>
5:13 pm - Tuesday April 19, 2208

የጌታ ልደት... !!! (በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ ) 

የጌታ ልደት… . !!!

በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ 

💥 በነቢያት በተነገረው ትንቢትና በተቈጠረው ሱባኤ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት የተፀነሰው አምላክ 9ወር ከ5 ቀን ሲፈጸም ከቅድስት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና በቤተልሔም ተወለደ፡፡
💥 ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ጌታ ሊወለድ ሲል ከአውግስጦስ ቄሳር ትእዛዝ የወጣበትን ምስጢር ሲገልጸው፦
✍️ “ጌታ አዳምን በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ሊጽፈው በፈለገ ጊዜ ሕዝብ በሕዝብ ቈጠራ መዝገብ ይመዘገብ ዘንድ ትእዛዝ ወጣ (ሉቃ ፪፥፩)፤ ትእዛዛቱ አንድ ላይ ተጣመሩ፤ አንዱ ከላይ ከከፍታ እና ሌላኛው ከታች ከጥልቁ ምክንያቱም የኹለቱ ስፍራዎች ነገሥታት ሕዝብ ሊቈጥሩ ነበርና ቄሳር በሰብኣዊ ቈጠራ መዝገብ ሰዎችን ይጽፋል (ይመዘግባል)፤ ወልድ ግን ደቂቀ አዳምን በሕይወት መዝገብ ውስጥ ያትማል (መዝ ፹፯፥፮)።
💥 ቄሳር ሰዎችን ለራሱ ባለ ዕዳ አድርጎ የሚያስገዛበትን መንገድ ይቀይሳል። ጌታ ግን ባለዕዳዎቹን ይቤዣቸው ዘንድ ያውጠነጥናል፤ መልእክታቸው ግልጽ የኾኑ የኹለቱ ነገሥታት መጻሕፍት (መዛግብት) ተገናኙ ምክንያቱም ንጉሡ በምድር፤ ወልድም በሰማይ ስሞችን መዝግበዋልና
💥 እያንዳንዱ ሰው ስሙን በየራሱ አገር ውስጥ መመዝገብ እንዳለበት ትእዛዝ ተላለፈ (ሉቃ ፪፥፫) ስለዚኽም ለአዳም ርሱ (ክርስቶስ) ስሙን (የአዳምን ስም) በዔዴን ውስጥ መዘገበለት፤ አገሩ ርሷ ናትና በበረከት ምድር፣ በወገኖች ኹሉ መዲና አምላኩ ስሙን ጻፈለት በቀደምት አገሩ በወገኖቹ መኻከል ርሱ ስሙን ጻፈለት።
💥 እና ይኽ ምልክት ከሰማይ በተላከ ጊዜ ይኽ በምድር ይፈጸም ዘንድ ቄሳር አዘዘ፤ እያንዳንዱ ሰው ወደ ከተማው እና ወደ የሰፈሩ (መንደሩ) ይመለስ ዘንድ የመመለስ ምሳሌ ሊኾን፤ ምክንያቱም የተሰደደው ርሱ ወደ ዔዴን ይመለስ ዘንድ ነበርና፤ ትእዛዙ በይሁዳ ምድር ላይ የሚገዛ ስለነበር፤ ኹሉም ሕዝብ በቈጠራው ተመዝግበው ነበርና ተቈጣጣሪዎች ወደ ማርያም እጮኛ ወደ ዮሴፍም መጡ።
💥 ርሱም ይኼድና በዳዊት ከተማ ስሙን ያስመዘግብ ዘንድ ርሱም የድንግልና ውበት ምላት የኾነቺው ርሷን እየመራ መጣ፤ በትእዛዙ መሠረት ስሙን ይጽፍ ዘንድ ወጣ፤ በዚያ ያበራ ዘንድ ንጉሡ ወደ ነገሥታት ከተማ ወጣ በልደቱ የሰውን ዘር በሕይወት መዝገብ ውስጥ ይጽፈውም ዘንድ፤ ብላቴናዪቱ ድንግል በንጹሕ ማሕፀኗ ውስጥ የነገሥታትን ንጉሥ ተሸከመችው ተጉዛም ከዮሴፍ ጋር ወደ ኤፍራታ ወጣች (ሚክ ፭፥፪)።
💥 እነርሱም ወደ ንጉሡ ምድር በደረሱ ጊዜ ርሱ የራሱ የኾነውን ዐወቀ እናም ይገባና በራሱ ግዛት ይቀመጥ ዘንድ ራሱን አዘጋጀ፤ ልጇን መውለድ ነበረባትና ብላቴናዪቱን እናት ጊዜ ወሊድ ኾነላት ምክንያቱም የሕፃናት ሠሪ የመወለጃው ጊዜ ደርሶ ነበርና፤ ርሱ የዳዊትን ከተማ ዐወቃት እናም ገብቶ በርሷ ዐደረ የርሱ አባት በንጉሡ ማደሪያ ይከብር ዘንድ።
💥 ነገር ግን በቤተልሔም ለእናቱ ምንም ስፍራ ስላልነበረ የዐለታት መጠለያ ወደኾነው ዋሻ (በረት) ገብተው በዚያ ተቀመጡ፤ ድኾቹ ባለጠጋውን ርሱን ይዘው ወደተውሶ መኖሪያ ቤት ገቡ ትሑታኑ ከኀያሉ ጋር በባዶ ስፍራ ውስጥ ተቀመጡ፤ ወጣቲቱ በግ የአንበሳ ደቦሉን ለመውለድ ጉልበቷን ዐጠፈች (ዘፍ ፵፱፥፱)፤ ያዕቆብ በበረከቱ ውስጥ ስለ ርሱ የጻፈውን ኀያሉን ለመውለድ (ዘፍ ፵፱፥፰‐፲፪)፤ ወጣቲቱ ርግብ በድንግልናዋ ውስጥ ጋደም አለች ወጣቱን ንስር ታላቁን ንጉሥ በታናሽ ዋሻ ውስጥ ልትወልደው፤ የተወደደችው ጊደር በወጣትነቷ ውስጥ ጋደም አለች (መዝ ፷፰፥፴፩፤ ኢሳ ፯፥፳፩‐፳፪)።
💥 በኀጢአተኞች ፈንታ መሥዋዕት የኾነውን የሠባውን በሬ (ኮርማ) ልትወልደው፤ የሕፃናት አባት (አስገኝ) ራሱን በአካለ ሥጋ ወለደ ርሱም ከማሕፀን ወጣ የድንግልና ማኅተም ግን ምንም ሳይኾን (ሳይነካ) ቀረ፤ የርሱ ልደት መለኮታዊም ሰብአዊም ነው (ቅድመ ዓለም ከአብ፤ ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን) የርሱ ተአምር (ድንቅ) ወሰን የለሽ በመኾኑ ምክንያት የሚመረመር አይደለም፤ ርሱ የባሕርይ አምላክ ነው ማሕፀን በድንግልና ወግ ወልዶታልናል ርሱ ሰው ነው ምክንያቱም ማሕፀን በአካለ ሥጋ ወልዶታልና፤
💥 ርሱ እሳትን ለብሷል፤ በመጠቅለያ ጨርቅም ተጠቅልሏል፤ ግን ደግሞ ከመታወቅ በላይ ነው፤ በዙፋን ላይ ተቀምጧል እንዲኹም በግርግም ተኝቷል፤ ግን ደግሞ አይመረመርም
💥 በኪሩቤል ጀርባ ላይ ተቀምጧል እንዲኹም ጉልበቶች ተሸክመውታል፤ እናም በዚያ ምክንያት ርሱ ታላቅ ነው፤ ርሱ የተፈጠሩ ፍጥረታትን ያላውሳቸዋል እንዲኹም ርሱ አካለ ሥጋን ተውሕዷል እናም እነርሱ ድንቁን ይናገራሉ።
💥 ርሱ ወገኖችን ያኖራቸዋል ርሱ እንዲኹም ወተት ይጠባል፤ ርሱን ይረዳው ያውቀው ዘንድ ማን ይችላል?፤ ርሱ ዝናብን ያዘንባል፤ ርሱ ደግሞ ጡት ይጠባል፤ እናም ድንቁን ተመልከቱ ርሱ ልዑል እና አስፈሪ ነው።
💥 ርሱም የሚቀኝለት ነው፤ እነሆ ድንቁ፤ ሰማይ ለርሱ እጅግ ያንሰዋል እናም ርሱ መኖሪያን ፈለገ፤ እነሆ እንዴት ያለ ጸጋ ነው! ሱራፌል ራሳቸውን ይሸፍናሉ (ይጋርዳሉ)፤ ዮሴፍ ይሰግዳል አንዳች ድንቅ በዚኽ አለና፤ ሥልጣናት ተዘርግተዋል ሰዎችም ደካሞች ናቸው፤ ያስተውል ዘንድ ግን ማን ይችላል?) በማለት አስተምሯል፡፡
ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ታላቅና አስደናቂ ስለሆነው የልደት ምስጢርን በመጽሐፈ ምስጢር ላይ ሲገልጸው፦
✍️ “በዚያ ያለ እናት አባት አለው (መዝ ፪፥፯፤ ዳን ፯፥፲፫-፲፬) በዚኽም ያለምድራዊ አባት እናት አለችው (ሉቃ ፪፥፯)፤ በዚያ ገብርኤል በፍርሀት ይቆማል (ሉቃ ፩፥፲፱) በዚኽም ገብርኤል በሐሤት የምሥራችን ይናገራል (ሉቃ ፩፥፳፮)፤ በዚያ በጽርሐ አርያም የሚደነቅ ከማይታይ አብ የመወለድ ምስጋና አለው በዚኽም በቤተልሔም ከድንግል መወለድ ምስጋና አለው (ሉቃ ፪፥፩-፯)።
✍️ በዚያ ከሰማያውያን ካህናት በወርቅ ማዕጠንት የዕጣኑን መዐዛ ይቀበላል (ራእ ፰፥፫-፬) በዚኽም ወርቅንና ከርቤን ዕጣንንም ከሰብአ ሰገል ተቀበለ (ማቴ ፪፥፲፩)፤
✍️ በዚያ ኪሩቤልና ሱራፌል ከግርማው የተነሣ ይንቀጠቀጣሉ በዚኽም ማርያም ዐቀፈችው ሰሎሜም አገለገለችው፤ በዚያ የመብረቅ ብልጭልጭታ በፊቱ ይገለባበጣሉ የእሳትም ወላፈን ከአዳራሹ ይወጣል (ሕዝ ፩፥፲፫) በዚኽም አህያና ላም በትንፋሻቸው አሟሟቁት (ኢሳ ፩፥፫)።
✍️ በዚያ የእሳት ዙፋን አለ በዚኽም የደንጊያ በረት አለ፤ በዚያ የእብነ በረድ የሰማይ ንጣፍ አለ በዚኽም የላሞች መጠጊያ በረት አለ፤ በዚያ የትጉሃን ሥፍራ በሰማያት ያለች ኢየሩሳሌም አለችው በዚኽም የእንስሳት ጠባቂዎች ማደሪያ በኣት አለው (ሉቃ ፪፥፯)፤ በዚያ ርዝማኔ የማይታወቅ የዳንኤል ብሉየ መዋዕል አባት አለው (ዳን ፯፥፲፫-፲፬) በዚኽም የዓመቶቹ ቊጥር በሰው ልጅ ዐቅም መጠን የኾነ ሽማግሌ ዮሴፍ ተሸከመው።
✍️ የአምላክን ልጅ ሰው መኾኑን በዓል እናድርግ የተሸከመችውን ማሕፀን እናመስግን፤ ላቀፉት ጉልበቶች እንስገድ፤ ላሳደጉት ጡቶች እንዘምር፤ የዳሰሱትን እጆች እናመስግን፤ ለሳሙት ከንፈሮች እናሸብሽብ፤ ከእረኞች ጋር ምስጋናን እናቅርብ፤ ከሰብአ ሰገልም ጋር እጅ እንንሣ።
✍️ እንደ ዮሴፍ እናድንቅ እንደ ሰሎሜም እናገልግል በተኛበት በረት እንስገድ፤ በተጠቀለለበት በረት እንበርከክ፤ ለእግዚአብሔር በሰማያት ምስጋና ይኹን በምድርም ሰውን ለወደደ እንበል (ሉቃ ፪፥፲፬)፤ እግዚአብሔር ሰው ኾነ የሰው ልጅ ሴት ልጅም የእግዚአብሔር እናት ኾነች፤ ለርሱ ምስጋና ይኹን ለርሷም ስግደት ይገባል ለዘላለሙ አሜን ይኹን) በማለት በጥልቀት ገልጾታል፡፡
💥 ይኸው የቤተ ክርስቲያን ሊቅ በድጋሚ በሰኞ አርጋኖን መጽሐፉ ላይ፦
✍️ “ሥርዐተ ሰማይ ከማሁ ተሠርዐ በዲበ …” (የሰማይ ሥርዐት በምድር ላይ ተሠራ፤ ቤተልሔምም እንደ ሰማይ ተመሰለች፤ በሚጠልቅ ፀሓይም ፈንታ በቅዱሳን ላይ ዘወትር የሚያበራ ኅልፈት ጥልቀት የሌለበት አማናዊ ፀሓይ ኢየሱስ ክርስቶስ በውስጧ ወጣ (ሚልክ ፬፥፪)።
✍️ ከብርሃኑ ጒድለት መምላትን የማያፈራርቅ በጨረቃ ፈንታ የድንግልናዋ ምስጋና ዘወትር የማይጐድል በኹሉ የመላ በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባለች የተመረጠች ድንግል ማርያም ተገለጠች (መሓ ፮፥፲)፤ በክዋክብት ፈንታም የብርሃን መላእክት ታዩ (ሉቃ ፪፥፲፫)። በማለት የእናትና የልጅን ነገር በጥልቀት ሃይማኖታዊ አገላለጽ ገልጾታል፡፡
💥 ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያም የአምላክ እናትነቷን በእናትና በልጅ መኻከል ያለውን መለያየት የማይችል ፍጹም ፍቅርን ሲገልጸው
💥 “ስለእኛ መዳን በቤተ ልሔም ውስጥ ወለደችው በመናኛ የመታቀፊያ ኩታ ጨርቅ ጠቀለለችው፤ በከብቶች ማደሪያ በረት ውስጥ አኖረችው፤ እንስሳትም ርሱን ተመልክተው ዐውቀውት ተገዙለት (እስትንፋሳቸውን ገበሩለት) (ሉቃ ፪፥፮-፯)። ቅድስት ድንግል ማርያምም የቀኝ ክንዶቿን ዘርግታ በእጆቿ አንሥታ በግራ ክንዶቿ ውስጥም እንዲያርፍ አደረገችው …።
💥 ርሷም ርሱን ስማ በጉልበቶቿ ላይ አሳረፈቻቸው፤ ዐይኖቹን ወደ ፊቷ አዞራቸው እጆቹንም ዘርግቶ ጡቶቿን በመሳብ ከመና ይልቅ በጣም ጣፋጭ የነበረውን ወተቷን ባፉ ውስጥ ጨመራቸው፤ ጣእሙም ከኖኅ የመሥዋዕት ሽታ ጣዕም የበለጠ ለርሱ ጣፋጭ ነበረ (ዘፍ ፰፥፳-፳፩) ከንጹሓት ጡቶች ወተትን እየጠባ “የእኔ እናት” ብሎ ይጠራል።
💥 እግዚአብሔር ማርያምን “እናቴ” እያለ በመጣራት አፎቿን ሲስማት ኑና ተመልከቱ፤ ርሷም ኹልጊዜ አፉን እየሳመች “ጌታዬና ልጄ” እያለች ትጠራዋለች፤ ታመልከዋለች፤ ጡቶቿንም ስትመግበው ራሷን ለክብሩ ወደርሱ ታስጎነብሳለች፤ ርሱም እንደ ዐምድ ሲቆም “ጌታዬ እና ልጄ” በማለት ታመልከዋለች፤ እናም ከእነዚኽ ነገሮች በኋላ እጆቹን በመያዝ በመንገድ ላይ ይዛው ስትጓዝ “የኔ ጣፋጭ ልጅ ትንሽ ተራመድ” እያለች ልክ ሌሎች ልጆች ኹሉ መኼድ እንደሚማሩት ኹሉ በእግሩ እንዲኼድ ታስተምረዋለች።
💥 የባሕርይ አምላክ ክርስቶስም ያለምንም ችግር ተከትሏት ይጓዛል፤ በትናናሽ ጣቶቹም ይይዛት ነበር፤ በየመኻሉም በመቆም በርሱ ፍጥረታት ኹሉ እንደተያዙ እንደተንጠለጠሉ ርሱም በእናቱ ሸማዎች ላይ ይንጠላጠላል ፍጥረት በመላ በርሱ የተያዙ የሚኖሩት ርሱ ወደ ፊቷ ይመለከታል። ወደ ሰውነቶቿ አስጠግታ አጥብቃ ዐቅፋው በክንዶቿ ወደ ላይ አንሥታ ትሸከመዋለች፤ እናንተ ሴቶች ሆይ በመላ ኑና ከርሷ መወለድ የመረጠው እግዚአብሔር ፊቶቹን አንሥቶ ሲስማት ተመልከቱ፡፡”
በማለት ትክክለኛውን የቤተ ክርስቲያን የእውነት ትምህርትን አጒልቶ አስተምሯል፡፡
💥 በድንግልና የኾነው ልደት ፅንሱና በግብረ መንፈስ ቅዱስ የኾነ የእግዚአብሔር ልጅ ሲፀነስ የእናቱን ማኅተመ ድንግልና ሳይጥስ እንደኾነ ኹሉ ሲወለድም አለወጠውም፤ ክብር ይግባውና ልዑል እግዚአብሔር በኢሳይያስ 7፡14 እና በሕዝቅኤል በምዕ ፵፬፥፩-፪ ላይ የእናቱን የዘላለማዊ ድንግልናዋን ነገር በትንቢት አናግሮላታል፡፡
💥 ከዚኹ ጋራ የዘላለማዊ ድንግልናዋ ምሳሌ የሚኾኑ በርካታ ምሳሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሲኖሩ በተጨማሪም የኅቱም ድንግልናዋ ምሳሌ የሚኾኑ የሊቃውንት ምሳሌዎች አሉ።
✍️ ይኸውም የእያንዳንዱ ሰው መልክ በሰው የዐይን ብሌን ውስጥ ገብቶ ይታያል።
❤ ኹለተኛም ፀሓይ የመስኮት መስታዮትን ሳትሠነጥቅ ወደ ቤት ውስጥ ገብታ ትታያለች።
❤ ሦስተኛም የእያንዳንዱ ሰው አምሳለ መልክእ መስታዮትን ሳይሰብር (ሳይሰነጥቅ) በውስጡ ይታያል።
❤ዐራተኛም ግንባራችንን ሳይሰነጥቀው ወዛችን (ላባችን) ይወጣል፤ እነዚኽ ግዙፋን እንኳን የርቀት ሥራ ሲሠሩ ረቂቅ ዘእምረቂቅ የኾነው የባሕርይ አምላክ አካላዊ ቃል ክርስቶስም የእናቱን የቅድስት ድንግል ማርያም ማኅተመ ድንግልናዋን ሳይጥስ እንደተፀነሰ ኹሉ ዳግመኛም ማኅተመ ድንግልናዋን ሳይለውጥ በኅቱም ድንግልና በቤተልሔም ተወልዷል።
💥 ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዳኢ ይኽነን ሲያስረዳ ✍️ “ተወልደ እምድንግልና እንዘ ኅቱም ድንግልናሃ ከመ ልደተ ንጻሬ ዐይን ወከመ ልደተ ሐፍ እምገጽ፤ ወከመ ልደተ መልክእ እመጽሔት”
(ከዐይን ንጻሬ፣ ከግንባር ወዝ ሳይሰነጥቀው፣ ከመስታዮት አምሳለ መልክእ ሳይሰብረው እንዲወለድ ጌታም ማኅተመ ድንግልናዋን ሳይፈታ በኅቱም ድንግልና ተወለደ) በማለት ምሳሌውን እንደ ወርቅ አንከብሎ እንደ ሸማ ጠቅልሎ አስቀምጦታል፡፡
💥 አምላካችን እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ፀንሳው በኅቱም ድንግልና እንድትወልደው ትንቢት ሲያናግርላት ምሳሌም ሲያስመስልላት ምስጢሩ ግን ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንደገለጸው ነው፤ ይኸውም ሊቁ በሃይማኖተ አበው ላይ፦
✍️ “ወሶበሂ ወለደቶ ዐቀበ ድንግልናሃ ዘእንበለ ርኲስ ከመ በፅንሳ መንክር ትኩን መራሂተ ለሃይማኖት ዐባይ” (በወለደችውም ጊዜ ድንግልናዋን ያለመለወጥ አጸና፤ ድንቅ በሚኾን ፅንሷ ለደገኛው ሃይማኖት መሪ ትኾን ዘንድ) በማለት እንዳስተማረው።
✍️ ርሷ ስትወልደው ማኅተመ ድንግልናዋ አለመለወጡ ሰው ኹኖ ባሕርየ መለኮቱ ላለመለወጡ።
✍️ ርሷ “ድንግል ወእም” (ድንግልም እናትም) እንደምትባል፤ ርሱም “አምላክ ወሰብእ” (አምላክም ሰውም) ሲባል የመኖሩ የሃይማኖት ምስክር ናትና በእውነት ርሱ የባሕርይ አምላክ እናቱም ወላዲተ አምላክ እንደ ኾነች ለማጠየቅ በኅቱም ድንግልናዋ ፀንሳ በኅቱም ድንግልናዋ ወልዳዋለች፡፡
💥 በዚኽም ወልድ ዋሕድ አካላዊ ቃል ክርስቶስ ኹለት ልደታት ብቻ አሉት። እነርሱም፦
1) ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ (ማቴ 3፡17፤ ማቴ 17፡5-7)
2) 5,500 ዘመን ሲፈጸም ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለአባት (ማቴ 1፡19-23፤ ሉቃ 1፡27-38፤ 2፡7)
💥 በተጨማሪም ጌታችን ልደቱን በዘር በሩካቤ ያላደረገው ያለ ዘር ያለ ሩካቤ ያደረገው ለኹለት ምክንያቶች ሲኾን፦
፩ኛ/ በኹለተኛው ልደት ቀዳማዊዉን ልደት ለመግለጽ ነው ይኸውም ፭ሺሕ፭፻ ዘመን ሲፈጸም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ ዘር ያለ አባት መወለዱ፤ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት መወለዱን ያስረዳልና፤ “ልደት ቀዳማዊ ተዐውቀ በደኀራዊ ልደት” እንዲል
፪ኛ/ በተጨማሪም ጌታ ልደቱን በዘር በሩካቤ አድርጎት ቢኾን ኖሮ ተጠራጣሪዎች ዕሩቅ ብእሲ ነው አንጂ የባሕርይ አምላክ አይደለም ባሉ ነበርና በእውነት የባሕርይ አምላክ እንደ ኾነ ለማጠየቅ ጌታችን ልደቱን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ያለ ዘር ያለ ሩካቤ አድርጎታል።
💥 ሊቁ ዮሐንስ አፈ ወርቅም ይኽነን ሲገልጽ “ሶበሰ ወፅአ እምትድምርተ ሰብሳብ ዘከማየ ብዙኀን እምተሐዘብዎ ወእምሐሰውዎ” (እንደ እኔስ በዘር በሩካቤ ተወልዶ ቢኾን ብዙ ሰዎች ዕሩቅ ብእሲ ባሉት ነበር፤ አምላክነቱንም በካዱ ነበር) ብሏል፡፡
💥 ከቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና የተወለደው ዐማኑኤል የመላእክት ፈጣሪ ነውና መላእክት አመስግነውታል፤ እውነተኛ እረኛ ነውና እረኞች ከመላእክት ጋር በኅብረት “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ” (በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን በምድርም ሰላም ኾነ ለሰው በጎ ፈቃድ) (ሉቃ 2፡14) በማለት ዘምረዋል፡፡
💥 የእንስሳት ፈጣሪ ነውና ላምና አህያ እስትንፋሳቸውን ገብረውለታል (ኢሳ 1፡3)።
💥 የነገሥታት ንጉሥ ነውና ሦስቱ ነገሥታት ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤ ገብረውለታል፡፡ በልደቱ ሕይወትን ለሰጠን ከቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና ለተወለደው ለአምላካችን ለለዐማኑኤል ክብር ምስጋና ይኹን አሜን።
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
የቴሌግራም ቻናል https://t.me/Rodas9
Filed in: Amharic