>

ሹርባው:- ቴዎድሮሳዊነት የለውጥና የዘመናዊ ስልጣኔ አንጓ ...!!! (ሲሳይ አልታሰብ)

ሹርባው:

ቴዎድሮሳዊነት የለውጥና የዘመናዊ ስልጣኔ አንጓ …!!!
ሲሳይ አልታሰብ

ሹርባው የጀግንነት፣ የእምቢ ባይነት፣ እጅ ያለመስጠትና የዘመናዊ ስልጣኔ መሻት ምልክት ጭምር እንጅ ፀጉር ብቻ አይደለም። ወደ 1860ዓ.ም ተመልሶ ለአፍታ እንኳን በማንሰላሰል የቴዎድሮስን ዕዳ ማስታዎስ አንዳች የእልህና የቁጭት ውቂያኖስ ውስጥ እንድትሰምጥ ያስገድድሃል። ቴዎድሮሳዊነት በጨለማ ዘመን ሐይቅ ዳር ሁነህ እንደምትመለከተው  በማለዳ ፀሐይ ብርሐን  መስሎ የዘመናዊ ስልጣኔ ሐሳብን ያዋለደ ለቀጣዩ ትውልድ የተበረከተ ሕያው ዕዳ ነው የምንለው ለዚህ ነው።
 ዘመናዊት ኢትዮጵያን ለማዋለድ ለ17 አመታት የተደረገው እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ መቅደላ አምባ ላይ በካሳ የክብር መስዋትነት አላማው ዳር ሳይደርስ ለትውልዱ ቁጭትን ዘርቶ ተፈፀመ። ቋራ ተወልዶ፣ ደራስጌ ማሪያም ላይ ንግስናውን ጭኖ፣ ቤተ መንግስቱን ደብረታቦር ላይ ቀልሶ፣ ጋፋትን የቴክኖሎጅ መንደር ውጥን፤ የዘመናዊ ስልጣኔ ጅማሮ አድርጎ መቅደላ አምባ ላይ በክብር የወደቀውን ንጉስ ፀሐፊያኑ ዘመናዊ ስልጣኔ የገባው የመጀመሪያው ንጉስ ሲሉ ያሞካሹታል።
የዘመነ መሳፍንትን ፍፃሜ ያበሰረው ታላቁ ካሳ  ተወልዶ ከአደገበት ማህበረሰብ ወግና ባህል አንፃር ሲመዘን የሚጋጩ የዘመናዊነትና አያሌ የለውጥ ህልሞችን በልቡ አትሞ ደፋ ቀና ሲል የተረዳው አገርኛ ወዳጅ አልነበረውም። ተራማጅ ሀሳቡ ተቀባይ አጥቶ ረጅም ውጥኑ በአጭር ስለተቀጨበት የስልጣኔ ርሃብተኛው  ንጉስ ብዙ ነገር ተብሏል። ከአገሬው ሰው ይልቅ  ካሳን በወጉ የተረዱት ነጮቹ “ጊዜውን ቀድሞ የተወለደ ንጉስ”  ሲሉ ገልፀውታል። እኛማ ካሳን ገና አላዎቅነውም።
የካሳን ነገር ገና መመርመር አለብን። ከዛይላ አስከ ምፅዋ የተንጣለለውን የአባቶቹን ሰፊ ግዛት እያማተረ በምድሩ ስልጣኔንና ዘመናዊነትን ለማንበር የተጓዘበት የእልህና የቁጭት ጉዞ በቅጡ ገና አላወቅነውም። አፄውን በቅጡ  ያወቁት ነጮቹ  ንጉሱ መቅደላ አምባ ላይ በእጅ አልሰጥም ባይነት በክብር ሲያልፍ የካሳን ሹርባ ላጭተው መውሰድ ካሳን እስከ ነፍሱ እንደመውሰድ ባይሆንላቸውም ቅሉ ሹርባውን በክብር ወስደው ነገረ ቴዎድሮስን በሹርባው መርምረዋል።
 የንጉሱ ሹርባ በእንግሊዝ ብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ ለ150 አመታት በክብር ተቀምጧል። ሹርባው ፀጉር በቻ አይደለም የምለው በምክኒያት ነው። ሹርባው ዘመናዊ ስልጣኔ ፈትል፤ የተራማጅ ሐሳቦች አንጓ፣ የለውጥ ፍላጎት የተገመደበት ሚስጢረ ጥበብ ጭምር ነው።
Filed in: Amharic