>

ታላቁ ኢትዮጵያዊ የጥበብ አርበኛ — ታላቁ የ3ኛው ዓለም የጥበብ ተጋድሎ እና እኛ...!!! (አሳፍ ሀይሉ)

ታላቁ ኢትዮጵያዊ የጥበብ አርበኛ — ታላቁ የ3ኛው ዓለም የጥበብ ተጋድሎ — እና እኛ…!!!
አሳፍ ሀይሉ

እንግዲህ አሁን ልንናገር የምንጀምረው ስለ አንድ አብረቅራቂ ኮከብ ነው፡፡ ስለ አንድ ኢትዮጵያዊ ዕንቁ፡፡
የዚህ ሰው እጆች ከእዝጌሩ ተቀብተው የተሰጡት — ግዑዙን ነገር ህይወት ይዘራበት ዘንድ ነው፡፡ የዚህ ሰው አዕምሮ፣ የዚህ ሰው ዕይታ፣ የዚህ ሰው ሁሉ ነገሮች ከፈጣሪው የተሰጡት የእኛን — ምድራዊውን — ህይወታዊውን ነገር ሁሉ — ህያውነቱን እስከ ዝንተዓለም እንደጠበቀ — ከትውልድ ትውልድ ድረስ — ለታሪክ፣ ለንግርት ለለውጥ — ህያው ሆኖ እንዲቀር በሚያስችለን  ዕንቁ ጥበብ ይራቀቅ ዘንድ ነው፡፡
ይህ ሰው ይተኩሳል፡፡ ተኳሽ አርበኛ ነው፡፡ የሚተኩሰው ግን ጠብ-መንጃ አይደለም፡፡ የዚህ ሰው መዋጊያ ዲሞትፈርም አይደለም፡፡ ይህ ሰው አነጣጥሮ የሚተኩሰው — በሚታወቅበት ድንቅ ካሜራው ነው፡፡ ባለ ካሜራው ተኳሽ!
አዳኙ ባለካሜራችን፡፡ በካሜራው ሥርቻችንን እያደነ አነጣጥሮ ያነሳዋል፡፡ በካሜራው ጉድለታችንን እያሰሰ አንጥሮ ያወጣዋል፡፡ በካሜራው አሣዛኝ ታሪካችን ላይ አነጣጥሮ ይተኩሳል — እናም ህያው አድርጎ መልሶ ለራሳችን ያሳየናል ግዳዩን፡፡
ይህ ሰው የመላ ጥቁር ሕዝቦች አምባሳደር ተብሎ እስከመጠራት የደረሰ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው የኢትዮጵያዊነት ልቀት ህያው ማሣያ ነው፡፡ ይህ ሰው አንድ ሰው ነው፡፡ እርሱም ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ የተሰኘ — ድንቅ አብረቅራቂ የጥበብ ኮከብ ነው፡፡
ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ — በየካቲት 25 ቀን፤ 1938 በጎንደር ተወለደ፡፡ ልብ እንበል ይህን፡፡ ፕ/ር ኃይሌ ገሪማ የተወለደው — ፋሺስት ኢጣልያ — በሃገራችን ሕዝቦችና በተዋጓት ጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች ላይ — የምትችለውን ሁሉ ጥፋቶችና መቅሰፍቶች አድርሣ — በአልበገርም ባዮቹ ጀግኖች አርበኞቿ ተጋድሎና አልገዛም-ባይነት — ከዚህች የጥቁር አናብስት ምድር — በመጣችባቸው እግሮቿ — የጀግኖቹን እመጫት ነብሮች ታላቅ ክንድ ቀምሳ — ከሃገራችን በወጣች በ5ኛ ዓመቱ መሆኑ ነው፡፡
እና — ያኔ — የጀግኖች አርበኞች ቆራጥ የአፍሪካዊ አይበገሬ መንፈስ ሳይበርድ — የጀግኖች አርበኞች ደም ሣይደርቅ — የቆራጦች ኢትዮጵያውያን ጉልበት ሣይልም — የኢትዮጵያዊነት፣ የአፍሪካዊነት፣ ታላቅ የአትንኩኝ-ባይነት መንፈስ በምድሪቱ ላይ እንደጋመ — ነው — ኃይሌ ገሪማ — ወደዚህች ጉደኛ የጀግኖች ምድር ብቅ ያለው፡፡
እናማ — ይህ የአርበኞች አይበገሬ መንፈስ — ያ የጥቁር ሕዝቦች ታላቅ የነፃነት ጭስ — ከኃይሌ ጋር — አብሮ ተወለደ — አብሮት ኖረ — እስካሁንም አብሮት አለ፡፡
ብዙዎች ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማን በአንድ ነገር ግለጹት ቢባሉ — መምህር ብቻ ነው ብለው አያቆሙም፡፡ የሚገርም የሲኒማ ድርሰት ፀሐፊ ነው ብለውም አያበቁም፡፡
በዕዝነ ህሊናው መቶ ዓመታትን ወደኋላ ገሥግሶ — ልክ አሁን ያለና በዓይኑ በብረቱ ያየው አስመስሎ — የጥንቱን እንደ አዲስ ሕይወት ዘርቶ — ከሽኖና አስውቦ — የሚያቀርብልህ — አስማተኛ ምልከታዎች ያሉት አስማተኛ የፊልም ዳይሬክተር ነውም ብቻ ብለው አያበቁም — የሚያውቁትን ሰዎች፣ እና ድርሳናት ሁሉ ብትጠይቃቸው — ስለ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ፡፡
ሁሉም የሚነግሩህ — ይህ ሰው “የጥቁሮች ነፃነት ሃዋርያ ነው!” ብለው ነው፡፡ ብዙዎችን ብትጠይቃቸው — ይህ ሰው የዓለምን ጭቁኖች ታሪክ — በካሜራው ጥበብ — እንደ አዲስ አድርጎ የተረከ — እንደ አዲስ አድርጎ ያሳየ — እንደ አዲስ አድርጎ በታሪክ ድርሳን፣ በፊልም ስክሪን፣ ለታሪክ ያኖረ — ድንቅ የፀረ-ባርነት ትግል ግንባር ቀደም አነጣጥሮ ተኳሽ ነበር ብለው ነው የሚነግሩህ!!!
በካሜራው እያነጣጠረ፣ በካሜራው የሚነሣ፣ የጥበብ ጀግና ነውና — የጭቁን ሕዝቦችን እውነተኛ አይበገሬነት — በካሜራው እያንበለበለ የሚተኩሰው — ይህ የኩሩ ማንነታችን አብሣሪ — ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ፡፡
ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ — በ1979 ዓመተ ምህረት — በእንግሊዝ ሃገር፤ በኤደንበርግ ዩኒቨርሲቲ በጎብኝ ሌክቸረርነት ተጋብዞ — ያቀረባቸው ሦስት ሌክቸሮች ነበሩ፡፡ በመጽሐፍም ታትመውለታል፡፡
እነዚያ የኃይሌ ገሪማ ሌክቸሮች ‹‹የሶስተኛው ሲኒማ ጥያቄዎች›› በሚል የብዙ የዘርፉን ምሁራን የተጻፉ የጥናት ጽሑፎች የተጠረዙበት ዕውቅ መጽሐፍ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ያ መጽሐፍ የጥቁር ሕዝቦችን፣ የሶስተኛውን ዓለም ሕዝቦች፣ የሲኒማ ጥበብ በሚተነትኑ ድርሳናት ላይ ሁሉ — እንደ ዋና ዋቢ መጽሐፍ ተጠቅሶ ታገኘዋለህ፡፡ እዚያ መጽሐፍ ላይ ፕ/ር ኃይሌ — በገጽ 65 ላይ — ‹‹ሀ›› ብሎ ጽሑፉን ሲጀምር — እንዲህ ብሎ ነው የሚጀምረው፡—
‹‹እኔ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለኝ፣
በስደት ሥራ እየሠራሁ በምኖርባት
አሜሪካ ነዋሪ የሆንኩ ኢትዮጵያዊ ነኝ››
ብሎ ነው፡፡ እንዲህ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነቱን የሚያስቀድም ቁርጥ የአፍሪካ ልጅ! አፍሪካዊነትህ፣ ጥቁርነትህ፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነትህ፣ ኢትዮጵያዊ መልክህ፣ እንደነብር የተዥጎረጎረው የአናብስት ማንነትህ — በዓለም ፊት ሊያኮራህ፣ ሊያጀግንህ እንጂ — እንደምንስ ብሎ አንገትህን ሊያስደፋህና ሊያሸማቅቅህ ይችላል?
በኢትዮጵያዊነት መሸማቀቅ በፍፁም አይታሰብም። ያ እንደማይሆን ነው ኃይሌ ገሪማ — በምሁራን መድረክ፣ በመጽሐፉ፣ በአንደበቱ ሁሉ — ‹‹እኔ ኢ ት ዮ ጵ ያ ዊ ነኝ!›› ሲል የሚገኘው፡፡
እንዴ!? ይህ ሰው እኮ ከአርበኞች ማጀት ውስጥ የተወለደ፣ የአርበኞች መንፈስ ባረበበባት ነፃይቱ የ1930ዎቹ ኢትዮጵያ ዘመን የተወለደ ልባም ኢትዮጵያዊ እኮ ነው! ንፁህ ልባም ኢትዮጵያዊ፡፡
ደስ የሚልህ ደግሞ — በዚያ መጽሐፍ ላይ — ስለ ሶስተኛው ዓለም የሲኒማ ፍልስፍና — እየተነተነ ብዙ ጥናቶችን ያቀረበው ሌላ ኢትዮጵያዊም ሰው ስታገኝም ጭምር እኮ ነው — የዩሲኤልኤ ፕሮፌሰሩን — በ2003 ዓ.ም. በ70 ዓመት ዕድሜው በሞት ያጣነውን — የድንቁን ኢትዮጵያዊ ምሁር — የፕሮፌሰር ተሾመ ወልደ ገብርዔልን የጥናት ጽሑፎች፡፡
ዛሬ ዛሬ የበዙ ድርሳናት ላይ የፕ/ር ተሾመ ወልደ ገብርኤልን ስም ታያለህ፡፡ ‹‹የሶስተኛው (ዓለም) ሲኒማ›› ምን ማለት እንደሆነ ፍቺ የሰጠው እርሱ ነውና — ከፅንሰ-ሃሳቡ ፈጣሪዎች — ከላቲኖቹ ከእነ ፈርናንዶ ሶላና እና ኦክታቪዮ ጌቲኖ ቀጥሎ ማለት ነው፡፡
ኃይሌ ገሪማ በተማረበት በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ — ከአጋሮቹ ጋር — የተሰጠው ቅፅል ስም ነበር፡— የ‹‹ኤል ኤ አመፀኛ!›› ‹‹የሎስ አንጀለስ እምቢ-ባዮች!›› የሚል፡፡ ‹‹LA Rebels›› ፣ ‹‹LA Rebellion›› የሚሰኝ፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ — ይህ ሰው — የትም ሄደ የት — አልበገርም ባይ እንደሆነ — ማሣያ የሚሆን — ምን ሌላ ማስረጃ ያስፈልጋል?!
ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ የዳይሬክቲንግ መምህር፣ የራሱን ፊልሞች በራሱ በጀት በመሥራት የሚታወቅ — አንቱ የተሰኘ አንጋፋ ፊልም-ሠሪ ነው፡፡
በእርሱ የተኮተኮቱ በርካታ የፊልም ባለሙያዎች — በየፊልም ኢንዱስትሪው ታላቅ ስኬትን ተቀዳጅተዋል፡፡ ለእርሱም ትልቅ አክብሮት አላቸው፡፡
እርሱ ግን በአንድ ወቅት ከሆሊውድ ፊልሞች ምኑን ወይም የትኛውን እንደሚያደንቅ ሲጠየቅ የሰጠው መልስ ብዙዎችን ሲያነጋግር ነበር፡፡ እንዲህ ነው ያለው፡—
‹‹እኔን እንዴት ስለ ሆሊውድ ፊልሞች
ትጠይቀኛለህ? ሌላ ሰው ብትጠይቅ
ይሻልሃል፡፡ እኔ በዕድሜዬ የሆሊውድ
ፊልሞችን ተመልክቼ አላውቅም፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ የአንድ የሆሊውድ
ፊልም ጀምሬ ነበር፡፡ አልጨረስኩትም።
እርሱንም አጋጣሚ ያገኘሁት በኢትዮጵያ
አየር መንገድ እየተጓዝኩ እያለ ስለተከፈተ
አማራጭ በማጣቴ ያደረግኩት ነው!››፡፡
ይገርማል ይህ ሰው፡፡ እርሱ የሚያስተምራቸው ተማሪዎች ናቸው ሆሊውድ ላይ ፊልሞችን የሚሰሩት፡፡ እነርሱን ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያገኛቸዋል፡፡ እና ምን ልሁን ብሎ ነው የእነሱን — እርሱ ‹‹ዕቃ-ዕቃ›› ወይም ‹‹ቀባ-ቀባ›› ብሎ የሚገልጸውን — የሆሊውድ ፊልም የሚመለከተው?፡፡
ግን ግን — ኃይሌ — ስለ ምን ‹‹ሆሊውድ››ን ጠምዶ ያዘው? — ምክንያቱ ይህ ነው፡፡
በ1960ዎቹ ‹‹ባለቀለም ቆዳ ያላቸው ሕዝቦች›› (‹‹ከለርድ ፒፕልስ››) የሚባሉት — ጥቁሮች፣ ሕንዶች፣ ሂስፓኒኮች፣ ቻይኖች(?)፣ እና የመሣሰሉት ሕዝቦች ናቸው። በእነዚህ ባለቀለም ሕዝቦች ላይ በነጭ መንግሥታት የሚካሄደው የጅምላ ዘረኝነትና ከባርነት ያልተናነሰ ኢ-ሰብዓዊ አገዛዝ — ከእነዚህ ማህበረሰቦች የበቀሉ ምሁራንን — ለአንድ ታላቅ እንቅስቃሴ አነሳሳቸው፡፡
ያም በስነፅሑፍ፣ በሥዕል፣ በሙዚቃ፣ እና በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች ውስጥ ያሉ የባለቀለም ዝርያ ያላቸው ምሁራን — ሆነ ብለው — በነጮቹ ከሚነገረው ማንነት የተለየ፣ በቅኝ ገዢዎቹ ከተጻፈው ታሪክና ትረካ የተለየ፣ ኢምፔሪያሊስቶቹ “ጥቁሮች እነዚህ ናቸው” ብለው ከሚስሏቸው አካይስት ምስል የተለየ ለማንፀባረቅ የተጀመረ ጥበባዊ እንቅስቃሴ ነበር።
የጥቁሮች፣ የላቲኖች፣ የህንዶች፣ የሌሎችም በጭቆና ሥር ያሉ ሕዝቦችን — እውነተኛውን — በኢምፔሪያሊስቶች ያልተበረዘውን፣ ያልተከለሰውን፣ ያልጠለሸውን — እውነተኛውን — የተለየውን — የራሳቸው የሆነውን — ድንቅ ልዩ ማንነታቸውን — በጥበብ ሥራዎቻቸው ሁሉ ሊያንፀባርቁ — ተማምለው፣ ተስማምተው፣ ቆርጠው እንዲነሱ አደረጋቸው፡፡
እናም ‹‹ዘ ብላክ ሬኔይሳንስ ሙቭመንት›› (‹‹የጥቁሮች ለተሻለ ለውጥ የመነሣሣት እንቅስቃሴ››) በምድረ አሜሪካ ተወለደ፡፡
የጥቁሮችን የተለዩ ጽሑፎች ይፅፉ የነበሩት እነ ዲ ኤች ሎረንስ፣ የጥቁሮች ሥዕል ይህ ነው ብለው በልዩ የአሳሳል ዘይቤ የሠሩት እነ ጃክሰን ፖሎክ፣ እነ እስኩንድር ቦጎስያን፣ የጥቁሮች ሙዚቃ ይሄ ነው ብለው ጉድ የሚያሰኝን የሙዚቃ ዛር ለምድረ አሜሪካ ብቻ ሣይሆን ለመላው ዓለም እንዲበቃ አድርገው ያንበለበሉት እነ ዱክ ኤሊንግተን፣ እና የሃርለም ሬኔሰንስ የጃዝ ሙዚቃ ጥቋቁር ፈርጦች በየሙያ መስኩ ተነሡ፡፡
ታላቁን፣ በጨቋኞች ተዳፍኖ የቆየውን፣ ያን ኃያል የጥቁሮች የጥበብ መንፈስ ተላብሰው — የተዛባን ታሪክ ሊያድሱ፣ ሆነ ብሎ እንዲጨቀይ የተደረገን ታላቅ ማንነት አንፅተው ሊገልጡ፣ ሁሉም — በታላቅ የአርበኝነት መንፈስ — ለታላቅ የጥበብ ተጋድሎ — ሆ ብለው በአንድነት ተነሡ፡፡
ኃይሌ ገሪማም በበኩሉ — ጥበብን፣ እና ያን የማይሞተውን ታላቁን ኢትዮጵያዊ የአርበኝነት መንፈሱን ታጥቆ — የሠለጠነበትን፣ የተራቀቀበትን፣ ያን አነጣጥሮ የሚተኩስበትን የጥበብ ነፍጥ — ካሜራውን አንግቶ — የጎበጠውን የጭቁኖች ታሪክ ሊያቃና፣ ከጠቆረው በላይ ጽልመት የተጋረደበትን የአፍሪካውያን የጭቆና ታሪክ፣ እና ታላቁን የተዳፈነ የአፍሪካውያንን የአይበገሬነት መንፈሥ — ከተቀበረበት ነፍስ ዘርቶ ሊያስነሣ — እነሆ ወደ ፍልሚያው ጎራ ተቀላቀለ፡፡
ለኃይሌ ገሪማ — እና ለአቻ የሙያ ጓደኞቹ — ሆሊውድ ማለት — እኛን ጥቁሮችን — እና ሌሎችን ዘሮች፣ ባህላችንን፣ ማንነታችንን፣ ታሪካችንን፣ እውነተኛ ፍላጎታችንን — እኛ እንደሆንነው ሣይሆን — ለገዢዎቹ በሚመች መልኩ ጠፍጥፎ — አርክሶ — አሰይጥኖ — አስቀይሞ — ለታዳሚ የሚያቀርብ ተቋም ነው፡፡
ለኃይሌ ገሪማ — ሆሊውድ ማለት — ከእውነት የራቀ — የዜጎችን አዕምሮ — በገዢዎች ዕዝነ አምሳል ሊቀርፅ የተነሳ — የውሸት መፈልፈያ ተቋም — የጭቁን ሕዝቦችን አሰቃቂ ጭቆና ከዓለምም ከራሳቸው ከጭቁኖቹም ዕይታ ለመሰወር የሚሰራ — የሐሰት መፈልፈያ — የጭቆና ማራመጃ — ዓለምን ከእውነቱ የማወናበጃ ኢንዱስትሪ ነው፡፡
ታዲያ እነ ኃይሌ ገሪማ ይህንን ብቻ ብለው አላቆሙም፡፡ የዓለምን ጭቁን ሕዝቦች ሁሉ እውነተኛ ታሪክ፣ እውነተኛ ያልተቀባባ የባርነት ህይወት፣ እውነተኛ የሕይወት፣ የኑሮ ጉስቁልና፣ በጨቋኞች ያልተበረዘ፣ በገዢዎች ያልደበዘዘ… እውነተኛ ውስጣዊ የጀግነት መንፈሥ የሚያሣይ ራሱን የቻለ የፊልም ኢንዱስትሪ ለምን አናቋቁምም? ብለው አሰቡ።
አስበው ብቻም አልቀሩም። ከምዕራባዊው የታይታና የዋዋቴ፣ ግልብ የሆሊውድ የፊልም ኢንዱስትሪ — ማለትም ከ1ኛው ዓለም ሲኒማ — በቅርፁም፣ በይዘቱም፣ በአሠራሩም፣ በዓላማውም፣ በሥርጭቱም፣ በሁሉ ነገሩ የሚለይ — ራሱን የቻለ የሲኒማ ፍልስፍናን ሰንቀው ተነሱ፡፡
ከዚያም ካለፈ ደግሞ — ይህ የሚፈጥሩት 3ኛው የሲኒማ ፍልስፍና — 2ኛው የሲኒማ ዓለም ተብሎ ከሚታወቀው — እና ከ1ኛው ዓለም የሆሊውድ ሲኒማም ከሚለየው — ከህንዶቹ የ2ኛው ዓለም የቦሊውድ ሲኒማም ራሱ የተለየ እንዲሆንም ጭምር ተለሙ — እነ ኃይሌ ገሪማ፣ ሴኔጋላዊው አንጋፋ የፊልም ሠሪ እነ ኦስማን ሴምቤን፣ ኢትዮጵያዊው (የባርባዶስ ተወላጁ) እነ ፕሮፌሰር አብይ ፎርድ፣ እና ሌሎችም የፊልም ዓለም ድንቃ-ድንቅ ፈርጦቻችን፡፡
እነ ኃይሌ ከ1ኛው ዓለም የሆሊውድ ሲኒማ ለመለየት ሲወስኑ፣ የ2ኛው ዓለም የቦሊውድ ሲኒማም ያለበትን ግድፈት በሚገባ አስምረውበት ነበር።
ምንም እንኳ — የ2ኛው ዓለም የቦሊውድ የፊልም ኢንዱስትሪ — ለአጫዋችነትና የኢምፔሪያሊስቶችን ማንነት ብቻ ለማቆየት ከሚሰራው ከ1ኛው ዓለም የሆሊውዱ የፊልም ኢንዱስትሪ በመሠረተ-ሃሳብ ደረጃ የተለየ ቢሆንም — በዓላማው ግን በዋነኝነት — ለንግድ ትርፍ ሲባል እየተመረተ የሚቸበቸብ የመሆኑ ነገር አልተዋጠላቸውም።
ምንም እንኳ ይህ የቦሊውድ የእስያኖች የፊልም ኢንዱስትሪ — የራስን ሃገር-በቀል የሕንዳውያን ሕዝቦች ባህልና ማንነት ማንፀባረቂያ ሆኖ ቢያገለግልም — ለቱሪስት መሣቢያነት እየተባለ ግን — ሕንዶችን እንደሆኑት እንደ እውነተኛ ማንነታቸው ሣይሆን — የውጭ ሃገር ሰዎች እንደሚስሏቸው ያለ ውሸተኛ ማንነት እያላበሰ የሚሰራ በመሆኑ — እነ ኃይሌ ገሪማ፣ እነ ጌቲኖ፣ እነ ሶላና፣ እነ ሴምቤን፣ እነ ተሾመ፣ እና ሌሎችም በርካቶች ሃቀኛ የጥበብ ፋናዎች አንድ ቁርጥ ውሳኔ አደረጉ፡፡
ያም ውሳኔ ይህ ነበር፡— የ3ኛው ዓለም ሲኒማ — ከ1ኛውም ዓለም ሲኒማ የተለየ፤ ከ2ኛውም ዓለም ሲኒማ የተለየ ሆኖ — ለተረሱ፣ ለተረገጡ፣ ታሪካቸውና ማንነታቸው ተከርቸም እንዲገባ ለተደረጉ ሕዝቦች እውነተኛ ማንነት ማሣያ፣ እና ካሉበት የጭቆና ካቴና ነፃ ይወጡ ዘንድ ለማታገያ መዋል አለበት።
የ3ኛው ዓለም ሲኒማ — ጭቁን ሕዝቦች እውነተኛ አይበገሬ የኋላ ማንነታቸውን እንዲፈልጉ፣ እንዲያገኙትና ያንን ያገኙትን ታላቁን ማንነት እንዲላበሱት፣ በአንድነትም ‹‹ሣንኮፋ ሣንኮፋ ሣንኮፋ›› ብለው በሕብረት እየዘመሩ — የጥንቶቹን የአያቶቻቸውንና የቅድመ-አያቶቻቸውን ታላቁን የአፍሪካውያን የጀግንነትና የአርበኝነት መንፈስ ተላብሰው — ለህዳሴያቸው፣ ለታላቅነታቸው፣ ለከፍታቸው “ሆ!” ብለው እንዲነሱ — ተግቶ የሚሠራ — ፍፁም እውነተና ማንነትን የተላበሰ — ልዩ የሆነ — ራሱን የቻለ — የጭቁን ሕዝቦች የፊልም ኢንዱስትሪ ይሆናል ብለው ተነሱ — ይህ — የ3ኛው ዓለም ሲኒማ፡፡
እና ለእንዲህ ዓይነቱ አፍሪካዊ ተፋላሚ ጥበበኛ — የሆሊውድ አርቲፊሺያል ‹‹ድሪንቶ›› ወይም (ከይቅርታ ጋር) ‹‹አርቲ-ቡርቲ›› — ከቶውኑ ምን ሊፈይድለት? — እናም አያየውም፡፡ በእኛ አውሮፕላን ላይ ካልሆነ በቀር፡፡
ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ በአሜሪካ ዩሲኤልኤ የፊልምን ጥበብ ከተማረ በኋላ — በወቅቱ ለጥቁሮች መብት ሆ ብለው እጃቸውን ጨብጠው እንደተነሱት — እንደ ዘመነኞቹ አፍሪካን-አሜሪካውያን አርበኞች — እንደ እነ ማርቲን ሉተር፣ እንደነ ማልኮልም ኤክስ፣ እንደነ ሁዌይ ኒውተን፣ እንደነ አንጄላ ዴቪስ፣ እንደ ቀደሙትም እንደነ ማርከስ ጋርቬይ ሁሉ — እርሱም — እነሆ የጥበብ መሣሪያውን ሰንቆ — ለታላቅ ግዳይ በግንባር ቀደምትነት ተሠለፈ፡፡
እናም የተረሱ ያልተዳሰሱ በጠንካራው የጭቆና መዳፍ ውስጥ የወደቁ እውነተኛ የተራቆቱ ነፍሶችን እውነተኛ ታሪክ በፊልም ሥራዎቹ ይሸነሽነው ገባ፡፡
ገና ያኔ — በ1964 ዓመተ ምህረት — ኃይሌ ገሪማ — ‹‹አወር ግላስ›› የተሰኘና ‹‹ቻይልድ ኦፍ ሬዚስተንስ›› የተሰኘ — ሁለት ፊልሞችን ሠራ፡፡ ቆየት ብሎ በ1968 ዓመ ምህረት ደግሞ ሁለት ፊልሞችን አከታትሎ እንካችሁ አለ፡— ‹‹ቡሽ ማማ››፣ እና ‹‹ምርጥ ሶስት ሺህ ዓመት›› (ወይም ‹‹ሃርቨስት 3000 የርስ››) የሚሉ ፊልሞቹን፡፡
ኃይሌ — ቡሽ ማማን ሲሠራ — በወቅቱ በታወቁ ሚዲያዎች ከሚቀነቀኑት — በሃሺሽ፣ ግድያ፣ እና የጨቀዩ የሴተኛ አዳሪ ሕይወቶች የተሞሉትን ስለጥቁሮች ህይወት የሚያወሱ ፊልሞችን ታሪክ በሚቀለብስና — የጥቁሮች እውነተኛ ሕይወት ይኸውላችሁ፣ የዚያም ምክንያቱ ይኸውላችሁ ብሎ ቅልብጭ አድርጎ ያሳየበትን የመሪ አቀንቃኟን ባተሌ የዶሮቲንና — ቬትናም ዘምቶ ወደሃገሩ ሲመለስ የጀግና አቀባበል ይደረግልኛል ብሎ ሲጠብቅ — ያላለመው ውርደት፣ ሥራ-አጥነትና ዘረኝነት የጠበቀውን ባሏን — የቲ.ሲ.ን ታሪክ የሚዘግብ ፊልም ነበር፡፡
በዚህ ፊልሙ — ኃይሌ — ድህነት፣ ውርደት፣ እና ተከትለው የሚመጡት አስከፊ ህይወቶች — ሆነ ተብሎ የተደራጀ የገዢዎች ተቋማዊ ጭቆና ውጤቶች መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ ለዓለም አሣየ፡፡ እናም ታሪክ ሰራ፡፡ እውነተኛውን የ3ኛውን ዓለም ሲኒማ እንካችሁ ብሎ፡፡
ደግሞ ኃይሌ ያን እውነተኛ የጥቁር አናብስትን የጀግንነት መንፈስ፣ ያን የጥቁሮች የማያልቅ የአርበኝነት ብርታትን ለማግኘትም የፈለገ ነው የሚመስለው ከላይ የገለጽነውን ‹‹ምርጥ ሶስት ሺህ ዓመት››ን ሊሠራ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ፡፡
በዚያም ፊልሙ በፊውዳላዊቷ ኢትዮጵያ የሚደርስበትን ተነግሮ የማያልቅ የጭቆና ቀንበር ሰባብሮ ጀግንነቱን ስላስመሰከረ ልባም ጭሰኛ ታሪክ ተረከበት፡፡
በ1970ም ዓመተ ምህረት ኃይሌ ወደ አሜሪካ ተመልሶ የሠራው፡- ‹‹ዊልሚንግተን 10 ዩኤስኤ 10000›› የተሰኘ ፊልሙ — የአሜሪካኖች የፍትህ ሥርዓት ምን ያህል በዘረኝነት የተጨናቆረ፣ የፍትህ ተቋማቱ ምን ያህል የግፈኞችና ዘረኞች መሣሪያ እንደሆኑ — ዊልሚንግተን ቴን እየተባሉ የሚጠሩትን 9 ጥቁሮች እና 1 ነጭ ፍርደኞች ሕይወት በመዳሰስ ለዓለም አሣየ፡፡
የጥቁሮችን አስከፊ የከተማ ድህነትና ጉስቁልና የሞላው እውነተኛ ህይወት ደግሞ እንዲሁ በ1976 ዓመተ ምህረት በሠራው — እና ዳግመኛ ከቬትናም ጦርነት ዘመቻ መልስ በድህነት ሊኖር ስለተጣፈ ስለአንድ ጥቁር ወጣት አሣዛኝ ህይወት — ‹‹አሽዝ ኤንድ ኤምበርስ›› በተሰኘ ፊልሙ — ዳግም እውነቱን በውብ ታማኝ ካሜራዎቹ እያፍረጠረጠ ተረከው፡፡
በ1978 ዓመተ ምህረት ደግሞ ስለአንድ ታዋቂ ጥቁር አሜሪካዊ ገጣሚ ህይወትና ስለኖረበት ዘመን ገጽታ የሰራውም ፊልም አለ፡- ‹‹አፍተር ዊንተር፡- ስተርሊንግ ብራውን›› የሚል ዶክመንተሪ (ዘጋቢ) ፊልም፡፡
እና በመጨረሻ — ይህ የጥቁሮች ነፃነት ታጋይ ጥበበኛ — ይህ የጥቁሮች ታሪክ ነጋሪ — ይህ የጭቁኖች ሕዝቦች አንደበት — ይህ የተረሱ ሕዝቦች ዓይን — ፕሮፌሰር ኃይሉ ገሪማ አራት ዕውቅ ፊልሞችን ሠራ፡— ‹‹ሣንኮፋ››ን (በ1986 ዓ.ም.)፣ ‹‹ኢምፐርፌክት ጆርኒ››ን በ1987፣ ‹‹አድዋ — የአፍሪካውያን ድል››ን በ1992 ዓ.ም.፣ እንዲሁም ‹‹ጤዛ››ን በ2001 ዓ.ም.፡፡
የዚህ ሰው ገድል እና ሥራዎች፣ እና አስደናቂ ታሪኩ፣ እና ሥኬቶቹ — እንኳን እንደኔ ባለ ኢምንት ብዕር — በሙያው በተካኑት ተማሪዎቹና የሙያ አጋሮቹ በሆኑት (ለምሳሌ በኢትዮጵያዊው የሃዋርድ ፊልም ምሁር በእነ ዳዊት ላቀው) ብዕር እንኳ ቢፃፍ ቢዘከር ራሱ — ለኃይሌ ገሪማ ህይወት እና ሥራዎች — ለዚህ ድንቅ ኢትዮጵያዊ አብረቅራቂ የጥበብ ፋና —እንኳን ይህች ገጽ — ብዙ ጥራዛት፣ ብዙ የፊልም ሪሎች አይበቁትም!!!
እናም ሌላ ጊዜ የምንመለስበት ሆኖ — ለአሁኑ — ስለ ሁለቱ ፊልሞቹ ብቻ ጥቂት ብለን እናብቃ፡፡ ስለ “ሳንኮፋ” እና ስለ “ጤዛ”፡፡
የፕ/ር ኃይሌ ‹‹ሣንኮፋ›› ፊልም ሥፍራውን ጋና ውስጥ ያደረገ ሥራ ነው፡፡ ጋና ውስጥ በውቅያኖሱ ዳርቻ — በኬፕ ኮስት ላይ — የሚገኝ — በጥንት የባርነት ዘመን — ከገባህበት የማትወጣበት — ‹‹ዘ ዶር ኦፍ ኖ ሪተርን›› የተሰኘ — ትልቅ አስፈሪ ጥንታዊ በር ያለበት ሥፍራ አለ።
የጥንት አፍሪካውያን ባሮች — ወደ አሜሪካ በባርነት በመርከብ ታፍገው ከመጫናቸው በፊት — ተጠርዘው፣ ተከርችመው የሚከርሙበት የባሮች ማራገፊያ ወደብ ነው የታሪኩ መጀመሪያ ሥፍራ፡፡ እና በዚህ ሥፍራ አንድ የአፍሪካውያን አታሞ ይደበደባል፡-
‹‹ሣንኮፋ! ሣንኮፋ!
እናንት የሞታችሁ መንፈሶች!
ተነሡና ታሪካችሁን ተናገሩ!››
እያለ ይጀምራል፡፡ “ሣንኮፋ” ማለት በጋናውያን የአካን ቋንቋ — “የአሁኑን ማንነትህን ለማግኘት ወደ ኋላህ ወደ ጥንቱ ታሪክህ ተመልሰህ መዳሰስ” ማለት ነው፡፡
እና በዚያን ሠዓት በዚያ ሥፍራ የተገኘች “ሞና” የተሰኘች አፍሪካ-አሜሪካዊት ሴት — እዚያ ጥንት ከገባህ የማትወጣበት የባሮች ቅፅር ውስጥ ስትገባ — የሰማችው የሣንኮፋ አታሞ — የጥንታውያንን የሞቱ አፍሪካውያን ባሮች መንፈስ ይቀሰቅስና — እርሷም — ወደ ጥንቱ የባርነት ዘመን — እንደ ‹‹ታይም ትራቭል›› ወይም ‹‹ፍላሽ ባክ›› በመሠለ የኋልዮሽ የዘመን ጉዞ ተመንጭቃ — በባርነት ካቴና ውስጥ ትገባለች፡፡
በዚያ ቅፅር በሣንኮፋ መንፈስ ወደ ባርነት ዘመን የተመለሰችው ሞና — ራሷን ምን ሆና ታገኘዋለች? በባርነት ወደ አሜሪካ ልትሸጥ የተዘጋጀች አፍሪካዊት ባሪያ ሆና፡፡ እና ነጮቹን የባሪያ ፈንጋዮችም ታገኛቸዋለች፡፡
በመጀመሪያ ራሷን ትክዳለች፡፡ ‹‹እኔ እኮ አሜሪካዊ ነኝ! አፍሪካዊ አይደለሁም!›› ትላለች፡፡ አይሰሟትም፡፡ “ማንም ሁኚ ማን.. አንቺ አንድ ባሪያ ነሽ!” ነው መልሳቸው፡፡ እና የስቃይ መዓት ያወርዱባታል፣ ይተለትሏታል፣ ይደፍሯታል፡፡ በመጨረሻም ወደ ላፋዬት ተወስዳ፣ በባሮች የሚታረስና የሚለቀም ሰፊ የአሜሪካ የጥጥ እርሻ ላይ በባርነት ትሰማራለች፡፡
እዚያ ሞና እጅግ የሚያሰቅቁትን የባርነት አስከፊ ገጽታዎች ትመለከታለች፡፡ ጆ የሚባል ከነጭ የተወለደ ጥቁር አፍሪካዊ የገዛ እናቱን ክርስቲያን ስላልሆንሽ ብሎ ሲገድል፣ ራሱን ሲያጠፋ ትመለከታለች፡፡ ልታመልጥ ስትል ተይዛ ለከፋ ስቃይ ትዳረጋለች፡፡
ሞና አፍቃሪም ታገኛለች፡፡ ከሕንድ በባርነት የመጣ፡፡ እውነተኛ የአፍሪካውያንን ጭቁን ማንነት ትረዳለች፡፡ እሱዋም ከእነዚያ ጋር አንድ እንደሆነች ትረዳለች፡፡ እና ለነፃነታቸው ከሚታገሉ ህቡዕ ቡድኖች ጋር ትቀላቀላለች፡፡ በመጨረሻም ነፃ ትወጣለች፡፡
በመጨረሻም ሞና ልክ በሣንኮፋ የከበሮ መንፈስ ወደ ኋላው ዝርዮቿ ወዳሳለፉት አስከፊ የባርነት ህይወት ተመልሳ — ያን አስከፊ ቅድመ-አያቶቿ የከፈሉትን መስዋዕትነት ስትረዳ — የራሷን እውነተኛ አፍሪካዊ ማንነት ተላብሳ ዳግም በገባችበት — ማንም ከገባ በማይመለስበት ‹‹ዘ ዶር ኦፍ ኖ ሪተርን›› በር — በነጻነት ትመለሳለች፡፡
ከበላይዋ ደግሞ የሣንኮፋን — የአፍሪካውያንን ቀደምት አይበገሬ መንፈስ የምትጠራው — የሣንኮፋ ዘማሪ ወፍ — በነፃነት ወደ አፍሪካ ሠማያት እየበረረች ስትቀዝፍ ትታያለች — ነፃነትን ለአፍሪካ ምድር! አንድነትን ለአፍሪካውያን! አፍሪካዊነትን ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ እየዘመረች!!!
እንዲህ ነበር እንግዲህ የኃይሌ ገሪማ — እውነተኛው — ከንፁህ አፍሪካዊ አርበኛ መንፈስ የተቀዳ — የሣንኮፋ የነፃነት ቅዳሴ!!!
የአፍሪካውያንን መንፈስ በካሜራዎችህና በማይነጥፍ አዕምሮህ ኃይል የቀሰቀስህ — አንተ ጋሼ ኃይሌ — አንድዬ የአፍሪካውያን አምላክ — ረዥም ዕድሜን ይሰጥህ ዘንድ በእናቶቻችን ምርቃት መረቅኩህ — አውሎ ያግባህ — ዕድሜ-ይስጥህ! ኑር! ተጓዝ! እና ሌሎችንም መንገድ ምራ!!!
አሁን በመጨረሻ እናገርለታለሁ ስላልኩት — ራሴም የመጀመሪያዋ ዕለት ካየሁበት የኤግዚቢሽን ማዕከል ሲኒማ ቤት — በፊልም-ነጣቂዎች ተሞጭልፎ በዲቪዲ እስከደረሰኝ የሥርቆት ኮፒ ድረስ ደግሜ ደጋግሜ ስላየሁት — የፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ — ‹‹ጤዛ›› ፊልም አስታወስኩ።
እና የመሪ ተዋናዩን የአንበርብርን — እና የከበበውን እግር-ተወርች የሚቆላልፍ የሃገራችን ከባቢ ህይወት፣ የመከነ ተስፋ፣ ወደፊት ያለዘመን ብራ ይሆንልን ዘንድ የምናሳድረውን የነገአችንን ጥልቅ ሕልም፣ እና እንደ አውራሪስ ቆዳ የጠነከረውን እርስበርሱ የማይጨራረሰውን የነገውን ኢትዮጵያዊ ልባም ትውልድ — ይህን ሁሉ — በዚህች አጭር ሥፍራ ለመተረክ — ጊዜና ቦታ አጠረኝ፡፡
እና ያን የኃይሌን ዝክር ደግሞ — በሌላ ጊዜ ራሱን በቻለ ጽሑፍ ላካፍል ቃል ገብቼ — ለአሁኑ ተሰነባበትኩ፡፡ የደበዘዘብንን መንገድ ለሚያመላክቱን፣ የጠፋብንን ማንነት ለሚጠቁሙን፣ ለእነዚያ እውነተኛ የአፍሪካ ጥቁር አንበሶች፣ ምሁር ትውልዶች፣ እውነተኛ የአፍሪካ አርበኞች — ከልብ ከመነጨ ክብርና ፍቅር ጋር — የኢትዮጵያ አምላክ በረከቱን ሁሉ እንዲያዘንብላቸው ተመኘን።
ላለፉትም ዘለዓለማዊ ነፍሳቸውን በአፀደ ገነቱ እንዲያሸበርቅልን — ከመላ አፍሪካውያን ልጆች ጋር አብረን — በጉባዔ ፀለይን — ከልብ ተመኘን — በእናቶቻችን በአባቶቻችን አንደበት — የምርቃትን መዓት አወረድን፡፡
ያለፈበትን ታሪክ የማያውቅ ሕዝብ ወደፊት የለውም፡፡ ይጠፋል፡፡ የቀደሙትን የማያከብር ትውልድም የማያላውስ ዳፍንት ይወርሰዋል፡፡ ባለበት ይውዘመዘማል፡፡ ታሪካችንን እንዘክር፡፡ ታላላቆቻችንን እናክብር፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ አበቃሁ፡፡
ለዚህ ትረካችን በምንጭነት የተጠቀምንባቸውን የጥበብ ሥራዎች፣ ደራሲዎች፣ ፀሐፍት፣ እና የድረ-ገጽ ምንጮች ሁሉ — በደፈናው ከመቀመጫችን ብድግ ብለን እጅ ነስተን አመሰገንን፡፡
መልካም ጊዜ ለሁላችን፡፡
Filed in: Amharic