>
5:21 pm - Wednesday July 20, 1960

"ክስን ስለማቋረጥ፤ ጥያቄ እና ለግንዛቤ ያህል....!!!"(ያሬድ ሀይለማርያም)

“ክስን ስለማቋረጥ፤ ጥያቄ እና ለግንዛቤ ያህል….!!!”
ያሬድ ሀይለማርያም

በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ-ሥርዐት አንቀጽ 122 ላይ ክስን ማንሳት ወይም ማቋረጥ ስለሚቻልባቸው መንገዶች በዝርዝር ተደንግጓል። ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ የአንቀጹን ሙሉውን ቃል እንደሚከተለው ተቀምጧል፤
1/ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በቁጥር 522 (ከባድ፣ የግፍ አገዳደል) ወይም በቁጥር 637 (ከባድ የወንበዴነት ተግባር) መሠረት ከቀረበው ክስ በቀር ዐቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ ያቀረበውን ማንኛውንም ክስ በፍርድ ቤቱ ፈቃድ ከፍርድ በፊት ክሱ በሚሰማበት በማንኛውም ጊዜ ክሱን ለማንሣት ይችላል።
2/ ክሱን እንዳነሣ በመንግስት ታዝዣለሁ ብሎ ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ሲያመለክት ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ሲያመለክት ዐቃቤ ሕጉ ክሱን እንዲያነሣ ከመንግስት የታዘዘ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ከተረዳ ፍርድ ቤቱ መፍቀድ አለበት።
3/ በቁጥር 119 መሠረት አዲስ ክስ ያልተዘጋጀ እንደሆነ ተከሳሹ ለጊዜው ይለቀቃል።
4/ ፍርድ ቤቱ ክሱን ለማንሳት ወይም ላለማንሣት ለሚሰጠው ውሳኔ ምክንያቱን መስጠት አለበት።
5/ በዚህ ቁጥር መሠረት ክሱ የተነሣ እንደ ሆነ ክሱን ለወደፊት ለመቀጠል የሚከለክለው አይሆንም።
ጥያቄ፤
ቀደም ሲል ዜናው እንደተሰማ በጉዳዩ ላይ ባካፈልኩት ጽሑፌ ሂደቱም ሆነ እስሩ ፖለቲካው ቅርጽ የያዘ ስለሚመስል የተሰጠውም ውሳኔ ፖለቲካዊ ነው ብያለሁ። ይህ ምልከታዮ እንደተጠበቀ ሆኖ የፍትሕ ሚኒስትሩ አደባባይ ወጥተው እኔ ነኝ ክሱን በሕግ አግባብ ያቋረጥኩት ስላሉ እና ጠቅላዩም አክለው በትላንቱ ንግግራቸው ‘እኔም ደንግጬ ነበር’ ስላሉ እነዚህን ጥያቄዎች ለማንሳት ወደድኩ።
1ኛ/ ከላይ በንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ እንደተደነገገው ክስ ማቋረት የሚቻለው የወንጀሉ አይነት በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በቁጥር 522 (ከባድ፣ የግፍ አገዳደል) ወይም በቁጥር 637 (ከባድ የወንበዴነት ተግባር) ውጭ ከሆነ ነው ይላል። ስለዚህ በሌላ አገላለጽ በከባድ እና የግፍ አገዳደል ወይም በውንብድና ተግባር በተከሰሰ ሰው ላይ ክስ ማንሳት አይቻልም ማለት ነው። የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ክሱን ያቋረጡባቸው መዝገቦች ላይ ያለው የወንጀል ክስ ምን ይላል? የተለቀቁት ሰዎች የቀረበባቸው ክስ ከላይ ከተጠቀሱት የወንጀል አይነቶች ውጭ ናቸው ወይ?
2ኛ/ አቃቤ ሕግ በራሱም ተነሳሽነት ሆነ በመንግስት ታዞ ክስ ማቋረጥ ሲፈልግ ምክንያቱን ዘርዝሮ ክስ ለማቋረጥ እንደሚፈልግ ጥያቄውን ለፍርድ ቤቱ ማቅረብ እንዳለበት እና ፍርድ ቤቱም የቀረበውን ጥያቄ አይቶ እና በቂ ምክንያት መኖሩን ከመረመረ በኋላ መፍቀድ ወይም መከልከል እንደሚችል ከላይ ያለው አንቀጽ ይደነግጋል። ባጭሩ አቃቤ ሕግ ክስ ይቋረጥልኝ ብሎ የመጠየቅ ሥልጣን ሲሆን ያለው ክሱ እንዲቋረጥ የሚወስነው ግን ጉዳዩን የያዘው ፍርድ ቤት ነው። በተለይም በንዑስ አንቀጽ 4 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው “ፍርድ ቤቱ ክሱን ለማንሳት ወይም ላለማንሣት ለሚሰጠው ውሳኔ ምክንያቱን መስጠት አለበት።’ ይህ አባባል የሚያመለክተው ፍርድ ቤቱ አቃቤ ሕጉ ያቀረበውን የክስ ይቋረጥ ጥያቄ ምክንያት ከመረመረ በኋላ ክሱን ለማንሳት ወይም ላለማንሳት ሥልጣን ያለው የበላይ አካል እሱ ብቻ መሆኑን እና ለውሳኔውም በቂ ምክንያት መስጠት እንዳለበት ፍርድ ቤቱ ላይ ኃላፊነትን ይጥላል፡፡
ስለዚህም በሰሞኑ ጉዳይ ይህ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ሥነ-ሥርዓት በተከበረበት መልኩ ነው ወይ የክስ ማቋረጥ ሂደቱ የተካሄደው? በዚህ አግባብ ከሆነ የተከናወነው ፍርድ ቤቱ ክሱን ለማቋረጥ የሂደበት አካሄድ እና የሰጠው ዝርዝር ምክንያት ለሕዝብ ይፋ ሊደረግ ይችላል ወይ?
– የሰሞኑ የክስ ማንሳት ሂደት በመንግስት ትእዛዝ እና በአቃቤ ሕጉ ድጋፍ ሰጪነት ብቻ ነው የተካሄደው ወይስ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ቀርቦ እና በዳኞች ውሳኔ ተሰጥቶበት ነው?
– ሂደቱ ከላይ የተገለጸውን የክስ ማቋረጥ ሂደት የተከተለ ካልሆነ ሕዝብ በሕግ የበላይነት ላይ እና በፍትሕ ተቋማት ላይ ያለውን እንጥፍጣፊ ተስፋ እና እምነት አያሟጥጠውም ወይ?
አሁንም ስለ ክስ አነሳሱ ጉዳይ ከፍትሕ ሚኒስትሩ በቂ ማብራሪያ ቢሰጥበት ጥሩ ነው ብዮ አምናለሁ
Filed in: Amharic