ተቆርጦ የቀረው ….!!!
(በእውቀቱ ስዩም)
በየነ ባልንጀራየ ነው፤ ጦርነቱ ሲጀመር “በዩማ ቲዩብ “ የሚል የዩቲዩብ አካውንት ከፍቶ መሸቀል ጀመረ፤ አንዳንዴ የድል ዜና ሲጠርርበት ሰለ አድዋ ወይም ስለዶጋሊ ድል በመተረክ ፕሮግራሙን ይሞላዋል፤ አንዳንዴ የኔን ግጥም ሳይቀር ከፌስቡኬ ላይ ወስዶ ይዶልበታል፤ ሳንቲም ማካፈሉ ይቅር ፤ ክሬዲት እንኳ ሊሰጠኝ አልፈለገም::
አንድ ቀን ንድድ ብሎኝ ፤
“ለምንድነው ግጥሜን አንብበህ ስሜን የዘለልከው? ”ብየ ጠየኩት::
“ ለደህነነትህ ስለማስብ ነው” አለኝ ኮሰተር ብሎ::
“ስለፍቅር በጻፍኩት ግጥም ምን አይነት የደህንነት ችግር ሊገጥመኝ ይችላል?
“ህዝብ በየግንባሩ እየተዋደቀ ስለፎንቃ መፈላሰፍህ ያናደደው አንዱ ደብድቦ ሊገልህ ይችላል! ጊዜውን መምሰል ያልቻለ እድሜው ያጥራል”
“ ጊዜውን መምሰል ያልቻለ እድሜው ያጥራል “ የሚለው የማን ጥቅስ ነው ?” አልኩት፤
“ የኔው ነው! የተልባ ማሻው ሚካኤል ነው ያቀበለኝ”
ትናንት በየነ ቤቱ ምሳ ጋበዘኝ፤ በጨዋታችን መሀል አማርኛው እንዴት እንደ ተለወጠ ታዘብሁ::
ስንበላ “ ባይሆን ከጎረድጎረዱ ቅመስ ! ይሄ አደገኛ ትርክት የመሰለ ፊትህ የማይወዛው ስጋ ስለማትበላ ነው “ አለኝ፤
በየጉርሻው ጣልቃ “ ብላ እንጂ ፤ ሆድና ግንባር አይሸሸግም” እያለ ይጎተጉተኛል፤
“ ቆይ! ግንባር የሚል ቃል ሳትጨምር ማውራት አትችልም?” አልሁት ::
“ በገዛ ቤቴ የፈለገኝን ማውራት መብቴ መሰለኝ ፤ ሁለተኛ ልታርመኝ ብትሞክር በዚህ ጠርሙስ ነው ግንባርህን የምተረክከው ! ግንብአራም !”
ማእዱ ከተነሳ በሁዋላ፤
“ከእምብርቴ በታች ውጥረት ነግሷል “ ብሎ ወደ መጸጃ ቤት ሄደ::
ከተመለሰ በሁዋላ ብዙ ተቀምጦ አልቆየም::
“አሁንም ሽንት ቤት ልቴድ ባልሆነ” አልሁት፤
“ አዎ! ተቆርጦ የቀረውን አራግፌ እመለሳለሁ”