>

ኦጋዴን ነዳጅ፡ የምዕራባዊያን አዲስ ካርታ? (የዓባይ፡ልጅ)

ኦጋዴን ነዳጅ፡ የምዕራባዊያን አዲስ ካርታ?

       ▪️Esleman Abay የዓባይ፡ልጅ✍️

ከቻይናው ፓሊ-ጂሲኤል ኩባንያ ጋር የተፈጠረው አለመግባባት እጅጉን የሚያሳስብ ነው። በተለይም የችግሩ ሰበብ ጂኦፖለቲካዊ ሽኩቻ መሆኑ ሲገለጥ። ኩባንያው ውሉ ላይ የተቀመጠውን ጊዜ በማዘግየቱ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ለአዲስ ዘመን የገለፀው የማዕድን ሚኒስቴር “የነዳጅና ኦጋዴን የሚገኘው የተፈጥሮ ሀብቱ የምርመራና የምርት ሂደቱን አልፎ ለገበያ የሚቀርብበት ደረጃ ላይ ቢደርስም ኩባንያው ባጋጠመው ውስጣዊና ዓለምአቀፍ ቀውስ ምክንያት ምርቱን ወደ ገበያ ሳያቀርብ ከአምስት ወራት በላይ አልፎታል።” ነው ያለው። ክስተቱ ሰኔ እና ሰኞ የሚባል አይነት  ነው።
  ፖሊጂሲኤል GCPoly በሚለው ስሙ በስፋት ይታወቃል። ታዲያ ከአሜሪካ ጥርስ የከተተው አንድ ጉዳይ አለ። ይህ ግዙፍ ኩባንያ በተለይም ፖሊሲሊኮን በሚባሉ የሶላር መሳሪያዎች በማምረት በግዝፈቱ ከአለም ሁለተኛ ነው። አሜሪካ ምርቱን በገፍ ትሸምተዋለች። ሻጯ ደግሞ ቻይና ናት። በዘመነ ትራምፕ በነበረው የንግድ ጦርነት ወቅት ምርቱ ለዋሽንግተን አስላጊ ስለሆነ ፖሊሲሊኮን ለሚያመርቱ የቻይና ኩባንያዎች የታክስ ጫና ርምጃው በተለየ እንዲነሳላቸው ለማድረግ ተገደው ነበር። ምክንያቱም ቻይና የአለማችንን 90 በመቶ ፖሊሲሊኮን የምርት ሂደት value chain የተቆጣጠረች ናት። በምርት ረገድ ደግሞ 50 በመቶው በቻይና ፋብሪካዎች የሚቀርብ ነው። አሜሪካ ከቻይና ጥገኝነት ለመላቀቅ በሰፊው ኢንቨስት ለማድረግ ብትሞክርም በሶላር ምርቶች በኩል ያሳካችው 40 በመቶ እንኳን በወጉ ያልደረሰ ነው። በዚህ ላይ የቻይና መንግስት ለዘርፉ ባመቻቸው ልዩ ህግ በሀገሪቱ ውስጥ ምርቱ በርካሽ እንዲመረት ሆኗል። በአለማቀፍ ገበያም እስከ 40 በመቶ የዋጋ ቅናሽ አለው። በዚህ የተነሳም አሜሪካ ቻይናን መገዳደርም ሆነ ከጥገኝነት ለመላቀቅ አልተቻላትም።
ይሁንና የባይደን አስተዳደር በቅርቡ Xinjiang Production and Construction Corps ወይም XPCC የተባለውን ኩባንያ ከማዕቀብ ዝርዝር ውስጥ አስገብቷል። ኩባንያው ጨርቃጨርቅ ላይ የተሰማራ ሲሆን በጉልበት ብዝበዛ ያመርታል በሚል ነው ዋሽንግተን ርምጃ የወሰደችበት። ታዲያ ይህ ኩባንያ ከፍተኛ የሆነ ድርሻው የ GCL-Poly ነው። ችግሩ እዚህ ጋ ይጀምራል ማለት ነው።
  በሌላ በኩል ፖሊጂሲኤል በኦጋዴን ከተሰማራ ጀምሮ ሶማሊላንድ ስትቃወመው ቆይታለች። ለአብነትም የጤና ጉዳት አመጣብን፣ ቻይና አላግባብ እየተስፋፋች ነው የሚሉ ዘመቻዎቿን መጥቀስ ይቻላል። የሶማሊላንድ ዋነኛ ምክንያቷ ግን ከሶማሊያ ጋር ካለባት ሽኩቻ የመነጨ ነው። በቻይና አካሄድ ስትበሳጭ ለታይዋን እውቅና በመስጠት ለቤይጂንግ ምላሿን አሳይታለች።
ከወራት ወዲህ በተለይም ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ በርካታ ምዕራባዊ የፖሊሲ ጥናት ተቋማት ሶማሊላንድ እውቅና ይሰጣት በማለት ተደጋጋሚ ጥናት አቅርበዋል። አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ያጣችውን ቦታ በዚህ በኩል ማሳካት ትችላለች የሚለው ነጥብ በተቋማቱ ጥናቶች ዋነኛው ፋይዳ ሆኖ ሲጠቀስ ተስተውሏል።
   ከቀናት ወዲህ ደግሞ አሜሪካ ለሶማሊላንድ ሉአላዊነት አውቅና ለመስጠትና ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ ህግ አርቅቃ እየመከረችበት ነው። የእንግሊዝ ምክር ቤትም ሉአላዊነቷን ለመቀበል ውይይት ጀምሯል።
ባለፈው የአዲስ አመት ዋዜማ ጳጉሜ ላይ“በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ  ክምችት መጠን እስከ ዛሬ ድረስ እንዳይታወቅ ተደርጎ ነው የቆየው። እኛ ወደ ዚህ ከመጣን በኋላ ከፍተኛ መጠን እንዳለን ማወቅ ችለናል። በሚቀጥሉት ከ3እስከ 5 ዓመታት ውስጥ  ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነዳጅ አውጥተን መጠቀም እንጀምራለን።” ስትል ከውጭ አገር ተጠርታ በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ስራ የጀመረችው ወጣት ኢንጂነር ሀና ብርሃኑ መናገሯን በዚሁ አጋጣሚ አውስተነው እንለፍ። በእግረ መንገዳችንም ፖሊ-ጂሲኤል ኩባንያ በርካታ የኮቪድ ክትባቶች ለኢትዮጵያ ያደረሰው በቅርቡ እንደነበር እናስታውስ።
“በሶማሌ ክልል የተፈጥሮ ጋዝ ልማት ያዘገየው የፖሊጂሲኤል ኩባንያ 2 ቢሊዮን ዶላር ማስተማመኛ እንዲያቀርብ የታዘዘው ባሳለፍነው ጥቅምት ነበር። ይህንን ተከትሎ ኩባንያው የተፈጥሮ ጋዙን ለማልማት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ  የሚገልጽ  ዝርዝር ለማዕድን ሚኒስቴር ማስገባቱ በወቅቱ የተዘገበ ሲሆን፣ ባቀረበው መረጃ ላይ ግን ማዕድን ሚኒስቴርና ኩባንያው መተማመን እንዳልቻሉ ነበር ሪፖርተር ጋዜጣ ያስነበበው።
በፖሊ-ጂሲኤል ኩባንያ የተፈጠረው መጓተት አሳሳቢ ችግርነቱ ግልፅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁናዊ የጂኦፖለቲካ ጥልፍልፎች ዙሪያውን እያንዣበቡ ከመሆኑ አኳያ ሲታይ ግን ቆም ማለትን የሚጠይቅ ነው። ኩባንያው ለቻይናም ለአለምም ግዙፍ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በቤይጂንግ እና ዋሽንግተን የንግድ ጦርነት ወስጥ የገባ መሆኑንም ከግምት ማስገባት ይጠይቃል። ለመፍትሄው ከኩባንያው ባለፈ ከቻይና መንግስት መምከር የሚጠይቅ ሊሆንም ይችላል።ብቻ፣ ለእንግሊዝ ሴራ እና ለአሜሪካ ቁማር እንዳይጎዳን ልንጠነቀቅ ይገባል።
Filed in: Amharic