>

አዲስ አበባ ተገቢ ጥያቄዎች ባለመጠየቋ ወፍ ዘራሽ ፍላጎቶች እያቆጠቆጡ ነው”  (ሐመሩ ‘ሐ’ ዋሸራ)

አዲስ አበባ ተገቢ ጥያቄዎች ባለመጠየቋ ወፍ ዘራሽ ፍላጎቶች እያቆጠቆጡ ነው” 
(ሐመሩ ‘ሐ’ ዋሸራ)
♦የራስ ብሩ ሜዳ (መስቀል አደባባይ) ጉዳይ!‼️ 

         ራስ ብሩ ለአፄ ምኒልክ ስመጥር መኳንንት አንዱ ከሆኑት ደጃች ወልደገብርኤል በ1882 ተወለዱ። ደጃዝማች ወልደገብርኤል በንጉሠ ነገሥቱ ምኒልክ ዘንድ በነበራቸው ከበሬታ እርሳቸው ሲሞቱ ልጃቸውን ከልዑላን ጋር ታላቁ ቤተ መንግስት አደጉ። በዚህም ለምሳሌ ራስ ብሩ በልጅነታቸው በቤተ መንግስት የግብር አመጋገብ ደረጃቸው ከልጅ ኢያሱ ሚካኤል፣ከራስ ተፈሪ(በኋላ አፄ ኃይለስላሴ)ና ከራስ ጌታቸው አባተ ቧያለው ጋር ነበር። ደጃች(በኋላ ራስ) ለምኒልክ በነበራቸው ልዩ ቀረቤታና ፍቅርም ራስ ብሩ የምኒልክ ልጅ ናቸው የሚል አሉባልታም በዘመኑ ተዛምቶ ነበር። ግን ሐሜቱ ከእውነቱ የራቀ ስለመሆኑ የፃፉ ብዙ ናቸው። ራስ ብሩ ወልደገብርኤል በሲዳሞ፣በከፋ፣በወላይታ ገዥነት፣በመከላከል ሚኒስትርነት አገልግለዋል።
      በማይጨው ጦርነት አዝመተው ከተዋጉ ጦሩ በኋላም ሲፈታ በ5ቱ የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራም በስደት ቆይተዋል።
ራስ ብሩ ደፋር፣አገር ወዳድ፣አይበገሬ፣ስልጡን መስፍን ነበሩ። ጀግና አርበኛ ወዳድ በመሆናቸውም ሁለቱ ልጆቻቸውን በራስ መስፍን ስለሺና በመርዕድ መንገሻ ስም መስፍንና መርዕድ ብለው ሰይመዋል።(በነገራችን ላይ ልጅ መስፍንና መርዕድ ብሩ ደርግ የሚፈፅመውን ግፍ ተመልክተው እንደነ ደጃዝማች ፀሐዩ ዕንቁሥላሴ ለደርግ እጅ ሳይሰጡ ታግለው ነው መስዋዕትነት የከፈሉት)። በኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩ መሳፍንት ቀዳማዊ ኃይለስላሴን ካለአንቱታ ‘አንተ’ ብለው የሚጠሩት ደፋሩ ራስ ብሩ ነበሩ።
ራስ ብሩ አለባበሳቸው ሽቅርቅርና ኩሩ መስፍንም ናቸው። መኪና ትራንስፖርት ከመጣ በኋላ እርሳቸው በመኪና እየሄዱ በፈረስ ይታጀቡ ነበር።
    ሌላው የራስ ብሩ ትልቁ መለያ ቸርና ለጋስነታቸው ነው። ራስ ብሩ ሰፊ ሀብት የነበራቸው ቱጃር መስፍን ነበሩ። በዘመኑ የራስ ብሩን ያህል ግብር የሚያበላ መስፍን አልነበረም። ‘ግብርስ እንደ ራስ ብሩ’ የተባለው በየዕለቱ ለደሀ ግብር በማንበሽበሻቸው ነበር።
    እኒህ መስፍን አዲስ አበባ የቱ ጋ ነበሩ ካሉ የዛሬው መስቀል አደባባይ ነው መልሱ። ይህ የመስቀል በዓል ማክበሪያ ቦታም ራስ ብሩ ሜዳ ነበር መጠሪያው። ዛሬ አዲስ አበባ ሙዚየም የተባለው ቸጋ ኪነ ህንፃ ቤት የህንዶች አሻራ ያረፈበት በ1912 ዓ.ም ገዳማ የተሰራው የራስ ብሩ ወልደገብርኤል መኖሪያቸው ቤት ነው። የራስ ብሩን ዘመናዊ ቤት አሰራር የተመለከቱ በርካቶች መሳፍንትና መኳንንት በውጭ አገር መሀንዲሶች እየከፈሉ ዘመን ተሻጋሪ ቤቶችን አስገንብተዋል። ራስ ብሩ ከሜዳቸው ቀንሰው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቶስን መስቀል ማክበሪያ አደባባይነት በርስትነት የሰጡትም/በገንዘብም ይሁን በነፃ) ወደውና ፈልገው ነው።
    ደርግ ወደስልጣን ሲመጣ መስቀል አደባባይን አቢዮት አደባባይ በሚል ቢቀይረውም የመስቀል ማክበሪያነቱም ሆነ የቤተ ክርስቲያን ይዞታነቱ አልተለወጠም ነበር። በኢህአዴግም እንደዛው። ከso callled 3 የለውጥ ዓመታት ወዲህ ግን መስቀል አደባባይ ወደ ነውጥ አደባባይነት መሰል ጉዳዮችን እየተስተናገዱበት ነው። ኢግዚቢሽን ማዕከልም ሆነ መስቀል አደባባይ መልከ ብዙ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያ ኪነ ጥበባዊ ጉዳዮች ለዓመታት ቢያስተናግድም ‘የጠል ፖለቲካ’ አራማጆች ግን መልኩን ለመለወጥ ሲታትሩ ይስተዋላል። የስያሜም፣ የግብርም። መነሻቸውም አንድም የሰልቃጭነት አባዜ፣ አንድም የምቀኝነትና የሌላ ጠል ኑዛዜ ነው።
    ይህ መዋቅራዊ(መንግስታዊም ሆነ ኢ-መንግስታዊ) ድጋፍም ስላለው በእስካሁን የሐይማኖትና የህዝብ አብሮት ላይ ጥላ የሚያጠላ፣ ብጥብጥ የሚዘራ ክስተት እንዳይሆን ስጋት አለው። በከተማዋ ባልጠፋ ቦታ የብሔርም፣ የሐይማኖት ገፅታ እየተላበሱ በየወቅቱ የሚያደርሱት ዙሪያ ገባ ትንኮሳና ጥቃትም ለዚህ ማሳያ ነው። ለእንደዚህ ኃይሎች የድፍረትማ ይሉኝታ-ቢስነት ጥግም ባለቤቱ ራሱን ለማስከበር ያሳየው የቸልተኝነት ስላለ እና ይሉኝታና ሞራል ሰገነትም ቅርፊት በመብዛቱ ነው።
    ለዚህም ማሳያዋም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን፣ አማኞቿ እና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው። አስፈላጊ ጥያቄዎች ባለመጠየቃቸውና መብትና ክብር ማስጠበቅ ባለመቻሉ ተቃራኒ ፍላጎቶች እያቆጠቆጡ ነው። ሕዝቡ ደርግ አዲስ አበባ ሙዚየም ያለውን ታሪካዊ ቤት ስያሜ በነፃ ለቅርስነት ባስረከበው ቤተሰብ ‘ራስ ብሩ ሙዚየም’ እንዲባል ባለመጠየቁ ነው።ታሪካዊቷና ባለውለታዋ ተቋም /ተዋሕዶ/ በመስቀል አደባባይዋ ግዙፍ የመስቀሉ ሐውልት ለማቆም ባለመድፈሯና ባለመጠየቋ፣ ማንነቷን ለማስከበር ባለመጣሯ ነው።
    የአዲስ አበባ ሕዝብ ከእቴጌ ጣይቱ ጀምሮ የአዲሱ አበባ ከተማ ምስረታና ዕድገት ትልቁን ድርሻ የተወጡ ባለታሪኮችን የሚዘክር መታሰቢያ በአዲስ አበባ ዐውደ ርዕይ (ኢግዚቢሽን) ማዕከል ውስጥ እንዲቆም ባለመጠየቁ ነው። ተገቢ ጥያቄዎች ባለመጠየቃቸው ወፍ ዘራሽ ፍላጎቶች እያቆጠቆጡ ነው። እነዚህ ፍላጎቶች ደግሞ ዕልቆ ቢስና አግበስብሶ አይጠረቄ ናቸው። አሁንም ቢሆን ‘የኢየሱስን ለኢየሱስ፣ የቄሳርን ለቄሳር’ ነውና ተገቢ ጥያቄዎች መጠየቅ፣ ለወፍ ዘራሽ ፍላጎቶች ማርከሻ ፈውስ መሆኑ ሳይሻል አይቀርም።
Filed in: Amharic