>
5:21 pm - Sunday July 19, 0961

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘኢትዮጵያ የአፍሪካ አባት (ተረፈ ወርቁ ደስታ)

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘኢትዮጵያ የአፍሪካ አባት

ተረፈ ወርቁ ደስታ


 

‘Haile Selassie I of Ethiopia: Father of the O.A.U.’’ (የናይጄሪያው ሳንዴይ ኦብዘርቨር፤ ጁላይ 23፣ 1972)

ኢትዮጵያዊ ታላቅ ሕዝብ ነው፡፡ ስለ አፍሪካ ነፃነት በጀግንነት የተዋጋ፣ ነፃነትም ቋሚ እንዲሆን፣ ሕዝቦቻችን ያለ ምንም የውጭ መንግሥታት ተቆጣጣሪነትና ጣልቃ ገብነት በተገቢ ሥልጣናቸው እየተመሩ የገዛ ራሳቸውን ዕድል እንዲመሩ ያላቸው ሥልጣን እንዲጠበቅላቸው የደከመ አፍሪካዊ ሕዝብ ነው፡፡ ይህ በንጉሡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ አስተባባሪነትና መሪነት፣ የአፍሪካውያኖች ጉባኤ የተደረገው በኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ስለሆነ፣ አዲስ አበባና ኢትዮጵያ አሁንም የበለጠ ከአፍሪካ ታሪክ ጋር የተሳሰሩ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት በአንድ አኅጉር ሕዝቦች ፈቃድ ተነሳስቶ በሚመራው የዕድገት ፍላጎትና ሥራ ሁሉ ሳይቋረጥ ስማቸው ተያይዞ የሚኖር ይሆናል…፡፡’’ (የጊኒው ፕ/ት የነበሩት ሴኮቱሬ)

የትናንቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የዛሬው የአፍሪካ ህብረት የተመሰረተው ከ59 ዓመታት ግንቦት 16 ቀን 1955 ዓ.ም ነበር፡፡ ወቅቱ የአፍሪካ አገራት በሁለት የተከፈሉበት ነበር፡፡ በአንድ ወገን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ሀገራቱ በፍጥነት ተዋሕደው አፍሪካ አንድ ልትሆን ይገባል የሚለው የካዛብላንካ ቡድን፤ እንዲሁም አንድ ከመሆን በፊት ሌሎች ትብብሮች ሊቀድሙ ይገባል የሚለው የሞኖሮቪያ ቡድኖች ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያም በወቅቱ የሞኖሮቪያን ቡድን ተቀላቅላ ነበር፡፡ በኋላ ኢትዮጵያ ባደረገችው ከፍተኛ ጥረት ሁለቱ ቡድኖች የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመስረት ባስቻለው ስብሰባ ላይ ለመታደም አዲስ አበባ ከተሙ፡፡

ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በጉባኤው ላይ ለተገኙት የአፍሪካ መሪዎች ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንዲህ አሉ፡-

“በዚህ በዛሬው ቀን በዚህች በዋና ከተማችን በአዲስ አበባ የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ተካፋይ ለመሆን የመጣችሁትን የነፃ አፍሪካ አገር መሪዎች፣ ወንድሞቻችን በራሳችንና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ስንቀበል በጣም ደስ ይለናል፡፡ ይህ ዛሬ እኛ የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት መሪዎች የምናደርገው ጉባኤ በዓለም ላይ እስካሁን ድረስ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ የዚህን ታላቅ ጉባኤ መደረግና የመላው አፍሪካ አገሮች መሪዎች ተካፋይ በመሆን ለዚህች ክፍለ ዓለማችን በውስጧም ለሚገኙት ሕዝቦቻችን ላለን ጥልቅ አሳቢነት ዓይነተኛ ምስክር ነው፡፡ ባጭሩ ይህ ቀን ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን በመላ ታሪካዊና ታላቅ ቀን ነው…፡፡’’

ዕለታዊው የአዲስ ዘመን የወርኻ ግንቦት 15 ቀን 1955 ዓ.ም. ዕትሙ በፊት ለፊት ገጽ ላይ፣ ‘‘ሠላሳ የአፍሪካ መሪዎች በተገኙበት ጉባኤ በአፍሪካ አዳራሽ ተከፈተ፤ ግርማዊ ጃንሆይም የጉባኤው የክብር ሊቀመንበር እንዲሆኑ ተመረጡ፡፡’’ በሚል ዐቢይ ርዕስ ስር እንዲህ ይላል፡-

“ቁጥራቸው ከ250 ሚሊየን በላይ በሆኑ አፍሪካውያን እጅግ በጋለ ስሜት ይጠበቅ የነበረውና መላው ዓለም ሁኔታውን በቅርብ ይከታተለው የነበረው የ30ዎቹ የአፍሪካ ነጻ መንግሥታት መሪዎች ጉባዔ ግንቦት 14 ቀን ትናንት ከእኩለ ቀን በኋላ በአፍሪካ አዳራሽ ተከፍቷል፡፡ ጉባኤውን የከፈቱት ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጉባኤው ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የአንድ ደቂቃ የኅሊና ጸሎት እንዲደረግ አሳስበው ጸሎት ተደረገ፡፡’’ 

ቀጥሎም የሊቀመንበር ምርጫ እንዲደረግ አሳስበው የጊኒው ፕሬዚደንት ሴኩቱሬ የመጀመሪያውን ምርጫ እንዲያደርጉ ተጠየቁ፡፡ እርሳቸውም የኢትዮጵው ንጉሥ ኃ/ሥላሴ የጉባኤው ሊቀመንበር እንዲኾኑ ጠቆሙ፤ የፕሬዚደንት ሴኩቱሬ ሐሳብ በጉባኤው አባሎች በሙሉ በመደገፉ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ የአፍሪካ አንድነት ደርጅት የመጀመሪያው ፕሬዚደንት ኾነው ተመረጡ፡፡ ከዚህ በኋላ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ለዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ሥራ ታላቅ መመሪያ የሚሰጥ የሚከተለውን ንግግር አደረጉ፡፡

“ዛሬ የገጠመን ዕድል በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ መቼም ያልተገኘ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ በፊታችን የተደቀኑት ችግሮች ያንኑ ያህል ከፍ ያሉና ከባድ ናቸው፡፡ ታሪክና ጊዜ የጣሉብን ከፍተኛ ኃላፊነት ሁላችንም ረጋ ብለን እንድናስብና እንድናመዛዝን ያስገድደናል፡፡ የተነሳንበትን ከፍተኛ ተግባር በመልካም አከናውነን ብንገኝ ስማችንና ተግባራችን በታሪክ መልካም ስም ይኖረዋል፡፡ ተግባራችንን ሳንፈጽም ብንቀር ግን ይታዘንብናል፡፡ ስለዚህ እምነታቸውን የጣሉብንን ሕዝቦቻችን በሚመጡት ጊዜያቶች ውስጥ ከእኛ የሚጠብቁትን ሁሉ ለመፈጸም እንዲያበቃን ሁሉን የሚችለውን ፈጣሪያችን ጥበብንና አስተዋይነትን እንዲሰጠን እናምነዋለን፣ እንለምንዋለንም፡፡’’

በወቅቱ በአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ የተገኙት የናይጄሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ታፌዋ ባሌዋ ለአፍሪካ አንድነት እውን መሆን ኢትዮጵያና ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ያደረጉትን ታላቅ አስተዋጽዖ ሲገልጹ ተከታዩን ብለው ነበር፤

“መላው የአፍሪካ መንግሥታት መሪዎችና የመንግሥታት ባለ ሥልጣኖች በአዲስ አበባ ላይ ሊገኙ ለመቻላቸው በግርማዊነትዎ ጥረት ስለሆነ በተለይ ለግርማዊነትዎ እጅግ ከፍ ያለ ክብር የሚያሰጥ ነው፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ አንድነት እንዲገኝ የምናደርገው ጥረት ወደፊት የኢትዮጵያን መናገሻ ከተማ የአዲስ አበባ ስም ደጋግሞ የሚያወሳ ስለሆነ የአዲሲቱ አፍሪካ ታሪክ የግርማዊነትዎን ስም በተቀዳሚው ገጹ ላይ አሳምሮ የሚያኖረው ለመሆኑ ጥርጥር የለበትም፡፡’’

የጊኒ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሴኮቱሬም በአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ለአፍሪካ አንድነት ምስረታ ኢትዮጵያ ያደረገችውን ታላቅ አስተዋጽዖ እንዲህ ገልጸውታል፡-

“… ኢትዮጵያዊ ታላቅ ሕዝብ ነው፡፡ ስለ አፍሪካ ነፃነት በጀግንነት የተዋጋ፣ ነፃነትም ቋሚ እንዲሆን፣ ሕዝቦቻችን ያለ ምንም የውጭ መንግሥታት ተቆጣጣሪነትና ጣልቃ ገብነት በተገቢ ሥልጣናቸው እየተመሩ የገዛ ራሳቸውን ዕድል እንዲመሩ ያላቸው ሥልጣን እንዲጠበቅላቸው የደከመ አፍሪካዊ ሕዝብ ነው፡፡ ይህ በንጉሡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ አስተባባሪነትና መሪነት፣ የአፍሪካውያኖች ጉባኤ የተደረገው በኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ስለሆነ፣ አዲስ አበባና ኢትዮጵያ አሁንም የበለጠ ከአፍሪካ ታሪክ ጋር የተሳሰሩ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት በአንድ አኅጉር ሕዝቦች ፈቃድ ተነሳስቶ በሚመራው የዕድገት ፍላጎትና ሥራ ሁሉ ሳይቋረጥ ስማቸው ተያይዞ የሚኖር ይሆናል…፡፡’’

ድርጅቱን በመመስረት ረገድ አፄ ኃይለ ሥላሴ የነበራቸውን ሚና አስመልከቶ፣ ኢንሳክሎፒዲያ ብሪታኒካ ስለ አፄ ኃ/ሥላሴ ባቀረበው አጠር ያለ ጽሑፍ ‘‘Haile Selassie played a very important role in the establishment of the Organization of African Unity in 1963’’ ብሏል፡፡

‘‘ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ቀኃሥ) የአአድ መሥራች እና አባቱም የሆኑለት ከድርጅቱ ዋናዎቹ አንቀሳቃሾች አንዱ እንደነበሩ የጋናው ዘጋኔያን ታይምስ በጁላይ 24፣ 1972 ዕትሙ የፊት ገጽ ላይ ጽፎአል፡፡

የናይጄሪያው ሳንዴይ ኦብዘርቨር ቀኃሥ 80ኛ ዓመታቸውን ባከበሩበት ሐምሌ 16 ቀን 1964 ዓ.ም. (ጁላይ 23፣ 1972) ባወጣው ዕትሙ ‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባት ኢትዮጵያዊው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› (Haile Selassie I of Ethiopia: Father of the O.A.U.) በሚል ርዕስ ስለግርማዊነታቸው ሰፊ ሐተታ አውጥቶ ነበር፡፡

እንደ ሰንዴይ ኦብዘርቨር አገላለጽ፣ ቀኃሥ ስለ አፍሪካ ያላቸው ውጥን እጅግ በጣም የተዋጣና የተቃና መሆኑን ጠቅሶ፣ አዲስ አበባ ‹‹የፓን አፍሪካን መዲና›› (የአፍሪካ አንድነት ከተማ) ለመባል የበቃችበትን ምክንያት አስታውሶ ነበር፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ኢትዮጵያ ስለአፍሪካ ሕዝብ የፖለቲካ ደኅንነት ላላት ተቆርቋሪነት ጉልህ ምልክት ነው፡፡ ድርጅቱ የተቋቋመውም በድንገት ከተፈጠረ ስሜት አልነበረም፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ በእርጋታና አንዳንድ ጊዜም በግላቸው የአፍሪካ አገሮች ገና ነፃነታቸውን ሳይጎናጸፉ የወደፊት መሪዎች ለሚሆኑት ሰዎች የትምህርትን ዕድል በመስጠት ረድተዋል፡፡ ግርማዊነታቸው በአፍሪካ አህጉር ያላቸው ተሰሚነት አገራቸው ከድንበሮቿ ውጭ ካላት ተሰሚነት የተገኘ ሳይሆን ንጉሠ ነገሥቱ ካተረፉት የመከበር ዕድል ነው፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም የአፍሪካ ኃይሎች ራሳቸውን ለመከላከል ይተባበሩ ዘንድ ግርማዊ ጃንሆይ ባላቸው እምነት መሠረት ፈቃዳቸውን ከግቡ ማድረሳቸው የሚያስደንቅ ነው፡፡ በዚህም መሠረት፣ በየትኛም የአህጉሩ ክፍል አምባጓሮ ቢነሳ ተገቢው ስምምነት እንዲፈጸም ግርማዊነታቸው ዓይነተኛ መድኅን ሆነዋል፡፡ በዚህም መሠረት የናይጄሪያ ችግር በተፈጠረበት ጊዜ የአስታራቂነት ዕርምጃ የወሰዱ ሲሆን ይህም ፍጻሜ እንዳገኘ በችግሩ ምክንያት አለመግባባት የተፈጠረባቸውን አፍሪካውያን መሪዎችን ፈጥነው ለማስማማት ችለዋል፡፡ ጃንሆይ ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ድርጅት ጋር በመተባበር የወጠኑት 16 ዓመታት የፈጀውን የሱዳንን ችግር በማስወገድ ታሪካዊ ስምምነት እንዲፈጸም አስችሏል፡፡

ግርማዊነታቸው ሴኔጋልና ጊኒ አለመግባባታቸውን ለማስወገድ በተስማሙበት ይኸውም በላይቤሪያ ዋና ከተማ በሞንሮቪያ ውስጥ በተደረገው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባ ሊቀ መንበር ሆነው መርተዋል፡፡ በዚህ መሠረት ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቀደም ሲል ጀምሮ የታሪክ ሥፍራቸውን መያዛቸው ጉልህ ነው፡፡

በውጩም ዓለም ቢሆን አፍሪካ ግንባራቸው ሳይታጠፍ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካና ከእስያ መሪዎች ጋር ለመቋቋም የሚችሉ ከፍተኛ መሪዎች ያላት መሆኑን ግርማዊ ጃንሆይ በሚገባ አስመስክረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ጋዜጦች በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ፣ ፈረንሣይኛና ጣሊያንኛ በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ልዩ ካቢኔ ፕሬስ ክፍል ከ1957 እስከ 1966 ዓ.ም. ይታተም የነበረው መጽሔት የቀኃሥን ተግባሮች መዘከሩ ይታወቃል፡፡ አንዱ የጠቀሰው ለንደን ታይምስ (The Times London) በጁላይ 22፣ 1972 (ሐምሌ 15 ቀን 1965 ዓ.ም.) ዕትሙ፣ ‹‹የንጉሠ ነገሥቱ ጽኑ ሥልጣን በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ታፋሪነትን አትርፎላቸዋል›› (Emperor’s firm authority earns respect among the Leaders of Africa) በሚል ርዕስ ሐተታውን አስፍሮ ነበር፡፡

በመጭረሻም፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ዋነኛ አላማው በቅኝ አገዛዝ ስር የነበሩ አገሮችን ነጻ ማውጣት ነበር፡፡ ድርጅቱ ሲመሰረት 32 ነጻ ሀገራት ብቻ የነበሩት፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በወቅቱ በቅኝ አገዛዝ ለሚማቅቁ አገሮች ተገቢውን ወታደራዊ ድጋፍና ስልጠና ሰጥቷል፡፡ የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረንስ /ANC/ አፓርታይድን እንዲዋጋና ZANU እና ZAPU የተባሉ የፖለተካ ድርጅቶች ዚምባብዌን ነጻ እንዲያወጡ ድርጅቱ መሳሪያና ወታደራዊ ስልጠና አበርክቷል፡፡

አፓርታይድን ለማውገዝ የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ በአህጉሪቱ እንዳይበር ማዕቀብ መጣሉና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን በማሳመን የተመድ አካል የሆነው የዓለም የጤና ድርጅት ከደቡብ አፍሪካ እንዲወጣ ማድረጉ ታሪክ ከመዘገባቸው የድርጅቱ ስኬቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ 

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በተመሰረተ በ39 ዓመቱ በ1994 ዓ.ም. ስሙን ለውጦ፣ ዛሬ 55ቱም የአፍሪካ አገራት አባል በሆኑበት የአፍሪካ ኅብረት ተተክቷል፡፡

 

 

Filed in: Amharic