>
5:13 pm - Monday April 19, 4483

የጀነራሉ መልዕክት ፡ ወደ ዲፕሎማሲ ሰዎች...!!! (በዘመንፈስ አክሱማዊ)

የጀነራሉ መልዕክት ፡ ወደ ዲፕሎማሲ ሰዎች…!!!
         በዘመንፈስ አክሱማዊ 

ጀኔራል ፃድቃን ገ/ተንሳይ ሰሞኑን ወደ አደባባይ ሁለት ጊዜ ብቅ ብለዋል፡፡ አንደኛው በቢቢሲ በኩል ሁለተኛው በራሳቸው በኩል፡፡ ጀኔራሉ ለበቢሲ በሰጡት ቃለ-መጠየቅ የጦርነቱን ሁኔታ በደምሳሳው ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ግን የቀራቸው ያለ ይመስላል፡፡ በቢቢሲው መግለጫቸው ላይ ደብረ-ብርሃን ደርሶ የተመለሰው ጦራቸው የመመለሱን ምክንያት አስረድተው ነበር፡፡ አንዳንዶች ድሮን ነው የመለሳቸው የሚለውን ጀኔራሉ ዋና ምክንያት አድርገው አልወሰዱትም፡፡ በእርግጥ ችግሩ ችግር ነበር፡፡ ዋናው ችግር ግን ከወታደራዊ ድሉ ጋር የሚመጣጠን የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ስራ አለመሰራቱ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ይመስላል ጀኔራሉ በሁለተኛ የሚዲያ ጉብኝታቸው በራሳቸው የተፃፈ ሰፋ ያለ ተንታኔ አቅርበዋል፡፡ እኛም የጀኔራሉን ትንታኔ ይዘን ቀርበናል፡፡
 
የጦርነቱ አላማ ምንድን ነው?
ጀኔራል ፃድቃን ገ/ተንሳይ ትግራይን ወደ ጦርነት ያስገባትን ምክንያት በመጀመሪያ የአለም ማህበረሰብ ይወቅልን ያሉትን አስቀምጠዋል፡፡ ጀኔራሉ በትግራይ በኩል የጦርነቱ አላማ ሁለት መሆኑን እወቁልን ብለዋል፡፡ አንደኛው በትግራይ ላይ እየደረሰ ያለው ዘርፈ-ብዙ ችግር ሲሆን ሁለተኛው በግልፅ ባይናገሩም የኢትዮጵያ ጉዳይ ነው፡፡ በሁለት ነጥቦች ያስቀመጧቸው የጦርነት አላማዎች የትግራይ ሀይል ወደ አዲስ አበባ እየገሰገሰ የነበረበት ምክንያት ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው፡፡
የትግራይ ጉዳይ ግልፅ ነው፡፡ የአብይ አህመድ ሰራዊት ትግራይን ለቅቆ የወጣው በተኩስ አቁም ሰበብ ቢሆንም ሁኔታው ግን ተኩስ አቁም ሳይሆን ከበባ ነው፡፡ የፌዴራል መንግስቱ በትግራይ ያለውን መብራት ስልክን ባንክን የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች አግልግሎት ካቆመ ወራት አልፎታል፡፡ ይህ ብቻ ሳያንሰው ትግራይ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በንግድ የምትተሳሰርበትን መንገዶች ዘግቶታል፡፡ ሌላው ቀርቶ የእርዳታ እህል አንዳይገባ አግዷል፡፡ በዚህ የተነሳ በትግራይ ህዝብ ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እየተከሰቱ ነው፡፡ ረሃቡ እንደተለመደው ብቻ ሳይሆን የጦርነቱ ሂደት አንዱ አካል ሆኗል፡፡
በትግራይ ያለውን ችግር ሲገልፁ በትግራይ የተከሰተውን ችግር እናንተ የምታውቁት በቴሌቪዥን ነው፡፡ እኛ ደግሞ የምናውቀው ከችግሩ ጋር በመኖር ነው ይላሉ፡፡ ስለዚህ ይህን የከበባ ችግር ለመስበር ጦርነቱን ከትግራይ ዉጪ እንዲቀጠል አስገዳጅ አድርጎታል ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል ጀኔራሉ የትግራይን ጉዳይ ብቻ የጦርነት አላማ ማድረጉ በቂ ሆኖ አላገኙትም፡፡ እሳቸው የሚመሩት ጦርነት አላማ ከትግራይ ውጪ በኢትዮጵያም ያለው ዘርፈ ብዙ ችግሮችን መሰረት ያደረገ አንደነበር ያስረዳሉ፡፡ ዋናው ትግራይን ከኢትዮጵያ ጋር ያገናኘው የጦርነት አላማ ደግሞ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ የገባበት አደጋ ነው፡፡ አብይ አህመድ ኢትዮጵያን የሚፈልጋት ጦርነቱን ለማስቀጠል ነው፡፡ እኛ ደግሞ ጦርነቱን የምንፈልገው ኢትዮጵያን ከመፍረስ አደጋ ለማዳን ነው የሚል እንድምታ ያለው አሳብ አንፀባርቀዋል፡፡
የአራት ኪሎውን መንግስት በአማራ ሊህቃኖች እየተነዳ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አፍርሶ በአሮጌው የአሃዳዊ ስርዓት የመተካት ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል፡፡ ይሄ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አካሃድ ደግም በጀኔራሉ እምነት አገሪቱን ብትንትን ያደረጋታል እንጂ የሚያመጣው መፍትሄ የለም፡፡ ይህ የአሃዳውያኑ አማራጭ መፍትሄ ሳይሆን ጊዜው ያለፈበትን ችግር በዘመናዊ ፖለቲካ መፍትሄ አድርጎ የማቅረብ ነው፡፡ ስለዚህ አገሪቱን ከማዳን ይልቅ ገድል የሚከታት እንደሆነ ጀኔራሉ አስፅንኦት አንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡ የትግራይ ሀይሎችም የአዲስ አበባ ግስጋሴ ተመሳሳይይ የፌዴራል አጀንዳ ያቸውን ወገኖች አካቶ አገሪቱን ከብተና ለማዳን የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለው ያምናሉ፡፡
ከአዲስ አበባ መመለስ፡- ጦርነቱን ያቆመው ምንድን ነው?
ጀኔራሉ ከዚህ በፊት ለበቢሲ በሰጡት ቃለ-መጠየቅ ከደብረ-ብርሃን እንዲመለሱ በማድረግ የአዲስ አበባውን ጉዞ የሰረዘው ምን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ እዚህ ላይ ብዙዎች ከድሮን ጋር የሚያያይዙት ያለ ቢሆንም ድሮን ግን በጀኔራሉ ዋንኛ ምክንያት ሆኖ አልቀረበም፡፡ የጀኔራሉ ዋና ምክንያት ከነበረው ወታደራዊ ግስጋሴ ጋር የሚመጣጠን የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ስራዎች አለመሰራታቸው ነበር፡፡
ጀኔራሉ ቢቢሲ ላይ ያሉትን እዚህም ፅፋቸው ላይ ትኩረት ሰጥተው ጠቃቅሰውታል፡፡ በወታደራዊ ዘርፍ በፍጥነት እየገሰገሰ የነበረው ሰራዊታቸው ደብረብርሃን ሲደርስ ግልፅ እየሆነ የወጣ ነገር ቢኖር ድሉን የሚመጣጠን የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ ስራ አለመሰራቱ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የሰራዊታቸውን ግስጋሴ ተከትሎ ከውስጥም ከውጪም እልቂት ይከሰታል የሚል ስጋት የነበራቸው ወገኖች ብዙ ናቸው፡፡ ይህንን ስጋት እሳቸውም እንደሚረዱት የተናገሩት ጀኔራሉ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ስራዎች እስኪሰሩ ድረስ ከደብረ-ብርሃን ለመመለስ ተገደናል ይላሉ፡፡ ተመለስናል ማለት ግን ጦርነቱ ቆሟል ማለት አይደለም፡፡ እና ይቀጥላል?
አብይ አህመድ በቅርቡ ሰራዊቱ ወደ ትግራይ ሳይገባ ባስለቀቃቸው ቦታዎች ፀንቶ ይቆያል ማለቱ ከብዙ ሰዎች የሰላም ሰው በሚል እንዲወደስ አድርጎታል፡፡ እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ አብይ አህመድ ወደ ትግራይ ሊገባ እየገሰገሰ ነበር፡፡ ወደ ትግራይ ያልገባው ባረፈበት ሀይለኛ ምት የተነሳ ነው፡፡ አልቻለም እንጂ ወደ ትግራይ ዘልቆ የመግባት ፍላጎት ነበረው፡፡ ጀኔራሉም ከዚኸኛው አሳብ ጋር የሚስማሙ ይመስላሉ፡፡
አሁንም ድረስ የኢሳያስና የአብይ ወታደሮች በምዕራብ ትግራይ ምድር መኖራቸውን እና ትግራይ ዙሪዋን በእነዚህ ሀይሎች መከበቧን ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህ ጦርነቱ መቆም የሚችለው በሁለት አይነት መንገድ ነው፡፡ አንደኛው ይህ በትግራይ ያሉ ወራሪዎች ሲወጡ እና የትግራይ የከበባ ችግር ሲፈታ ነው፡፡ ሁለተኛው መፍትሄው እሳቸውንና ሌሎች የህወሓት ባለስልጣናት በተደጋጋሚ እንዳሉት የጦርነቱ ማቆሚያ መፍትሄው ፖለቲካዊ ነው፡፡ ጉዳዮ የሚመለከታቸው የፖለቲካ ወገኖች ነፃና ገለልተኛ በሆነ አካል ጠረጴዛ ላይ ቁጭ ብለው በውይይትና ችግሩን በድርድር መፍታት አለባቸው፡፡ ለጀኔራሉ ጦርነቱ የሚቆመው በዚህ መልኩ ነው፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ስራዎች ካልተሰሩ ይላሉ ጀኔራሉ ጦርነቱ በትግራይ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከትግራይ ውጪ ባሉ ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ሊቀጥል ይችላል፡፡
የዲፕሎማሲ ሰዎች፡ አለም አቀፍ ማህበረሰብ ምን ማድረግ አለበት?
የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለችግሩ ትኩረት መስጠት ለምን እንደሚያስፈለግ ትኩረት ሰጥተዋል፡፡ ጀኔራሉ ትኩረቱን ከታሪካዊ ገፅታ በመጀመር ለማሳየት የሞከሩ ይመስላል፡፡ የመጀመሪያው ጉዳይ ትግራይ አፍሪካዊ አገር ናት፡፡ በጥንታዊ ታሪኳ ክርስትና እስልምና እና አይሁድ ሀማኖቶችን አቻችላ የመጣችና የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት ናት፡፡ በዚህ ታሪኳ በአፍሪካ የመጀመሪያው የሚባለው የጥቁር ነፃነት ትግል መሰረቱ ትግራይ ነው፡፡ ጉዳዩ ከታሪክ አንፃር ከታየ ከፍ ያለ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ በዘመናዊ ፖለቲካም ውስጥ ትግራይ ለአገሪቱ ያበረከተችው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ይህን ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ባለፉት 27 አመታት የተረጋጋ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ በመገንባት በኩል የትግራይ ፖለቲከኞች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የሚዘነጋ አይደለም፡፡
የትግራይ መረጋጋት የቀጠናው ሰላምና መረጋጋት መሰረት ነው፡፡ ምስራቅ አፍሪካ ከአየቅጣጫው የሚነሱ የተለያዬ ፍላጎት ያላቸው አገራት ትኩረት የሚስብ ነው፡፡ ከአገራቱ ጥቅም ባለፈ ደግሞ አሸባሪዎችን የመሳሰሉ አካላትንም ጭምር ትኩረት የሚስብ የፖለቲካ ቀጠና ነው፡፡ በዚህ ላይ ቀጠናው ለድርቅና ለረሃብ የተጋለጠ ስለሆነ ጦርነት ተጨምሮበት የሚፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው፡፡ ጦርነቱ ላይ አሁን የሚታየው የውጪ ጣልቃ ገብነት አዝማሚያ ተጠናክሮ ከቀጠለ በምስራቅ አፍሪካ ላይ ሶሪያና ሊቢያን በአይናችን የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ ይህ ቀጠና እንደ ሶሪያና ሊቢያ ከመፈራረሱ በፊት አለም አቀፍ ማህበረሰቡ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጀኔራሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡ ስለዚህ ትግራይ ላይ ያለውን የፖለቲካ ችግር ትኩረት ሰጥቶ መፍታት የምስራቅ አፍሪካን ዘርፈ ብዙ የፖለቲካ ችግሮች የመፍታት ያህል ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡
ጀኔራሉ መልዕከታቸው ያተኮረው ከአገር ውስጥ ይልቅ ለአለም አቀፍ የፖለቲካ ማህበረሰብ ነው፡፡ በዚህም ከላይ መጀመሪያ ላይ እንደ ችግር ያነሱትን የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ችግር ለመፍታት ያለመ ይመስላል፡፡ ለዲፕሎማሲ ሰዎች በተፃፈ የጀኔራሉ መልዕክት አለም ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ከወታደራዊ ይልቅ ዲፕሎማሲ ላይ ያተኮረ ጽሁፍ ነው፡፡ ፅሁፉ መጀመሪያ አካባቢ ከጦርነቱ ጋር በተያዘ ያጋጠማቸውን የዲፕሎማሲ ችግር ለመፍታት ያለመ ነው፡፡ ስለዚህ የጀኔራሉን አሳብ ጠቅለል ስናደርገው የዲፕሎማሲ ችግሩ ከተፈታ የወታደራዊ ጉዳይ ቀላል መሆኑን የሚሳይ ነው፡፡
Filed in: Amharic