>

ዝክረ ዘእሸቴ ሞገስ ፤ ወይታገስ ! (እስክንድር ነጋ፣ የህሊና እስረኛ፣  ቂልንጦ፣ አዲስ አበባ)

ዝክረ ዘእሸቴ ሞገስ ፤ ወይታገስ !
እስክንድር ነጋ፣ የህሊና እስረኛ፣
 ቂልንጦ፣ አዲስ አበባ 

1.1—– ቁምነገሩ
ከቶ ይህ ጥያቄ መጥቶልኝ አያውቅም፡፡ ሆኖም፣ ይህችን እስክሪብቶ ብድግ አድርጌ ስለ አባትና ልጅ ልፅፍ ስከጅል፣ድንገት ብልጭ ብሎብኛል፡፡  ግን ወደዚያ ከመግበቴ በፊት፣ የሚቀድም ነገር አለ፡፡ በዓለማችን የሰው ልጅ ብዛት የሰባት ቢሊዮንን መሥመር ያለፈው ባልፈው ዓመት ይመስለኛል፡፡  ከ200 ዓመታት በፊት አንድ ቢሊዮን ነበርን፡፡ ከመቶ ዓመታት በኋላ ሁለት         ቢሊዮን ደረስን፡፡  ከዚያም ወደ ሰባት ቢሊዮን ዘለልን፡፡ እመርታው እየፈጠነ ነው፡፡
 ይህ የሚያሳስበው ካለ፣ ይረጋጋ፡፡  ይህ ሁሉ ሰው ትከሻ ለትከሻ ቢቆም፣ ከማዳጋስካር ደሴት በላይ የማይፈለግ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ሲናገሩ ስምቻለሁ ። ዓለም በቂ ቦታ አላት፡፡ ህይወትን የሚያክል ውድና ብርቅ ነገር ለመቋደስ ወደዚች ዓለም የሚመጡትን ሁሉ በፀጋ መቀበል አለብን ብዬ አምናለኹ፡፡ እንደ ማለዳ ጤዛ ብልጭ ብላ የምትጠፋው የዚህች ዓለም ቆይታችን፣ ያለውን ተካፍለን ለመብላት አይከብደንም፡፡ ባለው ላይ በእጥፍ እጥፍ ለመጨመርም ጥበቡ አልጠፋንም፡፡
 ቁም ነገሩ ቁጥራችን አይደለም፡፡ ወደዚህች ዓለም መምጣታችንም  አይደለም፡፡ ቁም ነገሩ፣ ይህችን ብርቅዬ ህይወት እንዴት ነው የምንኖራት? የሚለው ነው፡፡ ሁለት መንገዶች አሉ፡፡  አንደኛው መንገድ፣ በፈጣሪ የምንመራበት ነው፡፡ ሁለተኛው፣ በራስ ህሊና መመራት ነው፡፡ በሁለቱም፣ “ሞራል” በምንላቸው ህጎች አሉ፡፡  ልዩነታቸው ህጎቹን የሚያወጣው አካል ነው፡፡ በአንደኛው፣ ደንጋጊው ፈጣሪ ሲሆን፣ በሁለተኛው የፈጣሪን ቦታ ሰው ወስዶታል፡፡
 በቅዱስ ሚካኤል ስም እየማለና የእኔን ልብ በሀዘንም በደስታም ተርትሮ ወደ መቃብሩ የወረደው የሸዋ ሮቢቱ እሸቴ ሞገስ፣ በፈጣሪው መንገድ ተግቶ ለመገኘት እየወደቀና እየተነሳ በዚህች ዓለም የነበረውን ሩጫ ጨርሷል ብዬ ከልብ እመኝለታለሁ፡፡ ይታገስም እንደዚያው። ሁለተኛው መንገድ ሞኝነት ነውና።
  አሁን፣ ያች “ብልጭ አለችብኝ” ወዳልዃት ጥያቄ ልምጣ፡፡ አንድ ሰው፣ ጠዋት ከእንቅልፉ ተነስቶ፣ ማታ እስኪያሸልብ ድረስ ስንት ቃላቶች ከአፉ ይወረውራሉ? ይህ ለመጀመሪያ ግዜ የተጠየቅ ነው የሚል ግምት የለኝም፡፡ እንደተጠየቀም፣ ምርምር እንድተደርግበትም፣ መልስ እንዳለውም አልጠራጠርም፡፡ እኔ ግን አላየኹትም፡፡ በደፈናው ግን ብዙ እንደሆነ መገመት እንችላለን፡፡ ያንን “ብዙ” ደግሞ፣ በሰባት ቢሊዮን ስናባዛው ሊገኝ የሚችል ቁጥርን ሊገልፅ የሚችለው የግዕዝ/ዐማረኛ ቃል “እልፍ” ነው ሊሆን የሚችለው፡፡
 ጥያቄ ጥያቄን ይወልዳል ይባላልና፣ ከዚህ “እልፍ” ስንት ቁምነገር፣ ስንት የሚጣል ነገር ይገኝ ይሆናል? ብልን ደግሞ አንጠይቅ፡፡ ይህን እንኳን፣ ተጠይቆ አያውቅም ባልልም፣ ጥናት ተደርጎበታል ለማለት ይከብደኛል፡፡ ለግዜው  በደመነፍስ ልመልሰው፡፡ “የሚጣለው እልፍ፤ ቁም ነገሩ አናሳ ነው” ብል የሚከፋ ሰው ይኖራልን? በራሴ የማውቀው ይህንኑ ነው፡፡ በቀን ብዙ አወራለኹ፡፡  ከዚያ መካከል ጥቂት ቁምነገር ቢገኝ፣ ጥሩ ቀን አሳልፌያለኹ ማለት ነው፡፡
 እንደ እሸቴ ሞገስ ዘመን የሚሻገር ቃላት ከአንደበታቸው የሚወጣ ሰዎችን፣ “ጥቂት” ብለን የምንገልፃቸው አይደሉም፡፡ እምኒት ናቸው፡፡ እምኒት፣ የጥቂት ጥቂት ነው፡፡ በጥሩም ሆነ በመጥፎ። ባለፉት 30 ዓመታት በዚህ ትርታ የሚመደቡ ሰዎችን ሳስብ፣ መለስ ዜናዊ ይመጡብኛል፡፡ “ባንዲራ ጨርቅ ነው” ያሉት ከቶ እንዴት ሊረሳ ይችላል? “ዘመነ–ወያኔ” ለመጪው ትውልድ ቁልጭ ብሎ የተቀመጠበት ነው፡፡  ስለ አፄ ቴዎድሮስ ብዙ ተብሎ፣በሐበሻውም በፈረንጁም ብዙ ተፅፎ፣ ዘመን የተሸገረው ግን፣
“መቅደላ ላይ ጩኸት በረከተ፣
የሴቱን አላውቅም፣ ወንድ አንድ ሞተ”
 የሚለው የአልቃሿ ሙሾ ሆኗል፡፡ ከጣሊያን በኋላ ያለው ኢትዮጵያ ፖለቲካ ደግሞ:-
“ኢትየጵያ ሞኝነሽ ተላላ፣
የሞተልሽ ቀርቶ፣ የገደለሽ በላ”
በሚል በስቅላት ህይወቱን ላጣው አርበኛ በላይ ዘለቀ የወጣለት ህዝባዊ ስንኝ ዘመንን ተሻግሮ እየተናገረ ይገኛል፡፡
1.2—– በደማቸው ያበሰሩን
 የእሸቴ ሞገስን የመጨረሻ ቃል አንደ አንድ ዘመን መግለጫ አድርጌ ለመመልከት ይከብደኛል፡፡ እሸቴ ጀግና ነው፡፡ በመንፈስም በተግባርም፡፡ ያለፉት 50 ዓመታት ግን፣ እንደ ህዝብና ሀገር የጀግንነት ዘመናችን አልነበሩም፡፡ ደግመን ደጋግመን፣ በቁማችን የሞትንባቸው ዓመታት ነበሩ፡፡ እነዚያ የጨለማ ዓመታት  ተደማምረው ሞራላችንን አላሽቀውታል፡፡  በዘመነ መሳፍንት እንዲህ ሆነን ነበር፡፡ ያኔ አለመግባባት ብቻ አልነበረም ያቃተን፡፡  ሞራሉም፣ጀግንነቱም፣ ቅንነቱም ተሰውሮብን ነበር፡፡ በዘመነ–ህወሓት ታሪክ ራሱን ደግሟል፡፡ የእሸቴ ንግግር የሚወክለው ነገር ካለ፣ ከዚህ ዘመን እየወጣን መሆናችንን ነው፡፡ ያለውን ሳይሆን፣ መጪውን ነው አመላክቶናል፡፡
ግን፣ ምንድን ነው በናፍቆት የምንጠብቀው መጪው ዘመን? አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ወኔ፣አዲስ ጀግንነት፣ አዲስ ማንነት፣ አዲስ ሞራል ነው የምንጠብቀው? ፈፅሞ አይደለም፡፡ አዲስ ወኔ፣ አዲስ ጀግንነት፣ አዲስ ማንነት፣ አዲስ ሞራል አያስፈልገንም።
 ጉዳዩ አዲስ ነገር የመጥላት አይደለም፡፡  አስተሳሰብም፣ ወኔም፣ ጀግንነትም፣ ማንነትም፣ ሞራልም በለውጥ ሂደት ውስጥ ካላለፉ ( ፈረንጆቹ እንደሚሉት unless they  are in a dynamic process of change) ይሞታሉ፡፡ ባለንበት ዘመን ለለውጥ የሚሆን ወይ መነሻ ወይ መሰረት ወይ ሥር መኖር አለበት፡፡ ይህ የሌለው ህዝብ የለም፡፡ የእኛ ችግር፣ የተዘነጋ መነሻ፣ የተናጋ መሠረት፣ የላላ ሥራ መኖሩ ነው፡፡  እኛን የናፈቀን፣ እሱን አበጃጅተን በላዩ ላይ አዲስ ታሪክ መሥራት ነው፡፡
 እስቲ በእሸቴ ሞገስ የመጨረሻ ንግግር ውስጥ ያሉትን ፍሬነገሮች  እንቃኛቸው፡፡ ያልወለደ የእሸቴን ስሜት በትክክል ሊረዳ አይችልም፡፡  ዓለም ላይ ብዙ ድንቅ ፀሃፍትን አፍርታለች፡፡ አንዳቸውም ግን የወላጅን ፍቅር በአግባቡ አልገለፁትም። የወለደ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ በቃላት ሊገለፅ የሚችል ነገር አይደለም፡፡  ለዚህ ጥልቅ ፍቅር እንደ መገለጫ ሆኖ፣ “ልጀቼ መጥፎ ነገር ሆነው ከማይ፣ እኔን አስቀድመኝ” ብሎ መፀለይ የተለመደ ነው።
 ግን፣ እንደ ዘመናችን የሞራል ድቀት መገለጫ ሆኖ፣ በደርግ ጊዜ ያየነው አለ፡፡ ልጆች ቤታቸው በር ላይ ተገድለው፣ ወላጆች እንዳያለቅሱ ትዕዛዝ ይሰጣቸዋል፡፡ ትዕዛዙም ይከበራል፡፡ ተደብቆ ይለቀሳል፡፡ እንዲህ ዓይነት ትዕዛዝ ለመስጠትም ሆነ ለመቀበል እንዴት ቻልን? ለሚለው ጥያቄ ያለው ምላሽ፣ ስለ እያንዳንዳችን ማንነት የሚናገር ባይሆንም ፣ በዚህ ዘመን እንደ ህዝብ ስለተላበስነው ባህሪ፣ ወይም እንደ ህዝብ ስላለን የሞራል ቁመና የሚናገረው ነገር አለ፡፡ ፈጣሪውን ክዶ ፈሪሃ እግዚአብሄር የሌለው ትዕዛዝ ስጪውም፣ እምነቱ ሳስቶ ሞትን በተጋነነ መልኩ ፈርቶ  ትዕዛዙን የተቀበለውም በብዙዎቻችን ውስጥ  አሁንም ድረስ አሉ፡፡
 አባቶቻችንና አያቶቻችን ግን፣ ልጅ ገድለው “አታልቅሱ” የሚሉ፣ ልጆቻቸው ተገድለውባቸው “አታልቅሱ” ሲባሉ “እሺ” ብለው በድብቅ የሚያለቅሱ አልነበሩም፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት ነው ገድለን “አታልቅሱ፣”  ተገድሎብን “እሺ አናለቅስም” ማለት የጀመርነው፡፡ የማናውቀው አዲስ ማንነት ነው፡፡
   በታሪክ የምናውቀው ብዙሃኑን ህዝባችን፣ ፈጣሪን የማይጠራጠርና ፈሪሃ እግዚአብሔርነት ያለውን፣ በእምነቱ  ከመቃብር ባሻገር ያለውን ተስፋ በመጨበጡ ሞትን አጋኖ የማይፈራ ነበር፡፡ እሸቴ ሞገስና ልጁ ይታገስ፣ ይህ ማንነታችን  እንዳልጠፋ አመላክተውናል፡፡ በእስራኤልም ታሪክ ይኸው ምሳሌ አለ፡፡ ነቢዩ ኤሊያስ፣ ንፁህ የሆነ አንድ ሰው እንኳን ፈልጎ ማጣቱን ለፈጣሪው በተሰበረ ልብ በነገረው ግዜ፣ “ለጣዖት ያልሰገዱ 7000 ሰዎች ለይቼ አስቀምጫለኹ” ነበር ያለው፡፡ እነዚህ 7000 የእስራኤል መድህን ሆነዋል፡፡ እሸቴ ሞገስና ልጁ ይታገሰ የእኛ 7000 ተምሳሌት ናቸው፡፡ የተዘነጋው መነሻ፣ የተናጋው መሠረት፣ የላላው ሥር የሚጠብቅበት እርሿችን ናቸው፡፡
እሽቴን እና ይታገስን ጀግና የምንላቸው ዘጠኝ ሰዎችን ስለገደሉ አይደለም፡፡ሰው የፈጣሪ አምሳል ነወ፤ ክቡር ነው። እንኳን ዘጠኝ፣ አንድ ሰውም መግደል ለህሊና ይሰቀጥጣል ፡፡ ጀግንነታቸው ሞትን መናቃቸው ነው፡፡ ሞትን መናቅ፣ ሞትን መናፈቅ ማለት አይደለም፡፡ ሰው ሆኖ ሞትን አለመፍራት አይቻልም፡፡ ጀግንነት የምንለው ለሞት ፍርሃት ባሪያ አለመሆንን ነው፡፡
 በዚህ ዘመን፣ የሞት ፍርሃት የልጅን ፍቅር ያህል ነገር አፍነን እንዳናለቅስ አድርጎን ነበር፡፡ አባትን ለገዳይ አሳልፈን እንድንሰጥ አድርጎናል፡፡ በጦር ሜዳ ሳንወጋ ተማርከናል፡፡ ይህን ዘመን  ሳያዩ ያለፉት አባቶቻችን በእጅጉ እድለኛ ናቸው፡፡ ይህ ማንነት የእኛ እንዳልሆነ፤ ይህ ዘመን እያበቃ ስለመሆኑ እሸቴና ታገል በደማቸው አብስረውናል፡፡ ህወሓት ነካክቶ ወደ ቀልባችን እየመለሰን ነው፡፡ እውነትም፣ ሳይደግስ አይጣላ!
Filed in: Amharic