>
5:13 pm - Thursday April 19, 5004

የሰሜን ጦርነትና የአፋር ቀጣይ እጣ ፋንታ: (አፋር በጦርነቱ ቁማር ተበልቷል?)  ሞሀመድ ያሲን

የሰሜን ጦርነትና የአፋር ቀጣይ እጣ ፋንታ: (አፋር በጦርነቱ ቁማር ተበልቷል?) 
ሞሀመድ ያሲን

(እውነታውን ማወቅ ለሚፈልግ ብቻ የተፃፈ: ረጅም ፅሁፍ)
1. ጦርነቱን ማነው የጀመረው?
በዱሮ አህአዴግ፤ በአሁኑ ብልፅግናና ህወሓት መሀከል የተፈጠረው የፖለቲካ ሽኩቻ ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀያየረ ቆይቶ በመጨረሻ ወደ አውዳሚ ጦርነት አደገ። የጦርነቱ ዋና መንስኤ ከሀገራችን ቆየ የፖለቲካ ችግር ጋር በቀጥታ የተያያዘ ስሆን የሰሜን እዝ ላይ የተፈፀመ አሰቃቂ ጥቃት የጦርነቱ መነሻ ነጥብ ተደርጎ ይወሰዳል። ጦርነቱ በትግራይ ስካሄድ በነበረው ወደ ስምንት ወር ጊዜ የአፋር ክልል መንግስትም ሆነ የአፋር ህዝብ የጦርነት ተሳትፎ አላደረገም ነበር። (እንደ ፌዴሬሽኑ አካል በሃሳብ ከመደገፍ ውጭ)። በሌላ አቅጣጫዎች ተዘግቶባቸው እያለ ገባያም ሆነ እርዳታ እንድገባላቸው ፈቅዶ ነበር። ከትግራይ የሚፈናቀሉ ወገኖችን በያሎ፣ በበራሕሌ፣ በአብዓላ እንድሁም በኩነባ አስጠልሎ ያበላቸው ነበር።  ወያኔ ተሸንፎ ጫካ ስገባ መቀለ እርዳታ ይዞ የገባው መጀመሪያ የአፋር ክልል መንግስትና ህዝብ ነበር። ይህ ወያኔ ያሎ ላይ ወረራ ከመፈፀሙ በፊት የነበረ ሁኔታ ነው።
2. የነገሩ መነሻ: ያሎ ላይ የሆነው ምንድነው?
የመከላከያ ኃይል ትግራይን ለቆ ከወጣ በኋላ ወያኔ አፋር ክልል ላይ ወረራ የፈፀመው በያሎ በኩል በከፈተው ጦርነት ነው። ልክ እንዳሁኑ ወደ አፋር ለመግባት ምክንያት ፈጥሮ ነበር። “ካሉዋን ላይ ያለው የመከላከያና የኦሮሞ ልዩ ኃይል ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሰለሚፈልግ አሳልፉን” አሉ። በዞን አራት ዋና ከተማ ላይ ጦርነት ላውጅ ነውና አሳልፉን ነው ያሉት። የአፋር ሽማግለዎች በግልፅ ቋንቋ “ጦርነት ወደ ክልላችን እንድገባ አንፈቅድም። እናንተ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ። እኛ ደግሞ ወደ እናንተ አንመጣም፣ በእኛ በኩል የሚመጣባችሁ ጥቃት አይኖርም ነበረ የተባሉት!”። ግን መጀመሪያም እቅዳቸው ሌላ ነበርና እዛው ሽማግሌዎችን በመግደል ነበር የጀመሩት።
የሚገርመው ገና ያሎን እንደተቆጣጠሩ ሃሳባቸውን ግልፅ አደረጉ። የወረዳ አመራሮችንና ቤተሰቦችን ለመግደል ነበር የሞከሩት። የገደሉም አሉ። ቀጣይ ያደረጉት ወረዳው ላይ የራሳቸውን አደረጃጀት መፍጠር ነበር። ቀጥሎ በያዙት የአውራ፣ የካሉዋንና የኡዋ ወረዳዎች ላይ ተመሳሳይ አካሄድ ነበር የተከተሉት። (ባላረጋገጥም ባንድራቸው እንደሰቀሉ የሚናገሩም አሉ!) ያ ብቻ ሳይሆን በፊት እንደለመዱት የጎሳ ግጭት ለማሰነሳት በተቆጣጠሩባቸው አካባቢዎች ላይ ያገኙትን ሰው ወደ ስልጠና በማስገባት ማስታጠቅና አፋርን እንድወጋ ለማድረግ ትልቅ ጥረት አድርጓል። የሆነው በተቃራኒ ቢሆንም። በኋላ ላይ በነበረው መልሶ ማጥቃት ላይ ወያኔን ለመምታት ራሳቸው ያሰለጠኑት ኃይል ነበር ትልቅ ጀብድ የፈፀመው። አፋርን አያውቁም የምንለው በምክንያት ነው።
3. አፋር ራስን ከመከላከል ውጭ ምርጫ ነበረው?
ከላይ በግልፅ እንደተቀመጠው የወያኔ እቅድ አፋር ክልልን ካሁን በፊት እንዳደረጉት በራሳቸው ሰዎች መግዛት ነበር። አሁን ያለው መንግስት ማፍረስ ነበር። ከዛ ከፍ ያለ እቅድም ነበራቸው።
እንግድህ አፋር ኢትዬጵያን የማዳን ግዴታ የለብኝም ብሎ ወያኔን ዝም ቢል እንኳ አፋር አሁን ከገባበት የባሰ ውጥንቅጥ መግባቱ የማይቀር ነበር። ከዛ የባሰው ደግሞ አሁን ያለው ክልላዊ መንግስት ይፈርስ ነበር። በቀጣይም እንደ ክልል ዳግም የመደራጀት አጋጣሚም በጣም አነስተኛ ይሆን ነበር። ያ ብቻ ሳይሆን በፌዴራል መንግስትና በወያኔ መሀል የሚካሄደው ጦርነት ሙሉ በሙሉ በአፋር ክልል ይካሄድ ነበር። የክልሉ ዋና ከተማ ጨምሮ የኢትዬ ጅቡቲ መንገድ የጦርነት ማዕከል ይሆን ነበር። አሁን ያሉት የአፋር ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ኃይል ይሰበር ነበር። ያ ብቻ ሳይሆን  የሱማሌ/ኢሳ ጥምር ኃይል ከገዋኔ እስከ ሚሌ ያለው ህዝብ በመጨፍጨፍ አካባቢዎችን ይቆጣጠር ነበር።
በመሆኑም አፋር ራሱን ለመከላከል ስወስን አማራጭ የለኝም ብሎ ወይም በፌዴራል መንግስት ተገዶ (ተሸውዶ) ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ሆኖበት ነው። ባይከላከል ኑሮ አፋር እንደ ክልል አይቀጥልም ነበር። ወያኔዎች በጣም ቸር ሆኑ ብንል ራሱ ክልሉ አሁን ካለው አምስት ዞኖች ሁለት ዞኖችን ወደ ትግራይ ያካልልና የቀሩት ዞኖች ስርአት አልባ እንድሆን ያድርግ ነበር።
4. አፋር ራሱን መከላከል ያለበት/የነበረበት የተለየ ምክንያት አለው?
ከላይ እንደገለፅኩት ወያኔ አፋር ክልል ለመግባት የፈለገው ጊዜያዊ የሆነ የራሱን ፖሎቲካዊና ወታደራዊ አላማ ለማሳካት አልነበረም። በቀጣይ ያላቸው ፖሎቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ እቅዶችን ለማሳካት ነበር።
እቅዶቹ የአፋር ክልል አሁን እየገነባ ያለው ፖሎቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ አቅም መስበር ብቻ ሳይሆን በቀጣይ አፋርን ማዕከል ያደረገ “የትግራይ ሪፓብሊክ” ለማቋቋም መሰረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ነበር። እሱም አፋር ላይ አሁን ያለው መንግስት መቀየር፣ እንደ ካሁን በፊቱ የራሳቸው ፑፒቶችን ማስቀመጥ፣ የዞን አራትና ዞን ሁለት ስትራቴጂክ ቦታዎችን ወደ ትግራይ በማካለል ቀጣይ ቀይ ባህርን ለመያዝ ለሚያደርጉት ዝግጅት የመጀመሪያ ምዕራፍ ማጠናቀቅ ነበር።
በመሆኑም አፋር ከወያኔ ወራሪ ኃይል ራሱን የሚከላከለው ከሌሎች ክልሎች የተለየ ምክንያት ሰላለው ጭምር ነው። እነሱም አፋርን የሚወሩት የተለየ ምክንያት ሰላላቸው ነው። ይህ እቅድ ከንግግራቸው፣ ከፖሎቲካዊ ዶክመንታቸው እንድሁም ከቀጣይ ስትራቴጂክ እቅድ ሰነዶቻቸው ላይ በቀጥታ የተወሰደ እንጅ ውንጀላ አይደለም። ማስረጃወን ማቅረብ ይቻላልና።
5. የአሁኑ ወረራ: መነሻ ምክንያት ምን ነበር?
ከላይ እንደገለፅኩት የወያኔ ወራሪ ኃይል በያሎ የጀመረው ወረራ ጊዜ ሙሉ ዞኑን ተቆጣጥሮ ነበር። ከዛ ተመቶ ከወጣ በኋላ ዳግም በጭፍራና በባቲ በኩል ገብቶ ሚሌን ለመቆጣጠር በሚል ሰበብ ክልሉንና ኢትዬጵያን ለማፍረስ ብዙ ጥረት አድርጎ ነበር። ሆኖም ግን ከአፋር በኩል ጭራሽ ያልጠበቁት ጀግንነት ነበር የገጠማቸው። አንዴ ኤርተራ፣ አንዴ ድሮን ላይ እያሳበቡ በአፋር ጀግኖች የደረሰባቸው ሽንፈት ለመሸፋፈን ብሞክሩም እውነታውን ከአለም መደበቅ አልቻሉም። የብዙ ወጣቶች ህይወት ገብሮ የተቆጣጠራቸው ቦታዎችን ለመልቀቅ የተገደዱት በአፋር በኩል ያቀዱት ሰለከሸፈባቸው ነበር።
ወያኔ በአፋር ጀግኖች ያጋጠማቸው ሽንፈት ሰላልጠበቁት በሰዓቱ ደንግጧል። ኢትዬጵያን ለማፍረስ ያደረጉት ጥረት ሰለከሸፈባቸው ደግሞ አፋር ላይ ቂም ይዟል። የባሰ ነገር ግን አለ። እነሱ ለመመስረት የሚያስቡት የትግራይ ነፃ መንግስት ለማቋቋም አፋር ጠንካራ መሆን አደጋ አለው። ትግራይ እንደ መንግስት ለመቆም የሰሜኑ አፋርና ቀይ ባህር መያዝ ቅድመ ሁኔታ ነውና።
በመሆኑም የአፋር ኃይል በዚህ ጦርነት ላይ ያገኘው ፖሎቲካዊና ወታደራዊ አቅም፣ የሞራል የበላይነትና የአልሸነፍ ባይነት መንፈስ መስበር የግድ ሆነባቸው። እናም አፋርን መውረር የግድ ነበር። ነገር ግን ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለአለም ህዝብ ወረራቸውን በአሳማኝ ምክንያት ማስደገፍ የግድ ሆነባቸው። ካልሆነ የሚያደረስባቸው ፖሎቲካዊና ድፕሎማሲያዊ ኪሳራ ቀላል አልነበረም። ለዚህ ደግሞ ሁለት ምክንያት አገኙ። ወደ ትግራይ እርዳታ የሚገባበት ብቸኛ መንገድ የአብዓላ መስመር መሆኑና የሰሜን አፋር ከኤርትራ ጋር ድንበር መጋራቱ። ሁለቱ ጉዳዬች ደግሞ የትግራይ ህዝብም ሆነ የአለም ህዝብ ለማሳመን  ካሁን በፊት ስራ ላይ የዋለ ነበር። በመሆኑም የመጀመሪያ እርምጃ ያደረጉት አብዓላ ላይ ጥቃት በመፈፀም መንገዱ እንድዘጋ ማድረግ ነበር። ቀጥሎ በዛ ስም ሙሉ ወረራ ማካሄድ። በአሁን ሰዓት በአምስት ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ ስሆን አሁንም ሽንፈትን እየተከናነቡ ወጣቶችን እያሰጨረሹ ይገኛሉ። ህዝባችን ላይ የፈፀሙት ዘግናኝ ጭፍጨፋ ግን ለዘመናት የማይረሳ ጠባሳ ሆኖ ይቀጥላል። ወይዳል እናቆምለታለን።
6. እውነት ኤርትራ ከአፋር ጎን ተሰልፋ ተዋግታለች? የቀይ ባህር አፋር  ኃይል ማነው?
ወያኔ በአሁኑ ወረራ እንደ ምክንያት ከተጠቀመችው አንዱ “የኤርትራ ጦር” የሚል ነው። ለይቶ ደግሞ የቀይ ባህር አፋር ኃይል የሚል ሃሳባዊ ኃይል ፈጥሯል። በየተኛውም መደበኛም ሆነ ኢ–መደበኛ ደረጃ “የቀይ ባህር አፋር ኃይል” የሚባል የለም። ያለው “የቀይ ባህር አፋር ድሞክራሲያዊ ድርጅት” የሚባል ስሆን ይህ ድርጅት ኤርተራን በመቃወም የትጥቅ ትግል የሚያካሄድ ድርጅት ነው። ስለዚህ ድርጅቱ ከኤርተራ መንግስት ጎን ተሰልፎ ጦርነት ልያካሄድ አይችልም። ስማቸውም አልተገለፀም። ሌላው ደግሞ “የኤርተራ ጦር” የተባለው ነገር ነው።
እውነት ለመናገር ወያኔ የኤርተራ ጦር አብዓላ አካባቢ መኖሩን ብታውቅ ኑሮ ወረራ ልፈፅሙ ቀርቶ በዛ አካባቢ ዝር አይሉም ነበር። ከኤርተራ ጋር ውጊያ ከፈለጉ እኮ ሰፊ ድንበር ይጋራሉ። በየቀኑ ይተናኮሳቸዋል። ከዛ በተጨማሪ በሁመራ በኩል ኤርተራን ፍራቻ ነው እስካሁን ለመግባት ያልደፈሩት። ምን እሱ ብቻ?! ባድመ፣ ዛላንባሳ፣ ሽራሮ አካባቢ ብዙ ቀበሌዎች በኤርትራ ጦር ተይዞባቸዋል። ታዲያ በኤርትራ የተያዘባቸው የገዛ መሬታቸውን ነፃ ማውጣት ነው የሚቀድመው ወይስ በሌላ ክልል “ልወሩን ነው” በሚል ሰበብ ወረራ መፈፀም? የማይመስል ነገር ነው።
ከላይ እንደፈለፅነው ሁለቱም ግዜ አፋር ላይ ወረራ ለማካሄድ ምክንያት ፈጥሮ ነው። ሁለቱንም ጊዜ ምክንያት የፈጠሩት የሌለ ነገር ነው። ልክ አሜሪካ ኢራቅን ለመውረር “ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ” አላቸው የሚል ሰበብ እንደፈጠረችው ነው። ተቀባይነት ያገኛል ብሎ የሚገመቱትን ምክንያት ያቀርባሉ። እውነታው ግን በተቃራኒ ነው።
7. እውነት አፋር የወያኔ ውለታ አለባት?
ሌላው የወያኔ አፈቀላጤዎች የሚያዞሩት ወሬ አለ። “አፋር የትግራይ ውለታ አለባት” የሚል። እውነታው ግን በተቃራኒው ነው። “ትግራይ የአፋር ውለታ አለባት!” ነው መሆን ያለበት። ምክንያቱም ካለ አፋር መሬት፣ ካለ አፋር ደጀንነት፣ ካለ አፋር ማዕድናት፣ ካለ አፋር ኃይል ትብብር፣ ካለ አፋር ድፕሎማሲያዊ ድጋፍ (በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ) ህወሓት የሚባል ድርጅት ከተራ ሽፍታነት በላይ ሚና አይኖረውም ነበርና። የቀዳማይ ወያኔና የአሁኑ ጦርነት ከሽፎ የሁለተኛ ወያኔ ትግል ለምን ስኬታማ ሆነ ብባል “የአፋር ድጋፍ መኖሩና አለመኖሩ” ነው የሚል መልስ ይሆናል። ኧረ አፄ ዩኃንስም ራሱ ከአፄ ቴዎድሮስ ተደብቆ የተረፍው አፋር ውስጥ ነው። የትግራይ የፖለቲካ ትግል ታሪክ እንግድህ ከዚህ ውጭ የለም። አክሱም ይቆየን።
ይልቅ አፋር ይህን ያክል ውለታ ለዋለችለት ወያኔም ሆነ ቅድመ ወያኔ የትግራይ ትግል ያተረፈው ወረራ ብቻ ነው። አፄ ዩሃንስ ከለላ የሰጠው ያኩሚን ወረረ። ወያኔ 17ቱም አመት ከለላ የሰጣቸውና የደገፋቸው አፋር ላይ ክህደት በመፈፀም የህልውና አደጋ ውስጥ እንድገባ አደረገ። አሁን ላይ ደግሞ እርዳታ እንድገባላቸውና ገባያ እንድያገኙ ያደረገላቸው አፋር ህዝብን ሦስቴ ወረሩ። 1988፣ አንድ ግዜ፣ አሁን ደግሞ በያሎ በኩልና በአብዓላ በኩል። የአሻጥሩና የሴራው፣ የሀብት መቀራመቱና የበጀት ምዝበራው፣ የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካው… ወዘተ አይወራም!
8. አፋር ቅድመ ወያኔ
ሌላው ወያኔዎች እንደ ውለታ የሚጠቅሱት “ክልል ሰጠናችሁ”  የሚለውን ነው። አፋር ከኢህአዴግ በፊት የነበረበት የአስተዳደር ሁኔታ በመግለፅ “አፋር መሬት አልነበረውም” ለማለት ይዳዳቸዋል። ለዚህ መልስ የሚሆነው ታሪክ ከየት እንጀምር? የሚለውን ነው። አፋር እንደ ማንኛውም ህዝብ የመንግስትነት ታሪክ፣ መንግስት ስያቋቁምም ስፈርስበትም እዚህ ደርሷል። በአንካሊ ዘመነ መንግስት አፋርን አንድ አድርጎ የሚመራ ጠንከራ መንግስት መስርቷል። ቀጥሎ በተለያዩ የሀገርቷ አካባቢዎች ላይ ኢማራቶችን መስርቶ ስመራ ቆይቶ በመጨረሻም የአዳል ሰርዎ መንግስት በበላይነት መስርቶ የአፍሪቃ ቀንድን መርቷል። በኋላ ላይ በአምስት ሱልጣኔትና በተለያዩ አካባቢያዊ መንግስታት ተዋቅሮ በባህላዊ ስንሰለት አንድነቱን አስጠብቆ ኑሯል። መጀመሪያም በኮሎኒያሊዝም፣ ቀጥሎም በአቢሲኒያ መንግስት መስፋፋት ጋር በተገናኘ አፋርን አንድ አድርጎ የሚያስተዳድር ባህለዊም ሆነ ዘመናዊ ማዕከላዊ መንግስት ሰላልነበረ የህለውና ትግል ብቻ በማድረግ በተለያዩ አካባቢ ያለ ፖለቲካዊ አንድነት ኑሯል። በመጨረሻም በ60ዎቹ በተቀሰቀሰው የራስን በራስ የማስተዳደር መብት ትግል በመቀላቀል ለመብቱና ለነፃነቱ ታግሏል።
በአፄ ኃይለስላሴና በደርግ ጊዜ አፋር በተለያየ የክፍለ ሀገር ግዛት ስር ቆይቶ በመጨረሻ አካባቢ የአሰብ ራሰ ገዝ ስር በአብዘኛው መተዳደር ጀምሮ ሰለነበረ ትግሉ ከባድ አልነበረም።
ግን በመጨረሻ የኢሳያስና የወያኔ ጥምረት አፋርን ከቀይ ባህር እንድነጠል በማድረግና ለሁለት በመክፈል ኑሮው በአርብቶ አደርነት ብቻ፣ መሬቱ በበርሃነት ብቻ፣ ማህበራዊ አወቃቀሩ በጎሳነት ብቻ፣ የኑሮ ዘይቤው ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ብቻ አድርጎ እንድሳል በማድረግ ኋላ ቀር፣ ታዳጊ፣ አጋር፣ አናሳ… የሚሉ ቅጥያዎችን እየጨመረ በማነንቱ እንድሸማቀቅ፣ የበታችነት እንድሰማቸው ለማድረግ ያላደረጉት ነገር አልነበረም። አፋር በተፈጥሮ ነፃ ሆኖ ሰለሚያድግ ፎርሙላው አልሰራላቸውም እንጅ።
እዚህ ጋር መታወስ ያለበት አፋር በወያኔ ምክንያት ለሁለት መከፈሉ፣ ከቀይ ባህር ጋር መነጠሉ፣ ከወንድሞቹ ጋር መለያየቱ እንደ በደል ሳይቆጠር ሰለ ክልል ውለታ ስያወሩ አለማፈራቸው ነው።
የክልልም ብሆን አፋር የትጥቅ ትግል በሚየካሄዱ ነፃ አውጪ ድረጅቶች ተወክላ የነበረ ስሆን አፋር አሁን ካለው ካርታና አደረጃጀት ውጭ ለድርድር የማይቀርብ ሰለ ነበረ እንጅ ሰሜን አፋርን ለመውሰድ ወያኔ ፈልጎ ነበር። የኤርትራም ቢሆን በሰአቱ ከነበረው የኃይል አሰላለፍ አንፃር ሆነ እንጅ አፋሮች አልተቀበሉትም። ወደፊት የሚሆነውን እናያለን።
9. የጦርነቱ ቀጣይ ሁኔታና የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት እጣ ፋንታ
ከላይ በዝርዝር እንደተገለፀው በአሁኑ ጦርነት አፋር ራሱን ባይከላከል ኑሮ ልክ በ1983 እንዳደረጉት አፋርን ለሁለት ይከፍሉ ነበር፣ ተላላኪ መንግስትን ይመስርቱ ነበር። አሁንም ወረራ የሚፈፅሙት ያንን አላማ ለማስፈፀም ነው።
በመሆኑም አፋር ያደረገው የህልውና ትግል እንጅ የአይዲዬሎጂ ወይም የስልጣን ሽኩቻ ጦርነት አይደለም። በዚህ ጦርነት ቁማር ልበሉ የነበሩት ወያኔን አምኖ ቢያሳልፏቸው ነበር። ከፈዴራል መንግስት ጎን አንሰለፍም ቢሉ ነበር።
ወያኔ ከሌሎች ጋር ያላት ጦርነት የኃይል አሰላለፍ ወይም የሽኩቻ ልሆን ይችላል። ከአፋር ግን ሰለ ነገ ያለን ህልም ይጋጫል። የአፋር መሬትን፣ የአፋር ሀብትንና ቀይ ባህርን ማዕከል አድርጎ ለመመስረት የሚያስቡት የታላቋ ትግራይ መንግስት አፋርን ከምድረገፅ በማጥፋት የሚሳካ ነው። በመሆኑም ከእንግድህ የሁለቱ ጦርነት ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል፣ ለዘመናት የሚዘልቅ መሆኑ የማይቀር ነው። ነገር ግን የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ዳይናሚክስ ልቀያየር የሚችል ብሆንም የትግራይ ሪፓብሊክ ምስረታ ቅዠት እስካልቀረ ደረስ የአሰላለፍ ለውጥ ብኖር እንጅ አብሮ መቆም የመኖር እድሉ አነስተኛ ይሆናል።
Filed in: Amharic