አገራችን ኢትዮጵያ….!
ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)
እንደመግቢያ
ኢትዮጵያ አገራችን የረጅም ዘመን ታሪክ ባለቤትና ጥንታዊ ስልጣኔ ያቆጠቆጠባት ሀገር ብትሆንም በ21ኛው ክፍለ ዘመን በድህነት ተተብትባ የምትገኝ ሀገር መሆኗ ሲታሰብ እድሏን አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ በነገራችን ላይ የአንድ ህዝብ ህልውና አስተማማኝ የሚሆነው በከርሰምድርና ከመሬት በላይ የሚገኘው የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ በጥቅም ላይ ሲውል መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ተፈጥሮ ለኢትዮጵያ ከለገሳት ዘላለማዊ ሀብት መካከል የውሃ ሀብቷ በቅድሚያ የሚጠቀስ ነው፡፡ ግን ባለመታደል የዚህ ሀብት ተጠቃሚዋ የሆነችው ኢትዮጵያ ሳትሆን በበጎ አይን የማይመከቷትና ምቹ ግዜና ወቅት ጠብቀው ህልውናዋን የሚፈታተኑ አገሮች ናቸው፡፡ ( ባለፉት ጥቂት አመታት ግብጽና ሱዳን አንዲሁም ከሌሎች የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በማበር ኢትዮጵያ ላይ የሚሰሩትን እኩይ ደባ ልብ ይሏል፡፡ )
ለምሳሌ የአባይን የውሃ ሀብት ብንወስድ የእኛው ጥቁር አባይና ከቪክቶሪያ ሐይቅ የሚፈሰው ነጭ አባይ ተዳምረው ከተቀላቀሉ በኋላ በጠቅላላው 80.84 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ ይይዝና ናይል የሚል ስም የያዘ ትልቅ ጅረት ሱዳንና ግብጽን ይታደጋል፡፡ 55.5 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ የሚሆነውን ውሃ ግብጽ በረሃዎቿን ለማልማት ትጠቀምበታለች፡፡ ግን በጥቁር አባይና በሌሎች ጅረቶች ለትልቁ የናይል ወንዝ ከመቶ ሰማንያ ስድስት እጁን ( 86 ፐርሰንት) ውሃ የኢትዮጵያ ድርሻ የነበረው ከአንድ ቢልዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ የሚያንስ ማለትም 0.6 ቢልዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ ብቻ እንደሆነ ዛሬ ኑሮአቸውን በምድረ ሲውዲን ያደረጉት እውቁ የውሃ ምህንድስና ተጠባቢ ዶክተር አድማሱ ገበየሁ ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ እንዳነበብኩ አስታውሳለሁ፡፡ የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው ይሏል ይሄ ነው፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ በአጼ ሀይለስላሴና በኮሎኔል መንግስቱ ዘመነ መንግስት የአባይን ወንዝ ለመገደብ ተጋድሎ ያደረገችው ኢትዮጵያ ዛሬ ተሳክቶላት በታላቁ የአባይ ወንዝ ላይ ግድብ በመገንባት የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት መንፈሳዊ ወኔ ታጥቃ ከተነሳችባቸው ካለፉት ሰባትና ስምንት አመታት ወዲህ ሱዳንና ግብጽ እንዲሁም የተባበረችው አሜሪካ አንዳንድ የአረብ ሀገራት ደንቃራ መሆናቸው ሲታሰብ የተፈጥሮ ሀብታችን የሆነውን የገዛ ውሃችንን ጥቅም ላይ እንዳናውል መሰናክሉ ብዙ እንደሆነ ነው፡፡ ግራም ነፈሰ ቀን በውስጥና ውጭ ምክንቶች ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት በአብዛኛው መጠቀም ያልቻለች ሀገር ናት፡፡
ዓይጥ የሠይጣን ግልገል
መሥፍን ኃብተ ማርያም የሚባሉ በፈጠራ ፅሑፍ አፃፃፍ ሙያቸው ግሩም ጸሃፊ የነበሩ ሰው ነበሩ ። ዛሬ በህይወት የሉም፡፡ አፈሩን ገለባ ያድርግላቸው፡፡
በቡና ቤት ሥዕሎች አፃፃፋቸው አንብቦ ወይም ሰምቶ ያልተደመመ የኔ ትውልድ ሰው አይኖርም ብዬ ልገምት ።
የዓይጥን መጥፎና ክፉ ፀባዩዋን ከተረዱ በኋላ የፃፉትና በ1985ቱ አካባቢ ከመፅሐፍት ዓለም ትረካ ሰኞ ጠዋት በኢትዮጵያ ሬዲዮ ስሙ በተዘነጋኝ አንድ ስመጥር ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ይነበብ የነበረ መፅሐፍ ነበረ ።
እንዴት ለመፃፍ እንደተነሳሱ መሥፍን ከትረካው በኋላ ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው ተራኪ ጋዜጠኛ ሲጠይቃቸው እንዲህ አሉት ።
ለጉብኝት ሆለታ እርሻ ምርምር ሄጄ ሳለሁ የዓይጥ ጥናትና መከላከል ክፍል ስገባ ያየሁትን የዓይጥ ዝርያ ዓይነት ናሙናዎች በባለሙያው ከተገለፀልኝ በኋላ ነው ይላሉ ።
በርግጥ መፅሐፉ በርሳቸው ውብ አድርጎ የመግለፅ ችሎታቸውን ይዞ እንደ ባለሙያ ደግሞ ሥነ ሕይወትና ፀባይዋን ሲገልፁት መሥፍን የዓይጥ ስፔሺያሊስት ይመስላሉ ። ድንቅ አድርገው ዓይጧን ገለጿት ።
እኔም ልጅ ሆኜም እፈራት ነበርና የበለጠም ፈራኋት ።
በአንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ኮርስ ላይ የባይሎጂ ክፍል ትምህርት ተማሪ የነበረ ጓደኛዬ የባሻወልዴ ችሎት አራዳ የላብራቶር ክፍል ይዦኝ ገብቶ በሰቀቀን ተምሬ ጨረስኳት ። የደረቀ ቆዳዋ ናሙና ተወጥሮ ባያት ሳገላብጣት ነፍስ የምትዘራ እየመሰለኝ ተቸገርኩኝ ።
ዓይጥ አጥፊ ነች ። ጠንቀኛም ቀበኛም ነች ።
በሰው ልጅ ጤናና በንብረቱ ላይ የምታደርሰው ጉዳትና ብክነት ከፍተኛ ነው ።
የኛዎቹ ሜቴኮችንና መሰሎቹንም ትበልጣቸዋለች ።
እነርሱም ከርሷ ተምረው ይሆን ጥፋትና ብክነትን ?
ጓደኛዬ በግብርና ሚ /ር ሳለ( አሁን በውጭ ሀገር ይገኛል) በሾላ አዝርዕት ጥበቃ ላብራቶር በፀረ – ተባይ ምዝገባና ቁጥጥር ክፍል ሲሰራ ሁለት ባልደረቦች በዓይጥ ጥናትና መከላከል ክፍል እንደነበሩት አውግቶኝ ነበር ።
ለማሠልጠንና ለማገናዘቢያም የሚሆን መፅሔትም ያሳተሙት ነበር ። ማንም ቢያነበው ይረዳዋል ።
በርካታ የዓይጥ ዝርያ ዓይነቴዎችም በአገራችን እንዳሉም ይታወቃል ።
ሰው መሰል ዓይጦች ከቀርጥፎቹ ጉዳታቸው ያንስ ይሆን ?የብዙ ሀገራት የድህነት መንስኤ በተለይም በአፍሪካ በአብዛኛው ሀገራት የድህነት መንስኤዎች ተዘርዝረው የማያልቁ ሲሆን ሰረታዊውና ዋነኛው ምክንያት የአልጠግብ ባዮች መሰሪ ተንኮል ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት ሰዎች ከታችኛው ማህበረሰብ እስከ ላይኛው ባለስልጣናት፣ፊደል ቆጠርኩ ከሚለው እስከ የአቦጊዳው ሽፍታ፣በግብርና ስራ ከሚተዳደረው እስከ ነጋዴው ወዘተ ወዘተ ውስጥ ተሰግስገው አሉ፡፡ የሙሰኛው ጉዳይ ተከድኖ ይብሰል፡፡ ለማናቸውም የአይጥ ባህሪ የተጠናወታቸው ሰዎች ለአንድ ሀገር ድህነት ውስጥ ዝንተ አለም መዘፈቅ መሰረታዊ ምክንያት ስለመሰሉኝ ነው የአይጥን ባህሪ ማምጣቴ፡፡
ዓይጥ መቼስ ቢሆን ቅዱስ ሆና ታውቃለች ?
አቤት እንደምታስጠላኝ ።
ልጆች ሳለን ዓይጧ መጣች እያሉ ያስፈራሩን ነበር ። ስናድግ ጥፋቷን ተማርን ።
ዓይጥ በአሥራ አራተኛው ክፍለ ዘመን መሰለኝ ” ጥቁር ሞት ” በመባል ለሚታወቀው በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አውሮጳዊያን ሞት ምክንያትም ጭምር ነች ።
በዛን ጊዜ የፈጀቺው ሰው ቁጥር ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ካጠፋቸው በላይም ነው ተብሎ ይገመታል ።
አደገኛ በሽታ አምጭ ህዋስ ተሸካሚና ወደ ሰው በቀላሉ ማስተላለፍ ትችላለች ።
ዓይጥ ገፊ ነች ። የታባቷንሳ !
ዓይጥ የሠይጣን ግልገል ነችና ጠንቋን ሳታስከትል በፊት ምሷን በጊዜ ማግኘት አለባት ።
የኢትዮጵያ ቆዳ ስፋት
እንደ አገኘሁት መረጃ የአገራችን የቆዳ ስፋት 1,221,480 ስኰር ኪሎ ሜትር ወይም 122,148,000 ሄክታር መሬት ነው።
ልብ በሉ ሰፊ ነው ። በ1980 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል የጂኦግራፊ መምህሬ የነበሩት ጋሼ ውብሸት በዛ ነጎድጓዳማ ድምጻቸው እንዳስተማሩን የኢትዮጵያ መሬት፣በከርሰ ምድሩ ውስጥ የተኛውን ውሃና ወራጅ ውሃ እንደፈለገው ገርቶ የአይምሮ፣መንፈሳዊና የጡንቻውን ሀይሉን ሙለበሙሉ መጠቀም የሚችል ህዝብ ቢያፈራ ኖሮ ከ400 ሚሊዮን በላይ ህዝብን መመገብ የሚችል ነበር፡፡ በአጭሩ በግዜው የአፍሪካ ህዝብ ወደ 400 ሚሊዮን የሚጠጋ ስለነበር አፍሪካን መመገብ ይችል ነበር ያሉን በቁጭት፡፡ እንኳን አፍሪካን ልንመግብ ዛሬም አብዝሃው ህዝቧ የተመጣጠነ ምግብ ብርቁ ነው፡፡ በእውነቱ ለመናገር ህሊናን ያደማል፡፡ሆድንም ይበጠብጣል፡፡
አንዳንዱ የኢትዮጵያ መሬትን የሸፈነው እጽዋት ቢከላምና ቢጋጥም ፤( እጽዋቶች ተጨፍጭፈው ቢያልቁም) አንዳንዱ መሬቷ ደግሞ ለምና ድንግል ነው ። አለም ከተፈጠረ ጀምሮ የሰው ልጅ ያልሰፈረባቸው ቦታዎች አሉ ይባላል፡፡ ለአብነት ያህል የሰሜን ኦሞ ሸለቆ፣የኢሊባቡር እና ጋምቤላ ፣ማጂ አንዳድ አካባቢ የሚገኙ ጥቅጥቅ ያሉ ጫካዎች ይጠቀሳሉ፡፡
ከአምስት አመት በፊት አንድ ኑሮአቸውን የተባበረችው አሜሪካ ያደረጉ ኢትዮጵያዊ የአፈር ሳይንቲስት ካቀረቡት የጥናት ወረቀት ላይ ባነበብኩት መረጃ መሰረት በደምሳሳው ለሕዝባችን ቁጥር ብናካፍለው ለእያንዳንዳችን ወደ 1.2 ሄክታር መሬት ይደርሰናል።
ጌቶችም አይደለን ?
ጥጋብ ነው በል ጃል !
ግን የግብርና ሥራን፤ ኑሮንና ተያያዢ ጉዳዮችን ስንታችን እንመኘው ይሆን ?
ሰው ጠፋ እንጂ መሬቱ መች ጠፋ !
ይህም ብቻ አልነበረም ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ በመባል የምትታወቅ ሀገር ስትሆን የበርካታ ወንዞችና ሀይቆች ባለቤት ናት፡፡ ለአብነት ያህል ባህርዳር በአባይ ወንዝና ጣና ሀይቅ የተከበበች ሲሆን ድሬ ደግሞ በከርሰ ምድር ውሃ ሀብት የታደለች ናት፡፡ ድሬ ባላት የከርሰ ምድር ውሃ ተጠቅማ በድሬዳዋና አካባቢው በአፍሪካ ውስጥ ዳርፉር ከሚባለው የሱዳን ግዛት በቀር በከርሰ ምድር ውሃ ሀብት የሚወዳደረው እንደሌለ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ግና አብዛኛው የድሬ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ለእርሻ ጥቅም አልዋለም፡፡ ድሬ ከቁልቢ ከፍተኛ አካባቢ የሚዘንበው ከፍተኛ ዝናብ በጎርፍ መልክ ለዘመናት ያረሰረሳት ከተማ ብትሆንም አሁን ድረስ በእርሻው መስክ እራስን ለመቻል ከመንግስትም ሆነ ከባለወረቶች አኳያ ንዋይ በማፍሰስ የተከናወኑ ታላላቅ ፕሮዤዎች የሉም፡፡ በእቅድ ደረጃ ግን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በአነስተኛ ደረጃም የመስኖ እርሻዎች አሉ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እነኚህ በቂ አይደሉም፡፡ ከዛሬ 13 አመት በፊት ድሬዳዋ የትምህርት ቢሮ ለ 3 አመታት በስራ አጋጣሚ በቆየሁባቸው ግዜያት አንዳንድ መንፈሰ ጠንካራ እና የስራ አርበኛ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ዜጎችን ተመልክቻለሁ፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ሰፊ የወተት ሀብት ልማት በማልማት የሚታወቁት አቶ አብዱላሂ(ስማቸውን ከተሳሳትኩ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡) ለድሬዳዋ ከተማ ወተት በማቅረብ የሚታወቁ ባለሀብት ነበሩ፡፡ ሌላው ባለሀብት አቶ በዙ የሚባሉ ሲሆን በቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዘመን ጀምሮ ለአመታት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገልግለው ጡረታ በወጡባት ድሬ ላባቸውን አንጠፍጥፈው የሼል ነዳጅ ማደያ፣አንድ ዘመናዊ ሆቴል እና ሰፊ የእርሻ ልማት ለማልማት የቻሉ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡ ግና ምን ያደርጋል የአቶ በዙ መጨረሻ አላማረም ነበር፡፡ ጸሃፊው ከባለሀብቱ ጋር በአንድ የማኪያቶ ወግ ግለሰቡ እንደነገሩትና ያለሙትን የእርሻ መሬት ጎብኝቶ እንደተመለከተው በግዜው በነበሩት አንድ የአካባቢው ባለስልጣን ትእዛዝ የደረሱ አትክልቶችና ፍራፍሬዎች ሙሉበሙሉ እንዲወድም ተደርጎ ነበር፡፡ አቶ በዙ የፍትህ ያለ በማለት እስከ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የክስ ዶሴ በመምዘዝ ብቻቸውን ያለ ህግ ጠበቃ ቢከራከሩም የመጨረሻውን የፍርድ ውሳኔ ለመስማት ሳይችሉ በተፈጥሮ ህመም ምክንያት ይህቺን አለም ተሰናብተዋል፡፡ በነገራችን ላይ አቶ በዙ በምንም አይነት መልኩ ለባለስልጣናት ምልጃ መስጠት ስለማይፈልጉ የመንግስት ግብር አልከፈልክም በሚል የጥቃት ሰበዝ እንደተፈተባቸው አውግተውኝ ነበር፡፡ ጉዳዩን ያነሳሁት አንባቢውን ለማሰልቸት፣ውዳሴ ከንቱ ለማቅረብ አይዶሎም፡፡ ማንም ሰው ደፍሮ ያልገባበትን የእርሻ ስራ የሚያከናውኑ ባለወረቶችን እንዲህ ተስፋ የሚያስቆርጥ ድርጊት ይፈጸምባቸው እንደነበር በማስታወስ፣ የዛሬዎቹ የድሬ አስተዳዳሪዎቹ ደግሞ ካለፉት አንዳንድ ሙሰኛ ባለስልጣናት ከሰሩት ከባድ ስህተት በመማር በድሬ የመስኖ እርሻ እናለማለን ለሚሉ ባለወረቶች ማበረታቻ መስጠቱ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ስለመሆኑ ማስታወስ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በድሬ በድጋሚ እያቆጠቆጠ ያለው የፋብሪካዎች ግንባታ ይበል የሚያሰኝ ሲሆን፣ ሰፊውን ህዝብ ደግሞ የበለጠ የሚጠቅመው የእርሻ ልማት ስለሆነ ትኩረት ቢሰጠው መልካም ነው፡፡ የድሬን የከርሰ ምድር ውሃ በዘመነ ሁኔታ መጠቀም ከተቻለ ድሬን ሙሉበሙሉ በከዚራ ጥላ መክበብ ይቻላል፡፡ የቀደሙት አባቶቻችን አንድ የከዚራ መንደር ጥለው እንዳለፉት ሁሉ አሁን ያለው ትውልድ ደግሞ በርካታ በትላልቅ አረንጓዴ ተክሎች የተከበቡ ከዚራዎችን መፍጠር አለበት፡፡
ይህንን ቀዳማይ የሐብት ምንጭ ( መሬት ) በአግባቡ ከተጠቀምንበትና ለምነቱን በዘመነና አካባቢን ለመጠበቅ በሚያስችሉ አሠራር ከተገለገልንበት ፤ ከዚሁ መዋዕለ ነዋይ በምናገኘው ትርፍና በምናስወልደው ተጨማሪ ንዋይ (ሃብት )ኑሯችንን እየኖርን መጭውን ትውልድ ዕዳና ቀውስ ውስጥ ሳናስገባው እኛም አሮጌዎቹ የጡረታ ዘመናችንን ትናንት ባፈራነው ሐብት ስንኖር፤ አዲሱ ትውልድ ደግሞ እኛን ተቀብሎ የኑሮ ግብ ግቡን ውጣ ውረድ በላቡ እንዲኖር እናደርገውና ብልጽግናውን እንዲደርስበት ማድረግ ይቻል ነበር ።
ልብ በል ! ይሄ ታዲያ ምኞትና ፍላጎት ነው አይከለከል !
ታዲያ ይህ መንግሥት የሚባለው ፖለቲካዊ ተቋም ሕግንና ሥርዓትን ማስከበር የሚችለው እንዲህ መሬቷ ተከፍታና ተቀብላ ያለኝን ልስጣችሁ እንዳለችን ሁሉ ፤ ያላትን ሃብት ያለ አድልዎና ማግለል ነዋሪዎቿን በአግባቡ በእኩልነት የሚገባቸውን ሲደለድሏት ነው ።
ሚዛኑ እንዳይንገጫገጭና ወዲያና ወዲህ እንዳይል መስፈሪያና መለኪያዎቹ ሁሉ መሬትን ለሚሰሩባትና ለሚወዷት በእኩል ካዳረሱት ነው ።
ጥቂቱን ብቻ ጠቅሞ ብዙሃኑን ማግለልና ወደ ድህነት ደረጃና መቀመቅ ወሰጥ መክተት የኋላ የኋላ አደጋ አለው።
ባልተጠበቀ መልኩ ሁከት ፤ ዐመፅ ፤ ረብሻ ፤ ነውጥ ፤ ጉም ጉም ፤ ድህነት ማብዛትና መቀፍቀፍ ነው።
ሁላችንም በተፈጠርንባት ምድር በፍትህ ፤ በእኩልነት፤ በነጻነትና በሥነ ምግባር መንፈስ ታንጸን መኖር መቻል አለብን ።
አንዱ ገዥ ሌላው ተገዢ ፤
አንዱ ጨቋኝ ሌላው ተጨቋኝ ፤
አንዱ ለብቻው የናጠጠ ሃብታም ሌላው መናጢ ድሃ ፤
አንዱ የጠገበ ሌላው የተራበ ፤
አንዱ ዘራፊ ሙሰኛ ሌላው ተዘራፊና ተሳቃቂ ፤
አንዱ ካለቅጥ ደስተኛ ሌላው ሃዘነተኛና ቅስሙ የተሰበረ ፤
አንዱ ሠራተኛና አምራች ሌላው ተቀማጭና አልማጭ፤
አንዱ ገዳይ ሌላውተገዳይ ፤
አንዱ አዳኝ ሌላው ታዳኝ ፤
አንዱ አጥፊ ሌላው ተጠፊ ፤
አንዱ ወርቅ ሌላው ነሐስ…ወዘተ ያለበት ማኀበራዊ የፖለቲካ ሥርዓት እየገነቡ ፤ ሕግና ሥነ ሥርዓት አስከብራለሁ ማለት አይቻልም ።
በተቃራኒው ሁከትና ሥርዓተ አልበኝነትን መፍጠር የመንግሥት ልዩ ተግባርና ሃላፊነት ይሆናል ማለት ነው ።
Do you follow me / ትከተላላችሁ ?
Have I made myself clear / ግልጥ ነኝ ?
የትኛውም ሰው ሆነ ሕዝብ ድህነትን በፈቃድና በደስታ የሚቀበል ይኖራል ተብሎ በጤነኛ ሰው አዕምሮ ቢታሰብ እጅግ ያስገርመኛል ።
በየዛኒጋባው ፤ በየመንገዱ ቤት አልባ ሆነው ፤ በደሳሳውና በዘመመው ጎጆ የሚኖሩ ሰዎች ሌሎችን በቪላ ቤቶችና በሚያማምሩ ሕንፃዎች የሚኖሩትን መመልከታቸው አይቀሬ ነው ።
ባዶ ሆዳቸውን ያደሩ ሰዎች የጠገቡ ሰዎችን በቴሌቪዥን ሳይሆን በገሃዱ ዓለም ነው እያዩዋቸው ያሉት ፤ በእግር የሚጓዙ ሰዎች በቄንጠኛ መኪና የሚንፈላሰሱትን ዜንጠኞችና በአናታቸው ላይ የሚያጓራውን ጠያራ መመልከታቸው የግድ ነው ።
በመቃብር ሥፍራዎች የሚታዩ ሃውልቶችና እንደ ነገሩ አፈር የለበሱ የመቃብር ሥፍራዎችን መመልከት የተለመደ ነው ።
የሐብታም ልጆች የትምህርት መስጫ ተቋሞችና የድሃ ልጆችን ት/ ቤት የሰማይ ያህል ርቀት መሆን የለበትም፡፡ የደሃ ልጆች የሚማሩበት ትምህርት ቤቶች ባላቸው አቅም ሁሉ ስርአቱን የጠበቀ ትምህርት እንዲያገኙ ልዩ ትኩረት፣ ክትትል መደረግ አለበት፡፡ በመንግስት ትምህርት ቤቶች፣በግል ትምህርት ቤቶች፣ በሚሽነሪና አለም አቀፍ ደረጃ ባለቸው ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ሁሉ ተመሳሳይ በሆነ እውቀት ባላቸው የእውቀት አባቶች ትምህርት ይገበያሉ ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በተጠቀሱት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ኢትዮጵያዊ ህጻናትና ወጣቶች ሁሉ የሀገሪቱ የትምህርት ሚንስትር ባወጣው አመታዊ የትምህርት መርሃ ግብር (ፕሮግራም) መሰረት እውቀት ስለመገብየታቸው ወላጆች፣የመንግስት የትምህርት ሚንስትር ባለስልጣኖች፣መምህራኖችና ዜጎችን ሁሉ ሊያሳስባቸው ይገባል፡፡ የትምህርት ጉዳይ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ጉዳይ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የበሽታ መፋወሻ ተቋሞች ለድሃው ሕዝብ ድርሽ እንዳይል ዋጋቸው ያስጠነቅቃል ፤ ለአብነት ያህል ጸሃፊው በገሃድ ያጋጠመውን እዚህ ላይ መጥቀስ ይፈልጋል፡፡ ማክሰኞ ታህሳስ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሽት ለአንድ ሰዓት ሩብ ጉዳይ ሲሆን የልጅነት ትዝታዬ ተቀስቅሶ ፒያሳ ልኡል ራስ መኮንን ኬክ ቤት ጎራ በማለት አንድ ባቅላባ በ35 ብር በመክፈል ከተመገብኩ በኋላ ወደ መኖሪያ ቤቴ አቀናሁ፡፡ ለሊቱን ግን ታምሜ አደርኩ፡፡ በሽታው ፋታ የሚሰጥ አልነበረምና አንድ ወዳጄ የሆነ የህክምና ዶክተር ሳማክረው ተገቢውን ምርመራ ካደረግለኝ በኋላ ሁለት አይነት መድሃኒት ጽፎ መድሃኒት ቤት በማቅናት እንድገዛ መከረኝ፡፡ እኔም በሃኪም የታዘዘልኝን መድሃኒት ለመግዛት ወደ ተለያዩ መድሃኒት ቤቶች ባቀናም የመድሃኒቱ ዋጋ በጣም አስደንጋጭ ነበር፡፡ ለሁለቱም አይነት መድሃኒቶች የተጠየኩት ዋጋ 986 ብር፡፡ ወዲያውኑ ወደ ህሊናዬ የመጣው የደሃው ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ነበር፡፡ በእኔ በኩል ዶክተሩን በድጋሚ ማማከር አለብኝ ብዬ ወደ ክሊንኩ አመራሁ፡፡ ዶክተሩም ሌላ አይነት መድሃኒት አዞልኝ አቅሜ የሚፈቅደውን መድሃኒት ገዝቼ አሁን ከበሽታዬ ለመፈወስ ችዬአለሁ፡፡ ዋናው ቁም ነገሩ ግን የእኔ መታመምና መፈወስ ሳይሆን ምን ያህል የመድሃኒት ዋጋ ሰማይ እንደነካ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚያውቁትን ችግር በድጋሚ ልብ ሊሉት እንደሚገባ ለማሳወቅ ነው ገጠመኜን ያወጋሁት፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ የምትለዋና ከብዙ አስርተ አመታት በፊት የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚንስቴር ግዜ የማይሽራትን ምክረሃሳብ ገቢራዊ ማድረጉ ለብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ የሚበጅ ነው ባይ ነኝ፡፡
ይህም ብቻ አይደለም የመዝናኛና የስፖርት ማዘውተሪያዎችም ድሃውን ሕዝብ በማይደፈረው ወጪያቸው ያገለሉ ይመስላሉ ። ዛሬ እን ጁቬንትስ፣ጎልፍ መጫወቻዎች ገብቶ መዝናናት ቅንጦት ይመስላል፡፡ ለአብነት ያህል የፒያሳና አካባቢው ወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ቢፈልጉ ምናልባት ወደ ሱሉልታ በአቶቢስ መጓዝ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡
በኢትዮጵያ በሚገኙ አብዛኞቹ ከተሞች ላይ ቆም ብሎ ለሚመረምር የህሊና ሰው ችጋር ቤቱን በእነማን ላይ እንደሰራ ማወቅ ይቻለዋል፡፡ ወይም እውነቱን ለመገንዘብ አይከብደውም፡፡ በብዙ የኢትዮጵያ ከተሞች በሚገኙ አውራ ጎዳናዎች ላይ የሚንከራተቱት የድሃ ልጆች እንጂ በሃብታም ወይም መካከለኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ልጆች አይደለም የተሞሉት ።
ባህር አቋርጠው፣ጫካ ሰንጥቀው እግራቸው ወደ መራቸው ሀገር የስደት ኑሮ ለመምራት( እንደ ኑሮ ከተቆጠረ ማለቴ ነው፡፡) የሚንከራተቱ በአብዛኛው ቀን የጎደለባቸው ከድሃ ቤተሰብ የተፈጠሩ ልጆች ናቸው፡፡ ይህ ሲባል ግን ሀብት ሞልቶ ከተረፋቸው ወላጆች የተገኙ ልጆች ሀገር ጥለው አይሰደዱም ማለት አይደለም፡፡ የተለያዩ ግለሰቦች በተለያዩ ምክንያቶች ሀገር ጥለው የስደት ህይወት የሚመርጡም አሉ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በኢትዮጵያ ትልቁና መሰረታዊ የስደት ምክንያት ድህነት ነው፡፡ ይህ ብዙም የሚያከራክረ አይመስለኝም፡፡
ኧረ ስንቱ ግፍና በደል ” ሰው በሰው ልጅ ” ላይ ተጠቅሶ ይዘለቃል?
ሰዎች ነንና ሌሎች ምስያዎቻችን (አምሳያዎቻችንን) የሚኖሩትን ኑሮ ብንመኝና እንደነርሱ ለመኖር ዕድሉን አትንፈጉን ብሎ መጠይቅና የድህነትና የስቆቃ ኑሮ ይብቃን ማለት ወንጀል ይሆን ?
ለዛሬው አበቃሁ!