>
5:18 pm - Tuesday June 15, 5610

"ጋሽ ታዲዮስ ታንቱ እና ወጣት እያስፔድ፤  በሃሳብ ተቃርኖ ጫፍ የቆሙ የፖለቲካ ምህዳሩ ፈተናዎች...!!!" (ያሬድ ሀይለማርያም)

“ጋሽ ታዲዮስ ታንቱ እና ወጣት እያስፔድ፤  በሃሳብ ተቃርኖ ጫፍ የቆሙ የፖለቲካ ምህዳሩ ፈተናዎች…!!!”
ያሬድ ሀይለማርያም

እነዚህ ሁለት ግለሰቦች በእድሜያቸው መካከል ካለው ስፋት በላቀ በሀሳብም ፍጹም የሚራራቁና የሚቃረኑ ሰዎች ናቸው። ስለ ኢትዮጵያዊነት፣ ስታሪክ፣ የታሪክ ጀግኖችን በተመለከተ፣ ስለቋንቋ እና በማህበረሰቡ መካከል ስላለው ዘርፈ ብዙ መስተጋብር ያላቸው አረዳድና ትንታኔ አራምባና ቆቦ ነው። ግን ሁለቱንም የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ፤ ሁለቱም ሃሳባቸውን የሚገልጱበት መንገድ ከተለመደው ትህትና እና ከአበሻ ይሉኝታ የራቀ፣ አንድን ማህበረሰብ ሊያስከፉ በሚችሉ ቃላቶችና አገላለጾች የታጀቡ፣ አንዳንዴም ጥራዝ የነጠቁ አገላለጾችን ያዘወትራሉ። የቆሙበትን ጫፍ ለማሳየት ያህል፤ ታዲዎስ የአጼ ምኒሊክን ገድል አውርተው አይጠግቡም። ለሳቸው ምኒሊክ ወደ ቅዱስነት የተጠጉ ናቸው። ለልጅ እያስፔድ ደግሞ በተቃራኒው ምኒሊክን ከፋሽስት ጋር አዛምዶ በማቅረብ ስማቸውን ያነሳ ውግዝ ይሁን የሚል ነው። እንደውም ስማቸውን ያነሳ በሕግ የሚጠየቅባት አገር እፈጥራለሁ ባይ ነው።
እነዚህ ሁለት ጽንፎች የራሳቸው ደጋፊና ሰልፈኛ አላቸው። ለእኔ እንደ መብት ተሟጋች የግል ምልከታዮ እንዳለ ሆኖ ታዲዮስም ሆኑ እያስፔድ በዚህ አመለካከታቸው ምክንያት ችግር ሲገጥማቸው ማየት ስለማልፈልግ ድምጼን ለሁለቱም አሰማለሁ። እኔ የምመኛት ኢትዮጵያ እነዚህን ሁለት ጽንፍ ሀሳቦች የሚያስተናግድ ሰፊና አቃፊ የፖለቲካ ምህዳር እንዲኖራት ነው። ታዲዎስ ሲታሰሩ ጮኼያለው። ሃሳባቸውን ስለምጋራ አይደለም። እያስፔድም ሲታሰር እንደዛው። ትላንት ታዲዎስ ታንቱ ካልታሰሩ እያላችሁ ስትጮኹ የነበራችሁ ሰዎች እያስፔድ ለምን ተነካ ካላችሁ፤ ትላንት ታዲዎስ ለምን ታሰሩ ብላችሁ ስታለቅሱ የነበራችሁ እያስፔድ ይታሰርልን ካላችሁ ኢትዮጽያ መቼም ከሀሳብ እስር ቤት ነጻ አትወጣም።
ሀሳብን የሚፈራ ማህበረሰብ ሁሌም ለጡንቻ ፖለቲካ የተመቸ ነው።  የሀሳብ ልዩነቶች በክርክር እና ውይይት የሚቋጩበት ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር አለመኖር ሁሌም ለግጭት በር ይከፍታል። ሃሳብ አንፍራ። አገር በግለሰብ ሃሳብ አይፈርስም በአፈና እንጂ። አፈና አመጽን ይወልዳል። አመጽ አቢዮትን ትጠራለች። አቢዮት አገር ያናጋል።
እንደመውጫ:-
 እያስፔድ ተስፋዬ   የታሰረው ሀሳቡን እና የፖለቲካ አቋሙን ከመግለጹ ጋር በተያያዘ ከሆነ አደጋ አለው ….
ጋዜጠኛና የፖለቲካ አክቲቪስት እያስፔድ ተስፋዬ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ በእስር እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ተችሏል። እስሩ ወጣቱ የለውጥ አቀንቃኝ በአደባባይና በድፍረት ሀሳቡን እና የፖለቲካ አቋሙን ከመግለጹ ጋር ተያይዞ ከሆነ ይህ አይነቱ እስር የመብት ጥሰት ከመሆኑም በላይ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ነጻነትን አደጋ ላይ ይጥላል።
Filed in: Amharic