>

"ድል ምርኮና ምህረት....!!!" (በእውቀቱ ስዩም)

“ድል ምርኮና ምህረት….!!!”

(በእውቀቱ ስዩም)

በአጼ ዮሀንስ አራተኛ ዘመነ መንግስት   የጎጃሙ ንጉስ ተክለሀይማኖት  እና የሸዋው ንጉስ ምኒልክ  በመሬትና በንብረት  ተጣልተው ሰራዊት አስከትተው እምባቦ በሚባለው ስፍራ ተገናኝተው  ተሸካሸኩ፤ በጦርነቱ ምኒልክ እና አጋሮቻቸው በለስ ቀናቸው፤      ንጉስ ተክለሃይማኖት  ብዙ ቦታ ቆስለው ተማረኩ፤ ምኒልክ  በጦርነቱ ማግስት  የግል ሀኪማቸውን በማዘዝ ምርኮኛውን ንጉስ  አሳከሟቸው፤ ክብራቸው የሚመጥን እንክብካቤም አደረጉላቸው፤
ከጥቂት ቀናት በሁዋላ አሸናፊና ተሸናፊ ከነተከታዮቻቸው  ምሳ እየበሉ ሲያወጉ፥  ምኒልክ
“  እኔን ማርካችሁኝ ቢሆን ኖሮ ምን ታረጉኝ ነበር?”  የሚል ጥያቄ ወረወሩ፤
 ምርኮኞቹ ለመቅለስለስ አልሞከሩም ፥ “ ቆራርጠን ያሞራ ራት እናደርገዎ  ነበር” የሚል ምላሽ ሰጡ::
“ ታድያ ከናንተ ጭካኔና ከኔ ርህራሄ   ይሻላል ?” አሉ ምኒልክ ፤ ( “ እንዴታ!  የርስዎ ምህረት ይሻላል እንጂ “ የሚል መልስ እንደጠበቁ እገምታለሁ)
በስፍራው ከነበሩ የጎጃም ምርኮኞች መካከል አንዱ መስፍን ረጋ ብለው  የሚከተለውን ምላሸ ሰጡ ;-
“ ንጉስ ሆይ ! ሲዋጉ ጭካኔ፤ ድል ሲያረጉ  ርህራሄ የተገባ ነው “
በዚች አባባል ውስጥ ያለው የመንፈስ ስልጣኔ   ቢተነተን አንድ ቅጽ መጽሀፍ ይወጣዋል፤
ለጊዜው  እፍታውን ብቻ እናቅርበው፤
ሰዎች ጥቃት፤ ባርነት፤ ቅሚያ ሲያንገፈግፋቸው የሚያደርጉት አልሞትባይ ተጋዳይነት ያስከብራል፤   ጠመንጃ ደግኖ ጦር ሰብቆ የመጣብህን ሰው ፤ ቅልጥሙን ልምታው ደረቱን ብለህ አታመነታም ፤ የራስህን ለመከላከል የያዘከውን ሁሉ በባላጋራህ ላይ ትወረውራለህ
 በተቃራኒው ፤ የተዳከመ፤ እጅ የሰጠ፤ ነጭ ባንዲራ የሚያውለበልብ ባላጋራውን የሚገድል ሰው እንደ ጀግና አይቆጠርም!  ራሱን መከላከል ያልቻለውን  አቅመቢስ ሰው  መግደል  በባህላችን ” ወስላታ፤ ግፈኛ፤ ፈሪ”  አሰኝቶ ያስነውራል::
በጦርነት ወቅት ፤  ከብላቴና እስከ ባልቴት  የሚደፍሩ፤ በባላገር ላይ ግፍ የፈጸሙና ንብረት ያወደሙ ሰዎች  ተይዘው፥ በፍርድ ቅጣታቸውን ማግኘት ይገባቸዋል፤ ፍትህ-ርትእ(ጀስቲስ) በሌለበት ሰላም አይኖርም፤ ይሁን እንጂ  ቅጣትና ካሳ ማሳለፍ የፍርድ ቤት ፋንታ ነው ፤ ዜጎች  ባሻቸው ጊዜና ቦታ  ወንጅለው የሚቀጡ ከሆነ ማህበረሰብ ራሱን እያወደመ ነው ማለት ነው::
ሰብአዊነቱን እንኩዋ ብናቆየው ፥ ትጥቁን የጣለ ጠላት መግደል   ከጦር መላ አንጻር ብናየው ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፤   በሁለተኛው አለም ጦርነት ጀርመኖች በሩስያ ግዛት ዘልቀው ገብተው  ብዙ አይነት  ጭካኔ ፈጽመዋል፤   ጄኔራል ዮአቺም ለመስን የተባለ የጀርመን መኮንን  ለበላዮቹ በጻፈው ሪፖርት: –
“  ሰራዊታችን፥ ምርኮኞችንና  የሸሹ ወታደሮችን በጭካኔ እየረሸነ መሆኑን ደርሸበታለሁ፤ …ይህ ውጊያ ሳይሆን ነፍሰገዳይነት ነው፤ ( በቅርቡ ሩስያኖች መሳርያ ያልታጠቁ ፤ እጃቸውን የሰጡ ወገኖቻቸውን ስፍር ቁጥር የሌለው አስከሬን ተረፍርፎ እንደሚገኝ  መስማታቸው አይቀርም፤   ያኔ  ጠላቶቻችን ፤ በየጫካው፤ በየሜዳው  እየተሸሸጉ መጋደላቸውን  ይቀጥላሉ፤  ስፍር ቁጥር የሌላቸውን  ጉዋዶቻችንን እናጣላን” ብሎ ነበር::
ይህ ማስጠንቀቂያ ሰሚ አላገኘም   ፤ ጀኔራሉ እንደ ፈራው፥  ሩስያኖች ከፊትለፊታቸው የተጋረጠው  ምርጫ  በምርኮና በሞት መካከል ሳይሆን ተንበርክኮ መሞትና ቆሞ መሞት መካከል መሆኑ ገባቸው ፤ እናም ቆመው ለመሞት  ተጋደሉ፤ የማታ የማታ  አሸነፉ::
ባሁኑ ጊዜ “  ምርኮኛ ማግበሰበስ አያስፈልግም  መፍጀት ነው እንጂ” ብለው የሚሰብኩ ሰዎች ጦርሜዳ ላይ የተሰማሩ  ወታደሮች አይደሉም፤ እንዲህ አይነቱ ጥሪ የሚመነጨው  በሶፋና በስልካቸው መካከል  ከሚኖሩ ሰዎች አንደበት ነው ፤ የኒህን ሰዎች የበቀል ፋንታዚ ይዘን ለትውልድ የሚተርፍ የበቀል አዙሪት ውስጥ እንዳንገባ እንጠንቀቅ!
መስዋእትነት ማለት ለሀገር ሲሉ መሞት ብቻ አይደለም፤ ለሀገር ሲሉ የበቀል ስሜትን መጨቆን፤ ፍርድን  ለፍርድቤት ማቆየት   የከበረ መስዋእትነት ነው ፤
Filed in: Amharic