የተለየ ሐሳብ ያለው ኢትዮጵያዊ ሐሳቡን የሚቀበል ሥርዓት አጥቶ ጫካ የሚገባበት ጊዜ መቆም አለበት❞
ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
ታኅሣሥ 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር የሐሳብ ስሪት ውጤት ናት፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች ሕብር ፈጥረው የሚገነቧት ሀገር በምጣኔ ሃብት፣ በፖለቲካ እና በማኅበራዊ ውቅሯ ጠንካራ ናት፡፡ ነፍጥ ካነገቡት በላይ የሐሳብ ልዩነትን ተቀብለው እና አስማምተው ሀገር ያቆሙት የተሻለ ለውጥ አምጥተዋል፡፡ የተለየ እና የተለያየ ሐሳብ መያዝ እና ማንጸባረቅ በራሱ ችግር አይደለም፤ ችግር የሚሆነው ግን የሐሳብ ልዩነት ወደ ግጭት ሲያመራ እና ዋጋ ሲያስከፍል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት በዚህ ብዙ ዋጋ ከፍላለች፡፡
ጥንታዊ ግሪካዊያን አርዮስ ፋጎስ የሚባል የሐሳብ አደባባይ ነበራቸው፤ ሰው ስለሀገሩ እና በሀገሩ የተለየ ሐሳብና እሳቤ ሲኖረው ሐሳቡን ከሌሎች ጋር የሚያንሸራሽርበት፡፡ በኢትዮጵያም እንደ ጎንደር ጉባኤ አይነት ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ልዩነቶች በልሂቃን የሚሞገቱባቸው አደባባዮች እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ጥንት ኢትዮጵያዊያን ፍትሕን አዋቂ ብቻ ሳይሆኑ ስለፍትሕ ሲሉ ራሳቸውን የገዙ እና ለሌሎች ሐሳብ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጡም እንደነበሩ ይነገራል፡፡
የቱ ላይ እንደተቆረጠ በውል ባይታወቅም በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ፖለቲካ ውስጥ የሐሳብ ልዩነት ከአደባባይ ማስታረቅ ይልቅ ለግጭት እና ለልዩነት የቀረበ እንደነበር ተደጋግሞ ታይቷል፡፡ የተለየ ሐሳብ ያላቸው ዜጎች የልዩነት ሐሳባቸውን የሚቀበል እና በአግባቡ የሚያስተናግድ ሥርዓት በማጣታቸው ብቻ በርካቶች ጫካ፣ ውስኖች ወህኒ እና አብዛኛው ደግሞ ከሀገሩ ተገፍቶ በውጭ እንዲያሳልፍ ተገዶ ቆይቷል፡፡
በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ የሚስተዋሉትን ልዩነቶች ለማጥበብ እና ሀገራዊ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ባለፉት ዘመናት አካታች ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር እንዲደረግ ሲጠየቅ ቆይቷል፡፡ በሽብር ቡድኑ ትህነግ መራሹ መንግሥት ዘመን የሐሳብ ልዩነትን በምክክር ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ግጭቶችን በመጥመቅ የሚያተርፉ ኃይሎች ጥያቄዎችን ሲገፉት ቆይተዋል የሚሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጊዜው ሲደርስ በቅርቡ እውን ለመሆን በቅቷል ይላሉ፡፡ የለውጡ የመንግሥት የሥራ ኅላፊዎች ብሔራዊ የምክክር መድረኩ እንዲደረግ ሲጠየቁ መቆየታቸውን ያወሱት አማካሪው ሂደት እና ዝግጅት ያስፈልገው ስለነበር እስከዚህ ጊዜ ድረስ መቆየቱን ነግረውናል፡፡ የተለየ የሚያደርገው ግን ተቋማዊ ኾኖ በኮሚሽን ደረጃ መዋቀሩ ነው ብለዋል፡፡
በበርካታ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ እይታዎች እና አረዳዶች አሉ የሚሉት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጉዳዮቹን ወደ ጠረንጴዛ በማምጣት መመካከር እና የጋራ አስተሳሰብ መፍጠር አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡
በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ፖለቲካ ሂደት ልዩነቶች ከጫካ ወደ አደባባይ ተሸጋግረዋል፡፡ ከዚህ የተሻለው ደግሞ የተለየ ሐሳብ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ልዩነታቸውን ይዘው በጠረንጴዛ ዙሪያ መምከር መቻላቸው የተሻለ ይሆናል ነው ያሉት፡፡ ለዘመናት የተለየ ሐሳብ የሚያራምዱ እና የያዙ ወገኖች ሲገፉ መቆየታቸውን በማውሳትም “የተለየ ሐሳብ ያለው ኢትዮጵያዊ ሐሳቡን የሚቀበለው ሥርዓት አጥቶ ጫካ የሚገባበት ጊዜ መቆም አለበት” ነው ያሉት ዲያቆን ዳንኤል፡፡
እንደ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል መመካከር ማለት በሁሉም ጉዳዮች መግባባት እና አንድ ድምዳሜ ላይ መድረስ ማለት አይደለም፤ ልዩነትን ተቀብሎ እና በብዙኀኑ የሐሳብ ገዥነት ማመን ግን ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን የተለየ ሐሳብ ያላቸው የሚሳደዱባት እና የልዩነት ገመድ ያለልክ ተወጥሮ የምንሳሳብባት ኢትዮጵያ መኖር የለባትም ነው ያሉት፡፡
ብሔራዊ የምክክር መድረኩ ከወቅቱ ጦርነት ጋር ተያይዞ ድርድር የሚል እንደምታ ይዟልና ግንኙነት ይኖረው ይሆን የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ሲመልሱ አሸባሪው ትህነግ በተፈጥሮው መመካከር እንደማይወድ ገልጸው የኮሚሽኑ መቋቋም ለእንደራሴዎች የቀረበበት ወቅት ከአሸባሪው ቡድን ሽንፈት ጋር በተመሳሳይ ወቅት በመቅረቡ የተፈጠረ ነው ይላሉ፡፡ ብሔራዊ ምክክሩ ድርድር ከሚባለው ጉዳይ ግንኙነት የለውም ብለዋል።
“ከቀደመ ነገር አሸባሪው ትህነግ በሐሳብ የበላይነት አምኖ ለምክክር የሚሆን ፖለቲካዊ ስሪት ያለው ድርጅት ቢሆን ኖሮ አሁን የምናየው ግጭት አይፈጠርም ነበር” የሚሉት ዲያቆን ዳንኤል አሸባሪው ቡድን መግዛት እንጂ መግባባት፣ ማጋጨት እንጂ ማግባባት እና በበላይነት እንጂ በእኩልነት የማያምን ድርጅት በመሆኑ ለዚህ አልታደለም ነው ያሉት፡፡