>

የእምዬ ላባ - መቶ አርባ ዓመቱ . . .  (አሳፍ ሀይሉ)

የእምዬ ላባ – መቶ አርባ ዓመቱ . . . 

አሳፍ ሀይሉ

እምዬ ምኒልክ ከሚታወቁባቸው ነገሮች ውስጥ ሩህሩህነታቸውና መሐሪነታቸው በቀዳሚነት ይጠቀስላቸዋል። ጀግና መሐሪ ነው። እምዬ እንደዚያ ነበሩ። ከሁሉ አብልጬ የምወደው አንድ የእምዬ ምኒልክ መሐሪነት ገንኖ የወጣበት ታሪክ አለ። በእምባቦ ጦርነት ተፈፀመ።
‹አጤ ምኒልክ› በተሰኘው ከዛሬ 113 ዓመታት በፊት በአፈወርቅ ገብረየሱስ በሮማ በታተመ መጽሐፍ.. በታሪክ ‹‹የእምባቦ ጦርነት›› ተብሎ ስለሚታወቀው ጦርነት ተጽፎ የተገኘው ታሪክ ጉድ ያሰኛል፡፡
የእምባቦ ጦርነት በሸዋው ወጣት ንጉስ ምኒልክ እና በጎጃሙ አዛውንት ንጉስ ተክለሃይማኖት መካከል የተደረገ ጦርነት ነበር፡፡
ንጉሥ ተክለሃይማኖት ‹‹በግላጭ ሜዳ እንገናኝና ይዋጣልን›› ብለው ለእምዬ ምኒልክ መልክተኞችን መስደዳቸውን ተከትሎ ነው ጦርነቱ የተነሳው።
ወጣቱ ምኒልክ እነ ራስ ጎበናንና ገረሱ ዱኪን እነ ወሌ ብጡልን አስከትለው… አዛውንቱ ተክለሃይማኖትም እነ አባ ወልደጊዮርጊስና ደጃች ስዩምን አስከትለው እምባቦ ላይ ተገናኙ። እና አሰቃቂ የሚባል የወገን ለወገን ጦርነት ተካሄደ። በግንቦት ወር 1874 ዓ.ም. ነው። የዛሬ 140 ዓመት ወደኋላ ማለት ነው።
በዚያች የእምባቦ እልህ የተሞላባት ጦርነት.. በጎጃሞች በኩል ከተሰለፉትም… ከምኒልክምበኩል ከተሰለፉትም… ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን ጎበዛዝት… ባንድ ጀንበር ህይወታቸውን አጡ!! በእምባቦው ጦርነት ድል የቀናቸው ምኒልክ ነበሩ።
/በነገራችን ላይ፡- ይህ ጦርነት በጎጃምና በሸዋ መካከል የተካሄደ የከፋ ጦርነት መሆኑ ሲታወስ፣ እምዬ ምኒልክ ያሰለፉት ከኦሮሞ ወገንም ከእነ ገረሱ ዱኪና ራስ ጎበና የተውጣጣ ታማኝ ጦራቸውን አስተባብረው መሆኑ ሲታወስ፣ እና እምዬ የዘመቱት በአማራ ወገን ላይ መሆኑ ሲታይ – “ምኒልክ ኦሮሞን ብቻ ነጥሎ ወጋ” የሚለውን የአንዳንድ የእምዬ ከሳሾች ስሞታ ሐሰተኝነትና፣ የሥልጣንና የሀገር ግዛት ጉዳይ እንጂ ምኒልክ ከዘረኝነት ጋር ግንኙነት የሌላቸው ንፁህ ንጉሥ እንደነበሩ መረዳት አያዳግትም። የሆነ ሆኖ አሁን የተነሳሁበት ርዕስ ይህ ስላይደለ ወደ ርዕሴ ልመለስ።/
ታዲያ የእምባቦ ጦርነት በምኒልክ አሸናፊነት አበቃ። አጤ ዮሐንስም ገና ገላጋይ ሆነው በቶሎ ለመድረስ አልበቁም። እምዬ ምኒልክ ግን አሸናፊ ሆነው ሳለ… ለተዋጓቸው የጎጃሙ ንጉስ ተክለሐይማኖት ያሳዩት አንድ  ድንቅ መልካምነት በታሪክ ሲወሳላቸው ይኖራል።
ስለዚሁ በደጃች አፈወርቅ ገብረየሱስ የ1902 “አጤ ምኒልክ” የተሰኘ መጽሃፍ የተዘከረው እንደወረደ እንዲህ ይላል፡-
‹‹የምባቦ፡ ጦርነት…በግንቦት፡ ፲፰፻፸፬
[1874] ዓመተ፡ ምሕረት ፡ ተደረገ። […]
ንጉሥ፡ ተክለ፡ ሃይማኖትም፡ ከዚያው፡
ላይ፡ ከብዙ፡ ስፍራ፡ ቆስለው፡ ተያዙ፡፡
ወዲያው፡ ተይዘው፡ ካጤ፡ ምኒልክ፡
ፊት፡ እንደ፡ ደረሱ፡ […] ይማሩኝ፡ ብሎ፡
ተግር፡ ወደቀ፡፡
‹‹አጤ፡ ምኒልክ፡ ግን፡ እንኳን፡ ቂም፡
ይይዙባቸው፡ አይዞህ፡ ምንም፡ አላደ
ርግህ፡ ተነሥና፡ ሳመኝ፡ ብለው፡ ዝቅ፡
ብለው፡ ደግፈው፡ አንሥተው፡ ሁለቱ፡
ተሳሳሙ፡፡
‹‹አጤ፡ ምኒልክ፡ ንጉሥ፡ ተክለ፡ ሃይማ
ኖትን፡ ከብዙ፡ ላይ፡ ቆስለው፡ ባዩ፡ ጊዜ፡
አዝነው፡ በንጉሥ፡ እጃቸው፡ እንደ፡ ወጌሻ፡
አረሩን፡ ፈልፍለው፡ አውጥተው፡ ቁስሉን፡
በዶሮ፡ ላባ፡ እያጠቡ፡ መድኃኒት፡ እያደረጉ፡
አዳኑ፡፡
‹‹…የእምባቦ፡ ጦርነት፡ ነገር፡ ባጭሩ፡
አደረግሁት፡ እንጂ፡ ብዙ፡ ነበረ፡፡ ከድሉ፡
በኋላ፡ አጤ፡ ምኒልክና፡ ንጉሥ፡ ተክለ፡
ሃይማኖት፡ ሲጨዋወቱ፡- እውነቱን፡ ንገረኝ፡
እስቲ፡ አንተ፡ አሸንፈህ፡ ቢሆን፡ ኖሮ፡ ምን፡
ታደርገኝ፡ ኖሯል? ብለው በጨዋታ ቢጠ
ይቋቸው፤ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ፡-
እውነቱን፡ ልናገረው፡ እኔ፡ ድል፡ አድርጌ፡
ቢሆን፡ ቶሎ፡ አስገድለዎ፡ ነበር፡ አሉ፡፡
ነገሩም፡ በሳቅ፡ ተከተተ፡፡››
/የተጠቀሰውን ፅሑፍ ያገኘሁት – “አፈወርቅ፡ ገብረ፡ ኢየሱስ፡ ዘብሔረ፡ ዘጌ” በሽህ፡ ተ፱፻፩፡ [በ1901] ዓመተ፡ ምሕረት፡ በሮማ፡ ከተማ፡ ካሳተሙት “ዳግማዊ፡ አጤ ምኒልክ ምኒልክ” መፅሐፍ፣ ከገጽ 32-37 ከቀረበው የታሪክ ድርሳን ላይ ነው፡፡/
በዚህ የእምዬ ድንቅ ታሪክ የተነሣ፣ ሁልጊዜም ስለ እምባቦ ጦርነት ሳስብ፣ ከሁሉ ነገር በላይ ያቺ እምዬ ምኒልክ የዶሮ ላባ ይዘው ዝቅ ብለው፣ የንጉሥ ተክለሃይማኖትን ቁስል ተእግራቸው ላይ እስኪድን ድረስ ያጠቡባት፣ አስገራሚ ኢትዮጵያዊ ሰብዕናቸው ትመጣብኛለች።
ለእኔ ያቺ የዶሮ ላባ የእምዬ ምኒልክን ሆደ-ሰፊነትና አርቆ አስተዋይነት ያለማወላወል ታሳየኛለች፡፡ እና አሁንም ከ140 ዓመታት በኋላም፣ ያቺ የእምዬ የዶሮ ላባ፣ ከሆነውና ከተፈጠረው ደም መፋሰስ ሁሉ በላይ ልቃ፣  በእምባቦ ሠማይ ላይ ስትንሳፈፍ ትታየኛለች።
ሳስበው ባሁን ጊዜ ያጣነው ያቺን የዶሮ ላባ ነው። ሳስበው አሁን ያጣነው ያቺን የይቅር ለእግዜር ተዓምር ነው። አሁን ያጣነው መሐሪነት የጀግና ልቡን ያራራው፣ ዝቅ ብሎ ያቆሰለውን ወገኑን ደም በይቅርታና ምህረት የሚያጥብ አንድ የእምዬን ፀጋ የተላበሰ ንጉሥ ነው።
ብዙ የዶሮ ላባዎች ያስፈልጉናል!!! መልካም የይቅርታና የእርቀ-ሠላም ጊዜ ለሁላችን ይሆንልን ዘንድ በረዥሙ ተመኘሁ፡፡
የኢትዮጵያ አምላክ በማያልቅ ምህረቱ ይጎብኘን።
Filed in: Amharic