“. አልወለድም”ን አምጦ የወለደልንን ማን ገደለብን? እንዴትስ ሞተ?
(በጥበቡ በለጠ)
ቀኑ ቅዳሜ ምሽት ነው፡፡ ወሩ የካቲት አንድ 1972 ዓ.ም ቦታው ደግሞ ጐጃም በረንዳ አካባቢ፡፡ ኢትዮጵያዊ ታላቅ የጥበብ ሰው አቤ ጉበኛ ቀበሌ 34 አካባቢ ከአስፋልቱ ዳር ተዘርግቶ ወድቋል፡፡ ጐጃም በረንዳ አካባቢ የሚኖሩ አቤን የሚያውቁ ሰዎች ተጠርተው መጡ፡፡ አቤ ‘‘አንሱኝ፣ አንሱኝ፣ ተጠቃሁ…’’ እያለ ያቃስታል፡፡ የመጡት ሴቶች ናቸው፡፡ ሊያነሱት ሞከሩ፡፡ ጐተቱት፡፡ ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡ ሌሎችም ተሰበሰቡ፡፡ ኃይል ሲገኝ አነሱት፡፡ ከዚያም የወሰዱት ሆስፒታል አልነበረም፡፡ አቤ ቀደም ብሎ ‘‘አርባ ምንጭ ሆቴል’’ የሚባል ሆቴል ውስጥ መኝታ ክፍል ተከራይቷል፡፡ እናም ወደ መኝታ ክፍሉ ወስደው አስተኙት፡፡
ሲነጋ ማለትም እሁድ ጠዋት ፖሊስ መጥቶ ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል ወሰዱት፡፡ ሆስፒታል ከገባ ከግማሽ ሰዓት በኋላ ዶክተሮቹ አቤ ጉበኛ መሞቱን አረጋገጡ፡፡ ‘ተጠቃሁ’ እያለ ሲያቃስት የነበረው አቤ ጉበኛ ማን መታው? ምን ሆኖ ሞተ?
ሞቱ ከተነገረ በኋላ ቀብሩ ታሰበ፡፡ ማን ይቅበረው? ከ20 መፃህፍት በላይ ያሳተመ ጐምቱ ደራሲ ቀባሪ አጣ፡፡ ማን ደፍሮ ሬሳውን ወስዶ ይቅበረው? ማዘጋጃ ቤት ሊቀብረው ዝግጅት ላይ ነበር፡፡ ነገር ግን ሲራክ ቀለመወርቅ የተባሉ ሰው ‘አቤን ቀበርሁና አልቀበርኩኝ ምን እንዳልኮን ነው ብዬ ቆርጬ ገባሁበት’ ብለው ገቡበት፡፡ በኋላም አስከሬኑ መመርመር አለበት ብለው በፖሊስ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ተወሰደ፡፡ ተመረመረ፡፡ ውጤቱ ምን ይሆን? አቤን ምን ገደለው?
ከምርመራው በኋላ አቤ ጉበኛ መቀበር አለበት፡፡ የጐጃም ወዳጆቹ ተባብረው አስከሬኑን ወደ ትውልድ ቦታው ወሰዱት፡፡ ከዚያም ማክሰኞ የካቲት አራት ቀን 1972 ዓ.ም በባህርዳር አውራጃ በአቸፈር ወረዳ ይስማላ ጊዮርጊስ ገዳም ተቀበረ፡፡ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ እጅግ ደማቅ ከሚባሉት ጥበበኞች መካከል አንዱ የሆነው አቤ ጉበኛ በምን ምክንያት ሞተ የሚለው ጥያቄ ሳይመለስ ለዘመናት ቆይቷል፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የገባውና የተመረመረው አስከሬኑም ውጤቱ እንዳይነገር ታፍኖ ለረጅም አመታት ተቀመጠ፡፡ በዘመኑ የነበሩት የፖሊስ መርማሪዎች ፖሊሳዊ ግዴታቸውን ሳይወጡ ቀሩ፡፡ በዚህም ታሪክ ይወቅሳቸዋል፡፡ የአቤ ጉበኛ ብዕር ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለሀገረ ኢትዮጵያ እድገትና ስልጣኔ የሚታትር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እሱ ሲሞት ደግሞ ሁሉም ዝም አለ! ሃቀኛ ደራሲ አድናቂዎች እንጂ ወዳጆች አይኖሩትም የሚለው የበአሉ ግርማ አባባል እውነት ነው፡፡ እናም የአቤ ጉበኛ ሞት ተደፋፈነ፡፡ ደሙን የሚጠይቅለት ጠፋ!
‘‘ኮከብ’’ የተባለ መጽሔት 1ኛ አመት ቁጥር 1 1985 ዓ.ም ላይ ያወጣውን ፅሁፍ ስለ አቤ ጉበኛ የህይወት ታሪክ የሚያወሳው መጽሐፍ ይዘክራል፡፡ እንዲህም ይላል፡፡
‘‘የልጆቹ እናት የልብስ ሻንጣውን ከ3ኛ ፖሊስ ጣቢያ በተረከቡበት ወቅት በግድያ ተጠርጥረው የታሰሩ ለጊዜው ማንነታቸው ያልታወቀ ሦስት ግለሰቦች እንደነበሩ ቢገለፅላቸውም ብዙም ሳይቆዩ ተጠርጣሪዎች በመንግስት ትዕዛዝ ተፈትተዋል፡፡
ከዚህ በኋላ ውሾን ያነሳ ውሾ ይሁን’’ ሆነና ቄሱም መጽሐፉም ዝም አሉ፡፡… እንዴት ሞተ? የሚለውን ጥያቄ ግን የትኛም ክፍል አላነሳም፡፡ ብቻ አልፎ አልፎ ሰዎች አፋቸውን አቀራርበው በሚኒሞ ማንሾካሾካቸው አልቀረም፡፡ ታዲያ ዙሪያቸውን በሚገባ ከቃኙ በኋላ ነው በዝቅተኛ ድምፅ ‘‘አቤን መንግስት ነው የገደለው’’ የሚሉት፡፡
የአቤ ጉበኛ ገዳይ በይፋ አልታወቅ አለ፡፡ እንደውም የደርግ ሊቀመንበር እና የሐገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም አደናጋሪ ንግግር አደረጉ፡፡ የአቤን ገዳይ እንዳይታወቅ ሆን ብለው መሸሸግ ፈለጉ፡፡ እናም ቅዳሜ ህዳር 27 ቀን 1973 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ህዝብ ንግግር ያደርጉ ነበር፡፡ ንግግሩ ደግሞ የተደረገው የኢትዮጵያ ህፃናት ቀን ሲከበር ነው፡፡ በንግግራቸው መሐል ስለ ሟቹ ደራሲ አቤ ጉበኛም ጣል አደረጉ፡፡ እንዲህም አሉ፡-
‘‘አብዮቱ ህፃናትን ከረሐብ፣ ከበሽታ፣ ከትምህርት ጥማት ብቻ ማስጣል ሳይሆን ከእንዲህ አይነቱ ርህራሄ ከሌለው ተፅእኖና የተሳሳተ አመለካከት ማዳን ይኖርበታል፡፡… በዚህ ረገድ ዛሬ ከመካከላችን የማይገኝው በጊዜው ተጨባጭ ሁኔታና ባለው ፀረ-ፊውዳላዊ አቋም ‘አልወለድም’ የተሰኘ ድርሰቱን ለኢትዮጵያ ህዝብ አበርክቶ የነበረውን የሟቹን የአቤ ጉበኛን አባባል ያስታውሰናል”
እያሉ መንግስቱ ኃይለማርያም ተናግረዋል፡፡ በቅኔ ሊናገሩ የፈለጉት እኔ አልገደልኩትም ነው፡፡ ግን አያሌ ማስረጃዎች የእርሳቸው መንግስት አቤን እንደገደለው ይመሰክራሉ፡፡ ምክንያቱም እንደ ኤልያስ አያልነህ ጥናት መንግስታዊ የሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ራሱ የአቤን ሞት በአጭር ዜና የዘገበው ከተቀበረ ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ነው፡፡ ለዚያውም በወቅቱ የነበረው የደራሲያን ማኀበር ባደረገው ውትወታ እና ጉትጐታ ነው ዜናው የተሰራለት፡፡
ለመሆኑ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ገብቶ የነበረው የደራሲ አቤ ጉበኛ የአስከሬን ምርመራ የት ደረሰ? ደርግ 17 አመታት ከገዛ በኋላ ወደቀ፡፡ ኢሕአዴግ ገባ፡፡ አዲስ መንግስት ተመሰረተ፡፡ ተዳፍኖ የኖረው የአቤ ሞት በልዩ ልዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ይፃፍበት ጀመር፡፡ ኤልያስ አያልነህ ደግሞ የአቤ ጉበኛን ብእራዊ ተጋድሎ በሰፊው ይሰራበት ገባ፡፡ አቤ ጉበኛ ከሞተ ከ19 አመታት በኋላ የዳግማዊ ምኒልክ የአስከሬን ምርመራ ውጤትን በመጽሐፉ አትሞት አወጣው፡፡ የአቤ አስከሬን ምርመራም ይፋ ሆነ፡፡ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የተተረጐመው ውጤት እንዲህ ይላል፡-
የሟች ስም፡- አቤ ጉበኛ ዕድሜ 41 ፆታ ወንድ
የሬሳ ቁጥር፡- 445/72 የምርመራው ቀን 3/6/72
ዜግነት፡- ኢትዮጵያዊ አድራሻ፡- አ.አ
የውጭ ሰውነት ምርመራ ውጤት፡- መጠኑ 3×4 ሴንቲ ሜትር ሆኖ የተቆረጠ ቁስል ግራ እግሩ ላይ ታይቷል፡፡ በቀኝ በኩል በሚገኘው የመሐል ጭንቅላቱ ቆዳ ላይ የተፋቀ ቁስለት አለበት፡፡ በቀኝ በኩል በሚገኘው የመሐል አንጐል ውስጠኛ ሽፋን ክፍሉ ስር 7x5x8 ሴንቲ ሜትር መጠን ያለውና ደም የቋጠረ እብጠት አለበት፡፡ አንጐሉ ውስጠኛ ሽፋን ክፍል ብዙ ደም አለበት፡፡ አንጐሉ አብጧል፡፡
በአጠቃላይ ለሞት ያበቃው፡- ስለት በሌለው (በድልዱም) መሳሪያ ጭንቅላቱ ላይ በመመታቱ ምክንያት ብዙ ደም የቋጠረ እብጠት ታችኛው አንጐል ሽፋን ክፍል ሥር በመከሰቱ ነው፡፡
አቤ ጉበኛ የተገደለው በሰው እጅ ነው፡፡ ያ ሰው ደግሞ ከደርግ መንግስት በተሰጠ ትዕዛዝ የፈፀመው እንደሆነ ይገመታል፡፡ ምክንያቱም አቤ ጉበኛ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ እስከ ደርግ አገዛዝ ድረስ እጅግ ሀይለኛ የሆኑ ፖለቲካዊ ፅሁፎችን እና ቴአትሮችን እየፃፈ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ መንግስታትን በድፍረት በመናገር፣ ለኢትዮጵያ ይጠቅማታል የሚለውን አስተሳሰቡን ምንም ሳይፈራ በግላጭ የሚፅፍ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ደራሲ ነው፡፡
አቤ ጉበኛ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ላይ የሰላ ሂስ በመሰንዘሩ ምክንያት በግዞት ወደ ጐሬ ተግዞ በስቃይ የኖረ ደራሲ ነው፡፡ በተለይ 1955 ዓ.ም ያሳተማት ‘‘አልወለድም’’ የምትሰኘው መጽሐፍ በንጉሱ ስርዓት ላይ ያለውን ጥላቻ ያሳየበት ነው፡፡ በዚህ ኢፍትሐዊነት ባለበት አገዛዝ፣ በዚህ አንዱ ተረግጦ፣ ሌላው ረግጦ በሚኖርበት ስርዓተ ማኀበር ውስጥ አልወለድም የሚልን ፅንስ መሠረት አድርጐ የተፃፈ ልቦለድ ነው፡፡ በዚህ ልቦለድ ውስጥ የአፄው ስርዓት ውስጥ የሚታዩ ጭቆናዎችና በደሎችን እያነሳ ያሳያል፡፡ እነዚህ ግፎች በተከማቹበት አገርና ማኀበረሰብ ውስጥ አልወለድም የሚልን አስገራሚ ገፀ-ባህሪ ፈጥሯል፡፡ ገፀ-ባህሪው እናቱ ማኀፀን ውስጥ ያለ ፅንስ ነው፡፡ መወለድ የለብኝም ብሎ የወቅቱን ፖለቲካዊ ትኩሳት ዝክዝክ አድርጐ የሚያሳይ ሥነ-ጽሑፍ ነው፡፡ ‘‘አልወለድም’’ በኢትዮጵያ የተቃውሞ ሥነ-ጽሑፍ ጐራ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆና የምታበራ የጥበብ ስራ ነች፡፡
እናም ይህች አልወለድም እና ሌሎቹም የድርሰት ስራዎቹ አቤን በግዞት እንዲሰቃይ ዋጋ አስከፍለውታል፡፡ አቤ ጉበኛ ትውልድን፣ መንግስትን፣ ህዝብን የሚነቀንቅ ሞገደኛ ደራሲ ነበር፡፡ ላመነበት ነገር የመጨረሻዋን የሞት ፅዋ ለመጐንጨት ፍፁም ወደ ኋላ የማይል የደራሲዎች አውራ ነው፡፡
ደርግ ከመጣ በኋላም የወታደሮች አገዛዝ ለሀገር አይጠቅምም፡፡ ወታደር አገርና ሕዝብን ነው መጠበቅ ያለበት፡፡ ወታደር የሲቪል አስተዳደር ውስጥ ገብቶ ማተራመስ የለበትም እያለ አቤ ስርዓቱን በግልፅ መቃወም ጀመረ፡፡ በ1968 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ፖለቲካና ፖለቲከኞች የተሰኘ ቴአትር ፅፎ ለመድረክ አበቃ፡፡ በዚህ ቴአትር ውስጥ የዘመኑን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሙልጭ አድርጐ የተቸበት ነው፡፡ ህይወቱን ሙሉ አሳልፎ የሰጠ ደፋር ፀሐፊ ነው፡፡ አቤ ሲፅፍ እንዲህ አለ፡-
‘‘ሕዝብን የምትጨቁኑበትን መንግስት በፍፁም እቃወማለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት ልትገድሉኝ ትችላላችሁ፡፡ ሞት ስትፈርዱብኝም የምፀፀት ይመስላችኋል፡፡ እኔ በዚህ ብፀፀት እንደ እናንተ ቂል ነኝ፡፡ መጥፎ ሥራችሁንና ህዝብን መጨቆኛችሁን የምትተው ካልሆነ መቶ ጊዜ እሞታለሁ፡፡ እንደገና ብወለድ፣ መቶ ጊዜ የገደላችሁኝ መሆናችሁንም ባስታውስ ይህ መቀጫ ሁኖኝ ዝም ልላችሁ አልችልም’’