>

መምህሬ የጥበብ አባቴ" ... ጁሊየስ ካምባራጌ ኔሬሬ...!!!" (እስሌይማን አባይ)

መምህሬ የጥበብ አባቴ” … ጁሊየስ ካምባራጌ ኔሬሬ…!!!”
እስሌይማን አባይ

ታንዛኒያዊያን ‘ሙዋሊሙ’ ይሏቸዋል። “መምህሬ የጥበብ አባቴ” እንደ ማለት..። ጁሊየስ ካምባራጌ ኔሬሬ፣ የመጀመሪያው የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙበት 59ኛ አመት። 
 
“ዴሞክራሲ እንደ ኮካ ኮላ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባው ቁስ አይደለም፤ ይልቁን ከሀገሩ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የምታበለፅገው ሥርዓት እንጂ” ይላል ጁሌስ ኔሬሬ።
በቀድሞዋ ታንጋኒካ በአሁኗ ታንዛኒያ ቡቲያማ የተወለደው ጁሊየስ ኒሬሬ አስራ ሁለት ዓመት እድሜው ላይ ከቀለም ተዋወቀ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላም ወደ ኡጋንዳ ተልኮ በካምፓላው ማኬሬሬ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሰለጠነ። ለስኮላርሺፕ ተወዳድሮ አሸነፈናም ታሪክና ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለማጥናት ወደ ብሪቲሽ ኤድንብራ ዩኒቨርሲቲ አቀና።
በኤደንብራ ቆይታው ከፋቢያን አስተሳሰብ አራማጅ ምሁራን ጋር ግንኙነት የነበረው ጁሊየስ ኔሬሬ የሶሻሊዝም ፍልስፍና ከአፍሪካዊያን ባህልና የአኗኗር ዘዬ ጋር የሚጣጣምበትን መንገድ ማሰብና ማበልጸግ እንደጀመረ ይነገራል።
ኡጀማ jamaa የሚባለው የኔሬሬ የሶሻሊዝም ፍልስፍና ርዕዮተ አለሙን እንደወረደ ህዝቡ ላይ ላለመጫን የተለያዩ እካቤዎችን ከግምት ያስገባ ነበር። ኡጀማ የሚባለው የኔሬሬ ታንዛኒያዊ የሶሻሊዝም እሳቤ በተለይም ብዙ የአፍሪካ አገራትን ካጠቃው የጎሳ ፖለቲካ ታንዛኒያን ተከላክሏታል የሚለው በስፋት ይገለፃል።
በትምህርቱ ዘርፍ ኔሬሬ ብዙ መሰረታዊ ለውጦችን አምጥቷል። “የትምህርት ዓላማ ፈተናን ከማለፍ የተሻገረና የሰውን ልጅን አስተሳሰብና አመለካከት ከመሰረቱ መቀየር ነው፡” ይላል መምህሩ ኔሬሬ።
የኤደንብራ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ታንጋኒካ የተመለሰው ጁሊየስ ኔሬሬ በመጀመሪያ በሚወደው የመምህርነት ሙያ ላይ ነበር የተሰማራው። በሚያስተምርበት ኮሌጅ ውስጥ ነበር ኔሬሬ TANሀ (Tanganyika African union) ፓርቲን ያቋቋመው። ይህ እንቅስቃሴው ግን ለቅኝ ግዛት ባለሥልጣናት የተዋጠላቸው አልነበረም።
ከሁለት አንዱን እንዲመርጥ ባስጨነቁት በአንድ ወቅት በምርጫዬ መምህር በአጋጣሚ ደግሞ ፖለቲከኛ ሆንኩ ብሎ ነበር።
ከዚያም ታንጋኒካን ነጻ ለማውጣት የተንቀሳቀሰው ኔሬሬ ብዙዎችን በድርጅቱ ዙሪያ ለማሰባሰብ ችሏል። የኔሬሬ TANU በሰላማዊ ተቃውሞ የሚያምን፣ ብዝሃነትን የተቀበለና የዘር መድሎን የሚጠየፍ ድርጅት እንደነበር ይነገርለታል። በዚህም ምክንያት አንደበተ ርቱዕ የነበረው ኔሬሬ በTANሀ መርህ መሰረት ያለምንም ደም ታንጋኒካን ነጻ ማውጣት ቻለ።
ታንጋኒካ በ1962 እኤአ ዓ.ም. ነጻ ስትወጣም ሙዋሊሙ ጁሊየስ ካምባራጌ ኔሬሬ የመጀመሪያው የታንጋኒካ ፕሬዝዳንት ሆኖ ተመረጠ። በ1964ዓ.ም. በዛንዚባር የተደረገውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ኔሬሬ መፈንቅለ መንግሥቱን ከመሩት ሰዎች ጋር በመደራደር ከስምምነት ላይ መድረስ በመቻሉ ታንጋኒካንና ዛንዚባርን ያዋኸደ የታንዛኒያ ሪፐብሊክ እንዲመሰረት ምክንያት ሆነ። ኒሬሬም የመጀመሪያው የነጻዋ ታንዛኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዝድዳንት ሆነ።
ፓን–አፍሪካኒስቱ ኔሬሬ ጎሳን መሰረት ያደረገ ፖለቲካን አምርሮ ይቃወም ነበር። የአፍሪካ መጻኢ እድል ብሩህ የሚሆነው በትብብር እና በአንድነት ብቻ ነው የሚለው ኔሬሬ በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ተገናኝተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ከመሰረቱት መሪዎች አንዱ ናቸው።
ጁሊየስ ኔሬሬን አንስተን ስለ ኔሬሬ ዶክትሪን አለማውሳት አይቻልም። የኔሬሬ ዶክትሪን በላይኛው ናይል ተፋሰሷ አገር ታንዛኒያ ፕሬዘዳንት  የተሰየመ ሲሆን የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶችን ውድቅ የሚያደርግ ነው።
ሙዓሊሙ ጁሊየስ ኔሬሬ የሀገሩን ታንጋኒካ(ታንዛኒያን) ነፃነት ተከትሎ በተለይም 1929 ላይ ብሪታንያ የምስራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛቶቿን በመወከል የፈረመችውን ውል ውድቅ በማድረግ የአገራቸውን አቋም ይፋ አድርገዋል። ስምምነቶቹን ከሕዝባቸው ፍላጎትና ጥቅም አንፃር ከመከሩበት በኋላ በሐምሌ 4 1962 ለብሪታንያ፣ ግብፅና ሱዳን በላከው መግለጫ  “በእንግሊዝ ግዛት ሥር ባሉ ሀገሮች ተፈጻሚ ይሆናል የሚለው የ 1929 ስምምነት ድንጋጌዎች በታንጋኒካ(ታንዛኒያ) ከዚህ በኋላ ተፈፃሚነት የላቸውም” የሚል ድምዳሜውን አድርሷል።
ለሶስቱ አገራት መንግስታት የተላከው ማስታወሻም “ታንዛኒያ በቅኝ ግዛት በተፈረመው ስምምነት አትገዛም። የናይል ውሃ ለሁሉም የተፋሰሱ አገራት አስፈላጊ በመሆኑ አጠቃቀሙም ለሁሉም የተፋሰሱ አገሮች በፍትሃዊና ለሁሉም ህዝቦቻቸው ከፍተኛ ጥቅም በሚሰጥ መልኩ መከናወን አለበት” ይላል።
በምንገኝበት ሰሞን ለታዳጊ አገራት እኔ አውቅልሃለው የሚለው የምዕራባውያን መታበይ ለከቱን ያጣበት ነውና የጁሊዮስ ኔሬሬ ድንቅ አባባል እንድገመው፦ “ዴሞክራሲ እንደ ኮካ ኮላ  ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባው ቁስ አይደለም። ይልቁን ከሀገሩ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የምታበለፅገው ሥርዓት እንጂ”
ሙዋሊሙ የታንዛኒያ የመጀመሪያ ፕሬዝደንት፤ ጁሊየስ ካምባራጌ ኔሬሬ
Filed in: Amharic