>
5:21 pm - Monday July 21, 0431

የእርዳታ ገንዘብ ለአፍሪካችን (ለመንግሥታችን)  -  ጠቅሞናል? ወይስ ገድሎናል? (አሳፍ ሀይሉ)

የእርዳታ ገንዘብ ለአፍሪካችን (ለመንግሥታችን)

       –  ጠቅሞናል? ወይስ ገድሎናል?

አሳፍ ሀይሉ

ዳምቢሳ ሞዮ። ዶክተር ዳምቢሳ ሞዮ። ስመጥር ዛምቢያዊት የኢኮኖሚክስ ምሁር ነች። የሀርቫርድ ማስተርሷን፣ ከኦክስፎርድ ዶክትሬቷ ጋር ጋማ ብላ በዓለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት ውስጥ ፖሊሲዎችን የምታማክር በአቋሟ ቀልድ የማታውቅ ድንቅ የምሁር አርበኚት ናት።
ዳምቢሳ ሞዮ እስከ አምና ድረስ አራት በምሁራን የተጨበጨበላቸው አነጋጋሪ መፅሐፎችን ለሕትመት አብቅታለች።
የመጀመሪያው ሥራዋ – “DEAD AID – Why Aid is Not Working and How there is a Better Way for Africa” የተሰኘውና – የብድር (እርዳታ) ገንዘብ አፍሪካን በቁሟ እየቀበራት ነው በማለት አስገራሚና አሳማኝ ትንተና የሰጠችበት ባለ 188 ገፅ እጥር ያለ/ች መፅሐፏ ነው። ሁለተኛው “How the West Was Lost” በሚል የዓለማችንን (በተለይ የዩናይትድ ስቴትስን) የልግስና ፖለቲኮ-ኢኮኖሚ በማብጠልጠል የፃፈችው መፅሐፏ ነው።
አሁን ብዙ የማውራት ዕቅድ የለኝም። በቀጥታ ላነሳ የፈለግሁት የዓለማችን ዲታ መንግሥቶች – ከሳህራ በረሃ በታች ለምንገኘው መናጢ የአፍሪካ መንግሥቶች ያፈሰሱልን – የብድርና እርዳታ ገንዘብ – በድህነት ባህር እየመላለሰ ዘፍቆናል በማለት ረጂዎችን የኮነነችበትን “ዴድ ኤይድ…” የተሰኘችዋን ሸግዬ መፅሐፏን ነው። ወይም ያስደነቀኝን ሀሳቧን ነው።
በቀላሉ – ዳምቢሳ ሞዮ እንዲህ ትለናለች – እስቲ እስከ 2009 (እ.ኤ.አ.) ድረስ ባሉት 50 ዓመታት ውስጥ ለአፍሪካ መንግሥታት በእርዳታ መልክ የፈሰሰውን ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ እንጠይቅ? – 1,000,000,000,000 (አንድ ትሪሊየን) የአሜሪካን ዶላር ነው! /ማለትም አንድ ሺህ ጊዜ አንድ ቢልየን ብር የሚያህል ነው!/ እንዲያውም ከዚያም ይልቃል ትለናለች።
ግን ግን በእነዚህ 50 ዓመታት – ለሚዲያና ለብድር ተቋማት ፍጆታ የሚለፈፍላቸውን የእነዚህን እርዳታ ተቀባይ አፍሪካውያን ዓመታዊ የዕድገት መጠን ለጊዜው ተወት አድርገን – ለባለፉት 50 ዓመታት ከሣህራ በታች ያለነው ድሆች እቅጩ አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገታችን – የአብዛኞቻችን – በዓመት ኔጌቲቭ 0.2 ፐርሰንት ብቻ ነው!! (ባለ ሁለት አሃዝ፣ ገለመሌ… የሚባለውን ቀልድ ለጊዜው እንርሳው!)።
ጠቅላላ የድህነት መጠናችንስ? በ70ዎቹ በአፍሪካችን ከአጠቃላዩ ሕዝብ በከፋ ድህነት ውስጥ ለመኖር የተጣፈው ሕዝብ ዓመታዊ አኀዝ 11 ፐርሰንት (ብቻ) ነበር። በ1998 (እ.ኤ.አ.) ላይስ? 66 በመቶ ገብተን እርፍ አልን። አሁንስ? – አይወራ የኛ ድህነት ነገር። ውሾን ያነሳ ውሾ። ብለን አንገታችንን አቀርቅረን። ዝም።
እንግዲህ – ትለናለች ዳምቢሳ ሞዮ – እንግዲህ ከዓለም ጦርነት ማግስት አውሮፓውያንን (እንግሊዝን፣ ፈረንሳይን፣ ጀርመንን፣ ሉግዘምበርግን፣ ዴንማርክን፣ ወዘተ) ከተንኮታኮቱበት አስከፊ የኢኮኖሚ ውድመት አንሠራርተው ለብልፅግና የበቁት – ከ1948 እስከ በ1952 (እ.ኤ.አ.) – በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በጆርጅ ማርሻል ዕቅድ መሠረት – አሜሪካ በየድርሻቸው ልክ ባከፋፈለቻቸው የ13 ቢሊየን ዶላር ብድር መነሻነት ነው።
ትቀጥልና – ታዲያ ይሄ የአውሮፓ የእርዳታ ገንዘብ ተዓምር 60ዎቹ መጨረሻ ከቅኝ ግዛት ለተላቀቁት አፍሪካውያን ለምን አልሠራም? – ብላ ትጠይቃለች – ዳምቢሳ ሞዮ። ብዙ ምክንያቶች አሉት። እርዳታን በሀገር ደረጃ የግል አዳኛችን አድርገን የመቀበላችን ነገር ዋናው የውድቀታችን ሁሉ ሥር ነው ባይ ናት ዳምቢሳ።
እና ደግሞ በእርሱ ላይ ጥገኛ ሆነን የመቅረታችን ነገር – “The Vicious Cycle of Aid” – ነው። ከዓመት ዓመት ከብድር ድጥ ወደ ብድር ማጥ እየዳከርን መገኘታችን ከድህነት ጋር አጣብቆ ያስቀረን ዋነኛው ሙጫ ነው።
በመንግሥታዊና ፖለቲካዊ ተቋማት የተንሰራፋው ሙስናና የአሠራር ግልፅነት ያለመኖር – ጠያቂ በተጠያቂ አፈሙዝ ሥር ሆኖ መገኘቱ ጭምር ደግሞ – ሌላኛው ከድህነት ጋር በመርዝ ማስቲች ያጣበቀን ደዌያችን ነው።
የይስሙላ ምርጫና የይስሙላ ዲሞክራሲ፣ የመሠረተ ልማት አውታሮች (መንገድ፣ ስልክ፣ ኢንተርኔት፣ ውሃ፣ መብራት፣ ጤና፣ ዕድሜ፣ ወዘተ) ከሕዝባችን አንፃር የአጭር አጭር ሆኖ መገኘት፣ መንግሥት በሁሉ ነገር ጠቅላይ-በዪ ሆኖ መገኘትና የታክስ-ከፋይ-ቤዝ መመንመን፣ የሥልጣን ወንበር የእርዳታ ገንዘብና የዝርፊያ ጥቅም ሽሚያ ዓይነተኛ መሣሪያ ሆኖ መገኘት – እነዚህ የድህነት ሙጫዎቻችን ናቸው።
ያልተማረ እና ወጥ ሆኖ ለመነደፍ ለሚችል ሀገራዊ ፖሊሲ የማያመች የተሰበጣጠረ ሕዝብ ይዞ መገኘት፣ በተፈጥሮ ሀብት ድርቀትም፣ በተፈጥሮ ሀብት ሥጦታም – በሁለቱም መበላላትና ግጭት መቀስቀስ፣ የፖለቲካችን አለመረጋጋት፣ የ99 ፐርሰንቱን ደሀውን ሕዝብ የኑሮ እንጦረጦስ እና የ1 ፐርሰንቱን ሀብታም ሕዝብ እንደ ርችት ወደ ሠማይ የጓነ የቅንጦት አኗኗር ለማቀራረብ (ለማስታረቅ) አለመቻል፣ ወዘተ ወዘተ ሁሉ – እነዚህም – ለዘላቂ ድህነታችን መንሥዔዎች ናቸው።
እና ዳምቢሳ ሞዮ የምትለን የእርዳታ ገንዘብ (ማለትም፦ የአስቸኳይ ጊዜ የእርዳታ ገንዘብና ቁሳቁስ፣ የበጎ አድራጎት ተቋማት የእርዳታ ገንዘብና ተግባር፣ እና የለጋሽ መንግሥታት የረዥም ጊዜ ብድርና ነፃ እርዳታዎች) በእነዚህ  ሁሉ – እኛ የሳህራ በረሃ ከአናታችን ያጠላብን ጥቁር የአፍሪካ ሀገሮች – ከድጡ ወደ ማጡ ተሸጋገርን እንጂ – በፍፁም አልተለወጥንም።
ምስክሩስ? – አንድ፦ ከዓለማችን በ21ኛው ክፍለዘመን የዓለም ኢኮኖሚን ተቀላቅለው ከሌሎች ጋር “የመበልፀግ ተስፋ-የሌላቸው ሀገሮች” (“Failed States”) ተብለው ከተፈረጁት 10ሩ ሀገሮች ውስጥ 7ቱ የሚገኙት – በእዚህ በእኛው ከሠሃራ በረሃ በታች ባለው የሞት ምድብተኞች ቀጣና ውስጥ መሆኑ…።
(ይሄን አንድ ምስክር አላችሁ?… እና ሌላውንስ ልቀጥል ኖሯል? ከተጠራው በላይ በራስ ላይ ሟርትን ደጋግሞ መጥራትማ የበጎም አይደል – ይቅር ግድየለም!)
ቆይ ቆይ – ከዳምቢሳ ማዮ መፍትሄዎች መካከል የተመቸችኝ (ኖኖ ቀልቤን የሳበችው) አንዲት ሁነኛ ነጥብ አለች። እንዲህ የምትል፦
“ለእንደ እኛ ዓይነቱ (ከሳህራ በታች ኗሪ) በድኅነትና በእርዳታ አረንቋ ውስጥ ለተቸከለ እና አማራጭ ያጣ ምስኪን ሕዝብ (እና ሁለት እጁን የተያዘ መንግሥት) – ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የተጋነነ የሕዝባዊ ምርጫ ግርግር አያስፈልገንም!!
“የሚያስፈልገን – ሀገሪቱን አረጋግቶ – ወደ ተፈለገው ሀገራዊ አቅጣጫ – ሰጥ-ለጥ አርጎ ይዞን የሚነጉድ – እና ከማስቲቻችን መንጥቆ የሚያላቅቀን – አንድ ቅን አምባገነን መሪ (ወይም አንድ ቅን አምባገነን ቡድን) – ብቻ ነው!!”
(ለማለት የከጃጀላት የዶክተር ዳምቢሳ ሞዮ የጉድ መፍትሄ!)
ሌላኛዋስ ኮምጠጥ ያለች መፍትሄ? ይቺ ደግሞ “shock therapy” የሚሏት ዓይነት ነች፦ ለጋሽ ሀገራት – በአምስት ዓመት ውስጥ እርዳታቸውን ቀ…ጥ!!! ቁርጥ!..)
አርበኛይቱን ምሁር ዳምቢሳ ሞዮን ከልብ አመሠገንኩ።
እርሱ አንድዬ ፈጣሪ አምላክ – በኪነ ጥበቡ – የእርዳታ ማቃችንን ጨርሶ ይግፈፍልን!
Filed in: Amharic