>

በሀገራዊ ጉዳዮች የህዝብን የልብ ትርታ ለማወቅና ድጋፉንም ለማግኘት የመንግስት ግልጽነት ወሳኝ ነው!  (አበጋዝ ወንድሙ)

በሀገራዊ ጉዳዮች የህዝብን የልብ ትርታ ለማወቅና ድጋፉንም ለማግኘት የመንግስት ግልጽነት ወሳኝ ነው!

   አበጋዝ ወንድሙ


በአንድ ወቅት የፓኪስታን ፕሬዘዳንት የነበረው ፐርቬዝ ሙሻረፍ እ.አ. አ.  2006 ሲቢኤስ የተባለ የአሜሪካ ቴሌቪዥን ላይ ለውይይት ቀርቦ፣ (ከአምስት ዓመት በፊት ስለሆነ ጉዳይ መሆኑ ነው) የአልቄይዳ ቡድን ላይ ለሚወስደው እርምጃ፣ ሀገሮችን ለማስተባበር ወደ ፓኪስታን ያቀናው የአሜሪካ ከፍተኛ ባለ ስልጣን ሪቻርድ አርሚታዥ የፓኪስታንን የደህንነት ሃላፊትብብር አናደርግም ካላችሁ ሃገራችሁን ወደ ድንጋይ ዘመን እንመልስላችዃለንበማለት አስፈራርቶት እንደነበር ጠቅሶብልግና የተሞላው አባባልመሆኑን አስምሮበት ነበር።

 ፓኪስታን በወቅቱ ከአሜሪካን ጋር ተባብራ ነበር።  ትብብሯን በወቅቱ የሰጠችው በጉዳዩ ዓምና ይሁን ወይንም መልዕክተኛው የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ስለነበር በማስፈራርያው አስገዳጅነት ነበር የሚለውን ለታሪክ የምንተወው ይሆናል።

ይሄን ቃለ መጠይቅ ያስታወሰኝ / አብይ የመከላከያን አዲስ ህንጻ በመረቀበት ወቅት፣ ከአንድ ቀን በፊት የነ አቦይ ስብሃትን ክስ ተቋርጦ መለቀቅ፣በህዝብ በኩል ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ቅዋሜና መጠራጠርን ማስከተሉን በመገንዘብ ይመስላል፣ ምክንያቶች ናቸው ያላቸውን በሚደረድርበት ወቅት፣ ውሳኔውእኛንም አስደንግጦን ነበርያለው፣ በቀናት ልዩነት ከአሜሪካው መልዕክተኛ ፌልትማን ጋር ተገናኝቶ ስለነበር ምናልባት ተመሳሳይ የእጅ ጥምዘዛ ተካሂዶ ነበር ወይ የሚል ጥርጣሬ ስላደረብኝ ነው።

ዛሬ ደግሞ / አብይ በትዊተር ገጹ ላይ ከአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጋር በስልክስለ ጊዜያው ሁኔታ፣ ስለ ሁለትዮሽ ግንኙነታችንና ስለቀጠናው ግልጽ ውይይት አድርገን ነበርብሎ የጻፈውን ሳይ (ካልተሳሳትኩ የአሜሪካው ፕሬዘዳንትና አብይ በቀጥታ ሲገናኙ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ይመስለኛል) ጥርጣሬየን አጉልቶታል።

 እስካሁን በመልዕክተኛና በጎረቤት አገር ፕሬዘዳንት በኩል የሚደረገው ግንኙነት ወደ ቀጥተኛ ግንኙነት ማደጉ በግርድፉ ሲታይ ፣ በበጎ መልኩ የሚታይ ቢሆንም፣ ይሄ ዕውን እንዲሆን የተከፈለ ዋጋ አለ ወይ

ከነዚህ ክፍያዎች አንዱ በታላቅ ወንጀል ተጠርጥረውና ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ ግለሰቦችን ክሳቸውን ለጊዜውም ቢሆን አቋርጦ መልቀቅን ይጨምራል ወይ? ይሄ ህዝብን ግራ ያጋባና ጥርጣሬ ያጫረ ድንገተ ውሳኔ በሚስጥር እንዲያዝና ወቅቱን ባላገናዘበ አጉል ጊዜ እንዲገለጥ ያደረገው ሂደት፣ ከቀጥተኛ ግንኙነት ውጭ ሌሎች ትሩፋቶች  የያዘ ነው ወይ

ለምሳሌ አሜሪካ ወደ ቀልቧ ተመልሳ ነው ቀጥተኛ ግንኙነት የተደረገው ወንስ ቻይና ለአካባቢው ልዩ መልከተኛ እንደምትሾም ማሳወቋና ኤርትራን ጨምሮ የቻይና ውጭ ጉዳይ ምኒስትር የምስራቅ አፍሪቃ  ጉብኝት አስደንብሯት

 ኢትዮጵያ እስረኞቹን ድንገት ከመልቀቅ ሌላ፣ (አብይ ስለ ቀጠናውም ተወያይተናል ስላለ) በቀጠናው ስላሉት ኤርትራና ሶማሊያና እንዲሁም ሁለቱ ሀገሮች ከኢትዮጵያ ጋር የመሰረቱት ወዳጅነትን አስመልክቶ  ደግሞ ፣ አሜሪካ ስለሚጎረብጣትና ቀና አመለካከት ስለሌላት፣ በዚህ በኩል የተደረገ የአቋም መሸጋሸግ አለ ወይ… ወዘተ የሚሉ በርካታ ጥያቄዎችን ያስነሳል።

ወሳኝ በሆኑና  መንግስት ውሳኔ ከመድረሱ በፊት በቅድሚያ ለህዝብ ግልጽ መሆን በሚገባቸውና ምክክር በሚያሻቸው  ጉዳዮች ላይ የመንግስት አካሄድ እጅግ ብዙ የሚቀረው መሆኑ የታወቀ ነው ። የሰሞኑም ውሳኔ የዚህ ቅድመ ውይይት ወይንም ገለጻ አለመኖር አይነተኛ ምሳሌ በመሆኑ እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን እንድናነሳ ግድ ይላል።  

መንግስት በጠቅላይ አቃቤ ህጉ / ጌደዎንም ሆነ /  በኩል የሰጡት ማብራሪያዎች አጥጋቢ መልሶች እንዳልሆኑ በመረዳት፣ ህዝብን ከጥርጣሬና ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ እንዳይሄድ ለመታደግ፣ የውሳኔውን ሂደት አስመልክቶ  ክስ አቋርጦ የመልቀቅን ሃሳብ ማን አነሳው? ምን አነሳሳው ? ማን ተወያየበት? ማንስ ወሰነበት? ሃገራዊ ፋይዳውስ ምንድን ነው ? የሚለውን አሁንም ቢሆን ብዙ አልረፈደምና በቅደም ተከተል ለህዝብ የማሳወቅ ሃላፊነት አለበት  በወሳኝ ሃገራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ህዝብ አምኖ፣ ለሚወሰደው እርምጃ ሙሉ ድጋፍና ትብብሩን እንዲሰጥ አስፈላጊም ከሆነ ለትግበራው ግብአት እንዲያደርግ፣ በተቋሞችም ላይ ሆነ በመንግስት ላይ ዕምነት እንዲያሳድር ተጠያቂነትን ታሳቢ ያደረገ ግልጽነት ወሳኝ ሂደት መሆኑን በመረዳትም በቀጣይ መንግስት በቅጡ ሊያስብበት የሚገባ ለመሆኑ፣ የሰሞኑ ውሳኔ ያመጣው ችግር ትምህርት ይሆነዋል የሚል እምነት አለኝ ።

Filed in: Amharic