“ወደ ሀገር መፍረስ ለመሸጋገር የሚቆረጥልን ቀጠሮና የሚተነበይልን ትንቢት የለም…!!!”
ሙሼ ሰሙ
ከመረጋጋት ወደ ግጭት፣ ከግጭት ወደ ጦርነትና መተላለቅ ቀጥሎም ወደ ሀገር መፍረስ ለመሸጋገር የሚቆረጥልን ቀጠሮና የሚተነበይልን ትንቢት የለም፤ የሚወስነን ሰላም፣ ልማትንና እድገትን ለማስፈን የሚያስፈልገው እውቀት፣ ችሎታና አስተዋይነትም አይደለም። የሚያስፈልጉን ተራ ጨለምተኝነት፣ ጭፍን ጥላቻ፣ ጨካኝነት፣ ግራና ቀኙን አላይም፣ አልሰማምና አላስተውልም የሚል ግትርነት ብቻ ናቸው። እነሱ ደግሞ በገፍ እንዳሉን በተግባር እያየን ነው።
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በሰበብ አስባቡ፣ በየፈርጁና በየረድፉ እየተደራጁ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ዜጎችን መግደል፣ በገፍ ማጋዝና ማፈናቀል፣ እርስ በርስ ማጋጨት፣ የሃይማኖት ተቋማትን ማቃጠል፣ ሴቶችን መድፈር፣ ሕጻናትንና አረጋውያንን ማረድ፣ ሕዝብን በጅምላ ማዋረድና ማንኳሰስን ያካተተ የእርስ በርስ ግጭትና አስከፊ ጦርነት አስተናግደናል።
ከተሞክሮ እንደምንረዳው ለመጨረሻው መጀመርያ እንዲሆነን የቀረን አንዱና አስፈሪ አጀንዳ ቢኖር የሀይማኖት ጦርነት ይመስለኛል። ለዚህም “የለውጡ ሐዋርያትን” “ተመስገን” እንበል መሰለኝ እስከዛሬ በተዓምር የዘለለን “የሀይማኖት ጦርነት” ከወዲሁ ልብ እስካልገዛን ደረስ ወደፊት የማይቀርልን አሰፈሪ እዳ እንደሆነ ፍንጮች እያየን ነው።
በጣት በሚቆጠሩ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከዓለም ሁሉ እጅግ አስከፊ የሆነውን ጦርነት፣ ማፈናቀል፣ ስደትና ማጋዝን አከናውነን “እጃችንን አጨብጭበን በመቅረት ወጤታችን ስለ ሰመረ” በረሃብተኛ መጠሪያችን ላይ “ጭካኔና ግፈኝነት” ታክሎበት ተጨማሪ እውቅና አግኝተን በዓለም አቀፍ የቋንቋ ስርዓት ውስጥ እንደ አዲስ ተመዝግበናል።
ይህ ማለት ትርጉሙ ሌላ አይደለም “ለመከራ የጻፈን ሕዝብ ስለሆንን ” ማፍራት የቻልነው የልማት፣ የሰላምና የእድገት ኋይል ሳይሆን በጭፍን ሴራ ታግዘው ግጭት፣ ጦርነት፣ ሁከት፣ ስደትና ማፈናቀልን ጠንስሰው መጋት የተካኑ ሰዎችን በገፍ እያመረትን ለኋላፊነት እያበቃን መሆኑን ብቻ ነው።
በዚህ ሰሜንኛ ተረት እንለያይ
አንዱ አርሶ አደር ለሌለው
“እንወራረድ ሞኝ ይረታል” ሲለው
“ምን ብሎ” ቢለው
“እምቢ አልሰማም አላይም ብሎ” አለው ይባላል።