>

ለፖለቲካዊ በህል አለመበልጸግ ትልቁ እንቅፋት የሥልጣን ብልግና ነው...!!! መኩሪያ መካሻ [ ረዳት ፕሮፌሰር ]

ለፖለቲካዊ በህል አለመበልጸግ ትልቁ እንቅፋት የሥልጣን ብልግና ነው…!!!
መኩሪያ መካሻ [ ረዳት ፕሮፌሰር ]

 

የሎርድ አክሽንን የታወቀ ኣባባል ልጠቀምና-“ሥልጣን ያባልጋል፣ፍፁማዊ ሥልጣን በፍፁም ያባልጋል” ይላል፡፡ ይህ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አገዛዝ ውስጥ የታየ ዕውነታ ነው፡፡በኢትዮጵያ ታሪክ፣በተለይም በሰሜኑ ፖለቲካ ውስጥ ሲካሄድ የቆየን የመጠፋፋት ሁኔታን እናነሳለን፡፡
በዳግማዊ እያሱ ዘመን በቋራና በወሎ መካከል የሚካሄደው ትግል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተካረረ ሄዶና ፈንድቶ ለጎንደር መንግሥት ውድቀት ምከንያት እነደሆነ ይታወቃል፡፡እያሱ ይህን የሥልጣን ውድቀት ሊገታው አልቻለም፣በመጨረሻውም በመርዝ ተገደለ፡፡ የሚገርመው ለሞቱ መንስኤ በልጅና(በእያሱ)፣በእናት (እተጌ ምንትዋብ) መካከል የተፈጠረ አለመግባባት ነው ይባላል፡፡ እናት የወለደችውን ልጅዋን እንደ ድመት የመግደል የከረረ የፖለቲካ ጭካኔ መሆኑ ነው፡፡ እንዲህ አይነቶቹ መራር እውነቶች በኢትዮጵያ የታሪክ ሂደት ውስጥ ፍፁም አላቆሙም፡፡ሁሌ እንደተቀጣጠሉ ናቸው፤አንድ ቦታ ላይ ግን መቆም አለባቸው፡፡
ከአጼ ቴዎድሮስ ህልፈት በኋላ ላስታ፣ትግሬና ሸዋ ዓይንና ናጫ  ሆኑ፡፡እነዚህ ሶስት የዘውድ ተስፈኞች አንገት ለአንገት መተናነቃቸውን አጧጧፉት፡፡ የላስታው ዋግሹም ጎበዜ፣ የትግሬው በዝብዝ ካሳ(አጼ ዮሀንስ) እና የሸዋው ገዢ ምነልክ፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ከሞቱ በኋላ በዝብዝ ካሳ  ለሥልጣን ግብግባቸው እንዲረዱአቸው ተቀራርበው እርስ በእርስ ከመነጋገገር ይልቅ ተስፋ ያደረጉት በባዳው የእንግሊዝ ሃይል ላይ ነበር፡፡
 በዝብዝ ካሳ የአጼ ቴዎድሮስ ሩቅ ሰው ሳይሆን እንደያውም ቤተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ዮሀንስ እንደ ምኒልክ ሁሉ በቴዎድሮስ ቤተ መንግስት ተቀምጦ የባላምበራስነት ማዕረግ ተቀዳጅቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ ቅርብርብ ግን ለሥልጣን ምንም ፋይዳ እነደሌለው በተከታታይ በታዩት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ተደጋግሞ ተስተውሏል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የአጼ ዮሃንስ 4ኛ እህት የጎንደሩ ንጉስ ተክለጊዮርጊስ ሚስት እንደነበረች እዚህ ላይ ልብ ይሏል፡፡ ፍትጊያው ከዘመዳሞች ጋር ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ ንጉስ ተማርኮ እንኳ ምህረት አላገኘም፣ በአባ ሰላማ ተራራ ላይ ለእስር ተዳርጎና ተሰቃይቶ ሞተ፡፡
አጼ ዮሀንስ ህብረ-መንግስትን ለመመስረትና የአንድነት ስሜት እንዲፈጠር ሲሉ በማስገደድ አንድ ሐይማኖት ብቻ ሐያል ሆኖ እንዲጸና ብዙ ባክነዋል፡፡ በ1878 ቦሩ ሜዳ ላይ በተደረገው ጉባኤ  በጎጃሙና በትግሬ የበላይነቱን የያዘው የካራ እምነት እንዲሆን ተወሰነ፡፡ ይህም በሸዋ የዕምነት አቅጣጫ ላይ የተጣለ ፖለቲካዊ ግዳጅ እንደነበር አይካድም፡፡ የአጼ ዮሀንስን ትእዛዝ የሚቃወሙ ሙስሊሞችንና አረማዊያንን ከአካል ቅጣት በተጨማሪ ሐገራቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ተደርገዋል፡፡ ትምባሆ የሚያጤሱ ልማደኞች እንኳ መሬታቸው እንዲነጠቅና ከንፈራቸው እንዲፎነን ሁነዋል፡፡ እንግዲህ ለብዙ ጊዚያት ህበረተሰቡ ውስጥ ስር ሰደው የቆዩ ልማዶችና ዕምነቶችን በመነጋገርና በመግባባት ከመፍታት ይልቅ በግዴታና በአዋጅ ጋጋታ ለመፈጸም መጣር የፖለቲካ ምህዳሩን ሌሎች እንዳይሞክሩት ቦታ ማሳጣት ነው፡፡
መኩሪያ መካሻ [ረዳት ፕሮፌሰር] አንጋፋ ጋዜጠኛ ፣ደራሲ ፣ተርጓሚና፣ መምህር ናቸው።
Filed in: Amharic