>
5:26 pm - Sunday September 15, 0824

ዝክረ የካቲት 12: ጀግናው  የታክሲ  ሹፌር  ስምኦን  አደፍርስ  /ከ1905-1929/ ማነው ? (ጥበቡ በለጠ)

ዝክረ የካቲት 12 ሰማዕታት

ጀግናው  የታክሲ  ሹፌር  ስምኦን  አደፍርስ  /ከ1905-1929/ ማነው ?

ጥበቡ በለጠ


 በእጅጉ አስገራሚ  ታሪክ ነው። አስገራሚ ያልኩት በብዙ ምክንያት ነው። አንደኛው ኢትዮጵያ ውስጥ የታክሲ ስራ መቼ ተጀመረ ብለን ብንጠይቅ በ1920ዎቹ ነው የሚል መልስ እናገኛለን። በ1928 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ስምንት ታክሲዎች ብቻ ነበሩ። ከነዚህ የስምንቱ ታክሲዎች አንደኛው ባለቤት ስምኦን አደፍርስ ይባላል። የያኔው ዘመናዊ ሰው። መኪና ሲነዳ እንደ ብርቅ እና ተአምር የሚታይ ነበር። ከተለያዩ የታሪክ መዛግብት ያገኘሁትን የዚህን ጀግና ኢትዮጵያዊ ታሪክ እንኮምኩመው፡፡
ስምኦን አደፍርስ፣ አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ግራዚያኒ ላይ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ቦምብ ሲወረውሩ የተባበራቸው ጀግና ነው። በታክሲው ይዟቸው መጭ ያለ ልበ ደፋር ሰው ነው። በኢትዮጵያ የታሪክ አለም ውስጥ ስለ እሱ ብዙ አልተባለለትም።
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ስለዚሁ ስምኦን ስለሚባለው አስገራሚ ኢትዮጵያዊ ሰፋ አድርገው ከጻፉ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።
ስምኦን ከአባቱ ከአቶ አደፍርስ አድጎ አይቸውና ከእናቱ ከወ/ሮ ሙሉ ብርሃን መሸሻ በሐረርጌ ክፍለ ሀገር በሐብሮ አውራጃ በአንጫር ወረዳ ልዩ ስሙ ጉባ ላፈቶ በሚባለው ሥፍራ በ1905 ዓ.ም ተወለደ። እድሜው ለትምህርት ሲደርስ በመጀመሪያ እዚያው ላፍቶ በሚገኘው የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ደብር ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በሕፃንነቱ በመምጣት በልደታ ማርያም ካቴድራልና በአሊያንስ ፍራንሴዝ ትምህርቱን በሚገባ አጠናቀቀ። ከዚያም በታክሲ ነጂነት ወደ ግል ሥራ ተሠማርቶ ይኖር ነበር።
ፋሽስት ኢጣሊያም ከጥንት የተመኘቻትን ኢትዮጵያ በ1928 ዓ.ም ወረረች። አዲስ አበባንም በቁጥጥሯ ሥር አድርጋ የግፍ አገዛዟን መዘርጋትና ማጠናከር ጀመረች። ስምኦን የእናት አገሩ መደፈርና በነጮች ሥር የቅኝ ተገዥ መሆን የሆድ ውስጥ ቁስል ሆኖበት ያዝን ነበር። ዘመዶቹና ወገኖቹ በየዱሩ ተበተኑ። ሌሎቹም ተሰደዱ። በተለይ ወንድሞቹ ደበበና አጐናፍር አደፍርስ በመጀመሪያ ጅቡቲ ቀጥሎም ኬንያ ተሰድደው የአርበኝነት ሥራቸውን ከውጭ አፋፋሙ። ስምኦን ወደ ስደት ውጣ ቢባልም መሰደድን አልመረጠም። ምርጫው አዲስ አበባ ውስጥ ተቀምጦ የውስጥ አርበኛ በመሆን ጠላቱን ፋታ ማሳጣትና ለአገሩ ነፃነት መዋጋት ነበር። ወንድሙ አጐናፍር አደፍርስ ከጅቡቲ በተጨማሪ ሌላ መኪና ልኮለት በሁለት ኦፔል መኪናዎች የታክሲ ሥራውን ቀጠለ። በነገራችን ላይ በዚያን ወቅት በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ውስጥ ወደ 8 የሚሆኑ ታክሲዎች ነበሩ። ማቆሚያቸው ጊዮርጊስ ሆኖ ከዚያ በመነሣት ወደ ለገሐር ወደ ገፈርሳና ወደ ግቢ እንዲሁም ወደ ሌላ አቅጣጫ እየተጓዙ ይሠሩ ነበር። በታክሲ ከ1 እስከ 5 ጠገራ ብር ከፍሎ የተሳፈረ ሰው ኩራቱ ሌላ ነበር።
ጠላት በማይጨው ጊዜዊ ድል አግኝቶ አዲሰ አበባ ሲገባ ስምኦን ገና ወጣት ነበር። ብቻውንም ይኖር ነበር። ጣሊያንንም በጣም ስለሚጠላ ለአገሩም በጣም ተቆርቋሪና ታማኝ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ስላወቁ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ባልንጀራቸው እንዲሆን ፈለጉት። ብዙም ከተቀራረቡ በኋላ የሆዳቸውን ምሥጢር ገለፁለት ። እሱም አሳባቸውን አሳቡ በማድረግ አብረው 3ቱም እቅድ ያወጡ ጀመር። በመጀመሪያ ለማንም ሳይናገሩ በመኪናው ሆነው ወደ ዝቋላ ሔዱ። እዚያም ለ15 ቀናት ያህል ተቀምጠው በግራዚያኒ ላይ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወስዱና ከወሰዱም በኋላ ምን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲያወጡና ሲያወርዱ ከረሙ። በተለይም የቦምብ መጣል ልምምድ ሲያደርጉ ሰነበቱ። የቦምብ ቁልፍ አፈታትና አወራወርን ያጠኑት ዝቋላ ነበር። ያስተማራቸውም የደጃዝማች ፍቅረ ማርያም መትረየስ ተኳሽ የነበረ ሰው ነው።
ከ15 ቀናት በኋላ ሲመለስ መልኩ ጠቋቁሮ ስላዩት ዘመዶቹ የት ነበርክ ብለው ጥያቄ ሲያበዙበት ሽርሽር ሔጄ ነበር አላቸው። ብዙም ሳይቆዩ የካቲት 12 ቀን 1929 ደረሰ። የአዲስ አበባ ሕዝብ ቤተ መንግሥት እንዲገኝ ታዘዘ። ግቢው ዙሪያውን መትረየስ ተጠምዶበት ይጠበቅ ነበር። ግራዚያንም ለድሆች ምፅዋት እሰጣለሁ ስላለ ብዙ ሰው ወደ ግቢው አመራ። አብርሃና ሞገስም መኪናህን ቤንዚን ሞልተህ ያው እንደተባባልነው መኪናዋን አዙረህ ፊት በር በደንብ ጠብቀን ብለው ስምኦንን ቀጠሩት። እነርሱ አስተርጓሚዎች ስለነበሩ ግቢ ገቡ። ስምኦንም መኪናዋን አዘጋጅቶ በተባባሉበት ቦታ ይጠብቃቸው ነበር።
ወደ 5 ሰዓት ገደማ ግራዚያኑ ሕዝብ ሰብስቦ ይደነፋል። የአርበኞቻችንን ስም እየጠራ ያንኳስሳል። የሁሉንም አንገት ቆርጬ ሮማ እልካለሁ ይላል። እነአብርሃም ቦምብ ጣሉበት። እርሱንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ጀኔራሎቸ አቆሰሉ። የአውሮኘላን አብራሪዎች ጀኔራል ሞተ። ከዚያም በተፈጠረው ረብሻ መትረየስና ጠመንጃ ሲተኮስ እነርሱ በፊት በር በኩል ሹልክ ብለው ወጥተው በተዘጋጀችው የስምኦን መኪና ወደፍቼ ተነሥተው ሔዱ። ስምኦንም እነርሱን እዚያ አድርሶ ወደ አዲሰ አበባ ተመለሰ።
የካቲት 19 ቀን በሳምንቱ ጣሊያኖች በጥቆማ መጥተው ስምኦንና የቤት ሠራተኛውን ያዙ። ለብቻ አሠሯቸው። እንዲህ እንዲህ ያሉ ሰዎች ይመጡ ነበር ወይ እያሉ ሠራተኛውን ጠየቁት። እሱም ያየውን ሁሉ ነገራቸው። ፈትተው ለቀቁት። ሠራተኛው ባደረገው ጥቆማ ብዙ የስምኦን ጓደኞች ታደኑ። ታሥረውም ተገደሉ። የስምኦን ታናሽ ወንድም ሱራፌል አደፍርስም ሲታደን ከርሞ ሊያዝ ሲል ሌሊት አምልጦ በእግሩ ከአዲስ አበባ ወደትውልድ ስፍራው ወደ ሐረርጌ ተመለሰ።
ስምኦን የመጀመሪያው የጭካኔ ቅጣት ከደረሰበት በኋላ ደጃች ውቤ ሰፈር አጠገብ በነበረው ወህኒ ቤት አሠሩት። ምርመራው በጥብቅ ቀጠለ። በመግረፍ፣ ጠጉሩን በመንጨት፣ የጣቶቹን ጥፍሮች በመንቀል የሥቃይ ውርጅብኝ ቢያወርዱበትም ስምኦን ከዓላማው ፍንክች አላለም። ሚሥጢር አላወጣም። አሠቃዮቹም ከእርሱ ምንም ማግኘት ስላልተቻላቸው ሚያዝያ 29 ቀን 1929 ገደሉት።
ዘመዶቹም ሳያውቁ ሥንቅ ለማቀበል ሲሔዱ አንድ ዘበኛ ስምኦን መሞቱን በ11 ሰዓትም 13 ሬሳ እንደሚቃጠልና የስምኦንም  ሬሳ ከእነርሱ ጋር እንደሚቃጠል ጨምሮ ነገራቸው። የስምኦንም እህት ወ/ሮ ሸዋረገድ አደፍርስ የእሥር ቤቱን ሐኪም ያውቁት ስለነበር ሐኪሙም ወርቅ ስለሚወድ አንድ ወቄት ወርቅ ከሰጡኝ ለማንም ሳያወሩ የስምኦንን ሬሳ እሰጥዎታለሁ አላቸው። ወርቅ ሰጥተው ሬሳውን በድብቅ ወስደው በጴጥሮስ ወጳውሎስ ካቴሊካዊት መካነ መቃብር ግንቦት 1 ቀን 1929 ቀበሩት። ስምኦን በደረሰበት ሥቃይ ሬሳው የሰው ገላ አይመስልም ነበር በማለት ከፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ጽሑፍ ጋር በሕይወት ያሉት እህቱ ወ/ሮ አሰገደች አደፍርስ በኃዘንና በእንባ ገልፀውታል።
ታዲያ የዚህ ወጣት ጀግና ታሪክ እንዴት እስከዛሬ ተዳፍኖ ቀረ? የአብርሀምና የሞገስ ስም ሲነሣ የሱ ለምን ተነጥሎ ቀረ? መቃብሩስ ምንም ዓይነት ምልክት ሳይደረግበት እስከዛሬ ሣር ብቻ ለብሶ የቀረው ለምንድነው የሚሉ ጥያቄዎች አንባብያንን ሳያሳስቡ አይቀሩም በማለት በ1977 ዓ.ም ተጠይቆ ነበር። መልሱ ግን እስካሁን አልተመለሰም።
ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ የወጣቱን አርበኛ የስምኦንን ንብረት ጣሊያኖችና ባንዳዎች ተከፋፈሉት። ጣሊያኖች ባንክ የነበረውን ገንዘብ ሲወስዱ ባንዳዎች ደግሞ ወንድሙ ከጅቡቲ ልኮለት ይሠራበት የነበረውንና የራሱንም ሁለት ኦፔል ታክሲዎች ተከፋፈሉ። በተለይም የንጉሱ እልፍኝ አስከልካይ የነበሩ ሰው እስከ ቅርብ ጊዜ የስምኦንን መኪና ይነዱ እንደነበረና የወጣቱ አርበኛ ስምም እንዳይነሣ ይከለክሉ እንደነበረ ብዙ ሰዎች ይናገራሉ በማለት እህቱ ከ40 አመታት በፊት ተናግረው ነበር።
በኢትዮጵያ የአርበኞች ትግል ፋሽስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን ለቅቃ ስትወጣ ኢትዮጵያ የተዋደቀችለትን ነፃነቷን አስከበረች። አርበኞች ልጆቿም ከየምሽጋቸው ወጡ። የወደቁላትንም ጀግኖች ልጆቿን ጀብዱም ለማውራት በቁ። ሆኖም ብዙ ባንዳዎች የነበሩ አስከፊና አፀያፊ የሆነው ለማውራት ሥራቸውን ለመደበቅና ለመሸፈን እንዲያውም እራሳቸውን አርበኞች አስመስለው ለመቅረብ ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያላስወሩት የሐሰት የጀብድ ወሬ የለም። እነዚህ የወገን ከሀዲዎች በግል ጥቅም የሰከሩ ስለነበሩ የዘረፉት እንዳይታወቅባቸው እንደስምኦን አደፍርስ ዓይነት ሐቀኛ የአርበኛና የትግል ሕይወት ተሸሽጎና ተቀብሮ እንዲኖር አድርገው ነበር። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ትግል እንደገና ነፃነቷን አስከብራ መኖር ስትጀምር እነዚያ የትናንት ባንዳዎች አርበኞች ተብለው የስምኦንን ታክሲዎች ወርሰው ሲነዱ መታየታቸው ነበር።
ምንጊዜም ቢሆን እውነት ተደብቃ አትቀርም። ወጣቱ ታጋይ ስምኦን አደፍርስ በተገደለበት ጊዜ ገና የ24 ዓመት ጐልማሳ ነበር። አላገባምም ነበር። ስለዚህ ለእናት አገሩ የዋለላትን ታላቅ ውለታ ማን ይንገርለት? ልጆች የሉትም። ዘመዶቹ ታግለው ደክመው የማይሆንላቸው ሲሆን ተውት።
ልጅ ባይኖረው፤ ዘመድም አቅም ቢያንሰው እናት አገሩ አልረሳችውም። አትረሳውምም። አሁንም ቢሆን ወደፊት አገራችን ኢትዮጵያ ተከብራና ታፍራ የምትኖረው እንደ ስምኦን አደፍርስ ዓይነት ባሉ ሐቀኛ ዜጎቿ እንጂ ባስመሳዮች አለመሆኑ እየተረጋገጠ ነው በማለት የወጣቱ ታክሲ ነጂ አርበኛ ቤተሰቦች ተናግረዋል።
የጽሁፍ ምንጮች 
1. አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሐምሌ 18 ቀን 1977 ዓ.ም “ምን ሠርተው ታወቁ” ? በተባለ አምድ ስር “ ስምዖን አደፍርስ /1905-1929/ አርበኛው ታክሲ ነጂ “ በሚል ርዕስ ታሪኩን አስፍሯል፡፡
2. በሪሳ ኢብሳ በ1977 ዓ.ም ስምዖን አደፍርስ /1905 -1929ዓ/ም በሚል ርእስ ታሪኩን በኦሮሚፋ አስፍሯል፡፡
3. በኢትዮጰያ ሬድዩ መጋቢት 25 ቀን 1978 ዓ.ም እንዲሁም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መጋቢት ወር 1978 ዓ.ም የታላቅ እህቱ የወ/ሮ አሰገደች አደፍርስን ቃል መጠይቅና ዘገባ ተላልፉል፡፡
4. Addis Tribune February, 27/2004/ Who was the third man? በሚል ርዕስ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፖንክረስት ስለ ስምዖን አደፍርስ ሚና የሰጡትን ምስክርነት አስፍሯል፡፡
5. Ian CampbelI, A Reconstruction of the Attempted Assassination of Rudolfo Graziani, Institute of Ethiopian Studies , Bulletin No , 35-40, 2003-2004 እትም ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ጥናት ምርምር ኢንስቲቲዩት ብሎቱን ላይ ስለ ስምኦን አደፍርስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርቧል፡
6. Ian Campbell, The plot to kill Grazianie, The Attempted Assassination of Mussolini’s Viceroy, Addis Ababa University press , 2010.
7. Ian Campbell The Massacre of DebreLibanos, Ethiopia 1937,Addis Abeba University Press 2014.
8. Ian Campbell, The Addis Abeba Massacre, Italy’s National Shame, Hurst and company, London 2017.
© Tibebu Belete
Filed in: Amharic