>

የመከልከል አባዜ በድጋሚ ሲፈተሽ (ከይኄይስ እውነቱ)

የመከልከል አባዜ በድጋሚ ሲፈተሽ

ከይኄይስ እውነቱ


በሕግ የተፈቀደን መብት መከልከል ላገራችን የመንግሥት አስተዳደር ተቋማት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የበለጠ የሚያስደነግጠውና የሚገርመው ግን ሕገ ወጥ ክልከላው በተግባር የማያስጠይቅ መሆኑ ነው፡፡ 

የአሁኑ ትዝብት ግን በርካታ የመንግሥት መ/ቤቶችን እግር ተወርች ጠፍሮ ከያዛቸው ማነቆዎች መካከል ለማሳያ የሚሆን አንድ ሰበዝ በመምዘዝ የብዙዎችን ጩኸት ለማስተጋባትና ከሚመለከተው ግለሰብ እስከ ተቋም ራሱን ፈትሾ የአሠራር ማስተካከያ እንዲደረግ ለማሳሰብ ነው፡፡

የመንግሥት የአስተዳደር ተቋማት በተለይም አገልግሎት በመስጠት የተሠማሩትን በግል ጉዳያችንም ሆነ የሌሎችን ጉዳይ በሕጋዊ ውክልና ለማስፈጸም ስንጎበኝ እንደጉዳዩ ዓይነት፣ እንደምንስተናገድበት መ/ቤት እና እንደሚያስተናግደን ባለሙያ ወይም ኃላፊ የሚገጥሙን ችግሮችና ተግዳሮቶች አሉ፡፡

ይህን ርእሰ ጉዳይ በሚመለከት ከዚህ ቀደም ባንድ ጋዜጣ ‹‹የመከልከል አባዜ/ “prohibition syndrome”›› በሚል አንድ መጣጥፍ አቅርቤ ነበር፡፡ ያው እንደተለመደው የማይሰማ ጆሮ፣ የማያስተውል አእምሮ ላይ ነው የወደቀው፡፡ በመነሻ ላይ ያሰፈረሁት ሃሳብ ጅምላ ክስ ስለሚመስል ዓውድ ለመስጠት ያህል ጉዳዩ የመንግሥት አስተዳደር መስሪያ ቤቶችን (የኢትዮጵያን ቢሮክራሲ)፣ ከነዚህም አስተዳደራዊ ሕግ በማውጣት የቊጥጥር ሥራዎች (regulatory functions) ላይ የተሰማሩትን  ይመለከታል፡፡ 

በኢትዮጵያ የመንግሥት አስተዳደር መ/ቤቶች በቊጥር እጅግ በርካታ የሆኑ መመሪያዎችን ያወጣሉ፡፡ ከብዛታቸውም የተነሣ አንዳንዶቹንም እስኪዘነጉአቸው፣ የተሻሩትን ሥራ ላይ ካሉት ለመለየት እስከሚያዳግት ድረስ፡፡ አለፍ ሲልም መመሪያ ከእናት ሕጉ (ሕገ መንግሥት፣ ዓዋጅና ደንብ) ተቃራኒ ድንጋጌዎችን ይዞ የሚወጣበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ የሕግ ዕርከን ውስጥ መመሪያ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኝ የሕግ ዓይነት ነው፡፡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ባይወጣም፣ በዕርከን በታችኛው መሰላል ላይ ቢገኝም ሕግነቱን የሚያስቀር ነገር የለም፡፡  በመሆኑም እንደማናቸውም ሌሎች ሕጎች መብት ይሰጣል፤ ግዴታም ይጥላል፡፡ ዓዋጆችንና ደንቦችን በዝርዝር ለማስፈጸምም ዋና መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ በመሆኑም የዜጎችንም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚቈዩ የውጭ ዜጎችንም ሕይወት ይነካል፡፡ 

የፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣን ባቆመው ዓዋጅ ቊጥር 3/1987 መሠረት ማናቸውም የፌዴራል መንግሥት ሕጎች በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ለሕዝብ እንዲደርሱ ቢደነግግም መመሪያ ከብዛቱም ሆነ ከሚወጣበት ድግግሞሽ እና ከወጪም አንፃር ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ በመሆኑ እንደሌሎቹ ሕጎች በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ አናገኘውም፡፡ ስለሆነም ተደራሽ የሚሆንበትን መንገድ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

እስካሁን ባለው አሠራር ሕጉ (መመሪያ) ለሕዝብ ወይም ለሚመለከታቸው ሁሉ ተደራሽ የሚሆንበት መንገድ አልነበረም፡፡ በመሆኑም አንድን መመሪያ ለማግኘት የእያንዳንዱን መ/ቤት መልካም ፈቃድና የግለሰብ ሠራተኞችንና ኃላፊዎችን ቅንነት ይጠይቃል፡፡ ዘመናዊው የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ከመጣም ወዲህ መሻሻል ቢኖርም አጠቃቀሙ በሁሉም የመንግሥት አስተዳደር ተቋማት ዘንድ ወጥነት የለውም፤ በየጊዜው በሚፈጠር ቴክኒካዊ ችግር ምክንያት ተደራሽ አይደለም፤ ሁሉም መመሪያዎች ይፋዊ በሆኑ ድረ ገጾች አይገኙም፤ ከሁሉም በላይ ድረ ገጾቹ ወቅታዊ አይደረጉም፡፡ ይህ ችግር አሁንም ቀጥሏል፡፡

በቅርቡ በወጣው የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ ዓዋጅ ቊጥር 1183/2012 በመንግሥት የአስተዳደር ተቋማት የሚወጡ መመሪያዎች በእያንዳንዱ ተቋማት ይፋዊ ድረ ገጽ እንዲለጠፉ ከማዘዙም በላይ ሕጋዊ ተፈጻሚነት የሚኖራቸው እያንዳንዱ የአስተዳደር ተቋም መመሪያዎቹን ለፍትሕ ሚኒስቴር ልኮ ሚኒስቴሩ መ/ቤት ሲመዘግባቸው ወይም በድረ ገጹ ሲለጥፋቸው መሆኑ ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም ሕጋዊ ተፈጻሚነት የሚኖራቸው መመሪያዎች ተጠቃለው በማዕከል በፍትሕ ሚኒስቴር እና በእያንዳንዱ ተቋም ድረ ገጽም እንዲገኙ በሕግ ግዴታ ተቀምጧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መመሪያዎቹን የሚፈልግ ሰው መመሪያውን ያወጣው ተቋም ዘንድ በአካል ቀርቦ የአገልግሎት ክፍያ በመፈጸም ቅጅ ማግኘት እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ 

በሕግ ረገድ የተወሰደው ርምጃ የሚያበረታታና የመመሪያዎችን ተደራሽነት ለማረጋገጥ በእጅጉ የሚያግዝ ቢሆንም አስፈጻሚዎቹ ተቋማት፣ ከተቋማትም ሰዎች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ በመከልከል አባዜ የተሞላ አእምሮ እንዲህ በቀላሉ ባንድ ጀምበር የሚለወጥ አይመስልም፡፡ የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ከወጣም በኋላ መከልከሉን የቀጠሉበት፣ ሂዱና ከፍትሕ ሚኒስቴር ውሰዱ እያሉ ተገልጋዩን የሚያጉላሉ ተቋማትን/‹ሠራተኞች›ን አሁንም እንታዘባለን፡፡

በቀደመ ጽሑፌ እንደገለጽሁት በፈቃድ ሰጭ አካላትም ይሁን የተለያዩ አገልግሎት በሚሰጥባቸው የመንግሥት አስተዳደር መ/ቤቶች የሚታይ ውሳኔን ያለመስጠት፣ በሕግ የተፈቀደን ወይም ግልጽ ክልከላ ያልተደረገበትን ጉዳይ የመከልከል፣ ሕግን ሥራ ላይ በሚውልበት መንገድ ሳይሆን በዘፈቀደ የመተርጎም ጉዳይ፣ ለተገልጋይ መብት ሳይጨነቁ ‹አይቻልም› ብሎ መሸኘት፣ ለክልከላም ሆነ ለፈቃድ ምክንያታዊ አለመሆን፣ የሚያስፈጽሙትን ሕግ ዓላማ የማያራምዱ ቅፆች ይዘት፣ ከሕግ በላይ የሆኑና የአሠራር ግልጽነትና ወጥነት የማይታይባቸው ለክልከላ የተቀመጡ ልማዳዊ አሠራሮች መስፈን ወ.ዘ.ተ. ምክንያቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፤

1ኛ/ የብቃት ችግር (በተሠማሩበት ሥራ በቂ ዕውቀትም ሆነ ልምድ አለመኖር) – የዐቅም ማነስ በራስ አለመተማመንን ያስከትላል፡፡ በራሱ የማይተማመን ሠራተኛ ደግሞ አንድ ጉዳይ መከልከሉን ወይም መፈቀዱን ርግጠኛ ስለማይሆን ‹ጎመን በጤናን› መርጦ መከልከልን አማራጭ አድርጎ ይወስዳል፡፡ በዚህም መከልከል መደበኛ አሠራር ይሆናል፡፡ በሌላ አነጋገር ለቦታው በብቃት/ችሎታ የማይመጥን ሰው ማስቀመጥ ለሕገ ወጥ ክልከላ በር ከፋች ይሆናል፡፡ የዐቅም ማነሱ ሌላ መገለጫ ደግሞ ትንሹንም ትልቁንም ጉዳይ ከፍተኛ ‹ምሥጢር› አድርጎ የመመልከት ሥር የሰደደ ቸግር ነው፡፡ ለሕዝብ ወይም ለሚመለከታቸው ወገኖች እንዲደርስ ተፈልጎ የሚዘጋጅ መመሪያ ‹ምሥጢር› አድርጎ ቈጥሮ የሚከለክል የአስተዳደር ተቋም ሠራተኛ ወይም ኃላፊ ከመነሻው ቦታው ላይ መቀመጥም የለበትም፡፡

2ኛ/ የበላይ ትእዛዝን በመፍራት – እዚህ ጋ በዐቅም ማነስ/በክፋት የተያዘው በኃላፊነት የተቀመጠው ሰው ሲሆን፤ የሕጉን መንፈስ ያራምዳል፣ አመክንዮአዊና ተገቢ ነው ብለው በሚያምኑበት መንገድ ለማስተናገድ የሚፈልጉ የበታች ሠራተኞች ሕገ ወጥ የሆነ ትእዛዝን የሚቀበሉበት ዋና ምክንያት ‹‹ግምገማን›› እና ‹‹ጉቦ ተቀብሎ ነው ያስተናገደው›› የሚል ክስን በመፍራትና ይህንንም ተከትሎ ከደረጃ ዕድገት እስከ ሥራ ዋስትና አጣለሁ በሚል ሥጋት ወይም ቀደም ብሎ በሌላ ሠራተኛ የተወሰደ ሕገ ወጥ ርምጃን እንደ መቀጣጫ በመፍራት ይሆናል፡፡ በዚህም በርካታ ሠራተኞች ‹‹የማያስጠይቀው›› የ‹‹ከልካዮች›› ጎራ ውስጥ እንዲቀላቀሉ ሆነዋል፡፡

3ኛ/ የቅንነት መጥፋት – አልቅሶ ወይም በዘመድ አዝማድ ተጎትቶ ገብቶ ተገልጋዩን የሚያስለቅስ ወይም ተቋማትን እንዲያማርሩ የሚያደርግ ሠራተኛ የተጠራበትን ተልእኮውን በጭራሽ የማያውቅ ነው፡፡ ቦታው ላይ የተቀመጠው ራሱን እንጂ ሕዝብ ለማገልገል አይደለምና፡፡ የቅንነት መጥፋቱ ችግር በኅብረተሰብ ደረጃ የሚታይ አጠቃላይ የሥነ ምግባርና የግብረ ገብነት መሸርሸር ውጤት በመሆኑ ችግሩ የበላይ የበታች ሠራተኛ አይልም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ግለሰብ በመከልከሉ ይኮራል÷ይደሰታል÷ እብጠትም ቢጤ ይሰማዋል፡፡

4ኛ/ ንቅዘት (corruption) – ከቅንነት መጥፋቱ ጋር የተያያዘ ቢሆንም ከግብር ከፋዩ ሕዝብ በሚሰበሰብ ገቢ ደመወዙን የሚያገኝ ሠራተኛ ለመደበኛ አገልግሎቱ ከተገልጋዩ ጉቦ ካልተሰጠው ለመከልከል ዝግጁ የሆነ ግለሰብን ይመለከታል፡፡ የንቅዘት ጉዳይ የዐደባባይ ምሥጢር በመሆኑ በዚህ ድርጊት ተገልጋዩም ተባባሪ በመሆን ለምንታዘበው የአሠራር ብልሹነት ድርሻ እንዳለው የማይካድ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሕገ ወጥ ክልከላ በራሱ የንቅዘት አንዱ መገለጫ ነው፡፡

5ኛ/ መከልከል በተግባር የማያስጠይቅ በመሆኑ – ክልከላ በራሳቸው ለማይተማመኑ ሰነፎች፣ በበላይ ትእዛዝ ለሚያሳብቡ ፈሪዎች፣ ንቅዘትና ክፋት ገነዘባቸው ለሆኑ ዋልጌዎች መደበቂያ ዋሻ ሆኖ አገልግሏል፡፡ የትኛው የመንግሥት ተቋም የሥራ ኃላፊ ነው የበታች ሠራተኛው በሕግ የሚፈቀድን አገልግሎት በመከልከሉ በሕግ ለመጠየቅ ይቅርና ተገቢ አይደለም ብሎ የሚገሥፅ? የትኛው የሥራ ኃላፊ ነው ሕገ ወጥ ክልከላን አጽድቆ የሚጠየቅ? ተገልጋዩም የሄደበት ጉዳይ ይበላሽብኛል በሚል ፍራቻ እና በመገዳደርም የሚፈጠርበትን እንግልት እየጠላ ሕገ ወጥ ከልካዮች እንዳሻቸው እንዲፈነጩ ሆኗል፡፡ 

እነዚህ ሕጋዊ ባልሆነ ምክንያት በመከልከል አባዜ የተጠመዱ ግለሰቦች ሥራ ቦታ ተገኝተው ቀኑን ሙሉ ሲከለክሉ ውለው እንደ ሌሎች ትጉሃን ሠራተኞች ‹ሥራ› ሠራን ብለው ወደ ቤታቸው ሲገቡ – ከሕሊናቸው ጋር ከሆኑ – ምን እንደሚሰማቸው አላውቅም፡፡

በመሠረቱ ሕግ (እንደ ወንጀለኛ መቅጫ ዓይነት ሕጎች ካልሆኑ በቀር) በዋናነት ፈቃጅ እንጂ ከልካይ አይደለም፡፡ ስለሆነም ደንቡ/ ልማዱ (the rule) መፍቀድ ሲሆን፤ መከልከል እንደ ልዩ ሁኔታ (exception) የሚታይ ነው፡፡ ይህንን እንደ መርህ ይዞ የማይሠራ የመንግሥት አስተዳደር ሠራተኛ የሕዝብ አገልጋይ ሊሆን አይችልም፡፡

በሕገወጥ ክልከላና በሌሎችም አስተዳደራዊ ጉዳዮች የሚፈጸሙ በደሎችን የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕጉ እና ሕጉን የሚተረጕሙት የዳኝነት አካላት ምን ያህል እንደሚቀንሱት ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ በነገራችን ላይ የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕጉ (በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች) እስከነ መግለጫው የተዘጋጀው በወያኔ አለቃ በመለስ ዘመን ሲሆን፣ ተቋሙም በዶ/ር ፋሲል መሪነት መካን እንዲሆን የተደረገው የፍትሕና የሕግ ሥርዓት ምርምር ነው፡፡ በሕጉ ዝግጅት ፋሲልም ሆነ የመንግሥት ባለሥልጣናት ደስታኛ ባይሆኑም ሃሳቡን ከማመንጨት ጀምሮ የሕጉን ረቂቅ በማዘጋጀት ረገድ ብቸኛ ለማለት የሚያስደፍር ሚና የነበረው ስሙን እዚህ የማልጠቅሰው አንድ የሕግ ባለሙያ ነበር፡፡ ረቂቁ ተጠናቅቆ አጀንዳው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከመቅረቡ በፊት ይኸው የሕግ ባለሙያ የመለስ የሕግ ጉዳዮች አማካሪ ከነበረው ዶ/ር ፋሲል ናሆም አንደበት የሰማሁት ነው ብሎ እንደነገረኝ ‹‹አንገቴ ውስጥ ሸምቀቆ አላስገባም›› የሚል መልስ ነበር ከመለስ ያገኘውና ጉዳዩ የተዘጋው፡፡ ከመነሻው ተጠያቂነትን ለማምለጥ ሕግ እንዳይወጣ ማገድ እና ሕግን አውጥቶ ሕጉ እንደሌለ ቈጥሮ በተቃራኒው መሥራት የአገዛዞች ዓይነተኛ ጠባይ ነው፡፡ ምናልባት የኋለኛው የአፈጻጸም ችግር ነው የሚል ሰንካለ ምክንያት ለመስጠት ሳይረዳ አይቀርም፡፡

በመጨረሻም በአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕጉ መሠረት በአስተዳደር ተቋማት የሚወጡ መመሪያዎችን መዝግቦ በድረ ገጹ እንዲለጥፋቸው ሥልጣን የተሰጠው የፍትሕ ሚኒስቴር መ/ቤት ድረ ገጽ ራሱ ተደራሽ አለመሆኑ ወይም መመሪያዎችን ከድረ ገጹ ለማውረድ (download ለማድረግ) በተግባር አዳጋች መሆኑን (የዚህ መጣጥፍ አቅራቢን ጨምሮ) ድረ ገጹን ከጎበኙ በርካታ ተጠቃሚዎች ስሞታ እየቀረበ በመሆኑ ሚኒስቴሩ መ/ቤት ችግሩን አስጠንቶ በአስቸኳይ የማስተካከያ ርምጃ እንዲወስድ በዚሁ አጋጣሚ በማክበር እናሳስባለን፡፡

Filed in: Amharic