>

የአማራ ህዝብ ትግል ዳራ እና የትግል አቅጣጫዎች (የመነሻ ሃሳብ, ባለ 63 ገጽ ሰነድ)  በመምህርት መስከረም አበራ የተዘጋጀ !

የአማራ ህዝብ ትግል ዳራ እና የትግል አቅጣጫዎች (የመነሻ ሃሳብ, ባለ 63 ገጽ ሰነድ) 
በመምህርት መስከረም አበራ የተዘጋጀ !
             የካቲት 2014
ይዘት
1. መግቢያ
2. የሰነዱ አስፈላጊነት
3. የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ አብዮተኞች ዕይታ- ከትናንት እስከ ዛሬ
4. ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝት፣የዘውግ ብሄርተኝነት እና የአማራ ህዝብ መስተጋብር
5. የዘውግ ፖለቲካ ከ1983-2010ዓም በአማራ ህዝብ ላይ ያደረሰው ጉዳትና የጋረጠው ፈተና
6. በድህረ-ህወሃት የአማራ ህዝብ የገጠሙት ፈተናዎች
7. የአማራን ህዝብ ጥያቄ በኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ ፓርቲዎች ማዕቀፍ ውስጥ መመለስ ያልተቻለው ለምንድን ነው?
8. የአማራ ንቅናቄ አስፈላጊነት እና ተፈጥሮ
9. የአማራ ንቅናቄ ትግል ውስንነቶች
10. የአማራ ንቅናቄ ሃይሎች በትግል ጉዟቸው ከግንዛቤ ሊያስቧቸው የሚገቧቸው አንኳር ጉዳዮች
11. የአማራ ህዝብ ያለበት ወቅታዊ ሁኔታ
12. የአማራ ህዝብ ዋነኛ ጥያቄዎችና የመደራደሪያ ነጥቦች
13. በብሄራዊ የምክክር መድረኩ የአማራ ህዝብ በማን ይወከል?
14. በምክክር መድረኩ የአማራ ተደራዳሪዎች ሊገጥማቸው የሚችሉ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች
15. ብሄራዊ ምክክር ለአማራ ህዝብ ሊያመጣው የሚችለው ፋይዳ
16. የአማራ ንቅናቄ የወደፊት ትግል እንዴት መቃኘት አለበት?
17. መደምደሚያ
1. መግቢያ
የአማራ ህዝብ1 ከኢትዮጵያ የሃገረ-መንግስትነት ታሪክ ጋር ጥብቅ የስነ-ልቦና ቁርኝት ያለው ህዝብ ነው፡፡ በመሆኑም ለምዕተ-ዓመታት ከአማራ ማንነቱ ይልቅ በኢትዮጵያዊ ማንነቱ ላይ ትኩረት ያደረገ የፖለቲካ ተሳትፎ ሲያራምድ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ባለፈችበት የታሪክ ምዕራፎች ሁሉ ልዩ ተጠቃሚነት ያለው ህዝብ ነበር ማለት አይደለም፡፡ ይልቅስ በሃገሪቱ የተነሱ አገዛዞች በሌሎች የሃገሪቱ ህዝቦች ላይ ያደርሱት የነበሩት በደልና ጫና ሁሉ በአማራ ህዝብ ላይም ደርሷል፡፡ በመሆኑም ሌሎቹ የሃገሪቱ ህዝቦችና የአካባቢ መሪዎች የተበደሉ ሲመስላቸው በነገስታቱ ላይ ያካሂዱ የነበረው አመፅ አሁን የአማራ ክልል በተባለው ህዝብና በአካባቢው ባላባቶችም ሲደረግ የኖረ ነው፡፡
የአማራ ህዝብ ነገስታቱ ያደርሱብኛል ያለውን የአስተዳደር ግድፈት፣ ብዝበዛ እና በደል በህዝባዊ ግጥሞቹና የተለያዩ ስነ-ቃላዊ ተግባቦቶቹ ሲገልፅ ኖሯል፡፡ በደሉ ከፍ ያለ ሲመስለውም ነገስታቱን የሚቃወም ግልፅ ዓመፅ ሲያካሂድ ነበር፡፡ ለዚህ ቀዳሚው ተጠቃሽ እማኝ የጎጃም ገበሬዎች አማፅ ነው፡፡ ይህ አመፅ በሃገራችን የተለያዩ ቦታዎች ከተደረጉ አመፆች አንዱ ነው፡፡ በባሌ፣ በጌዲኦ፣ በትግራይ ከተደረጉ አመፆች እኩል በጎጃምም የገበሬዎች አመፅ ተካሂዷል፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው ዛሬ በበርካታ አማራ ጠል የዘውግ ብሄርተኞች እንደሚታሰበው የነገስታቱ ስርዓት ለአማራው ህዝብ የተለየ ምቹ ፖሊሲ እንዳልነበረው ነው፡፡
ከገበሬው አመፅ በተጨማሪም በሌሎች የሃገራችን ክፍሎች እንደ ካዎ ጦና ያሉ የአካባቢ ባላባቶች በንጉሰ ነገስቶች አስተዳደር ላይ ያምፁ እንደነበረው ሁሉ በአሁኑ ወቅት የአማራ ክልል ተብሎ በተከለለው አካባቢ የነበሩ ባላባቶችም ያመፁ ነበር፡፡ ለምሳሌ በማይጨው ጦርነት በርካቶቹ የጎጃም፣ የወሎ እና የየጁ መኳንንት ንጉሰ ነገስቱን በመቃወም በጦርነት እንዲሳተፉ የቀረበላቸውን ጥሪ እስከ መግፋት ደርሰው ነበር፡፡ በተመሳሳይ በዛሬው የአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችን ይመሩ የነበሩ ራስ፣ ደጃዝማቾች በአንድ የአማራ ማንነታቸው ህብረት ፈጥረው ሌሎችን የሚወጉ ሳይሆኑ እርስ በእርሳቸው የማያባራ ደም መፋሰስ ያስከተለ ውጊያ የሚያደርጉ ነበሩ፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በሸዋው ንጉስ ምኒልክና በጎጃሙ ራስ ተክለሃይማኖት መካከል የተደረገው በደም አፋሳሽነቱ ወደር የሌለው የኢምባቦ ጦርነት ነው፡፡

(የመነሻ ሃሳብ, ባለ 63 ገጽ ሰነድ) /የአማራ_ህዝብ_ትግል_ዳራ_እና_የትግል_አቅጣጫዎች 

Filed in: Amharic