>

"ነጻ ህዝብ እና ነጻ ሀገር የመፍጠር ድርብርብ እዳዉ....!!!" (ሸንቁጥ አየለ)

“ነጻ ህዝብ እና ነጻ ሀገር የመፍጠር ድርብርብ እዳዉ….!!!”
ሸንቁጥ አየለ

 ነጻ ያልሆነ ህዝብ/በባርነት ቀንበር ስር ያለ ህዝብ/ የሚባለዉ በአካል በዉጭ ሀይሎች ተወሮ ተይዞ አካላዊ የበላይነት ባላቸዉ ጠላቶቹ እግር ስር የወደቀ ማለት ብቻ አይደለም።  ነጻነት የአካል የመንፈስ የስነልቦና እና የአስተሳሰብ የነጻነት ዘርፎችን ያካትታል። ይሄም ማለት አንድ ህዝብ ነጻ ህዝብ የሚባለዉ የአካል የመንፈስ የስነልቦና እና የአስተሳሰብ ነጻነት ሲጎናጸፍ ነዉ።
በተለመደዉ አስተሳሰብ መሰረት አንድ ህዝብ በባርነት ቀንበር ዉስጥ ወደቀ የሚባለዉ በዉጭ ሀይል ወይም በቅኝ ገዥ እግር ስር ሲወድቅ ነዉ። ሁለተኛዉ በባርነት ሁኔታ ዉስጥ የመዉደቅ እዉነታ ደግሞ የአንድ ሀገር ዜጎች በሁለት እና በሶስት መደብ ተለያይተዉ አንዱ መደብ/አንዱ ማህበረሰብ ላይ የባርነት ስርዓት በመጫን ህጋዊ በሆነ መልክ ሲገዛዉ ነዉ። እንዲህ አይነ ሁኔታ ዉስጥ የወደቀ ሀገርና ህዝብ አንዱ ባሪያ አንዱ ነጻ ሰዉ ተብሎ ቅቡል እና ክቡር በሆነ የህግ ስም ጸድቆለት ባሪያና የባሪያ እና ጌታ ተብሎ ይሰዬማል::
ሶስተኛዉ የባርነት አይነት ደሞ በዲሞክራሲና እኩልነት ስም እየማሉና እየተገዘቱ የአንድ ሃገር ዜጎች እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ፡ እኩል   ሰዉ ሆነዉ ከመኖር ይልቅ በጎሳ ተከፋፍለዉ አንዱ ጎሳ ሌላዉን ጎሳ ሰዉነቱን እንዲነጥቀዉ ብሎም እንዲያጠፋው የሚሰራ ስርዓት ነዉ። በአንዲት ሃገር ውስጥ የጎሳ የፖለቲካ ስርዓትተና የጎሳ ፖለቲካ ሲሰፍን የተለያዩ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች የራሳችን የሚሉትን ጎሳ ከሰዉነት በላይ ክፍ አድርገው ለመስቀል ይታገላሉ።የእነሱ ያልሆነዉን ጎሳ ደግሞ ከሰዉነት በታች እንዲሆን ይሰራሉ።ይሄ ሁሉ የሚከናወነዉ ዲሞክራሲያዊ የጎሳ ፖለቲካ ርዕዮተ አለም ቅቡል በሆነ ህግ ነዉ።እዚህ ጋ ዲሞክራሲ የሚለዉን ምጡቅ ቃል ለማጭበርበሪያነት እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ ማስተዋል መልካም ነዉ::
 በአንዲት ሀገር አንድ ጊዜ የጎሳ የፖለቲካ ስር ዓት የበላይነት ካገኘ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ወይም በሰላማዊ ትግል እንዲህ አይነቱን ስርዓት መለወጥ አይችልም::ምክንያቱም የጎሳ ስርዓት በአንዲት ሀገር ዉስጥ በሚሰፍንበት ጊዜ መዋቅራዊና ተቋማዊ በሆነ መልክ በዝባዥ እና ተበዝባዥ:ገዥና ተገዥ:ገፊና ተገፊ:ገዳይ እና ተገዳይ:አሳዳጅና ተሳዳጅ:ባለ ጊዜ እና ጊዜ የጣለዉ የሚልተጨባጭ በኢኮኖሚያዊ ጥቅሞ ላይ የተመሰረተ  የነገዶች ክፍፍል ይኖራል::
በጎሳ ስርዓት ዉስጥ ይሄን አይነት የባርነት አስተሳሰብ አምድ ላይ የቆመ አስተሳሰብን በምንም መልክ ማስቀረት አይቻልም::በመሆኑም የጎሳ ስርዓት ድርብ ባህሪዉ በመደቦች ቅራኔ የተሞላ መሆኑ ጭምር ነዉ::የመደቦች ቅራኔዉ እና ትግሉ ደግሞ የአንዲት ሀገር ዜጎች እንደ ሰዉ እንዳያስቡ የሚያስቀምጥላቸዉ ጎሳዊ ድንበር ስለሚኖር የሰዉ ልጅ የአስተሳሰብ ልዕልና ምንጩ ተሟጦ ይደርቃል::በዚህም አስተሳሰቡ ጭምር በባርነት ቀንበር ዉስጥ ይወድቃል::
በኢትዮጵያ ለሰላሳ አመታት የሰፈነዉ የጎሳ ስርዓት ከላይ የተነሱትን እያንዳንዳቸዉን ጭብጦች የሚያሟላ ሆኖ ይገኛል::በዚህም የኢትዮጵያ ህዝብ  ከላይ እንደተባለዉ
የአካል: የመንፈስ የስነልቦና እና የአስተሳሰብ የነጻነት ዘርፎቹን ሙሉ ለሙሉ ተነጥቋል ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ በኢኮኖሚቂያዊ እና ማህበራዊ እሴቶች/መሰረቶች ማህበረሰቧ ወደ ባሪያና ጌታ (ዘራፊና ተዘራፊ) የነገዶች አሰላለፍ ደረጃ ላይ ደርሷል::ይሄንንም እዉነታ ተከትሎ የነገዶች አሰላለፍ በአጥፊና ጠፊ መራራ መሰረት ላይ ቆሟል::
ይሄም እዉነታ በኢትዮጵያ ዉስጥ የሚነሱ ማናቸዉም ከፍ ያለ ራዕይ ያላቸዉ ትግሎችን ሽባ እና ቅቡልነት የሌላቸዉ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል::እነዚህ ከፍ ያለ ሀገራዊ ራዕይ ያነገቡ ትግሎች ከጎሳ ጥቅሞች ይልቅ ሀገራዊ ጥቅምን ስለሚያስቀድሙ እና ጎሳዎችም ከሀገራዊ ጥቅም ይልቅ ጎሳዊ ጥቅማቸዉን እንዲያስቀድሙ ስለተደረገ የሀገራዊ ምልዓታዊ ነጻነት ትግል እና ጉዳይ ባለቤት አልባ ነዉ::
ጎሳዎችም በአጥፊና ጠፊ የመደብ ተቃርኖ ጎራ የተሰለፉ ከመሆን በዘለለ የአንዱ ጎሳ ህልዉና ለሌላዉ ጎሳ ህልዉና መሰረታዊ የስጋት ምንጭ ነዉ የሚለዉ አስተምህሮት ሀገራዊ ቅቡልነት ስለሚያገኝ ጎሳዎች በአንድ ተሰልፈዉ በመተማመን ለአንድ ታላቅ ሀገራዊ  ራዕይ ለመታገል ትልቅ ፈተና ይሆንባቸዋል::
በዚህ መስመር ወደ ትግል የሚገቡ ሀይሎች  ማወቅ ያለባቸዉ  ነጻ ህዝብ እና ነጻ ሀገር የመፍጠር ሂደቱ በድርብርብ ቀለበታማ የባርነት ሰንሰለት የተያዘ መሆኑን ነዉ::ይሄ የባርነት ሰንሰለትም በተለመደዉ ተራ የትግል አካሂያድ እና ህሳቤ ከቶም ሊበጠስ እንደማይችል ታጋዮች ግንዛቤ ካልወሰዱ እና የጎሳ ስርዓትን ስሩን ለመንቀል የሚያስፈልገዉን የትግል ዝግጅት ካላደረጉ እንኳንስ ሀገር እና ህዝብ ነጻ ሊያወጡ እራሳቸዉ ታጋዮችም ጎሳቸዉ እየተቆጠረ በፈጣኑ የባርነት ባቡር ተመትተዉ ከትግል መስመርዝ ዘወር ይላሉ:::
Filed in: Amharic