>

እውነታና እርቅ ማፈላለግ ፣ብሔራዊ ውይይት ለሽግግር በኢትዮጵያ (ደረጀ መላኩ - የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

እውነታና እርቅ ማፈላለግ ፣ብሔራዊ ውይይት ለሽግግር በኢትዮጵያ

 

ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com


ነጻነትና ዴሞክራሲ በሰፈነባት ሀገር ውስጥ ብሔራዊ  ውይይት ገቢራዊ የሚሆነው ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እውን በማድረግ፣ በተመረጡ እና ገለልተኛ በሆኑ ተወካዮች እንዲሁም በመገናኛ ብዙሃን አመሃኝነት እና ሃላፊነታቸውን በብቃት የሚወጡ እንዲሁም የህብረተሰቡን ጥያቄዎች የሚመልሱ መሪዎች መኖር አለባቸው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እንዲህ አይነት ነጻነት በሌለባቸው ሀገራት  ብሔራዊ የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት ልዩ የብሔራዊ የውይይት መድረክ መዘጋጀት አለበት፡፡ በነገራችን ላይ ነጻነት በሌለበት ሀገር የሚደረግ ብሔራዊ ውይይት የመንግስትን ስልጣን አደጋ ላይ የሚጥል ከመሆኑ ባሻግር ሀገሪቱን ወደ ደም መፋሰስ የሚወስዱ ውጣዊ ግጭቶችን የሚያባብስ ይሆናል፡፡ ለአብነት ያህል በየመን ተጀምሮ የነበረው የብሔራዊ ውይይት መድርክ ጅምሩ ሰናይ የነበረ ቢሆንም መጨረሻው አላማረም ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዛች ሀገር ላይ ነጻነት ያልሰፈነ በመሆኑ ነበር፡፡ የስልጣን ጥመኞች፣ጎሰኞች እና የሃይማኖት ጽፍ ፣ መሪዎች ከተለያዩ የአለም ሀገራት ( በተለይም ከምእራቡ አለምና በፔትሮል ዶላር በሰከሩ እንደ ሳኡዲአረቢያን በመሰሉ በሚዘንብላቸው ዶላር እና የጦር መሳሪያ እርዳታ በመታገዝ ሀገራቸውን የደም አባላ አልብሰወታል፡፡ ውድ ኢትዮጵያውያን በፍጥነት አውቀን እንታረም፡፡ በኢትዮጵያ ይካሄዳል የሚባለው ብሔራዊ የውይይት መድረክ ወይም እርቅም በሉት በቅንነትና በወንድማማችነት መንፈስ እንዲሆን የሁላችንም ሃላፊነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ የኢትዮጵያ ገዢዎች እና የፖለቲካ አመራሮች ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ጉዳዩ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ጉዳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ብሔራዊ የውይይት መድረክ ህዝባዊ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ሀገሪቱን ወደ ሰላምና መረጋጋት የሚወስድ ሽግግርን እውን ማድረግም ያለበት ይመስለኛል፡፡

አንድ የፖለቲካ አዋቂ እንደተናገረው ብሔራዊ የውይይት መድረክ አንዲት ስር በሰደደ የፖለቲካ ደዌ ፍዳዋን በመቁጠር ላይ ለምትገኝ ሀገር ከአገዛዞች በተለየ ሁኔታ የመፍትሔ ሃሳቦችን የሚመነጭበት ነው፡፡ ( በሌላ አነጋገር አገዛዞች ለብቻቸው ከሚያመነጩት የመፍትሔ ሃሳብ በተሻለ መልኩ ሌሎች ለሀገር መድህን የሚሆኑ ምክረ ሃሳቦች ይቀርቡበታል፡፡) ሆኖም ግን ይሁንና ብሄራዊ የውይይት መድረኩ አለአግባብ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ የሀገሬው መንግስት ስልጣኑን ሊያጠናክርበት ይቻለዋል፡፡ ከገዢው ፓርቲ ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆኑ የአላማቸው ማስፈጸሚያ አድርገው ሊጠቀሙበት ይቻላቸዋል፡፡ ለሀገሪቱ አንድነት የሚደማ ልብ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከፖለቲካ ጨዋታ ውጭ መሆናቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ በሌላ በኩል ብሔራዊ እርቅ በህሊና ሚዛን ላይ ተቀምጦ የሚካሄድ ከሆነ ውጤት አለው፡፡

የተባበረችው አሜሪካ የሰላም ተቋም እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2015  ባሳተመው መጽሔት ላይ ሱዛን ስቲጋንት እና ኤልዛቤት ሙሪ የተባሉ ምሁራን ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ ‹‹ ብሔራዊ የውይይት መድረክ  ወደ ግጭቶች የሚወስዱ መንገዶችን በመለየት ሁሉአቀፍ የሆኑ የመፍትሔ ሃሳቦች የሚመነጩበት ነው፡፤›› ሁለቱ አሜሪካዊ ምሁራን  በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያቀረቡት ጽሁፍ የበለጠ ገላጭ በመሆኑ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

 “national dialogues offer the potential for meaningful conversation about the underlying drivers of conflict and ways to holistically address these issues” (US Peace Institute, 2015 by Susan Stigant and Elizabeth Murray 2015)  

የኢትዮጵያ ጉዳይ እንቅልፍ የነሳቸውና ህሊና የፈጠረባቸው ኢትዮጵያውያን እንደሚያምኑት ከሆነ አንዳንድ አክራሪ የጎሳ ፖለቲከኞች ተገንጥለው የራሳቸውን ነጻ መንግስት ለመመስረት ቆርጠው ከተመሱ ውለው አድረዋል፡፡ አንዳንዶ እጅጉን የተጨነቁት ምሁራን ደግሞ ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት ክፉ እድል በመነሳት የታላቁ መሪ ብሮዝ ቲቶ ሀገር የነበረችው የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ (ነበረች ልበል ዛሬ ያቺ ስመ ገናና ሀገር በህይወት ስለሌለች ) ከደረሰባት ውድቀት ጋር ያመሳስሏታል፡፡ ሆኖም ግን ታሪካዊት ሀገር ኢትዮጵያ ከዩጎዝላቪያ ጋር የምትወዳደር አይመስለኝም፡፡ አነርሱ ( ሁለቱም) የተለያዩ ሀገራት ናቸው፡፡ ሁለት የተለያዩ ስልጣኔዎች ናቸው፡፡ ሁለት የተለያዩ ታሪካዊ እውነታዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በማናቸውም አይነት መንገድ ተለያይታ መኖር አይቻላትም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ የአንዱ አክራሪ የጎሳ ቡድን መሪ እንደው ዝም ብሎ ተነስቶ ተገንጥያለሁ ብሎ ሊያውጅ ይቻለዋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና  አንደኛውም ቡድን በኢኮኖሚ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ አውድ የጠነከረ መንግስት እውን ማድረግ አይቻለውም፡፡ ወይም በሰላም ለመኖር ይሳነዋል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፣ ለዘመናት በማያባራ የርስበርስ ጦርነት ውስጥ መዶላቸው እሙን ነው፡፡ መገንጠል እውነታ አይደለም፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያን ጥንታዊ ሀገርነት ታሪክ በሚገባ ለሚያውቁ ዜጎች አማራጭ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት አብረው የኖሩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰረው የጋራ ገመድ ጠንካራና የተወሳሰበ ነው፡፡ ሰለሆነም በመገንጠል አቀንቃኞች አንዲህ በቀላሉ በኖ የሚጠፋ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ለገባችበት የተወሳሰበ የፖለቲካ ማጥ የመፍትሔ መንገዱ በረጀም ግዜ ውስጥ የሚካሄድ እውነተኛ ብሔራዊ ውይይት ነው፡፡ ሆነም ግን ይሁንና ይህ ብሔራዊ ውይይት በእውነታና እርቅ ሂደት ማለፍ ያለበት፣ ሰላምና መከባበር የሰፈነበት፣ ልዩነቶችን በወጉ የሚያከብር ስለመሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ በብሔራዊ የውይይት መድረክ የሚካፈሉ ቡድኖች አንኚህን የጠቀሰኩትን መራር እውነታዎች መቀበላቸው ትርጉም ላለው ብሔራዊ ውይይት ፋይዳው የትዬየሌሌ ነው፡፡

በአንድ ሀገር የሚደረግ ብሔራዊ የውይይት መድረክ አላማው ሸግግር ከሆነ ብሔራዊ የውይይት መድረኩን የሚያመቻች፣ የራሱን ምክረ ሃሳብ የሚሰጥ፣ እውቅና ያለው የሽግግር መንግስት መኖር ያለበት ይመስለኛል፡፡ ሁኔታዎችን የሚያመቻች አካል በሌለበት ሁኔታ ሽግግር እውን ሊሆን አይቻላቸውም፡፡ ስለሆነም የሽግግር መንግስት ሊመሰረት የሚችለው በገለልተኛ ቡድን ሲሆን፣ ይህ ገለልተኛ ቡድን ደግሞ የሚወከለው በፓርላማ ነው፡፡ ወይም ፓርላማው ራሱን ከማፍረሱ በፊት ህዝባዊ ውይይት በማድረግ ህገመንግስቱን ከልሶ የሽግግር መንግስት ማዋቀር ይቻለዋል፡፡ ሆኖም ግን ይህን ገቢራዊ ለማድረግ መንፈሳዊ ወኔ መታጠቅ ግድ ይላል፡፡ መንግስት የሀገሪቱን አስቸኳይ ፍላጎት ከራሱ ጥቅም የሚያስቀድም መንግስት መኖር አለበት፡፡ ሽግግር የሚፈልግ ህዝብም እንዲሁ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለሆነም የችግሩ አካል ከሆነ መንግስት የሽግግር መንግስት እንዲመሰርት መጠበቅ የዋህነት ይመስለኛል፡፡ ብቁ አለመሆንና ጠባብነት በአንድ ሀገር ላይ የተወሳሰበ የፖለቲካ ችግር የሚፈጥሩትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ብሔራዊ የውይይት መድረክ ደረጃውን የጠበቀ፣ መንግስታዊ ባልሆነ ኮሚሽን የሚደራጅ መሆን እንዳለበት ምሁራን ምክረ ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡ ከዚህ ባሻግር ወይም አስፈላጊ ከሆነ የብሔራዊ ውይይት መድረኩ ከአፍሪካ ህብረትና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እገዛ ያስፈልገዋል፡፡

በብሔራዊ የውይይት መድረኩ ላይ የሚካፈሉ ተሰብሳቢዎችን ለመጥራት ሃላፊነቱ የውይይቱ ተካፋዮችና የኢትዮጵያ ህዝብ ሃላፊነት ይመስለኛል፡፡ በርካታ ስመጥር የፖለቲካ ምሁራን አበክረው እንደሚያሳስቡት ከሆነ በብሔራዊ የውይይት መድረኩ ላይ የሚካፈሉትን ቡድኖች መምረጥ የመንግስት ሃላፊነት አይደለም፡፡ ብሔራዊ ምክክር መድረክ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሚከበርበት ነው፡፡ ብሔራዊ የውይይት መድረክ አንቂዎችን፣ጋዜጠኞችን፣ እና ሌሎችን የመብት ተከራካሪዎችን በየግዜው ዘብጥያ በምትወረውር ሀገር ውስጥ እውን መሆን አይቻለውም፡፡ ስለሆነም ብሔራዊ የውይይት መድረክ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ የግል ደህንነትና ነጻነት ምሉሄበኩልሄ ሆኖ መከበሩ አማራጭ የለውም፡፡

በነገራችን ላይ ብሔራዊ የውይይት መድረክ አሁን ባሉት የመንግስት ተቋማት ስር እውን መሆን እለማይቻለው ገለልተኛ የተባለ የብሔራዊ ውይይት መድረክ አሰና ኮሚሽን በኢትዮጵያ አየተመሰረተ ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

ብሔራዊ የውይይት መድረክ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል የራሱ ህግና ደንብ ያለው ሲሆን፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያላቸው ስብስቦች ያሉበት ነው፡፡ ውጤታማ የሆነ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ሁሉን አቀፍ እና ነጻነቱን የጠበቀ መሆን እንዳለበት የፖለቲካ ምሁራን ምክረ ሃሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡

ግልጽነትና ህዝባዊ ተሳትፎ

ምንም እንኳን ይሁንና ወጉ ደርሶን ( እንደ ወግ ከተቆጠረ ማለቴ ነው) ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎች አካታች የሆነ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት መንፈሰዋ ወኔ ብንታጠቅም፤ ምልአተ ህዝቡ ብሔራዊ የውይይት መድረኩ ላይ ስለተነሱት ነጥቦችና የውይይት ሀሳቦች በተመለከተ በቂ መረጃዎችን ማግኘት ግድ ይላል፡፡ ብሔራዊ የውይይት መድረኩ ውጤታማ መሆን የሚቻለው ከብሔራዊ ውይይቱ በፊት፣በሂደቱና ፍጻሜውን በተመለከተ ለህዝቡ ትክክለኛ መረጃ በግዜው ሲደርሰው ብቻ ነው፡፡ ብሔራዊ የውይይት መድረኩ በውይይቱ ቤት ውስጥ ከሚገኙት ተወያዮች ባሻግር ለህዝቡ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ባሻግር ብሔራዊ የውይይት መድረኩ በሀገሪቱ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አለበት፡፡ አብዛኛውን ግዜ ስምምነት ላይ ለመድረስ ወራቶች ወይም አመታት ሊፈጁ ይቻላቸዋል፡፡ ለአብነት ያህል ግጭትን የሚያባብሱ ነዳጆችን ለመክላት፣ብሔራዊ ማንነትን  እና የሃይማኖት ተልእኮን በተመለከተ፣የፖለቲካ መብትን ፣መሰረታዊ ነጻነቶችን፣የተቋማትን እንደገና የማዋቀር ስራዎች፣ የምርጫ ስርአት፣የመንግስትን መዋቅር ( የፌዴራል ስርአቱን በተመለከተ) ወዘተ ወዘተ ስምምነት ላይ ለመድረስ ብዙ ግዜ ሊፈጅ ይቻለዋል፡፡ ብሔራዊ የውይይት መድረኩ በሀገሪቱ የተፈጸሙትን አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ውይይት በማድረግ አጥፊዎች ለህግ የሚቀርቡበት  እና ተጎጂዎች ወይም የተጎጂ ቤተሰቦች ደግሞ ካሳ የሚያገኙበትን መንገድ መፈለግ ሁነኛ ስራው መሆን እንዳለበት ሳስታውስ በአክብሮት ይሆናል፡፡

ብሔራዊ የውይይት መድረክ በውይይቱ መጨረሻ ላይ የሚሰጠው ምክረ ሃሳብ ገቢራ መሆን የሚቻለው በአዲስ ህገመንግስት፣ህግ፣ፖሊሲና በሌላ ፕሮግራም መሆኑን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ልብ ልንል ይገባል፡፡ በአዲስ የወይን ጠጅ ጠርሙስ የቆየ ወይን ጠጅ መጨመሩ ውጤታማ አያደርገንም የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ሰፋ ባለ የሽግግር ግዜ መካሄድ ከተቻለው የሽግግር ፍትህ፣የህገመንግስት ክለሳ፣ ወዘተ ማድረግ እንደሚያስችል ምሁራን በየግዜው ከሚሰጡት ሃሳብ መገንዘብ ያስችላል፡፡ በነገራችን ላይ ብሔራዊ የውይይት መድረክን በአግባቡ መጠቀም ካልሆነልን ዘለግ ያለ ግዜ እና የሀገሪቱ ሀብት ከፈሰሰበት በኋላ ምንም አይነት ተጨባጭ ውጤት ሳያመጣ ሊቋረጥ እንደሚችል መገንዘቡ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡

እውነተና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን በደቡብ አፍሪካ ሪፐብሊክ (Truth and Reconciliation Commissions (TRC) in South Africa )

ብሔራዊ የምክክር መድረክ ቀጣይነት ያለው ሰላም አንዲያመጣ  የእውነታና እርቅ ኮሚሽን እውን መሆን ጠቃሚነቱ መተኪያ የለውም፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ የብሔራዊ የውይይት መድረክ ጽንሰ ሃሳብ ሲወራ ወይም ሲንሸራሸር ስለ እውነታና እርቅ ኮሚሽን እያወራን ስለመሆኑ ልብ ልንል ይገባል፡፡ በተለያዩ አፍሪካዊ የፖለቲካ ምሁራን በደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክ፣ ሩዋንዳ እና ላይቤሪያ ውስጥ ተካሂደው የነበሩትን የእውነተና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን የስራ ሂደቶችን በተመለከተ ያዘጋጁትን የጥናት ወረቀቶች ያነበብን ሰዎች አሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ እነኚህ ተከታታይነት የነበራቸው ድርጊቶች ( በተጠቀሱት ሶስቱም ሀገራት የተካሄዱትን የእውነታና እርቅ ኮሚሽን ሂደቶችን ማለቴ ነው) በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የመወያያ ነጥቦች ነበሩ፡፡ በነገራችን ላይ በደቡብ አፍሪካ፣ሩዋንዳና ላይቡሪያ ስለተካሄዱት የእውነተና እርቅ ኮሚሽን ሂደቶችን በተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ በማዘጋጀት ኢትዮጵያ እንዴት ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባት በብዙ መልኩ የደከሙት፣ አይናቸው ደም እስኪመስል፣እጃቸው እስኪዝል የጻፉት እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም( ነብሳቸውን በሰላም ያሳርፍልን )፣ አቶ ያሬድ ሀይለማርያምን የመሰሉ እውቅ ኢትዮጵያዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ እንዲሁም አለም አቀፍ የህግ ምሁሩ ዶክተር ያቆብ ሀይለማርያም፣ ስመ ጥሩው የግጭቶች ምክንያቶችና መፍትሔዎቻቸው ተጠባቢ ዶክተር ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ወዘተ ወዘተ ለአብርክቷቸው ታሪክ ስፍራውን አይነሳቸውም፡፡ እውን እነኚህ ኢትዮጵያዊ ምሁራን ሰሚ አግኝተው ይሆን ? አይመስለኝም፡፡ ለማናቸውም መልሱን ለአንባቢው ትቼዋለሁ፡፡ በእኔ በኩሌ በዚሁ ጉዳይ ላይ፣በዚችው የሀበሻ ገጽ መጽሔት ላይ የአቅሜን ያህል ሁለት ዘለግ ያሉ ጽሁፎችን ማቅረቤን አስታውሳለሁ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ የእርቅ ሁኔታ ( ምልከታ) የተሳሳተ ትርጉም ሲሰጠው ይስተዋላል፡፡ እውን ስለ እውነት በመናገር ብቻ እርቅ ማውረድ ይቻላልን ? በዋነኝነትና በመጀመሪያ ስለ እውነት በሚነገርበት ግዜ፣ ሁሉም እውነቶች መነገር አለባቸው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እውነት ራሱ ብቻውን እርቅ ለማውረድ ብቸኛ መሳሪያ ለመሆን አይቻለውም፡፡ 

የኢትዮጵያ ህዘብ በሰላምና ተከባብሮ አብሮ መኖር የሚቻለው ሁሉም እውነቶችና ታሪካችን ለህዝብ በአደባባይ ሲነገርና ውይይት ሲደረግበት፣ እንዲሁም በግዜው የተፈጸሙ ወንጀሎች እውቅና ተሰጥቷቸው ዛሬ መማሪያ ሲሆኑ እና ስምምነት ተደርሶባቸው ፍትህ ሲሰፍን፣ ወንጀልን ያቀጣጠሉና   የፈጸሙ ተለይተው በፍትህ አደባባይ ላይ ቆመው ፍርዳቸውን ሲቀበሉ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም የወደፊቷ ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ የሚወሰነው በእውነት፣ፍትህ፣ከሳና እርቅ እንደቅደም ተከተላቸው እውን ሲሆኑ ብቻ ነው ብዬ አስባለሁ፡ The future of Ethiopia depends upon Truth, Justice, Reparations and Reconciliation in this order

አዲሶቹ የኢትዮጵያ ገዢዎችና የፖለቲካ ልሂቃን ( በመንግስት ዙሪያም ሆነ በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ዙሪያ የተሰባሰቡት ልሂቃን፣የዩንቨርስቲ የታሪክ ምሁራን ጭምር ) ወደ አደባባይ በመውጣት ህዝቡን ከውሸት ፕሮፓጋንዳና ታሪክ እስር ነጻ ማውጣት ያለበቻው ይመስለኛል፡፡ በዚች ዲጂታላይዝድ አለም እውነትን ለመናገር አስቸጋሪ ሊሆን ይቻለዋል፡፡ አለም በውሸት ታሪክ የታጨቀች ናት፡፡ ኢትዮጵያም በውሸት አንዷ ተጠቂ ናት ብዬ እሰጋለሁ፡፡ የፍትህ አላማ ወንጀለኛን መቅጣት ወይም ማስተማር ብቻ አይመስለኝም፡፡ ሆኖም ገን ይሁንና ተጎጂዎች ዘለቄታው በተጠበቀ ሁኔታ ህይወታቸውን እንዲቀጥሉ ማድረግ፣ ማህበረሰቡ ያጣውን ንብረት መልሶ እንዲያገኝ ማስቻል ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው፣ ይገባኛል ማናቸውም የፍትህ ሥርአት ሰዎች አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሳይፈጸምባቸው በፊት ወደ  ነበረው የህይወት ዘይቤ ወይም የቀደመ የኑሮ ደረጃቸው አይመልሳቸውም፡፡ ተጎጂዎች የሚኖሩት በሞት የተለዩ ቤተሰቦቻቸውን፣ወዳጆቻቸውን እያስታወሱ፣በስነ ልቦና ችግር እየተሰቃዩ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ወንጀለኞችና ወንጀሉ የተፈጸመባቸውን ግለሰቦች በአንድ መድረክ ላይ እንዲገናኙ በማድረግ፣ወንጀለኛው ስለፈጸመው ወንጀል እንዲናዘዝ፣ተበዳዮች ደግሞ ይቅር ለእግዛብሔር እንዲሉና ካሳ ከተከፈላቸው ቢያንስ ፣ ቢያንስ በህይወት የተረፉት የተጎጂ ቤተሰቦች  የወደፊቱን ህይወታቸውን ለመምራት ተስፋ ላይቆርጡ ይቻላቸዋል፡፡ እርግጥ ነው ይህ ዘዴ ብዙ በህብረተሰቡ ላይ የደረሰውን ግፍ፣የስነልቦና ችግር ለመክላት ግዜያትን ሊፈጅ ይቻለዋል፡፡

በነገራችን ላይ የደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክ የሽግግር ፍትህን በተመለከተ አለም ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ያደረግችው ሀገር መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡ በዳይና ተበዳይን አንድ ላይ ባመቆም ወይም ፊትለፊት ባመገናኘት  የሚሰጥ ፍትህ (a more specific type of restorative justice) ዘለቄታ ያለውን ሰላም ያስፈናል፡፡ በደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክ ፍትህ እንዲሰፍን ህዝቡን ወክለው ሁነኛውን ሚና የተጫወቱት ሟቹ ብጹ አቡነ ዴዝሞንድ ቱቱ ነበሩ፡፡( the late Archbishop Desmond Tutu ) ዴዝሞንድ ቱቱ ስለ ፍትህ አስፈላጊነት ህዝባቸውን ሌትተቀን ሰብከው ነበር፡፡ ወንጀል ፈጻሚዎች የሰሩትን ሀጢያት ስለተናዘዙ ብቻ ነጻ እንደማይወጡ፣እንደ ወንጀላቸው እንደሚቀጡ፣ ህዘቡ ይቅር ለእግዛብሔር ያላቸውም ምህረት እንደሚደርግላቸው አስተምረዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በህዝብ ፊት ወንጀለኞች የፈጸሙትን ግፍ ስለተናዘዙ ይቅር ተጎጂዎች ለእግዜአብሔር ቢሉም ይህ ብቸኛው የይቅርታ መንገድ አለመሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ከዚህ ጋር እኩል ጠቀሜታ ባለው ሁኔታ ሀጢያትን ከመናዘዝ ባሻግር ታማኝነትና በተጨባጭ ላይ የተመሰረቱ ሁሉአቀፍ ውይይቶች መደረግ አለባቸው፡፡ በደቡባዊት የአፍሪካ ሪፐብሊክ የተካሄደው  የእውነታና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን ያስገኘው ፍትህ በዛች ሀገር ላይ በግለሰብ ደረጃም ሆነ በሀገር ደረጃ አንድ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ሰዎች ታሪካቸውን ይናገራሉ፣ህሊናቸውን ንጹህ ያደርጋሉ፣ በመጨረሻም ሰላምን ከእውነት ይፈልጋሉ፡፡ አንድ የደቡብ አፍሪካዊት የታሪክ ምሁራን እንደገለጹት ‹‹ ይህቺን ሀገር በአጭር ግዜ የሚያድን( የሚፈውስ) ተአምር የለም፡፡ ሆኖም ግን ሀገሪቱ ለመጀመሪያ ግዜ ብዙዎች ከተሰቃዩበት ህመም ባሻግር ማየት የቻሉበት ሀገር ሆናለች ካሉ በኋላ  እውነትን ተናግረን ደሃ ብንሆን ይሻላል፣ እውነት የታሪካችን አንዱ ጠቃሚ አካል እንደሚሆን አምናለሁ፡፡ብለው ነበር፡፡››

As one South African historian put it, “nothing short of a miracle can heal a country” but “for the first time it was possible to see beyond the pain that many had suffered. As a country we would have been much poorer had the truth not been told. I believe it was truly a necessary part of our history.

በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተጎጂዎችና ወንጀለኞች ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ወይም ንግግር አድርገው ነበር፡፡ ንግግራቸው የአንድ ወገን ብቻ አልነበረም፡፡ ከዚህ ባሻግር የኤኤን ሲ ትግል ህጋዊ እንደነበረም ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በኤኤንሲ ስም የተፈጸሙ አንዳንድ ወንጀለኞች ለፍርድ ቀርበው ነበር፡፡ ወንጀለኞቹ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በመንግስት ስም ሳይሆን በድርጅታቸው ስም ቀርበው ነበር ሃጢያታቸውን የተናዘዙት፡፡ ንስሃ ከገቡ በኋላ ነበር የኮሚሽኑ ስራ የቀጠለው እና ለተጎጂዎች ካሳ እንዴት ማከፋፈል እንደሚቻል መመሪያ መስጠት የጀመረው፡፡ በአንድ ጥናታዊ ወረቀት ላይ እንዳነበብኩት ከሆነ ወደ 300 የሚጠጉ የአፓርታይድ ስርአት አራማጅ የነበሩ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት መቅረባቸውን አስታውሳለሁ፡፡ በሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበውም ሀጢያታቸውን በመናዘዛቸው ለብሔራዊ እርቅ እውን መሆን አግዘዋል፡፡ አንድ የፖለቲካ ሳይንቲስት እንደተናገረው፡-

ዋነኛው የኮሚሽኑ ስራ ሪፖርት ማቅረብ ብቻ አይደለም፡፡ በቴሌቪዝን ቀጥታ የታየ ጉዳይ ነበር ህዝቡን እምባ ያራጨው ‹‹ የእውነታና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽኑ እውቀትን ተቀባይነት እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡

 ›› (As one political scientist put it, what the truth commission did was convert knowledge into acknowledgment

ከላይ የተጠቀሱት ሁሉ መልካምና ጥሩ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ገቢራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ኮሚሽኑ መፈጸም ያልቻላቸው ተግባራት ነበሩ፡፡ ስለሆንም በኮሚሽኑ ውጤት ላይ ከብዙ አቅጣጫዎች የዘነቡ ትችቶች ነበሩ፡፡ ስለሆነም በደቡብ አፍሪካ ሪፐብሊክ የእውነታና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን ከነበሩ ክፍተቶች ላይ መማሩ ኢትዮጵያ ለተዘፈቀችበት ጥልቅ የፖለቲካ ችግር ለመገላገል ይረዳታል በሚል አንዳንድ የነበሩበትን ችግሮች እንደሚከተለው መጥቀሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡-

 1. ኮሚሽኑ ስራውን በፍጥነት ነበር ተግባሩን የሚያከናውነው፣ከዚህ ባሻግር ፍጹም ላይተገበሩ የሚችሉ ተግባራትን ጀምሮ ነበር፣ ለአብነት ያህል ይቅርታ ለማድረግና ተጠያቂዎችን ለፍርድ ከማቅረብ አኳያ ክፍተት ነበር፣ ይቅርታ የሚሰጠው ለየትኛው ወንጀለኛ ነው የሚለው አስቸጋሪ መሆኑ፣ ኮሚሽኑ ራሱን አምቢሽስ ማድረጉ፣ ወዘተ ዘወዘተ ይጠቀሳሉ፣
 2. እጅግ ለተወሳሰቡ ችግሮች፣ አብዝሃው የደቡብ አፍሪካ ዜጋ ውስጥ ጠለቀው ለሚታወቁ የአፓርታይድ ግፍ ፈጻሚዎች ላይ ጥልቅ ምርመራ ሳያደርግ በፍጥነት መፍትሔ ወደ ማፈላለጉ ስራ መግባቱ፣
 3. የእውነታና እርቅ አፈላላጊ ኮሚቴው ጥልቀት ያለው ስትራቴጂክ እቅድ አልወጣለትም ነበር፣
 4. ኮሚሽኑ  በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት አራማጆች እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1960 እስከ 1994 የተፈጸሙትን አስከፊ የመብት ጥሰቶችን ለማጥናትና ለመሸፈን ጥረት ማድረጉ መልካ ሆኖ ሳለ ፣ወንጀል ፈጻሚዎችን በፍትህ አደባባይ ለማቅረብ የተሰጠው የግዜ ገደብ አጭር መሆኑ የተሳካ ስራ ለማከናወን አላስቻለውም ነበር፣
 5. በኮሚሽኑ የተቋቋሙ የተለያዩ ኮሚቴዎች ግልጽ የሆነ የስራ ዘዴ አልነበራቸውም፣
 6. በርካታ ይቅርታዎች እውን እንዲሆኑ በመደረጉ፣ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ተጎጂዎች ብርቱ ሀዘን ላይ ተዱለው ነበር፣
 7. ወንጀለኞች በነጻነት በአደባባይ ሲነቀሳቀሱ ማየት፣ተገቢው ካሳ ለተጎጂዎች አለመሰጠቱ ሌላው የኮሚሽኑ ጉድለት ነበር፣
 8.  የእወነታና እርቅ አፈላላጊ  ኮሚሽን ዋና ዳይሪክተር የነበሩት ሚስተር ስታን ሄንክማን ( The executive director of the TRC Institute for Justice and Reconciliation, Stan Henkemann ) እንደተናገሩት ከሆነ የደቡብ አፍሪካ የፍትህ ተቋም በይቅርታ አሰጣጡ ሂደት ላይ ክሽፈት አጋጥሞት ነበር፡፡ አንድ ቤተሰቡ በአፓርታይድ ስርአት አረማጆች የተገደለበት የደቡብ አፍሪካ ዜጋ ወንጀለኞች ሳይቀጡ በአደባባይ ሲጎማለሉ ማየት ያማል ሲሉ ተከራክረው ነበር፡፡ በሌላ በኩል የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የነጻነት ታጋይ የነበሩት ታላቁ የአፍሪካ ልጅ የደቡብ አፍሪካ እውነታና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን ድክመቶች ቢኖሩትም ሊመሰገን እንደሚገባው ተናግረው ነበር፡፡ ሌሎች የማንዴላ ሃሳብ ተቀናቃኞች በሰጡት አስተያየት ሚስትር ማንዴላ እና ኮሚሽኑ አንዳንድ የአፓርታይድ ስርአት አራማጅ የነበሩ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ለአፓርታይድ ስርአት መውደቅ እገዛ ስላደረጉ በይቅርታ መታለፋቸውን እንደ በጎ ተግባር ቆጥረውት ነበር፣
 9. ኮሚሽኑ ሀብትን ወደ ሰፊው ህዝብ ከማስተላለፍ አኳያ ክሽፈት ገጥሞት ነበር፣
 10. ይቅርታ የተነፈጉ ወንጀለኞች በፍትህ አደባባይ ላይ ቆመው ፍርዳቸውን ሳይቀበሉ ቀርተው ነበር

ማስታወሻ፡- በደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክ ምድር የተካሄደው ብሔራዊ የእርቅ ጉባኤ አንዲት በኢኮኖሚ ጠንካራ ዲሞክራቲክ ሀገር ማዋለዱን፣ የአፓርታይድ ስርአትን ከስሩ መንግሎ መጣሉን፣ ሆኖም ግን ይሁንና በዛች ሀገር ላይ የኢኮኖሚ ነጻነትን ለማስፈን ሳይችል መቅረቱን ኢትዮጵያውያን ልብ ልንል ይገባል፡፡ ይህ ኮሚሽን አለም አቀፍ እውቅና ያላቸውን ስመ ገናናውን የነጻነት ታጋይ መንፈሰ ጠንካራውን አቡን ዴዝሞንድ ቱተና ሌሎች ታላላቅ የዛች ሀገር ልጆችን ያካተተ በመሆኑ በብዙ መልኩ አርአያነቱን መከተል ይቻላል፡፡ ስንዴውን ከእንክርዳዱ መለየቱ የኢትዮጵያውያን መሆኑን ሳስታውስ በታለቅ አክብሮት ይሆናል፡፡

እውነታና እርቅ ማፈላለግ በላይቤሪያ

ለ14 አመታት በርስበርስ ጦርነት ፍዳዋን በቆጠረቸረው ላይቤሪያ፣ 250000 ዜጎቿ እንደ ቅጠል የረገፉባት ላይቤሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿ ለስደት ተዳርገውባት የነበረችው ላይቤሪያ፣ ከአራት ሚሊዮን ትንሽ ከፍ የሚል ህዝብ የሚኖርባት ሚጢጢዋ ላይቤሪያ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2003 በጋና አክራ ተካሂዶ በነበረው ሁሉ አቀፍ የሰላም ስምምነት መሰረት የእውነታና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን እውን ሆኗል፡፡ የእውነታና እርቅ አፈላላጊው ኮሚቴ አላማ የነበሩት፡-

 • ብሔራዊ ሰላም ፣
 • ጸጥታ፣
 • የሀገሪቱን አንድነትን እና ብሔራዊ እርቅ ማስፈን የነበሩ ከመሆናቸው ባሻግር አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎችን ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግን የሚያካትቱ ነበሩ፡፡

የላይቤሪያን የእውነትና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን ልእለ ስራዎች በቅርበት የተከታተሉ አጥኚዎች በምርምር ጽሁፎቻቸው ላይ እንደጠቀሱት ከሆነ በ14ቱ አመት የርስበርስ ጦርነት ውስጥ በርካታ ተጎጂ የነበሩ ሲቨል ዜጎችነ፣ ፖለቲከኞችን፣ የአይን ምስክሮችን አነጋግረው በደረሱበት ድምዳሜ የኮሚሽኑ ስራ ከባድ ነበር፡፡ የኮሚሽኑ የስራ ሃላፊነትም በፍጥነት አልተነገረም ነበር፡፡ የኮሚሽኑ የስራ ሃላፊነት ወይም ህግ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2005( ከ3 አመት በኋላ መሆኑ ነው) ላይ ተሻሽሎ ነበር ስራውን የጀመረው፡፡ ይህን ተከትሎ የአይን እማኞችን ሰብስቦ ቃላቸውን መቀበል ተጀምሮ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በሚከተሉት የጦርነቱ ዳፋ ምክንያቶች የተነሳ አብዝሃው የላይቤሪያ ዜጋ በከባድ የስነልቦና ችግር ውስጥ ተዱሎ ነበር፡፡ ለአብነት ያህል፡-

 • ከባድ የኢኮኖሚ ድቀት ( ችጋር)፣
 • በሰላም ንግግሩ ላይ ብዙሃኑ ዕንዳይካፈሉ መገለላቸው፣
 • ለብሔራዊ እርቁ የተመደበው በጀት አለመለቀቅ ወዘተ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ በነገራችን ላይ ያንዬ የሀገሪቱ ፕሬዜዴንት የነበሩት  ሚስስ ሰርሊፍ (President Sirleaf ) ሙስናን በመዋጋት ብሔራዊ እርቅ ማምጣት አልቻልኩም በማለት ስልጣናቸውን መልቀቃቸው በታሪክ ተጽፏል፡፡

ሁላችንም መገንዘብ ለብን ነገር ቢኖር ያለፍትህ እርቅ ብቻውን እውን ሊሆን አለመቻሉን ነው፡፡ ሰዎች ለፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ ሆነው ፍርዳቸውን ካልተቀበሉ ማሀበረሰቡ ጦርነቱ ካደረሰበት መአት አይድንም፡፡ ሰዎች ወደ የርስበርስ ጦርነት ውስጥ የዶሏቸው ጨካኞችና ወንጀለኞች በፍትህ አደባባይ ቆመው ተጠያቂ ካልሆኑ በቀር የሰብአዊነት ስሜታቸው ይደበዝዛል፡፡ ፍትህ የሰላም፣አብሮ በሰላም የመኖርና የልማት መሰረት ነው፡፡ ፍትህ ማለት በአንድ ወንጀለኛ ላይ የክስ ዶሴ መምዘዝና የፍርድ ሂደት ማካሄድ ማትም ነው፡፡ ለአብነት ያህል ናዚስቶችና ፋሺስቶች በኑርመበርግ ፍርድ ቤት ( Nazis and fascists were put on trial at Nuremberg )፣ እንዲሁም የሩዋንዳ የዘር ፍጅት አራማጆች፣የኮንጎ ሊዝ እና ኡጋንዳ የጦር አበጋዞች፣የላይቤሪያው የጦር አበጋዝ ቻርልስ ቴይለር ሳይቀሩ በፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ( በነገራችን ላይ ቻርልስ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበረው በላይቤሪያ ምድር ለፈጸሙት የጦር ወንጀል ሳይሆን በሴራሊዮን ምድር ለፈጸሙት የጦር ወንጀል መሆኑን ማወቁ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም ፡፡)  

በላይቤሪያ ተቋቁሞ የነበረው የእርቅ ኮሚሽን ያቀረበው ምክረ ሃሳብ ገቢራ ቢሆን ኖሮ ፍትህ ሰፍኖ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ግን አልሆነም፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ አንዳንድ ወንጀለኞች ከላይቤሪያ ውጭ በሚገኙ ሀገራት ከተሸሸጉበት ተለቅመው ፍርድ ቤቶች ውስጥ ቀርበው ነበር፡፡ ለአብነት ያህል በፈረንሳይ፣ቤልጂዬም፣ ታላቋ ብሪታንያ፣ እና የተባበረችው አሜሪካ  የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ወንጀለኞችን ከመቅጣት አኳያ ይጠቀሳሉ፡፡ በነገራችን ላይ ስህተት መፈጠሩን በማያምን ህብረተሰብ ውስጥ ፍትህን ማስፍን አይቻልም፡፡ ወንጀለኞች በህብረተሰቡ ፊት ቀርበው ሀጢያታቸውን ተናዘው ካበቁ በኋላ ተበዳዮች ይቅር ለእግዛብሔር ማለት፣ካሳም ማግኘት አለባቸው፡፡ ይህ ነው ወደ የፍትህ መንገድ የሚወስደን፡፡ አሁን ድረስ በአለም ላይ ብዙ ቦታዎች ፍትህ አልሰፈነም፡፡ ወይም በታሪክ የተፈጸሙ ወንጀሎችን በማስረጃ አስደግፎ ወንጀል ፈጻሚዎችን በመለየት ወደ ፍትህ የሚወስዱ መንገዶችን ለማበጀት አልተቻለም፡፡ ከዚህ ባሻግረ፡ አለመታደል ሆኖ ፍላጎቶቻችን መጨረሻ የላቸውም፡፡

በአጠቃላይ በላይቤሪያ የእውነትና እርቅ ኮሚቴ፡

 • ሁሉም እውነቶች አልተነገሩም፣
 • ፍትህ አልሰፈነም፣
 • የካሳ አካፋፈል ስርአት በቅጡ አልተካሄደም ( አልነበረም)፣
 • በጨቋኞችና ተገዢዎች መሃከል ወይም በታሪክ ለባርነት በተዳረጉ ዜጎችና ገዢዎቻቸው ፣በጦር አበጋዞችና በርስበርስ ጦርነቱ ፍዳቸውን ሲቆጥሩ በነበሩ ሲቪል ዜጎች መሃከል፣ ወዘተ ወዘተ ብሔራዊ እርቅ አልተደረገም ነበር፡፡ ስለሆነም በላይቤሪያ የነበረው የእውነታና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን ስራውን በክሽፈት ነበር የቋጨው፡፡ ተምሳሌትነቱ ለኢትዮጵያም ሆነ ሌሎች በፖለቲካዊ ችግር ፍዳቸውን ለሚቆጥሩ ሀገራት የሚበጅ አይመስለኝም፡፡

የእውነታና እርቅ አፈላላጊ በሩዋንዳ

የብይነ መንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ከጥር 1 1994 እስከ ታህሳስ 31 1994 ድረስ ባሉት በሩዋንዳ ድንበር ውስጥ በሩዋንዳ ዜጎች፣ እንዲሁም በሩዋንዳ ሀገራት ድንበሮች ላይ አስከፊ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ያስፈጸሙና የፈጸሙ የጦር ወንጀለኞችን ለመቅጣት ያስችለው ዘንድ አለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለሩዋንዳ ማቋቋሙ የሚታወስ ነው፡፡ The UN Security Council established the International Criminal Tribunal for Rwanda

በግዜው የአለሙ ጸጥታው ምክር ቤት በሩዋንዳ የዘር ፍጅት ተፈጽሟል ብሎ በማመኑ ነበር ይህ ፍርድ ቤት የቆመው፡፡ ፍርድ ቤቱ ተቋቁሞ የነበረው በታንዛኒያ አሩሻ ከተማ ሲሆን፣ጽህፈት ቤቱ ደግሞ በሩዋንዳ ኪጋሊ ከተማ ሲገኝ የይገባኝ ፍርድ ሂደቱ የታየው ደግሞ በአውሮፓዊቷ ሀገር ኔዘርላንድ ሄግ ነበር፡፡ በግዜው በነበረው አለም አቀፍ መረጃ መሰረት 63 ግለሰቦች ጥፋተኛ ተብለው መቀጣታቸውን፣10ሩ ደግሞ በሩዋንዳ ብሔራዊ ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር፡፡ ወደ ወህኔ አምባ ከተወረወሩት ውስጥ ከፍተኛ የጦር መሪዎች፣የመንግስት ባለስልጣናት፣ባለሀብቶች፣የሀይማኖት ተቋማት መሪዎችና የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች ይገኙበታል፡፡ እነኚህን አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙና ያስፈጸሙ ወንጀለኞች እንዲቀጡ ከማስቻሉ በላይ ይህ አለም አቀፍ ፍርድ ቤት በብዙ ምክንያት ጠቃሚ ነበር፡፡ በታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ ይህ አለም አቀፍ ፍርድ ቤት የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈጸሙ አረመኔዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ከማስቻሉ ባሻግር፣ አስገድዶ የመድፈር ወንጀል  የዘር የማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸም ምክንያት ሊሆን ይችላል በሚል  እውቅና የሰጠም ተቋም ነበር፡፡

ሌላኛውና መረሳት የሌለበት ቁምነገር አለም አቀፉ ፍርድ ቤት በሩዋንዳ ምድር የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸምና እንዲቀጣጠል የነዳጅ ማርከፍከፍ እኩይ ሴራ ሲፈጽሙ የነበሩ የስም ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት ቀርበው በህግ እንዲጠየቁ ማድረጋቸው ነበር፡፡

በሌላ በኩል የሩዋንዳ ብሔራዊ ፍርድ ቤት ስርአት እና የሩዋንዳ ባላዊ ፍርድ ቤት (the Gacaca Community Courts ) አስከፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈጸሙና የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸም እቅድ ያወጡ ወንጀለኞች ተጠያቂ እንዲሆኑ አድርገው ነበር፡፡ ለአብነት ያህል አስገድዶ የመድፈር ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች መዝገብ የሚጠቀስ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻግር እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ2006 አጋማሽ ላይ ወደ 10,000 ግድም የሚጠጉ ወንጀለኞች ተከሳሽ ሆነው ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ2007 ደግሞ ሩዋንዳ የሞት ፍርድ እንዲቀር ወስናለች፡፡ ይህ ውሳኔ ደግሞ በዘር ማጥፋት ወንጅል ተከሰው በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩ ግለሰቦች ጉዳይ ወደ ሩዋንዳ ብሔራዊ ፍርድ ቤት ያለምንም ችግር እንዲዘዋወር አስችሎት ነበር፡፡

በነገራችን ላይ በማናቸውም ሀገራት መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር  ወይም እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የሰብአዊ መብት ፈጻሚዎችን በፍትህ አደባባይ ለማቅረብ ተግዳሮቶች   እንዳሉ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በሩዋንዳ ተፈጽሞ የነበረው የዘር ፍጅት ወንጀል በአሰቃቂነቱ ትቶት ያለፈው ጠባሳ መረሳት እንደሌለበት፣እንዲሁም የዘር ፍጅቱን ወንጀል ደረጃ ለመዳኘት ዘመናዊ የፍትህ ስርአት እና ከፍተኛ የህግ እውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች ግድ ይል እንደነበር ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡

በሩዋንዳ ምድር እንዲህ አይነት የፍርድ ሂደት ለማካሄድ እጅጉን አስቸጋ ነበር፡፡ ምክንያቱም የዘር ማጥፋት ወንጀል በተፈጸመበት ግዜ በርካታ ዳኞች፣ጠበቆችና የፍርድ ቤት ሰራተኞች በመገደላቸውና የሀገሪቱ መሰረተ ልማቶች በመውደማቸው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እንዲህ አይነት ተግዳሮቶች የነበሩ ቢሆንም የሩዋንዳ መንግስት የታወቁ ህጎችንና የሀገሪቱን ህብረተሰብ ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን (community-based gacaca courts. ) በመጠቀም ፍትህን ለማስፈን ቆርጦ ተነስቶ ነበር፡፡

ጋካ (Gacaca )ምን ማለት ነው ?

ጋካ ማለት እርጥብ ሳር ማለት ይመስለኛል፡፡ (Gacaca literally means “clean cut grass ) በጋካ ስርአት በታችኛው እርከን በቀበሌ ደረጃ የሚኖረው ማህበረሰብ የራሳቸውን ዳኛ በመምረጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመፈጸምና ለማስፈጸም እቅድ ካወጡት በቀር በሁሉም የሰብአዊ መብት ጥሰት በመፈጸም የተጠረጠሩ ወንጀለኞችን ጉዳይ የፍርድ ሂደቶችን አዳምጦ ፍርድ ሰጥቶ ነበር፡፡ 

የተቋቋሙት ፍርድ ቤቶች በሰሩት ወንጀል የተጸጸቱ እና ለፈጸሙት አስከፊ ወንጀል ማህበረሰቡን ይቅርታ የጠየቁ ወንጀለኞችን አነስተኛ ቅጣት ሰጥቷቸዋል፡፡ (repentant and seeks reconciliation) በአብዛኛው ጸጸት ያደረባቸው ታሳሪዎች የእስር ግዜያቸው እያጠረ ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል፡፡ ወይም ለማህበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ሁኔታዎች ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ስለሆነም ሩዋንዳ በሀገሯ ምድር የበቀለ ባህላዊ የፍርድ ቤት ለማንበር ተሳክቶላታል ብሎ መደምደም ይቻላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለአብነት ያህል ሌቦችን መቅጣት፣ጋብቻ የፈጸሙ ግለሰቦች በፍቺ እና በመሬት ባለቤትነት ምክንያት የተከሰቱ ግጭቶችን፣ እንዲሁም በንብረት ላይ ለሚደርሱ ጉዳቶች ኢመደበኛ በሆነ ሁኔታ ፍትህ ይሰጡ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ስለደረሱት ጉዳቶች ወይም እሰጥ እገባዎች በተመለከተ የመንደሩ ሰዎች ሁሉ አስተያየት እንዲሰጡበት እድሎች ከተመቻቹ በኋላ ወንጀል የፈጸሙት በህብረተሰቡ መሃል ቆመው ሃጢያታቸውን ከተናዘዙ በኋላ የፍትህ አሰጣጡ  ሂደት ተከናውኖ የተከበሩ፣ታማኝ የሆኑ፣ ማህበረሰቡ ይሁንታ ሰጥቷቸው በተመረጡ በታወቁ የሀገሬው ሽማግሌዎች. (Well-respected elders, known as Inyangamugayo, ) አመሃኝነት ፍትህ ይሰጣል፡፡

 ይህ የባህላዊ ፍርድ ቤት ወንጀል የፈጸሙትንና ወንጀል የተፈጸመባቸውን የማህበረሰቡን ክፍሎች አንድ ላይ በአንድ መድረክ እንዲገናኙ ሁኔታዎችን ካመቻቸ በኋላ ወንጀል ፈጻሚዎች የሠሩትን ሀጢያት ምንም ሳይሸፋፍኑ እንዲናዘዙ በማድረግ ተበዳይ ወገኖች ከልባቸው ይቅር ለእግዛብሔር እንዲሉ ፣እንዲሁም የካሳ ክፍያ እውን እንዲሆን በማድረጋቸው ፍትህን ለማስፈን አስችሏቸዋል፡፡ ይህ የባህላዊ ፍርድ ቤት የተዘጋው እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ግንቦት 2012 የነበረ ሲሆን፣ በተመሳሳይ አመት ( እ.ኤ.አ. ጥር 31 2012 ማለቴ ነው) 1,951,388 የዘር ፍጅት ወንጀሎች (genocide cases) ፍርድ ከተሰጠባቸው በኋላ ተጠናቀዋል፡፡

ለሩዋንዳውያን ይህ ታላቅ ድልና ስኬት ሲሆን፣ቀሪው የአፍሪካ ክፍልም የሩዋንዳ ባህላዊ ፍርድ ቤት እንደ ጥሩ ሞዴል የሚወሰድ ነው፡፡ ይህን የሩዋንዳን ባህላዊ ፍርድ ቤት ከምእራቡ አለም የፍርድ ቤት ደረጃ ጋር ማወዳደር ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡ እጅግ ባልተለመደ ግዜ ያልተለመደ የመፍትሔ ሃሳብ አስፈላጊ ሊሆን ይቻለዋል፡፡

ሩዋንዳ አጋጥሞት በነበረው የመከራ ዘመን፣ብሔራዊ አደጋ፣የህልውና ጥያቄ ወዘተ ወዘተ ሰራሄ መፍትሔ ለመሻት ሩዋንዳውያን ባህላዊ የፍርድ ሂደት ለመጠቀም ፈጠራ እውን ባመድረጋቸው ምክንያት ያን የመከራ ዘመን ምእራፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ለመፍታት መንፈሳዊ ወኔ ታጥቀው ዛሬ ለደረሱበት ስኬት በቅተዋል፡፡ በአንድ ሀገር ላይ ብሔራዊ እርቅና ሰላም ለማውረድ አንድ የታወቀ ሰነድ ላይኖር ይቻለዋል፡፡ (There is no manual for reconciliation and peacekeeping) በእኔ የግል አስተያየት ለመርህ ተገዢና የመርህ ሰው መሆን ለብሔራዊ እርቅ ይበጃል ብዬ አስባለሁ፡፡ ህዝብን ከአመድ ላይ አንስቶ ሀገርን ለመገንባት መብትና ነጻነት ሳይሸራረፉ ገቢራዊ መሆን አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለሆነም ሩዋንዳውያን ባህላዊ ፍርድ ቤቶቻቸው ነጻነትና መብትን፣ፍትህን ያጎናጽፉናል በማለት እምነት በመስጠታቸው ከገጠማቸው አስከፊ የመከራ ዘመን ለመገላገል በቅተዋል፡፡ ሩዋንዳውያን አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ለደረሰባቸው ሩዋንዳውያን የገንዘብ ካሳ ከመክፈል  ይልቅ አትኩሮታቸው የነበረው ለወደፊቱ ህዝባዊ የኑሮ እድገት ላይ ነበር፡፡ ለአብነት ያህል አውራ ጎዳናዎችብ እና የህዝብ መኖሪያ ቤቶችን መገንባት ላይ በይበልጥ ትኩረት ሰጥተው ነበር፡፡ እንዲህ አይነት ውሳኔዎች ለህዝብ የሚጠቅሙ ፕሮዤዎች ገቢራዊ ከሆኑ የሩዋንዳን ህዝብ በአጠቃላይ፣የሰብአዊ መብት ጥሰት ለተፈጸመባቸው ሩዋንዳውያን በተለየ መልኩ ይጠቀማሉ ብሎ የሩዋንዳ መንግስት ያምን ነበር፡፡ሀገራቸው እንደገና ስትገነባ፣ስትታደስ ሩዋንዳውያን በአጠቃላይ ደስተኛ ነበሩ፡፡ይህ ማለት ግን አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው ሩዋንዳውያን ካሳ አላገኙም ማለት አልነበረም፡፡

አንዳንድ የምእራቡ አለም ምሁራን የየሩዋንዳን ባህላዊ ፍርድ ቤት አካሄድ የተቹም ነበሩ፡፡ ለአብነት ያህል የቦሰቶን ዩንቨርስቲ ምሁር የሆኑት ቲምሎንግ ማን .( Boston University scholar Tim Longman) የሩዋንዳ ባላዊ ፍርድ ቤት የጎሳ ልዩነት ሊያመጣ ይቻለዋል፡፡ ምክንያቱም በሩዋንዳ የአርበኞች ግንባርና ቱትሲስ ጎሳዎች የተፈጸሙ የብቀላ ጥቃቶችን በፍርድ ሂደቱ ስላልሸፈነ ነው በሚል ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የሩዋንዳ ምሁራን የተለየ አመለካከት ነበራቸው፡ የጠፋውን የሩዋንዳ ሰብአዊነት፣ሰላም፣ተከባብሮ አብሮ በሰላም ለመኖር፣አንድነት፣ በሩዋንዳውያን መሃከል ብሔራዊ እርቅ ለማውረድ ባህላዊው ፍርድ ቤት መተኪያ አልነበረውም ብለው ይከራከራሉ፡፡ ከዚህ ባሻግር የሩዋንዳ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በአስር አመት ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ መርምሮ ፍርድ መስጠቱ የሚያሳየን ጉዳይ ቢኖር ሩዋንዳውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መንገድ መፍታት መቻላቸውን ነው፡፡

…[T]ransitional justice in Rwandan experience has a record of enormous success if viewed from its angle of ultimate goals: a) to restore the lost Rwandan element of humanity, peace, co-existence, unity and reconciliation of Rwandans. [authors’ emphasis] … The establishment of Gacaca Courts that tried nearly two million suspects within ten years was not only impeccable but also a strong signal to Rwandans that solutions to their problems are within their means. 470 

ከዘር ፍጅቱ ጥቂት ግዜያት በኋላ አንዳንድ ለውጦች ቢኖሩም የችግሩን መሰረታዊ ችግር ለመፍታት እጅጉን አዳጋች ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የዘር ፍጅቱ ከተፈጸመ ሃያ አመታቶች በኋላ ሩዋንዳውያን የተፈጸመባቸውን አስከፊ ወንጀል ሳይረሱ ይቅር ለእግዛብሔር ተባብለው ከአይምሮ ጓዳቸው የጥላችን መንፈስ ለማስገወድ መንፈሳዊ ወኔ የታጠቁ ሲሆን፣አስደንጋጭ ወንጀል የፈጸሙ ሃላፊነቱን ወስደዋል፣ተጤቂም ሆነዋል፣ካለፈው ከባድ ስህተትም ተምረዋል፣በህሊናቸው ተመርተው የሚዋደድ፣የሚከባበር፣አንድነቱን የጠበቀ ሰላማዊ ዜጋ አንብረዋል፡፡

በእውነቱ ለመናገር ሩዋንዳውያን ያን ክፉ ግዜ አልፈው፣ሰላማዊ እና የተረጋጋ ህይወት ለመምራት መብቃታቸው ሲታሰብ የሞራልና መንፈሳዊ ልእልናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ሩዋንዳውያን ለቀሪው አለምም ሆነ ለአፍሪካ በተለይም በጎሳ በሽታ ተለክፈው ለሚሰቃዩ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ታላቅ ዩንቨርስቲ ናት፡፡ ከተማርንበት ማለቴ ነው፡፡ ሩዋንዳውያን ለዚህ የበቁት በመከባበር፣ግልጽነት ባህሪ በማሳየት፣በወንድማማችነት ስሜት እና አንቺ ትብሽ፣አንተ ትብስ በመባባል ነበር፡፡ እነርሱ ቂም በቀልን ወደ ጎን ትተው፣ ያለፈውንን በደል ሳይረሱ ይቅር ለእግዛብሔር በመባባለቸው ነው ዛሬ በአፍሪካ ተምሳሌታዊት ሀገር ለመገንባት የበቁት፡፡ ሩዋንዳውያን ጠንካራ መሪ እንደነበራቸውም ለአለም አሳይተዋል፡፡ ያለ ጠንካራ መሪ አንዲት ሀገር በረብሻና ተስፋ በቆረጡ ህዝቦች የተሞላች ናት፡፡ ፕሬዜዳንት ካጋሚ የሚታይና የሚጨበጥ ተግባር አከናውነዋል፡፡ አንዳንዶች ኪጋሚ ጠንካራ በመሆናቸው ምክንያት አንዳንዶች ሲተቿቸው ይስተዋላል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሊብራል ዴሞክራሲ በአንዳንድ ማህበረሰብ አኳያ ላይሰራ እንደሚችል ማወቁ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵውያን ሀኬተኝነት፣ቂመኝነት፣ጎሰኝነት፣ጥላቻና መናናቅ እንደማይጠቅመን አውቀን የህብረት ችቦ እንድንለኩስ እማጸናለሁ፡፡የያዝነው የጎሰኝነት መንፈስና መንገድ እንጦርጦስ  እንደመዶለን መገንዘብ አለብን፡፡ ጊዜ ሰጠን ብለን በወንድሞቻችን፣እህቶቻችን፣እናቶቻችን፣አባቶቻችንና ልጆቻችን ላይ የጥቃት ሰበዝ የምትመዙ የከንቱ ከንቱዎች ይህ ክፉ ድርጊታችሁ ዋጋ እንደሚያስከፍላችሁ በማወቅ ወደ ህሊናችሁ ትመለሱ ዘንድ እንማጸናለን፡፡ የጎሰኝነት መጨረሻው ፋሺዝም ነው፡፡ ፋሺዝም ደግሞ ፍጅት ነው፡፡ ልክ እንደ ሩዋንዳውያን ሁሉ በመጨረሻው ላይ ወደ እርቅ መመጣቱ አይቀርም፡፡ ወደ ሌላ፣ወደ ከፋ እልቂት ከመደረሱ በፊት አክራሪ ብሔርተኞች ( ጎሰኞች) ወደ ልቦናችሁ በመምጣት ከሩዋንዳውያን ወንድሞቻችሁ ትምህርት በመውሰድ በሰላም፣በአንድነት፣በመከባበር ስሜት ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችሁ ጋር አብራችሁ ህይወትን ትመሩ ዘንድ እንማጸናለን፡፡ ከዚህ አኳያ ፖል ኪጋሚ የሩዋንዳያንን የተጎዳ ልብ ለማከም፣ሽግግር ለማድረግ፣ ሚሊዮኖች ቀስበቀስ እንዲድኑ፣መከባበርና ግልጽነት በሩዋንዳ ምድር እውን እንዲሆን የካጋሚ ሚና ምትክ አልተገኘለትም ነበር፡፡

በአፍሪካ ውሰጥ ወደር በማይገኝለት መከራና ስቃይ ተዘፍቃ የነበረችው ሀገር ዛሬ በአፍሪካ ምድር በብዙ መልኩ በርካታ ሀገራትን በእድገት ቀድማ የምትገኝ ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡ ይህ መሆኑ እውነት ነው፡፡ ምክንያቱም ሩዋንዳውያን ጥላቻና በቀልን ገሸሽ በማድረግ መከባበርና በሰላም፣አብሮ ተቻችሎ መኖርን እውን በማድረጋቸው ነው ለዚህ የበቁት፡፡ ሁቱስና ቱትሲዎች (Hutus and Tutsis) ግንኙነት ያደርጉ የነበሩት ያለጥላቻ መንፈስ፣ አንድ ላይ በህብረት በመስራት እና እርሻ በማረስ፣ የማህበረሰብ ግዴታዎችን አብሮ ተባብሮ በመስራት መንፈስ በመሆኑ  ህዝቡ የደህንነት ስሜት እንዲሰማው ሆኗል፡፡ እርስበርስ የመፈራራት ስሜቱም ቀንሷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳላ ሩዋንዳ በሯን ለማናቸውም አልሚዎች በሯን ወለል አድርጋ ከመክፈቷም ባሻግር በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አኳያ የላቀ እድገት ለማመዝገብ በቅታለች፡፡ ዛሬ ሩዋንዳ በአፍሪካ ምድር ከሚገኙት ሀገራት ሁሉ ከቦትስዋና በመለጠቅ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማእከል ሀገር ተብላ ለመጠራት በቅታለች፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩዋንዳ በአፍሪካ ውስጥ ካሉት ሀገራት ሁሉ ሙስና ያልተስፋፋባት ሀገር ናት፡፡ ህዝቧ ትኩረቱ በእድገትና ብልጽግና ላይ ነው፡፡ ወደ ኋላ ሄዶ ለመብሰለሰል ጊዜ የላቸውም፡፡ ምንም እንኳን በኡጋንዳ ድንበር አካባቢ አንዳንድ የኢንተርሃምዌይ አቀንቃኞች ቢኖሩም አብዝሃው የሩዋንዳ ህዝብ የህብረት ችቦ ለኩሶ በእድገት ጎዳና ላይ መንጎድ ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ በነገራችን ላይ የታላቁ ሀይቅ አካባቢ ሀገራት የተወሳሰበ የጸጥታ ችግር ያለበት ነው፡፡ ሩዋንዳ ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ኡጋንዳና ቡርንዲ ያላት ችግር በፍጥነት መወገድ ያለበት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ምንም እንኳን የኪጋ አስተዳደደር በብዙ መልኩ የሚተች(  በተለይም አምባገነን ባህሪው ማለቴ ነው) ቢሆንም በሚከተሉት ተግባራቱ የሚመሰገን ነው፡-

 • ያለምንም ማገነን የሀገሪቱን ጸጥታ ማስከበር ችለዋል፡፡ ሌላ ግጭት በዛች ሀገር ላይ ዳግም እንዳይከሰት በማድረጋቸው ታሪክ ስፍራውን አይነሳቸውም
 • ጥቂት የአፍሪካ መሪዎች ናቸው እንደ ኪጋሊ የሀገራቸውን ጸጥታ ማስጠበቅ የቻሉት
 • እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በታህሳስ 2018 የወጣው ታወቂው ፎርቤስ ሜጋዚን የአፍሪካ በአደረጉት ታላቅ ስራ የአመቱ የአፍሪካ  መሪ በማለት ሰይሟቸዋል ፡፤
 • በአፍሪካ የንግድ እንቅስቃሴ አሸናፊ የሚያደርጋቸውን ልእለ ስራ በሩዋንዳ እንዲከናወን አመራር ሰጥተዋል ( ሩዋንዳን በእድገት ጎዳና እንድትገሰግስ አመራር ሰጥተዋል)
 • ሩዋንዳ በኪጋሚ አመራር ከመከራና ሀዘን ለመውጣት ችላለች

እውነታና እርቅ አፈላላጊ ኮሚቴ በሌላው የአለም ክፍል

በደቡብ አፍሪካና ሩዋንዳ የተካሄደውን የእውነታና እርቅ አፈላላጊ ኮሚቴ ስናወዳድር የምናገኘው ትምህርት ግልጽ ይመስለኛል፡፡ ሁለቱም ሂደቶች በአብዛኛው የነበራቸው አላማ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ውጤታቸው በጣም የተለያየ ነበር፡፡ በእኔ የግል አስተያየት በርካታ ትችትና አስተያየት ቢሰጥበትም ከደቡብ አፍሪካ ሪፐብሊክ ይልቅ በሩዋንዳ ተካሂዶ የነበረው የእውነታና እርቅ አፈላላጊ ሂደት የበለጠ ውጤታማ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡

 በሩዋንዳ እውነቱ በግልጽ ተነግሮ ነበር፡፡ ( መቶ በመቶ ትክክክል ነው ባይባልም) ተጎጂዎች  እና ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ባሉበት እውነቱ ተነግሯል፡፡ ከዚህ ባሻግር ፍትህ በሩዋንዳ ባህላዊ ፍርድ ቤት፣በሩዋንዳ የፍርድ ስርአት፣ በአለም አቀፉ የፍርድ ቤት  (through the ICTR)፣በታንዛኒያ አሩሻ ልዩ ፍርድ ቤት (special tribunal in Arusha) አመሃኝነት ፍትህ ለግፉአን ሩዋንዳውያን ተሰጥቷል፡፡ በደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክ ወንጀል የፈጸሙ ሁሉ ለፍርድ አልቀረቡም፡፡ አፓርታይድ ስርአት ለአራት የከፈላቸው ደቡብ አፍሪካውያን ( ነጮች፣ኢንዲያንስ፣ከለርድ እና ጥቁሮች) ሁሉም አንድ ላይ ያካሄዱት ብሔራዊ እርቅ ውጤታማ አልነበረም ፡፡ ሩዋንዳ በሌላ በኩል የተሳካ ታሪክ አስመዝግባ ነበር፡፡ ስለሆነም ቀሪው አለም ተጨማሪ እውነት ያስፈልገዋል፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉት ሀገራት እውነት መውጣት አለበት፡፡

የእውነታና እርቅ አፈላላጊ ኮሚቴ በትክክለኛው መንገድ መሰራት አለበት

ባለፉት ሶስት አስርተ አመታት ውስጥ በአለም ላይ ካናዳን፣ቺሊ፣ኢኳዶር፣ጋና፣ጓቲሟላ፣ኬንያ፣ሩዋንዳ፣ጋምቢያ፣ላይቤሪያ፣ሞሮኮ፣ፊሊፒንስ፣ሴራሊዮን፣ደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክ ደቡብ ኮሪያን ጨምሮ ከ40 በላይ በሆኑ ሀገራት ውሰጥ ተቋቁሟል፡፡ ሬስትሮቲቭ ፍትህ ከሪትሪቢዩቲቭ ፍትህ በተሻለ ፍትህን እንደሚያስገኝ የኑርመበርግ ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደት ታሪካዊ ምስክር ነው፡፡

ከዚህ ትርጉም ባሻግር በኢትዮጵያ  እንዴት የሽግግር ፍትህ ማስፈን ይቻላል ? እስቲ በያካባቢያችሁ ተወያዩበት ሰላም ፡፡ Beyond definitions, how would transitional justice look in the case of Ethiopia? Emphasis would be given to four elements: 

እንደ መደምደሚያ

‹‹ ጥንታዊቷንም፣ የዛሬዬቷን ኢትዮጵያችንን የወደፊትም እንድትሆን ካስፈለገ በቅን መንፈስ በፍቅርና በመተባበር ደግፈን እናዘልቃለን ብለን ካልተነሳን በቀር በአሉባልታና በመቃቀፍ በሐሰት በመነዳትና በወሬ በመሰልጠን በንጹሁና በተባረከውም ህዝቧ ተንኮል በመዝራት እንዲሁም በሰው ሀገር ጉዳይ ውስጥ እየገቡ አሳቢ በመምሰል የሕዝቧን መነጣጠል ለሚገፋፉ ባእዶች ደጋፊና ተባባሪ ሆኖ በመገኘት ጥቅም ይገኛል ብሎ የሚያስብ ቢኖር በተሳሳተ መንገድ መሄዱን ይረዳው፡፡ ከእንደዚህ ያሉም ሰባኪያን መራቅ የማንኛውም ሀገሬን እወዳለሁ የሚል ሰው ጥንቃቄ  መሆን አለበት፡፡

        ‹‹ አውቀን እንታረም ገጽ 16-17 ››

       ‹‹ ሌ/ ጄሜራል ዐብይ አበበ ››

በመጨረሻም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ውይይት የምታደርጉ የፖለቲካ ሃይሎች አመራሮች ሁሉ የምታደርጉት ምክክርም ሆነ ብሔራዊ ወይም ብሔራዊ የውይይት መድረክና ብሔራዊ እርቅ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ እንዲሆን መንፈሳዊ ወኔ ትታጠቁ ዘንድ በማስታወስ እሰናበታለሁ፡፡ ሰላም

የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ.ም.

Filed in: Amharic