>

ለዓብይ አህመድ የቀረበለት ሁለት ምርጫዎች፣ (ኤርሚያስ ለገሰ)

ለዓብይ አህመድ የቀረበለት ሁለት ምርጫዎች፣

ኤርሚያስ ለገሰ

(ኢሳያስ አፈወርቂን ተቀብሎ ከአለም መነጠል ወይም ከኢሳያስ አፈወርቂ ፍቺ ፈጽሞ ወደ ሰፊው ዓለም መቀላቀል!)
“በኢትዮጵያ በተከሰተው ግጭት ሳቢያ ከምዕራብ አገሮችና አለም አቀፍ ተቋማት ጋር የተቀዛቀዘውን የውጭ ግንኙነት መልሶ ማሻሻያ ስትራቴጂ ” በሚል ርዕስ በኢትዮጲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋጀውን ባለ 51 ገጽ ዶክመንት መላልሼ አነበብኩት።
ሰነዱ ከህውሃት ጋር ወደ ድርድር የመገባቱ ነገር አይቀሬ እንደነበርና በሶስት ሁኔታዎች ሊፈፀም እንደሚችል አመላክቷል።
የመጀመሪያው ለኢትዮጵያ ወሳኙ መፍትሔ ጦርነቱን ግልጽ በሆነ የበላይነት በማሸነፍ አሸባሪውን ኃይልና ተባባሪዎችን በማንበርከክ የተጀመረውን የህልውና ዘመቻ የመጨረሻ ምዕራፍ በድል መቋጨትና ሙሉ አቅሙን ወደ ልማት ማዞር እንደሚያስፈልግ የተዘጋጀው ዶክመንት ያስገነዝባል።
ሁለተኛው  የአማራና የአፋር ክልል ነዋሪዎችን የሚያረጋጋና ህውሃትን ቆንጠጥ የሚያደርግ ወታደራዊ እርምጃ ከተወሰደ ቡድኑ ሳይወድ በግድ ወደ ድርድር ይገባል።
ሶስተኛው ሁኔታ ይሁን እና ጦርነቱ እየተራዘመ በሄደ ቁጥር ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ በኩል የሚመጣው ጫና አገር ውስጥ እየተስፋፋ ካለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስና ሰብዓዊ ኪሳራዎች ጋር ተደማምሮ ወታደራዊ የበላይነት ባልታየበት ሁኔታም ቢሆን ወደ ድርድር የመገባቱን ነገር አይቀሬ ሊያደርገው ይችል እንደነበር ሰነዱ ያብራራል።
በሰነዱ ላይ የተለያዩ አገሮችና አለም አቀፋዊ ተቋማት በግጭቱ ዙሪያ ያላቸው እይታና የሚያራምዱት አቋም በተመለከተ የጎረቤት አገሮች ፤ የአፍሪካ አገሮችና ተቋማት፤ የአሜሪካን፤ የአውሮፓ አገሮችና የአውሮፓ ህብረት ፤ የአለም አቀፍ ድርጅቶች፤ ሚዲያዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንዲሁም የሌሎች ኃያላን አገሮች ዕይታና አቋም በዝርዝር ቀርቧል።
የአፍሪካ አገሮች በተለይም ጎረቤት አገሮች በአመዛኙ ጦርነቱን የአገር ውስጥ ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ችግሩን በራሳችን አቅም እንድንፈታው የተባበሩ ቢሆንም ሱዳን ግን አጋጣሚውን በመጠቀም የአገራችንን ድንበር ጥሳ በመግባት ወረራ መፈጸሟን ሰነዱ አመላክቷል። ጅቡቲን በተመለከተም የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ከራሷ ህልውና ጋር ስለሚተሳሰር የህውሃት ቡድን ጨርሶ የመደምሰሱ አስፈላጊነት ላይ እንደምታምን መግለጿን ዶክመንቱ ያትታል።
በአጠቃላይ መልኩ የአፍሪካ አገሮች በተለይም የጎረቤት አገሮች አጠቃላይ አቋም ሲገመገም ከታወቁት የግብጽና የሱዳን መንግስት ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም በስተቀር ቀሪዎቹ የጎረቤት አገሮች አቋም ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን የመቆም ነው ለማለት ያስደፍራል ይላል።
የምዕራቡ አገሮችና ተቋማት ዕይታና አቋም በተመለከተም በአሜሪካ የሚመራው የምዕራቡ አለም ባለው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተልዕኮዎች የመፍጠር እንዲሁም የሚዲያና የአለም አቀፍ ተቋማትን የመቆጣጠር አቅሙን ተጠቅሞ የግጭቱን አውድ በማዛባት ኢትዮጵያ ላይ ከባድና ለመቋቋም አስቸጋሪ የሆነ ጫናን ፈጥሯል።
 እነዚህ ምዕራባውያን የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብት እየጣሰ እንደሆነ፤ ረሃብን እንደ ጦርነት መሳሪያ እየተጠቀመ እንደሆነ፤ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳይደርስ እንቅፋት እየፈጠረ እንደሆነ እና ሌሎች ክሶችን ሚዛኑን በሳተ መንገድ በማራገብ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ ይላል።
በተለይም ምዕራባውያን ከኤርትራ መንግስት ጋር ባላቸው የሻከረ ግንኙነት ምክንያት የኤርትራ መንግስት በጦርነቱ መሳተፍ ሁኔታውን ውስብስብ እንዳደረገውና የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ እና በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያደረገ ነው በማለት እንደሚከሱ ሰነዱ ይገልጻል።
የአሜሪካ መንግስትን አድራጊ ፈጣሪነትና በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳሳደረች  አምኖ የተቀበለው ይህ ሰነድ የአሜሪካ እየተከተለች ያለችው አቋም ከብሔራዊ ጥቅሟ እንደሚቀዳ ያስገነዝባል። አሜሪካ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ወሳኝ አገር መሆኗን በመገንዘብ፤ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ወሳኝ ሚና እንደምትጫወት እምነት አላት።
 ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካና አውሮፓ አገሮች የቀይ ባህር አካባቢን ፓለቲካ ለመቆጣጠርና የቻይናን እና የሩሲያን እንቅስቃሴ ለመገደብ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር አካባቢ ካላት ጂኦ-ፓለቲካል ጠቀሜታ እንዳላት እንደሚገነዘቡ ሰነዱ ያትታል።
ጦርነቱ ኢትዮጵያ ይህንን ሚናዋን እንድትወጣ እንቅፋት ስለሚፈጥርባት የተከሰተውን ቀውስ ከወታደራዊ እርምጃ ይልቅ በሰላማዊ መንገድ በድርድር እንዲፈታ አሜሪካ የፀና ፍላጎት እንዳላት ዶክመንቱ ይገልጻል።
በሌላ በኩል አሜሪካ ወታደራዊ እርምጃው የሚቀጥል ከሆነ የህውሃት አመራር ስለሚደመሰስ ወይም ለሕግ ስለሚቀርብ የድርጅቱ ሕልውና ሊያከትም ይችላል የሚል ስጋት እንዳላት የሚገልፅ ሲሆን የአሜሪካ የድርድር ፍላጎት ከሚመነጭበት አንዱ ምክንያት ህውሃትን ለማዳን እንደሆነ ሰነዱ አጽንኦት ይሰጣል። አሜሪካ ለምን የህውሃት ህልውና እንዲጠፋ እንዳልፈለገች ሁለት ምክንያቶች አቅርቧል። የመጀመሪያው ህውሃት የአሜሪካንን ፍላጎት ለማሳካት ተባባሪ እንደነበረች ይገልጻል። ሁለተኛው ደግሞ ህውሃት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነትን ለማሻከር ዋነኛ መሳሪያ ሆና ታገለግላለች ይላል።
የአሜሪካ መንግስት የኤርትራ መንግስት ያመጣው የፓሊሲ ለውጥ የለም በማለት የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ መንግስት ፓሊሲ ለውጥ ላይ ተጽዕኖ አላደረገም የሚል ቅሬታ ያነሳሉ። አሜሪካውያን  የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን አምርረው ስለሚጠሉ እና ከስልጣናቸውም እንዲነሱ ሰለሚፈልጉ አብይ አህመድ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ወዳጅነታቸውን ማጠናከራቸውን የኤርትራ ሰራዊት በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት መሳተፍና ከኢትዮጵያ ግዛት ሙሉ በሙሉ ለቆ በፈለገው ጊዜ አለመወጣቱ ያስቆጣቸው ሲሆን፤ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ያላቸው እምነት እንዲሸረሸር አድርጓል ይላል።
“አሜሪካኖች ከኢትዮጵያ ምን ይፈልጋሉ?” ወይም “አሜሪካኖች ከኢትዮጵያ ምን አጥተው ነው?” በማለት ጥያቄዎችን የሚያነሳው ይህ ዶክመንት የተለያዩ ምክንያቶችን በምላሽነት ያቀርባል።
የመጀመሪያው አሜሪካ በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ በተፈለገው መንገድ አልሄደም እንዲያውም ተቀልብሷል ብለው ያምናሉ ይላል።
 ሁለተኛው ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቷን በተለይም ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት ይቀዛቀዛል የሚል እምነት እንደነበራቸው ይገልጻል። ሶስተኛው ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ በመሆኗ፤ አራተኛ አሜሪካን ከግብጽ ጋር ያላት ግንኙነት እንደሆነ ያስገነዝባል።
በመጨረሻም አሜሪካኖች ኢሳያስን አምርረው ስለሚጠሉ እና ከስልጣናቸውም እንዲነሱ ፍላጎት ስላላቸው እንደሆነ ሰነዱ ያትታል። ይህም የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ አጣብቂኝ ውስጥ የሚከተው ይሆናል። ኢሳያስ አፈወርቂን ተቀብሎ ከአለም መነጠል አሊያም ከኢሳያስ አፈወርቂ ፍቺ ፈጽሞ ወደ ሰፊው ዓለም መቀላቀል!!
Filed in: Amharic