ ያለን ኋይልና አደረጃጀትን እያየና እየሰማ እራሱን በአማራነት አደራጅቶ መመከትና መዘጋጀት ሲጋባው ከኢትዮጲያዊያነት ማማ ላይ አልወርድም በሚለው ኋላቀር ፍልስፍናው ታብዮ ለጠላቶቹ ያልተደራጀ ምቹ ኢላማ ሆኖ የጠበቀ ሆነ። በዚህም ምክንያት በ1991 ላያእነዚህ በጸረ አማራነት እራሳቸውን ለዓመታት ያደረጁት ህወሃት፣ ኦነግና መሰል ኋይሎች አማራው ስልጣን ይዘው የሀገሪቱንም መተዳደሪያ ሕግ በአዲስ መልክ ሲያረቁ ያልተደራጀው አማራ ግን ተወካይ በማጣቱ የበይ ተመልካች ከመሆኑም በላይ በሁለቱም ኋይሎች ወዲያውኑ ለተከፈተበት ማንነት ተኮር ዘመቻ ሙሉ በሙሉ ተጋላጭና ምቹ ሆኖ በመገኘቱ የአሰቃቂ ጭፍጨፋ ሰለባ ለመሆን ቻለ።
ይህ አማራ ተኮር ጭፍጨፋ ለላፉት ሶስት ዓስርተ ዓመታት ውስጥ መጠነ ሰፊ በሆነ ይዘት ተደጋግሞ ሲፈጸም በ1992/3 ላይ በእውቁ ምሁር ፕ/ር አስራት ወልደየስ ከተቌቌመው የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መዓሕድ) በስተቀር የአማራን ሕዝብ በመወከል የተነሳ ኋይል አልነበረም። በዚህ በጨነገፈው ሶስት የለውጥ ዓመታት ውስጥ በአማራ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ጭፍጭፋ በኦሮሞ፣በትግራይና በጉምዝ ጽንፈኛ የፖለቲካ ኋይሎች የተፈጸመበትና ዛሬም እየተፈጸመበት ያለ ህዝብ ሊሆን የቻለበት ምክንያት እንደ ጠላቶቹ የኦሮሞና የትግራይ ፖለቲካ ኤሊቶች እራሱን  በወታደራዊ ኋይል፣በፖለቲካና በመሰል አማራዊ ማንነት ላይ ባተኮረ አደረጃጀት እራሱን እራሱን አደራጅቶ ስላላጠናከረ ብቻ ዛሬ በህልውናው እጣፈንታ ላይ ወሳኙ እራሱ አማራው ሳይሆን የአማራው ጠላት የሆኑት እንደነ ህወሃት/ብአዴን (ኢህአዴግ) እና ዛሬ ደግሞ ኦህዴድ/ብአዴን (ብልጽግና) የሚወስኑለት ሕዝብ ለመሆን ተገዷል።
የሰላሳ እና የአርባ ሃምሳ ዓመቱን ጸረ አማራዊ ጭፍጭፋዎችን፣ትርክቶችንናሕግጋቶችን  ተወት አድርገን በዚህ በሶስት ተኩል ዓመታት ውስጥ በአጠቃላይ የአማራ ሕዝብ ላይ – ማለትም በመተከል ቤኒሻንጉል፣በወለጋ መላ ኦሮሚያ፣በአጣዬ፣ከሚሴ፣ደራ ሰሜን ሸዋ፣ወሎና ሰሜን ጎንደር የተፈጸመውን የተስፋፊው ኦህዴድ/ኦነግ የጉሙዝና የትህነግን የወረራ ዘመቻን ብቻ ያየን እንደሆነ ይህ ሁሉ አሰቃቂ ዘመቻ በአማራው ላይ ሊፈጸም የቻለው በዚሁ አሁን ስልጣን ላይ ባለው ኦህዴድ/ብአዴን መራሹ የብልጽግና መንግስት ፈቃደኝነት ፈጻሚነትና አስፈጻሚነት ብቻ የተፈጸመ ሳይሆን በእኛ በአማራዊያን በኩል ይህንን የጠላት ኋይል አደረጃጀትና አሰላለፍን ሊመጥን በሚችል መልኩ አማራዊ የሆነ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አደረጃጀት ስሌለንም ጭምር ነው ብለን የምንገልጸው።
ወያኔ ኦነግ ኦህዴድና ጉሙዝ በአማራ ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋና ወረራን መፈጸም የቻሉት ኢትዮጲያ ብቁ የሆነ ወታደራዊ ኋይል ስለሌላትና መንግስት አልባ ስለሆነች -አሊያም በሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ የአማራ ተወላጆች ያልመታቀፍ ምክንያት ሳይሆን
በጸረ አማራዊ ትርክት ተደራጅቶ ለስልጣን በበቃና ሀገርንም እየገዛ ባለ ጸረ አማራ መንግስት ስር ሆነን ሕዝባችንን  የሚጠብቅ አንድ አማራዊ የታጠቀ ጠንካራ ኋይል እንደ ባላጣዎቻችን መፍጠር ስላልቻልን ብቻ እና ብቻ ሆኖ ነው የምናገኘው።
♦  በሰሜን በወራሪው ትህነግ በደቡብ በተስፋፊው ኦነግ/ኦህዴድና በምእራብ በጉሙዝ/ኦህዴድና በሱዳን/አቢይ ወራሪ ጸረ አማራ ኋይሎች ስር ላለው አማራ – አንድ የአማራ ሕዝባዊ ኋይል/ፋኖ ወታደራዊ ኋይል መገንባት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ እንጂ  የምርጫ ጉዳይ አይደለም።
እጅግ በሚደንቅ ሁኔታ ሰሞኑን የአብኑ  ክርስቲያን ታደለ በአማራ ብሄርተኝነታዊ የህልውና  ትግል ውስጥ ሊደጋገም ቀርቶ ሊታሰብ እንኴን እማይገባን እጅግ የገዘፈ ስህተት ይሁን ሆን ብሎ  አማራን የማዳከም ሚና ባልገባን ሁኔታ እየደጋገመ የአማራ ወጣት በሙሉ ወደ መከላከያ እንዲገባ እያለ ሲቀስቀስ እያደመጥን ነው።
እዚህ ላይ እያንዳንዱ አማራ በአጽንኦት  እንዲያንሰላስልና በአንክሮ እንዲመለከተው የምፈልገው ነገር ቢኖር የሚከተሉትን ወሳኝ ጥያቄዎችን እራሱን በራሱ እየጠየቀ ሁኔታዎችን ለመረዳት እንዲጥር ነው፦
 1ኛ- የአማራ ህልውናዊና ማንነታዊ ዘርፈ ብዙ ጥቅምና መብት ተጠናክሮ የሚጠበቀው በጸረ አማራ መንግስት በሚመራው መከላከያ ሰራዊት ነው??  ወይንስ በራሱ በተደራጀና በተጠናከረ አማራዊ ወታደራዊ ኋይል ነው??
 2ኛ-  ክርስቲያን ታደለ የአማራን ወጣት ወደ መከላከያ ተቀላቀሉና ሕዝባችሁን ጠብቁ ሲል በዚህ ሶስት ዓመት ውስጥና ዛሬም አማራው ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተፈጸመውና እየተፈጸመም ያለው ዛሬ ባለው የመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የአማራ ልጆች ስለሌሉ ነውን ???
3ኛ- ክርስቲያን ታደለ ልክ በኦሮሚያ በትግራይና መሰል እንደተመረጡት የኦህዴድና የትህነግ ተመራጮች 7/24ሰዓት ስለመረጣቸው ሕዝብ ኦሮሞ/ኦሮሚያ  ትግሬ/ትግራይ እያሉ ውክልናቸውን በአግባቡ ለመወጣት እንደሚጥሩት ባላንጣዎቻችን ክርስቲያንም የተመረጠው በአማራ -ለአማራ ሆኖ ሳለ እና ይህንን መሰረት አድርጎ ለአማራ ሕዝብ ጥቅም ብቻ መንቀሳቀስና የአማራን ሕዝብ ጥያቄን ማስተጋባት ሲገባው  እሱ ግን የቸገረው ያልበላውን ያካል እንደሚባለው አይነት እራሱን የሀገር መሪ ስፍራ በማስቀመጥ ስለአማራው ሳይሆን ስለመከላከያውና መሰል የፌዴራል ጉዳዮች ላይ ይበልጥ መሰማራቱ ለምንድነው ?? ይህ የሚሰራውን ካለማወቅ የመነጨ ስህተት ነው ወይንስ ልጁ የሚያራምደው ድብቅ አጀንዳ ስላለው ነው ?? አሊያም የአለመብሰል እንጭጭነት ውጤት ነው??
4-  ክርስቲያን ታደለ ለምን እና እንዴት አድርጎ ቢያስብ ነው የመከላከያ ሰራዊቱን  ማጠናከር ሲል
የአማራን ሕዝባዊ ኋይል ተደራጅቶ  እንዳይጠናከር የፈለገው??  ለአማራ መብት ጥቅምና ህልውና መከበር የምታገል ነኝ የሚል እንደ ክርስቲያን ታደለ አይነቱ ሰው አማራው የራሱ የሆነ የተደራጀና የተጠናከረ አንድ አማራዊ ወታደራዊ ኋይል/ፋኖ አያስፈልገውም ለአማራ አይጠቅመውም ብሎ የሚያምንበት ምክንያትና መንስኤ ምንድነው ትላላችሁ??
የኦሮሞው፣የትግራዩ፣የቤኒሻንጉሉ፣የደቡቡና የወዘተ ክልል ፖለቲከኞች አማራ የራሱን ወታደራዊ ኋይል አይስፈልገውም ቢሉ ምንም የሚደንቅ አይሆንም። የጸረ አማራ ኋይሎች የትሮዣን ፈረስ ሆኖ አማራን በባርነት እያስገዛ ያለው ጃንደረባው ብአዴንም የአማራ ክልል ልዩ ኋይልም ሆነ የአማራ ሚሊሺያና የአማራ ሕዝባዊ ኋይል/ፋኖ አያስፈልገውም ብሎ ቢያውጅ አሁንም አያስገርምም። ግን እንደ አብን አይነቱ የአማራ ሕዝብ እውነተኛ ተወካይና ድምጽ እሆናለሁ ብሎ የተመሰረተ ድርጅትና አመራሮቹ ከበለጠ ሞላ ጀምሮ ክርስቲያን ታደለ ዩሱፍ ኢብራሂም ጋሻው መርሻ ጣሂር መሀመድ ወዘተ አይነቶቹ ብድግ ብለው የአማራ ወጣት በሙሉ ወደ መከላከያ ግባ አማራ የራሱ የሆነ ጠንካራ ልዩ ኋይል ሕዝባዊ ኋይል/ፋኖ እና ሚሊሺያ አያስፈልገውም እያሉ ቢቀሰቅሱ ምን ይባላል?? እንዴትስ ይታያል??  የሚሉትን ወሳኝ ጥያቄዎች እያንዳንዱ የአማራ ልጅ እያንሰላሰለ እንዲያስብበትና መልሱንም ከአጠቃላይ የአማራ ሕዝብ ትግል አኴያ እየፈለገ እንዲመልስለት ያስፈልጋል።
ዛሬ ያለንበት ሁኔታ – ማለትም የወያኔ ወረራ በራሱ ይህንን የአማራውን የተጠናከረና የተደራጀ ታጣቂ የአማራ ኋይልን አስፈላጊነት በእጅጉ አስፈላጊ መሆን ጉዳይ ግልጽልጽ አድርጎ እያሳያ ባለበት ወቅት – መላው የአማራ  ሕዝብ የስልጣን ጥማት ያሰከራቸውን ደጅ ጠኚዎችን መሰረት የለሽ ተራ ፕሮፖጋንዳንና ቅስቀሳን ጆሮ ዳባ ብሎ ገና ለተጀመረው ጦርነትና በፊት ለፊቱ ለሚጠብቀው ትልቁና ዋነኛው የህልውና ጦርነት ብሎ በሙሉ ሃይሉ አቅሙና አትኩሮቶ አደርጅቶና አጠናክሮ ማውጣት የሚገባው የራሱ የሆነውን የአማራን ሕዝባዊ ኋይል/ፋኖን እና መሰል  የታጠቀን ኋይል ብቻ እና ብቻ ነው!!!
ዘርፈ  ብዙው የአማራ ሕዝብ ሁለንተናዊ መብት ጥቅምና ህልውና በማይናወጥ አለት የተጠበቀ የሚሆነው በራሱ አንድ ነጻና ኋያል የታጠቀ የአማራ ኋይል ብቻ ነው!
Filed in: Amharic