>

እምዬ ምኒልክ (እና ኢጣልያኖች) — ከአድዋ ድል በኋላ...!!! (አሳፍ ሀይሉ)

እምዬ ምኒልክ (እና ኢጣልያኖች) — ከአድዋ ድል በኋላ…!!!

አሳፍ ሀይሉ

« ከአድዋው ጦርነት ጥቂት ጊዜ በኋላ ሽለላ፣ ፉከራ፣ የድል ዘፈን፣ እልልታ ማስተጋባት ጀመረ፡፡ አጤ ምኒልክም፣ ‘በዛሬው ቀን በዚህ ጦር ሜዳ ተዋግተው የወደቁት ወገኖቻችን ብዙ ናቸውና፣ ዘፈኑ ሆነ ሽለላውን ወዲያው እንዲቆም’ ሲሉ አዘዙ፡፡
« አጤ ምኒልክም፣ ለክብራቸው ተዘርግቶ የነበረውን ቀይ ዣንጥላ ታጥፎ በምትኩ ጥቁር ዣንጥላ እንዲዘረጋ አዘዙ፡፡ ከባድ ዝናብም ጣለ፡፡ እቴጌም ለሀገራቸው ክብር የወደቁትን ጀግኖች ስም ሲነገራቸው እንባቸውን ያፈሱ ነበር፡፡
« ምንም እንኳ ጦርነቱ በኢትዮጵያውያን ድል አድራጊነት ቢጠናቀቅም፣ መኳንንቱና ሠራዊቱ በዚያች ቀን ጀንበር ሳትጠልቅ በጦርነቱ ላይ የወደቁትን፣ በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻቸውን እያሰቡ በኀዘን ተውጠው ነበር፡፡
« የአድዋ ጦርነት በታላቁ አጤ ምኒልክ መሪነት፣ ኢትዮጵያውያኑ አንድ የሰለጠነን የአውሮጳ ጦር በማሸነፍ ተጠናቀቀ፡፡ በዚህ ጦርነት 13,300 ኢጣልያኖች ሲሞቱ፣ 700 ተማርከዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ጦርነቱን የመሩት 2 ጄኔራሎች አሪሞንዲና ዳቦርሚዳ ሲገደሉ፣ ጄኔራል አልቤርቶኒ ደግሞ ተማርኳል፡፡ በኢትዮጵያውያን በኩል 20,000 ሲወደቁ፣ 7,000 ደግሞ ቆስለዋል፡፡
« አጤ ምኒልክም ከጦርነቱ ፍጻሜ በኋላ የሞቱትን ጀግኖች ሬሣ ሲያስቀብሩ፣ ሀገር እያረጋጉ ሰነበሩ፡፡ ቀጥሎም ለአውሮጳ መንግሥታት፣ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ራሷን የቻለች ነፃ ሀገር መሆኗን ገልጠው፣ ለአድዋ ጦርነት መነሻ የሆነውን ምክንያት በመዘርዘርና፣ ከዚያም ኢጣልያ በጦር ኃይል አስገብራለሁ ብላ የብዙ ጦብያውያንን ደም እንዲፈስ ማድረጓን፣ ነገር ግን ከጥንት ጀምሮ ሀገራችንን ጠብቋት የሚኖር አምላክ ስላልተለየን ድል ማድረጋቸውን የሚገልጥ ደብዳቤ ላኩላቸው፡፡
« ..በመጨረሻም የተማረኩትን የኢጣልያ ምርኮኞች እና ብዙ መሣሪያዎች ይዞ መናገሻ ከተማቸው ለመሄድ ዝግጅት ተጠናቀቀ፡፡ አጤ ምኒልክ መናገሻ ከተማቸውን በለቀቁ፣ በስምንተኛ ወር.. በድል አድራጊነት ጦራቸውንና፣ የተማረኩትን የኢጣልያ ወታደሮች እየመሩ፣ እንጦጦ ገቡ፡፡
« እንጦጦ ሲደርሱ ሕዝቡ፣ ንጉሡ እና ሠራዊቱ በደህና መመለሳቸውን፣ በእልልታ፣ በጭፈራ፣ በጭብጨባ እና በሽለላ ወጥቶ ሲቀበላቸው፣ ካህናቱ ደግሞ ዝማሬያቸውን ያሰሙ ነበር፡፡ የኢጣልያ መንግሥት፣ የኢትዮጵያን ጦር እንዲወጋበት ተልኮ አድዋ ላይ የተማረኩት መድፎችም፣ በዕለቱ፣ ለበዓሉ ክብር መቶ ጊዜ እንዲተኮሱ ተደርገዋል፡፡
« ከበዓሉም ፍፃሜ በኋላ፣ ተማርከው የመጡት የኢጣልያ ወታደሮች፣ በኢትዮጵያና በኢጣልያ መንግሥት መካከል ስምምነት ተደርሶ እስኪመለሱ ድረስ፣ የተለያዩ ባላባቶች በኃላፊነት እንዲጠብቋቸው ተሰጡ፡፡ እነዚህንም እስረኞች ለማስፈታት የኢጣልያ መንግሥት መልዕክተኞችን ደጋግሞ ቢልክም፣ ምኒልክ ቀደም ብለው ስለ ውጫሌ ውል መፍረስ የኢጣልያንን ቃል ካልተቀበሉ እስረኞቹን እንደማይፈቱ የሰጡትን መልስ ሰጡ፡፡
« በዚህ መኻል የሮማው ሊቃነ ጳጳስ ፖፕ ሊዎን 13ኛ፣ እስረኞቹ እንዲፈቱ የሚማፀን ደብዳቤ ለአጤ ምኒልክ ላኩ፡፡ አጤ ምኒልክም ለሮማው ፖፕ፣ የጻፉት ደብዳቤ እንደደረሳቸውና፣ ስለ ክብራቸው ሲሉ እስረኞቹን ሊፈቱ አስበው እንደነበር፣ ነገር ግን እነዚያ በጦር ሜዳ የወደቁትን የኢትዮጵያ ልጆች ሲያስቡ፣ እስረኞቹን መልቀቅ የማይቻላቸው እንደሆነ ገለጹ፡፡ ይሁን እንጂ ‘እስረኞቹ እዚህ በሚቆዩበት ጊዜ ምንም ሳይጓደልባቸው ተንከባክቤ እይዛቸዋለሁ’ በማለት መልስ ሰጡ፡፡
« ነገር ግን አንድ ተራ ምርኮኛ ወታደር እናቱ የጻፈችለትን ደብዳቤ አንብቦ፣ በጣም እያለቀሰ ማስቸገሩን ምኒልክ ሰምተው፣ እስረኛው እንዲመጣ አድርገው ደብዳቤው እንዲነበብ አደረጉ፡፡ የእስረኛው እናትም በደብዳቤዋ ላይ የጻፈችው ቃል፦
« ልጄ፣ ሞተሃል ብለውኝ ተስፋ ብቆርጥ እንደ
ሌሎቹ እናቶች ሁሉ አልቅሼ በወጣልኝ ነበር፡፡
አሁን ግን ቀንም ሌሊትም ላንተ ለልጄ እንዳለቀስሁ
ነኝ፡፡ ምን ቦታ ወድቀህ እንደሆነ አላይህም፡፡ ከአፌ
እየነጠልሁ ያለችኝን ደህና ምግብ እያበላሁ ያሳደግ
ሁህ ልጄ ዛሬ የምትበላውን አላውቅም፡፡.. ልጄ
እንደምወድህ ታውቃለህ፡፡ የማምነው አምላክ
በሰላም ያገናኘናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ …ልጄ
በሕይወት መጥተህልኝ ዓይንህን እስካይ ድረስም
ውሎዬ ከቅድስት ማርያም ቤተ ክርስትያን ነው፡፡ …
ለቤተ ክርስትያኗም በየቀኑ አንዳንድ ሻማ ስለት
ተስዬ በየቀኑ እያበራሁ ላንተ ለልጄ እየተንበረከክሁ
እፀልያለሁ፡፡ … በፀሎቴ ብርታት ተለቀህ እንደምት
መጣ ተስፋ አለኝና፣ አንተም ባለህበት ፀልይ፡፡ …
የምወድህ ልጄ፣ አይዙህ በርትተህ ኑር… አንተም
እንደምትናፍቀኝ አውቃለሁ፡፡ ለቅሶዬ ባክኖ
አይቀርምና እንገናኛለን…»
« የሚል ነበር፡፡ ርኅሩሁ እምዬ ምኒልክም ደብዳቤውን ካዳመጡ በኋላ፣ አዝነውና አልቅሰው፦ ‘ሂድ በነፃ አሰናብቸሃለሁ፡፡ የእናትህ እንባ አማለደህ’ ብለው በበቅሎ አድርገው አሥመራ ድረስ አሸኝተው ሰደዱት፡፡
« የኢጣልያ መንግሥትም፣ አጤ ምኒልክ አዲስ ውል ተፈርሞ የውጫሌ ውል እስካልተሻረ ድረስ፣ እስረኞቹን እንደማይፈቱ ስላወቀ፣ በመጨረሻ ‘የውጫሌ ውል መፍረሱንና ኢትዮጵያ ራሷን የቻለእ ነፃ ሀገር መሆኗን አረጋግጣለሁ’ አለ፡፡ በኦክቶበር 26 ቀን 1896 ዘጠኝ ክፍል ያለው ሰነድ፣ አጤ ምኒልክ በፈለጉት ዓይነት ተዘጋጅቶ፣ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ተፈረመ፡፡ በተጨማሪም ኢጣልያኖች 10 ሚሊዮን ሊሬ ካሳ እንዲከፍሉ ተደረገ፡፡
« አንድ የጥቁር ሀገር፣ በዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀን የአውሮጳን ጦር ማሸነፉ ዓለምን ያስገረመና የኢትዮጵያን ዝና ከፍ ያደረገ፣ ነገር ግን ኢጣሊያንን ያሳፈረ ነበር፡፡ ይህ የአድዋ ድል በተለይም ደግሞ በባርነት ሥርዓት ሲገዙና ሲጨቆኑ የነበሩ ሕዝቦች፣ እነሱም ከተባበሩና ከተደራጁ፣ ወራሪዎችንም ማሸነፍ እንደሚችሉ የተስፋ ጭላንጭል በሕሊናቸው እንዲፈነጥቅ ምክንያት ሆነ፡፡»
— ከላይ የቀረበው ጽሑፍ፣ የአድዋን ድል በዓል ምክንያት በማድረግ በየካቲት 22 ቀን 2005 ዓም.፣ «አጤ ምኒልክና ኢጣልያኖች» በሚል ርዕስ፣ የደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞን  ‹‹አጤ ምኒልክ›› መፅሐፍ በምንጭነት ጠቅሶ፣ በ17 ገጾች፣ በበእደ ማርያም እጅጉ ረታ ከተሰናዳው ታሪካዊ አርቲክል የተገኘ ነው፡፡
«The study of history is the best medicine for a sick mind!» – Livy
«የታሪክ ጥናት ለሕሙም አዕምሮ ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡»
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡
Filed in: Amharic