>

“በጥቁር አንገት ላይ የቆመው የነጭ ተረከዝ ካልተነሳ በቀር እረፍት የለኝም....!!! ”   (ኃይለጊዮርጊስ ማሞ)

“በጥቁር አንገት ላይ የቆመው የነጭ ተረከዝ ካልተነሳ በቀር እረፍት የለኝም….!!! ”
  ኃይለጊዮርጊስ ማሞ

( ለጥቁሮች ሲታገል ፣ በጥቁሮች የተገደለው ጥቁር አርበኛ )
ፌቡርዋሪ 1925 እ.ኤ.አ ፦ አንድ ቀን ምሽት የቄስ ኧርል ሉትል ቤት በፈረስ ተቀምጠው ፊታቸውን በጥቁር ጨርቅ በሸፈኑና ጠምንጃ ባንገቱ ሰዎች ተከበበ። ከበባውንም አስከትለው ለጥቂት ደቂቃዎች ጥይት ወደ ሰማይ ብሎም ወደቤቱ አቅጣጫ መተኮሳቸውን ተያያዙት። የስድስት ወር እርጉዝ የነበረችውና ሦስት ልጆቿን አስተኝታ የባሏን መምጣት ስትጠባበቅ የነበረችው የቄስ ኧርል ባለቤት ሉዊስ ኖርተን ሂል ልጆቿን እየጎተተች ወደ በረንዳ ወጣች።
ከፊታቸው ላይ ባደረጉትና መስቀል በተሳለበት ጥቁር ጭምብል የሰዎቹን ማንነት ለየች። የ<< ኩ – ክለክስ >> ቡድን የሚባሉትና <<የጥቁር ዘር ከአሜሪካ ምድር ሊጠፋ ይገባዋል >> የሚለውን እንቅስቃሴ የሚመሩት የነጭ አክራሪ ቡድን አባላት ነበሩ። ከመካከላቸው አንዱ ወደ በረንዳው ቀረበና <<ባልሽ ሲመጣ ንገሪው ፣ ከአሜሪካ ምድር ጥቁሮች የሚጠፉበት ቀን ደርሷል ፣ እሱንም ቤተሰቡንም ሳንጨርስ ቶሎ ይህን ግዛት ለቆ እንዲወጣ ..!> አላት ይህን ብሎ ወደ ተከታዮቹ በመዞር የጠመንጃውን አፈሙዝ ወደሰማይ አነሳ። በማስከተል የተደረገ ነገር ቢኖር በቄስ ኧርል ቤት ላይ በጥይት እሩምታ ማውረድ ነበር። የተወሰነው የቤቱ ክፍል መቃጠል ሲጀምር አቃጣዮቹ የድል ጩኸት እያሰሙ ወደመጡበት ተመለሱ።
በዚያ ምሽት በማርከስ ጋርቬይ ‛‛ Back to Africa “ ፕሮግራም ላይ ሊካፈል የሄደው ቄስ ኧርል ወደቤቱ ሲመለስ ያልጠበቀውን አስደንጋጭ ትዕይንት ተመለከተ። በወቅቱ በተለያዩ መድረኮች ላይ ለጥቁሮች መብት ለመሞት መዘጋጀቱን ያሳወቀውና ይኽንኑም ዓላማውን በተግባር ያስመሰከረው ቄስ ኽርል በቤተሰቡ ላይ በተፈፀመበት ጥቃት እጅግ ተበሳጨ። የሚስቱና የሦስት ልጆቹ ጥያቄና ውትወታም የዚያን ምሽት ተጀመረ ፦… <<ግዛቱን ለቀን እንሂድ !>> አሉት።
ቄስ ኧርል በጥያቄያቸው ቢስማማም ለመሄድ የሚፈልገው ግን ሚስቱ ለእሱ ሰባተኛ ለእሷ ደግሞ አራተኛ የሆነውንና በሆዷ የሚገኘውን ልጇን ስትወልድ ብቻ እንደሆነ አስታወቀ። በዚሁ ስምምነት አድርገው ለዓመታት ቤታቸውን ሠርተው ፣ ልጆች ወልደው በኖሩባት የኦማራ ግዛት በሆነችው ኔብራስካ ለሦስት ወራት ተቀመጡ። ከሦስት ወራት በኋላ ሜይ 19/1925 ፣ ቤታቸው በተቃጠለ ቀን ምሽት በእናቱ ሆድ የነበረውና የቄስ ኧርል ቤተሰብ በኦማራ ግዛት ኑሮውን ለጊዜውም ቢሆን ለመቀጠል ምክንያት የሆነው ፣ አድጎም መላው ጥቁር ሕዝብ የመኖሩን ምክንያት እንዲያውቅ ያደረገው ሕፃን ማልኮልም ኤክስ ተወለደ።
ማልኮልም ከተወለደ በኋላ አባቱ ቄስ ኧርል ግዛት ለቆ የመሄድ ሐሳቡን ሰረዘ። ቄስ ኧርል የቱንም ያህል የሃይማኖት ሰባኪ ይባል እንጂ በይበልጥ የሚታወቀው በፖለቲካ ተናጋሪነቱና ይልቁንም ደግሞ በጥቁር መብት ታጋይየነቱ ነበር። ማርከስ ጋርቬይ በኒውዮርክ የጥቁርን አመጽ ሲያፋፍም በኔብራስካ የእሱ ወኪል አድርጎ ያስቀመጠውም የማልኮልምን አባት ቄስ ኧርልን ነበር።
የማልኮልም እናትም ብትሆን በጥቁርነቷ ከማንም በላይ የምትኮራና የምትመካ ሴት ነበረች። በተለይ በባሏ በቄስ ኧርል በኩል ከነጮች የመጣባትን አስቸጋሪ ፈተናዎች ሁሉ በጥንካሬ እያለፈች ልጆቿንም የጥቁርን ሕዝብ ትልቅነትና ብርታት ዕለት ዕለት ታስተምር ነበር።
ማልኮልም አድጎ ስለእናቱ ሲናገር ፦ በባህርይዋ ንፁህ እና አፍቃሪ ብትሆንም ለነጮች ግን የተለየ ጥላቻ ነበራት። ይህ ጥላቻዋ ደግሞ አንዳንዴ በልጆቿ ላይም ሳይታወቃት ይንፀባረቅ ነበር ….» ብሏል። ከእነዚህም አጋጣሚዎች ውስጥ አንዱ በራሱ በማልኮልም ላይ ደርሷል።
እናታችን ከልጆቿ ሁሉ የተለየ ፍቅር የነበራት ለታላቃችን ለዊልፍሬድ ነበር። ይህም ያለምክንያት ሳይሆን የቆዳው ቀለም እጅግ ጥቁር ከመሆኑ ብቻ የመጣ ነው። በተለይ እኔ ቆዳዬ ፈካ ያለ በመሆኑ ትበሳጭ ነበር። አንድ ቀን ቤት ስትገባ ወንበር ላይ ተቀምጬ መጽሐፍ ሳገላብጥ አገኘችኝ። ማልኮልም ስትል ጮኸች ፦ .. ውጣና ፀሀይ ላይ ተቀመጥ ፣ ፀሐዩ የቆዳህን ቀለም እንዲያጠቁረው እፈልጋለሁ » አለችኝ። ምንም እንኳን ልጅ ብሆንም በዚያ ጨቅላ አእምሮዬ ስለእናቴ የተረዳሁት ነገር ቢኖር ከልክ ያለፈ የነጮች ጥላቻ በውስጧ መሰንቀሩን ነው።
ከቤተሰቡ ቀጥሎ በአከባቢው ሰፍኖ የነበረውን ነጮች ለጥቁሮች የነበራቸውን ጥላቻ ሲመለከት ያደገው ማልኮልም ገና በልጅነቱ በነጮች ዘንድ የተሰጠውን ቦታ በሚገባ እንዲያውቅ አደረገው። በተለይም “ ኒገር ” “ ዳርኪ ” እና “ ራስታ ” የሚሉት መጠሪያዎች ከስድስት አመቱ ጀምሮ በነጮች ሲጠራባቸው የኖሩ ስሞች በመሆናቸው ከሕፃንነቱ የነጭና የጥቁር ሕዝብን “ ልዩነት ”  እንዲረዳው አስችሎታል።
በ1931 እ.ኤ.አ ማልኮልም የስድስት ዓመት ልጅ ነበር። አንድ ከሰዓት አባቱ ለወትሮው እንደሚያደርገው “ እግሮቼን ላፍታታ ” በማለት ከቤቱ ወጥቶ ሄደ። ነገር ግን ከቤቱ ብዙም ርቆ ሳይሄድ የማልኮልም እናት በሩጫና በጩኸት እያለከለከች ከኋላው ደርሳ ወደቤት እንዲመለስ አዘዘችው። በወቅቱ እናቱን ተከትሎ አባቱ ጋ የደረሰው ማልኮልም የዚያን ጊዜ ትዝታውን ሲናገር ፦ እናቴ የአባቴን እጅ ይዛ መጥፎ ራዕይ እንደተገለጠላትና ባይሄድ እንደሚሻል አጥብቃ ወተወተችው። … አባቴ ግን የእናቴን ንግግር ከቁብም ሳይቆጥር እሷም እያለቀሰች እኔም ልብሷን ይዤ እየተንቀጠቀጥኩ ጥሎን ሄደ …. ወደ ማታ ላይ በቤታችን ተሰብስበን ተቀምጠን የሳሎኑ በር ተንኳኳ። በሩን የከፈትኩት እኔ ነበርኩ ፣ ወደቤታችን ተከታትለው የዘለቁትን ፖሊሶች እናቴ ስታይ በድንጋጤ ተንበረከከች። ብዙም ሳይቆይ ማንነቱ ባልታወቀ ግለሰብ አባታችን በጥይት ተደብድቦ ሆስፒታል መግባቱ ተነገረን። በነጋታውም አባታችን አረፈ ……… ልጅም ብሆን የዚያን ቀን የተረዳሁት እንድ እውነት ቢኖር እኔም አንድ ቀን በነጮች ጥይት መሞቴ እንደማይቀር ነበር።
ይቀጥላል ……
Filed in: Amharic