>

የኢትዮጵያ ፊደል አባቱን አገኘ ! (ማኪ ግርማ)

የኢትዮጵያ ፊደል አባቱን አገኘ !

ማኪ ግርማ

በልጅነቴ ትምህርት ቤት ገብቼ ከፊደል ጋር ፣ ከማንበብና መጻፍ ጋር ፣ ከዕውቀት ጋር ስተዋወቅ በኋላም የፀሎት መጻሕፍትን ጨምሮ መንፈሳዊ ይዘት ያላቸውን መጻሕፍት ገለጥ ሳደርግ ከአንድ የባለውለታዬ ሥም ጋር እገጣጠማለሁ። ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ።
ማንበብና መጻፍ ዋናው ቁምነገር በሆነበት ዘመን ፤ እናትና አባቶቻችን እንኳን መጻሕፍትን ከወዳጅ ዘመድ የተላከውን የናፍቆት ደብዳቤ አንብቦ መልዕክቱን የሚገልጥ ፊደልን የለየ ሰው ማግኘት ከባድ ነበር። ምክንያቱም የአማርኛ ፊደል ማንበብና መጻፍ በቤተክህነትና በቤተመንግሥት ተገድቦ ስለነበር ነው።
ታዲያ ይህ ገደብ ክፍለሃገር ከሚኖሩ ቤተሰባቸው አዲስ አበባ ወደሚኖረው ወንድማቸው የመጡትን የያኔው ታዳጊ ተስፋ ገብረሥላሴንም ጎድቷል። ወደመሐል ሀገር ከመጡ ወዲህ እራሳቸውን ለመለወጥ ሽቶ ከመሸጥ ጀምሮ ያሉ ንግዶችን ሞክረዋል። ፍላጎታቸው ግን መጻሕፍትን መሸጥ ነውና ከተለያዩ ንግዶች ያገኟትን እያስቀመጡ ባጠራቀሙት ጥሪት መጽሐፎችን እየገዙ መሸጥ ጀመሩ።
መቼም ማንበብና መጻፍ እንደህልም የራቃቸውን ማህበረሰብ መጽሐፍ ግዙኝ ማለት ይፈትናል። እንዲያውም አንዳንዶች “አንተን አብረንህ ካልገዛን ማን ያነብልናል” የሚል ምላሽ ይሰጧቸው ነበር። ይህም ለንግዱ እንቅፋት እንደፈጠረባቸው ተረዱና መላውን ይፈልጉ ጀመር። እናም መፍትሔውንም አገኙ።
በወቅቱ በእንጦጦ ማርያም ፣ በበዓታ ለማርያም እና በመካነየሱስ ሥላሴ አጥቢያዎች እንዲሁም በገጠር አቢያተክርስቲያናት ፣ ገዳማትና ዋሻዎች ብቻ ተወስኖ የኖረውን የአማርኛ የፊደል ቅርፅን አሰቡ። አስበውም አልቀሩ። ቀለማቸውን በጥብጠው ከሸንበቆ ብዕር ቀርፀው ብራና ወጥረው ሚያዚያ ፳፫/፲፱፻፲ ዓ.ም የፊደል ገበታን ፈለሰፉ። ማተሚያ ቤት ያልተስፋፋበት ዘመን ነበርና “ዕውቀት ይስፋ ፣ ድንቁርና ይጥፋ ፣ ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ” እያሉ ሳይሰለቹ በእጃቸው መጻፋቸውን ቀጠሉ። ይህንን ያዩ ታላላቅ ሰዎች የኢትዮጵያ ፊደል አባት አገኘ ሲሉ “የኢትዮጵያ የፊደል ገበታ አባት” በማለት ይጠሯቸዋል።
መጻፋቸው በሀሁ ብቻ አልተገታም። አቡጊዳን ፣ መልዕክተ ዮሐንስን ጨምሮ ከ300 በላይ የሃይማኖት መጻሕፍትን ለማዘጋጀትና ለማሳተም በቁ።
የዚሁ መጻሕፍት አዘጋጅና አሳታሚ ፣ የፊደሉ ገበሬ ታዲያ በዛሬው እለት ታህሣስ ፳፬/፲፰፻፺፭ ዓ.ም ከመምህር ገብረሥላሴ ቢልልኝ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ሥዕለ ሚካኤል ወልደአብ በብሔረ ቡልጋ ነው የተወለዱት።
የእኚህን የዕውቀት በር ፣ ድንቁርናን አጥፊ ታላቅነትና ባለውለታነት መታሰቢያ በማቆም ሲዘክር የተመለከትሁት አንድ ተቋም ብቻ ነው። ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ። አንደኛውን ላይብረሪ በስማቸው ሰይሟል። ሌሎቻችንስ?! ያጎረሰንን እጅ የምንነክሰው እስከመቼ ይሆን???
ነፍስ ኄር!
Filed in: Amharic