>

እነሆ ጀግና!   (አቻምየለህ ታምሩ)

እነሆ ጀግና!  

አቻምየለህ ታምሩ

 

*….. “እኔ እናንተን የምወጋው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጠላት ስለሆናችሁ ሳይሆን የእናት አገሬ የኢትዮጵያ ጠላት ስለሆናችሁ ነው፤ ስለሆነም አገሬ ከግፍ ቀንበራችሁ ተላቅቃ ነጻ እስክትወጣ እከራከራችኋለሁ፤ ክንዴን እስክንተራስ ድረስም የጣሊያንን ወታደር መግደል አላቆምም፤ ያገሬ ልጅ ሁሉ መሳሪያውን ታጥቆ የጣሊያንን ወታደሮች እያደነ እንዲገድል በልቤ አስባለሁ።
*..…  “ሰው የሚጸድቀው፡ መንግሥተ ሰማይ የሚወርሰው ለአገሩ ሲሞት ነው”   
ደጃዝማች ዮሐንስ ብሒል  
የአባቶቻችን ኢትዮጵያ ከራሳቸው በላይ ለሆነ አላማ የኖሩ፣ ራሳቸውን ከነሱ በላይ ለሆነ አላማ የሰጡ፣ ከአንድ ግለሰብና ከአንድ ትውልድ በላይ በላይ ለሆነ አላማ ራሳቸውን ያስገዙ አገር ወዳድ ልጆች ነበሯት። ከራሳቸው በላይ ለሆነ አላማ ቆመው፣ ራሳቸውን ድልድይ አድርገው ክፉውን ዘመን ያሻገሩና የተረከቧትን የአባቶቻቸውን አገር ከነሙሉ ክብሯ ለቀጣዩ ትውልድ ካስረከቡ የኢትዮጵያ የምንጊዜም ጀግኖች መካከል ስመጥሩ አርበኛ ደጃዝማች ዮሐንስ ኢያሱ ሚካኤል አንዱ ናቸው።
ታላቁ ጸረ ፋሽስት አርበኛ ደጃዝማች ዮሐንስ ኢያሱ ከአባታቸው ከልጅ ኢያሱ ሚካኤልና ከእናታቸው ከወይዘሮ ወርቅነሽ ጎሹ በመናገሻ ከተማ በ1906 ዓ.ም. የተወለዱ ሲሆን ከመስከረም 24 ቀን 1928 ዓ.ም. እስከ ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ድረስ ያደረጉትን ጸረ ፋሽስት ተጋድሎ የጀመሩት የ22 ዓመት ወጣት ሳሉ ነበር። የደጃዝማች ዮሐንስ ኢያሱ አባት ልጅ ኢያሱ ሚካኤል የሸዋና የወሎ ተወላጅ ሲሆኑ እናታቸው ወይዘሮ ወርቅነሽ ጎሹ ደግሞ የጎጃምና በጌምድር ተወላጅ ናቸው።
ፋሽስት ጣሊያን አገራችንን በወረረበት ወቅት ሕዝቡ በአንድነት መተማመን ፈጥሮ በጋራ ጠላቱ ላይ መክሮ እንዳይነሳ ከተጠቀመባቸው የከፋፍለህ ግዛ ቄሳራዊ ዘዴዎች መካከል በየአካባቢው የተፈጠሩ ቁርሾዎችን ማስፋትና መለጠጥ ነበር። ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያን አቤቱታ በወቅቱ ለነበረው የተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ለማሰማት ወደ ጄኔቭ ማቅናታቸውን ተከትሎ ፋሽስት ጣሊያን የኢትዮጵያውያንን ልብ ለመግዛት ከተከተላቸው ስልቶች አንዱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተቀናቃኝ የሚላቸውን የነጋሲ ተወላጆች በስልጣን እየደለለ የፋሽስትን ቅኝ ገዢነት እንዲያውቁና ንጉሠ ነገሥት እንዲሆኑ ማግባባት ነበር።
ለዚህ የፋሽስት ቄሳራዊ ሴራ ከታሰቡና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ላይ ቁርሾ ስላላቸው ልጠቀምባቸው እችላለሁ ብሎ ፋሽስት ካጫቸው የነጋሲ ተወላጆች መካከል የልጅ ኢያሱ ልጅ የሆኑት ልጅ ዮሐንስ ኢያሱ [በኋላ ደጃዝማች] ቀዳሚው ነበሩ። አዲስ አበባ በፋሽስት እጅ ከወደቀች በኋላ በጎጃምና በበጌምድር በአርበኝነት መንቀሳቀስ ለጀመሩት ልጅ ዮሐንስ ኢያሱ ፋሽስት ጣሊያን በባንዶቹ በኩል የሚከተለውን መልዕክት ላከባቸው፤
——-
 የኢትዮጵያ ግዛት ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ 
      አዲስ አበባ ፳፮ ቀን ግንቦት ፲፱፻፳፱ ዓ.ም
ይድረስ ከልጅ ዮሐንስ ኢያሱ
ለጤናህ እንደምን ሰልብተሀል? እኔ ደኅና ነኝ።
እንደምታውቀው ታላቁ የኢጣሊያ መንግሥት ጠላትን የሆነውን ኃይለ ሥላሴን በጦር ኃይል ከዙፋኑ አውርዶ ኢትዮጵያ የኢጣልያ ንጉሥ የግርማዊ  ቪክቶር ኢማኑኤል ፫ተኛን የበላይነት እንድትቀበል ቸርነት አድርጓል።
አሁን ዘውዱ ፈት በመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ሆነ በኢትዮጵያ ውጭ የተገባው ገዢ ከቢክቶር ኢማኑኤል ፫ተኛ የኢጣልያ ንጉሥ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በስቀር ሌላ ሹም ወይም ገዥ እንዳትቀበል ፈርመህ በግርማዊነታቸው መንግሥት ውስጥ የአባትህን ዘውድ በመድፋት በዙፋኑ ላይ ትቀመጥ ዘንድ  የግርማዊ  ቪክቶር ኢማኑኤል ፫ተኛ መልካም ፈቃዳቸው ሆኗል።
ግርማዊነታቸው ይህን ቸርነት ማድረጋቸው ላንተ ጥቅም በመሆኑ ሹማምንቶችና ሕዝቡን አስከትለህ በመግባት በፋሺስት መንግሥት ትእዛዝ በኢትዮጵያ የተደረገው አዲስ ሕግ በሞላው እንዲፈጸም እንድታደርግ ተስፋ አለኝ።
ጠቅላይ ገዢው
የኢትዮጵያ የንጉሥ እንደራሴ
ሮዶልፎ ግራሲያኒ
——-
ለዚህ የፋሽስት ጣሊያን መደለያ የ23 ዓመቱ ወጣት ታላቁ ልጅ ዮሐንስ ኢያሱ የሰጡት መልስ ፋሽስቶችን ያሳፈረ፣ ቆሽታቸውን ያሳረረ፣ ጨጓራቸውን ያቃጠለ፣ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ከወርቅ ካባ የበለጠ የክብር መጎናጸፊያ፣ ለዘመናት ሲፈተን የኖረና በክብርም ቆሞ ግፈኛውን ፋሽስት ያሳፈረ የጀግንነት መገለጫ ነበር። ያ ሁሉ ራስና ልዑል የአገሩንና የሕዝቡን ክብር በሰባራ ሊሬ ሸጦ የፋሽስት አተላ ተሸካሚ ሲሆን አንዱ ፍሬ ልጅ ደጃዝማች ዮሐንስ ኢያሱ ግን የአገራቸውና የሕዝባቸውን ክብር ለምቾት አልሸጡም ብለው “ዘውድ እንጫንልህ፤ በዙፋኑ ላይ እናስቀምጥህ” ላሏቸው ፋሽስቶች የሰጡት መልስ እንዲህ የሚል ነበር፤
“እኔ እናንተን የምወጋው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጠላት ስለሆናችሁ ሳይሆን የእናት አገሬ የኢትዮጵያ ጠላት ስለሆናችሁ ነው፤ ስለሆነም አገሬ ከግፍ ቀንበራችሁ ተላቅቃ ነጻ እስክትወጣ እከራከራችኋለሁ፤ ክንዴን እስክንተራስ ድረስም የጣሊያንን ወታደር መግደል አላቆምም፤ ያገሬ ልጅ ሁሉ መሳሪያውን ታጥቆ የጣሊያንን ወታደሮች እያደነ እንዲገድል በልቤ አስባለሁ።”
በዚህ አኳኋን ከራሳቸው በላይ ለሆነ ታላቅ አላማ የቆሙ መሆናቸውን ያስመሰከሩት ታላቁ ደጃዝማች ዮሐንስ ኢያሱ ቀሪውን የፋሽስት የወረራ ዘመናት በተጋድሎ ያሳለፉት የበጌምድር አርበኞችን በማስተባበር ነበር። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሲመለሱም ደብረ ማርቆስ ላይ ተገናኝተዋቸው አብረዋቸው ወደ አዲስ አበባ መጡ። አዲስ አበባ ከተማ ጥቂት አመታት እንደቆዩ ከደጃዝማች ታከለ ወልደ ሐዋርያት ጋር ንጉሡን ገድለው ስዒረ መንግሥት ለማድረግ ተንቀሳቅሰዋል ተብለው ስለተጠረጠሩ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ ድረስ ደመወዝ እየተቆረጠላቸው ጅማ ውስጥ በግዞት ኖሩ።
በጅማ ቆይታቸው በአርበኝነቱ ዘመን ከሚያውቋቸው ከጠቅላይ ግዛቱ ሁለት እንደራሴዎች ጋር ቅርብ ወዳጅነት ነበራቸው።  የሚያውቋቸው የሁለቱ አርበኞች የካፋ ጠይላይ ግዛት እንደራሴ መሆን የግዞት ሕይዎታቸውን ቀንበር አቅልሎላቸዋል።
የመጀመሪያው የግዞት ወዳጃቸው እንደተጋዙ የጠቅላይ ግዛቱ እንደራሴ የነበሩት ራስ መስፍን ሲሆኑ ሁለተኛው የግዞት ወዳጃቸው ደግሞ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የካፋ ጠቅላይ ግዛት የመጨረሻው እንደራሴ የነበሩት ሰማዕቱ ደጃዝማች ፀሐዩ እንቁ ሥላሴ ናቸው።
ደጃዝማች ዮሐንስ ኢያሱ እንደ አያታቸው ንጉሥ ሚካኤል ሁሉ የአገር ፍቅር ስሜታቸው በጣም ከፍተኛ የነበረና ስለ አገር ፍቅር የነበራቸውን አስተሳሰብ አገር ወዳድ ሁሉ ቋሚ መርሁ ሊያደርገው የሚገባ ነው። ጅማ በግዞት ሳሉ የወለዷቸው ባሁኑ ወቅት ካናዳ የሚኖሩት ልጃቸው አባታቸው ደጃዝማች ዮሐንስ በግዞት ተወስነው ያሳድጓቸው በነበረበት ወቅት አንድ ሰው አገሩን እስከምን ድረስ መውደድ እንዳለበት ይነግሯቸው የነበረው ምክር ዘመን የማይሽረው ታላቅ ፍልስፍና ነው።
ደጃዝማች ዮሐንስ ኢያሱ ልጃቸውን ሲያሳድጉ ስለ አገር ፍቅር ያስተማሯቸው የነበርው “ሰው የሚጸድቀው፡ መንግሥተ ሰማይ የሚወርሰው ለአገሩ ሲሞት ነው” እያሉ ነበር። ይህ የደጃዝማች ዮሐንስ የአገር መውደድ ፍልስፍና ከእኔነት በላይ የገዘፈ፣ የጀግንነታቸው ምልክት ከሆነው ከኢትዮጵያዊነት ጋር የተገመደና በልባቸው ያረፈ የፍቅረ-ኢትዮጵያ ረቂቅ ማኅተም ነው። “ሰው የሚጸድቀው፡ መንግሥተ ሰማይ የሚወርሰው ለአገሩ ሲሞት ነው” የሚለው  የደጃዝማች ዮሐንስ ብሒል ራሳቸው የኖሩት ሕይዎት ነው።
ደርግ ወደ ሥልጣን እንደመጣ ከግዞት የተለቀቁት ደጃዝማች ዮሐንስ ኢያሱ በንጉሡ ዘመን የተፈቀደላቸውን ደምወዝ እያገኙ ከአያታቸው ከንጉሥ ሚካዔል በደረሳቸውን ቤት ውስጥ    አዲስ አበባ ውስጥ ይኖሩ ነበር። በዚህ ሁኔታ የተወሰነ እንደቆዩ ደርጎቹ ወደ ቤታቸው ሄደው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን እንደ ተራውና ተርታው በቴሌቭዥንና በሬድዮ እየቀረቡ ያወግዙ ዘንድ ጠየቋቸው።
ሚዛኑ ደጃዝማች ዮሐንስም ግን “ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተሻላችሁ መሆናችሁን በስራ ሳታሳዩ ንጉሡ ስላሰሩኝ ብዬ  እናንተን ደርጎችን  ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተሻላችሁ ናችሁ ብዬ ምስክርነት ልሰጥ ከቶ አይቻለኝም” ሲሉ አቋማቸውን አሳወቁ። በዚህ የተናደዱት ደርጎችም እንዲያወግዙላቸው የፈለጓቸው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ይቆርጡላቸው የነበረውን ደምወዝ አግደውና ከአያታቸው በውርስ ያገኙትን ቤት ቀምተው ሜዳ ላይ ጣሏቸው። በዚህ ሁኔታ ሀብታቸው በደርጎች የተወረሰባቸው ደጃዝማች ዮሐንስ ከቀደመው በከፋ ሲቸገሩ ቆይተው ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ጥር 19 ቀን 1969 ዓ.ም. በ63 ዓመታቸው ከዚህ በሞት ተለዩ።
እንዲህ አይነት ጀግንነት፣ የአገር መውደድ፣ ስብዕናና የሞራል ልዕልና የነበራቸው ደጃዝማች ዮሐንስ ኢያሱ ለእናት አገራቸው ቀድመው የደረሱ፣ አንተ በመባያ የልጅ እድሜያቸው አንቱ የሚያሰኝ ድንቅ ስራ የሰሩ፤ ላገራቸው ሩቅ አሳቢ ሆነው የወጣትነት ትኩረታቸው ብዙ ዘመን እንደተጠራቀመ የሽምግልና ምክር ለዘመናት የሚያስተጋባ ተግባር የነበራቸው ታሪካቸው ግን ያልተነገረላቸው፤ ከራሱ በላይ ለሆነ አላማ የኖረ፣ ራሱን ከነሱ በላይ ለሆነ አላማ የሰጠ፣ ከአንድ ግለሰብና ከአንድ ትውልድ በላይ  በላይ ለሆነ አላማ ራሱን ያስገዛ አገር ወዳድ አምጡ ድገሙ ቢባል ወደረኛ የሌላቸው የኢትዮጵያ የስለት ልጅ ነበሩ።
ክብር ለታላቁ የኢትዮጵያ ጀግና አርበኛ ለደጃዝማች ዮሐንስ ኢያሱ ይሁን! 
ከታች የታተሙት የደጃዝማች ዮሐንስ ኢያሱ ታሪካዊ ፎቶዎች ናቸው! በጋራ በተነሱት ፎቶ ላይ  የሚታዩት ሰዎች የሚከተሉት ናቸው። በስተቀኝ በኩል የሚታዩት የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የካፋ ጠቅላይ ግዛት የመጨረሻው እንደራሴ ታላቁ አርበኛ ደጃዝማች ፀሐዩ እንቁ ሥላሴ ናቸው።  ከደጃዝማች ፀሐዩ እንቁ ሥላሴ በስተቀኝ ጠቆር ያለ ሱፍ ለብሰው የሚታዩት ደግሞ ግዞተኛው ደጃዝማች ዮሐንስ እያሱ ናቸው። ከደጃዝማች ዮሐንስ በስተቀኝ የተቀመጡት ባለጉርድ ሸሚዝ  በወቅቱ የጠቅላይ ግዛቱ ፖሊስ አዛዥ የነበሩት የኤርትራ ጠቅላይ ግዛት ተወላጁ ጄኔራል በረከት ገብረ መድኅን ናቸው። ከጄኔራል በረከት ቀጥለው ፊታቸውን ዞረው የተቀመጡት የደጃዝማች ፀሐዩ ወንድም አርበኛው ደጃዝማች ወርቁ እንቁሥላሴ ናቸው።
Filed in: Amharic