>
5:16 pm - Thursday May 24, 5523

እምዬ ምኒልክ — የፈውስ ንጉሥ....!!! አሳፍ ሀይሉ

እምዬ ምኒልክ — የፈውስ ንጉሥ….!!!

አሳፍ ሀይሉ

 

‹‹መድኃኒት ጥቂቱ ይበቃል እያለች
የምኒልክ እናት አንድ ወልዳ መከነች….!!!››
እምዬ ምኒልክ፣ እነዚያ የአድዋ ጀግኖች ሁሉ፣ ጀግንነታቸው በጦር አውድማ ላይ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ በሠላሙም ጊዜ፣ ህልማቸውና ጥረታቸው ሁሉ፣ በሀገርና ህዝብ ፍቅር የተቃኘ ነበር፡፡
እምዬ ምኒልክ፣ ከአድዋው ከአንፀባራቂ ድል መልስ፣ ሀገራችንን ኢትዮጵያን በዘመናዊ አቅጣጫ ለማሳደግ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ ከእነዚህም መስኮች አንደኛው ዘመናዊ የህክምና ጥበብን ወደ ለገራቸው ሕዝብ ማስተዋወቃቸው ነው።
በአድዋ ጦርነት የቆሰለው በአስር ሺህዎች የሚቆጠር ሕዝብ ነበር። ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ሰው፣ የምኒልክን አዋጅ ተከትሎ ከየገጠር ጎጆው ምስስ ብሎ የከተተ የሠላም ጊዜ ቀዳሽ፣ የጦርነት ጊዜ ወታደር ሆኖ የሚያገለግል፣ ቢቆስልና አካሉ ቢጎድል አንዳች መጦሪያና ጥሪት የሌለው ምስኪን ሀገሩን ወዳድ ህዝብ ነበር።
ታዲያ እምዬ ምኒልክ ይህን ለሀገሩ በሁለመናው ውለታ የዋለ ሕዝባቸውን፣ ከገጠመው የጦርነት ጉዳት ለመፈወስ ያደረጉት ጥረት ሁልጊዜ በአንድናቆት በታሪክ ሊወሳ የሚገባው ነው፡፡
እምዬ ምኒልክ አድዋ ሲዘምቱ፣ ኢትዮጵያችን ውስጥ፣ ባለፍ ገደም ከውጭ ለምልክት ከሚመጡ የፈረንጅ ሃኪሞች በቀር፣ ይህ ነው የሚባል ዘመናዊ ሃኪምም፣ ዘመናዊ ህክምና መስጫ ተቋሙም አልነበረም፡፡
ዘመናዊ ህክምና፣ በቂ መድሃኒት፣ በቂ ጦርሜዳ-ወለድ ህመሞችን ማስታገሻና ማገገሚያ የሚሆን አንድም የህክምና ማዕከል ባልነበረበት ሁኔታ ነው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ላገሩ ነፃነት ሲል ለመስዋዕትነት (እና ለህመምና ስቃይ) ራሱን አሳልፎ የሰጠው፡፡
ያን መርሳት ጀግኖች አባቶቻችንን የመስዋዕትነት ልክ ማሳነስ ነው፡፡ ውለታቸውን ስናስብ ሃኪምና ማስታገሻ መድሃኒት ያልነበረውን ህመማቸውን፣ ሥቃያቸውን ማሰብ የግድ ይላል፡፡ ጀግኖቻችን ለዘለዓለም ይክበሩ!!
እምዬ ምኒልክ ይሄ የህዝባቸው ቁስል ውስጣቸው ድረስ ዘልቆ የጠዘጠዛቸው ንጉሥ ናቸው፡፡ እና በቻሉት ሁሉ የዘመናዊ ህክምናን ለህዝባቸው አስተዋውቀዋል፡፡ የህክምና ተቋማትን ተክለዋል፡፡ እና ህዝባቸውን ፈውሰዋል፡፡ እምዬ ምኒልክ – የኢትዮጵያ እናት፡፡ የፈውስ አባት፡፡
ምኒልክ ዘመናዊ ህክምናን “ሀ” ብለው ያስገቡት በአድዋ ዘመቻ ወቅትና ከአድዋ ማግሥት ጀምሮ ነው።  በመጀመሪያ ለአድዋ ቁስለኞች፣ ቀጥሎም ለመላ ኢትዮጵያውያን ለማዳረስ በማለም የተጻጻፏቸውን ቁጥራቸው ከ20 በላይ የሚሆኑ ኦፊሴላዊ ደብዳቤዎች ያየ በምኒልክ አሳቢነት እጅግ መደነቅ አይቀርለትም።
ሌላው ሁሉ ቢቀር፣ እነዚያ የመልዕክት ልውውጦች ብቻ፣ ስለ እምዬ ምኒልክ ሰብዓዊ ማንነት ለትውልድ ሲመሰክሩ የሚኖሩ ማስረጃዎች ናቸው።
ምኒልክ ለሀገራችን የመጀመሪያ የሆነውን የህክምና ቡድን ያስመጡት ከሩሲያ ነው። ከሩሲያ መንግሥት ጋር በጥብቅ ተወዳጅተው። ያለመታከት ደጅ-ጠንተው።
ወደ ኢትዮጵያ ያስመጡት የመጀመሪያው የሩሲያ የሐኪሞች ቡድን፣ በዛር ኒኮላስ መልካም ፈቃድ በ1888 ወደ ኢትዮጵያ የተላከው፣ ሰባት ሃኪሞች ያሉት ቡድን ነበር።
በጄኔራል ኒኮላዎስ ሸዊደው የሚመሩት እነዚያ ሰባት የሩሲያ ሃኪሞች፣ በቀይ መስቀል ሥር የመጡ ነበሩ። ዋነኛ ተልዕኳቸው በአድዋ ጦርነት የቆሰሉብንን ኢትዮጵያውያን ለማከም ቢሆንም፣ በርከት ያለ መድኃኒትና የህክምና መርጃ ቁሳቁሶችን ይዘው ነው የመጡት።
ሃኪሞቹ ለጥቂት ወራት ቆይታቸውን አራዝመው፣ ከጦርነቱም ውጭ ለነበሩም ኢትዮጵያውያን ጭምር፣ የህክምና አገልግሎታቸውን ሰጥተዋል።
ከእነዚህ የሩስኪ ሃኪሞች መሐል ሮድዝቪች፣ ብሮቭስቲን፣ ግሊንስኪ፣ ፔርፊሊኖፍና ያክሳቢክቭስኪ የተሰኙት ሀኪሞች ስማቸው ጎልቶ ይታወቅ ነበረ፡፡ በመጨረሻ በእምዬ ምኒልክ ለያንዳንዳቸው ለአገልግሎታቸው ዕውቅና ስጦታ ተበርክቶላቸው፣ በክብር ወደሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡
እዚህ ላይ ምኒልክ በአድዋ ለቆሰሉ ዜጎች የነበራቸውን የእናት-የአባት የመሠለ ልዩ ቅርበትና መቆርቆር የሚያሳየውን አንድ አስገራሚ ነገር ሳልጠቅስ ባልፍ ቅር ይለኛል።
እምዬ ምኒልክ፣ ለእነዚያ ለወራት በቀይ መስቀሉ የህክምና ማዐከል ለተኙ የአድዋ ጦርነት ቁስለኞች (ለበሽተኞች በሙሉ) በየዕለቱ ምግብ ተዘጋጅቶ እንዲሄድላቸው ያደረጉት፣ ከራሳቸው የቤተመንግሥት ወጥቤት ነበር። በየቀኑ እሳቸው የሚበሉትን ለቁስለኞቻቸው እያበሉ፣ በጦርነትም በሠላምም ሕዝብ የመሩ ደግ፣ የደግ ደግ፣ ንጉሥ ማን እንደ እምዬ!!!!
ሥራቸውን ያየ አዝማሪ፣ እንዲህ እያለ ገጠመላቸው፡-
‹‹መድኃኒት ጥቂቱ ይበቃል እያለች
የምኒልክ እናት አንድ ወልዳ መከነች፡፡
ጥንትም ጠቢብ ነበር ሠሎሞን አባቱ
ምኒልክ በለጠ ሰው ይዞ መብላቱ፡፡››
በመጨረሻ አካባቢ ግን የህዝቡ ቁጥር በዝቶ ከቤተመንግሥት እስከ ሃኪምቤት ድረስ ውሃና ስንቅ ማመላለሱ እጅግ አዳጋች እየሆነ በመምጣቱ፣ እና ሃኪምቤቱም በብዙ ቁሳቁሶች ራሱን እንዲችል ብርቱ እገዛ ስላደረጉለት፣ እዚያው ሐኪም ቤቱ ክልል ውስጥ ማድቤት ተሠርቶ ለህመምተኞችና ለሃኪምቤቱ ሠራተኞች ምግብ እንዲበስልላቸው ይደረግ ጀመር፡፡
እንዲህም ሲደረግ እኮ ምኒልክ የራሳቸውን የቤተመንግሥት የወጥቤት፣ የግምጃቤት፣ የጥበቃና ሌሎችም አስፈላጊ ሰዎችን ሁሉ መድበው እኮ ነው፡፡
ለሩሲያኖቹ የቀይመስቀል ሃኪምቤት ከተመደቡት የምኒልክ እልፍኝ ሠራተኞች መሐል፣ የቤተመንግሥት ወጥ ቤት የነበረችው ወይዘሮ አስካለ አጎ – ስሟና ጣት የሚያስቆረጥም ሙያዋ – በሩሲያኖቹ የህይወት ታሪክ መፅሐፍ ሳይቀር ተጠቅሶላት እናገኛለን፡፡ በሙያዋ እስከ መስኮብ ስሟ የተጠራው አስካለ አጎ፣ የቤተመንግሥት የጥበቃ ዘብ የነበረው፣ የአቶ ተመቸ ባለቤት ነበረች፡፡
ሌሎችም በእምዬ ምኒልክ መልካም ፈቃድ ከቤተመንግሥት የተዘዋወሩ የህክምና ማዕከሉን ግቢ በዘበኝነት ተመድበው የሚጠብቁ ስማቸው ለታሪክ ተከትቦ ይገኛል። አንዳንዴ ያስቀኛል የግለሰቦች ስም ሳይቀር ተፅፎ ለታሪክ መዋዕል የሚቀመጥበት ልማድ።
በዚያ ዝርዝር ውስጥ አቶ የምሩ ቱፋ በተባሉ የሥራ ኃላፊ ሥር ከሩሲያውያኑ ጋራ የሚሠሩ አቶ ሰናድር ጉሌ፣ አቶ ነፋቀና አቶ ተመቸ የሚባሉ ኢትዮጵያውያን ስማቸው ተጠቅሷል፡፡ የግምጃ ቤት ሹም የነበሩት አቶ ነመዋቅ፣ እንዲሁም በምኒልክ ለማዕከሉ የተመደቡ አራት የቤተመንግሥት ውሃ ቀጂ ሴቶችም ስም ከሃኪም ቤቱ ታሪክ ጋር ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡
ጉድ እኮ ነው! የዘንድሮ አወቅን ባይ ቆራጣ ምሁራን፣ የነገሥታቱ ታሪክ የሰፊውን ሕዝታሪክ አይወክልም እያሉ በየአጋጣሚው ሲደነፉና የከበረ ታሪካችንን ሲያጣጥሉ ሳይ እስቃለሁ። አለማወቅ የሚሠጠውን ድፍረት ያህል የሚሠጥ ሌላ ነጠር በበኩሌ አጋጥሞኝ አያውቅም።
አለማወቅ ደፋር ያደርጋል። ደፋሮች የምኒልክን ታሪክ የነገሥታት ታሪክ ሲሉት፣ ምኒልክ በበኩላቸው የወጥቤትና የዘበኛ፣ የዕቃግምጃ ቤት ሠራተኛና የውሃ ቀጂን ስምና ታሪክ ፅፈው አስቀምጠውላቸዋል።
እዚህ ላይ የእቴጌ ጣይቱም ሚና የሚረሳ አይደለም። ለአድዋ ቁስለኞች ማረፊያ የሚሆኑትን ታዛዎች ራሳቸው እቴጌይቱ በቀጥታ ኃላፊነቱን ወስደው በሃኪምቤቱ ድንኳን አስተክለው ቀኑን ሙሉ ሲለፉ ውለው ማታ ወደ ቤተመንግሥታቸው እንደሚመለሱ፣ እማኝ የውጪ ጸሐፊያን በከተቡልን የታሪክ ማሰታወሻዎች ተጠቅሶላቸው የምናገኘው ነው፡፡
ምኒልክና ጣይቱ ብቻም ደግሞ አይደሉም፡፡ በወቅቱ ከአድዋ ጦርነት በህይወት ተርፈው የመጡት የምኒልክ መኳንንት ሁሉ፣ ያለመታከት በየፊናቸው ተሰልፈጉዳት የደረሰባቸውን ቁስለኞቻቸውን ለማሳከምና ከስቃያቸው ለመገላገል፣ የቻሉትን ሁሉ ርብርብ አድርገዋል፡፡
የአባት የአያቶቻችን። እነዚያ ሳይማሩ የተማሩ። ውብ አስተዋይ ልብን የታደሉ መሪዎቻችን። ታሪካቸው ያኮራል፡፡ ለወገን የነበራቸው መንሰፍሰፍ፡፡ የወገንን ህመም እንደራሳቸው ተሰምቷቸው የሚይዙ የሚጨብጡት እንዴት እንደጠፋቸው፣ ያልሆኑት ነገር እንደሌለ፣ ስንት እጅግ ልብ የሚነካ ታሪክ አውርሰውናል! የሚያነበው። የሚያውቀው። የሚረከበው ሲኖር ነው ግን ልፋታቸው ዋጋ የሚኖረው።
ደግሞ ጥሩን ነገር ሲቀባበሉስ? ለምሳሌ በአዲስ አበባ እምዬ ምኒልክ ለአድዋ ቁስለኞችና ከህዝቡ መሀል በሌላም በሽታ ለተጠቁ ህመምተኞች ያደረገትን መልካም ሥራ ሁሉ በሐረርም ደግሞ በልዑል ራስ መኮንን ተደግሞ እናገኘዋለን፡፡
ልዑል ራስ መኮንንም ያልተቆጠበ ተመሳሳይ እገዛና ጥረት አድርገው የሩሲያ ቀይ መስቀል ሃኪምቤት የተወሰነ ቡድን በጂቡቲ-ድሬዳዋ በኩል ወደ ሐረር ገብቶ ጊዜያዊ የህክምና ጣቢያ እንዲቋቋምና ብዙ ኢትዮጵያውያን ቁስለኞች ዘመናዊ ህክምናን በወቅቱ እንዲያገኙና ከህመማቸው እንዲድኑ አድርገዋል፡፡
በሩሲያ የታሪክ ጸሐፊዎች በአኀዝ ተጠቅሶ ከምናገኘው የፈውስ ገድል ጥቂቱን እንመልከትና እናብቃ፡፡ ሩሲያውያኑ የህክምና ቡድኖች በማስታወሻዎቻቸው በዝርዝር ከመዘገቧቸው አሃዞች መሐል ከአድዋ መልስ በሁለት ወራት ብቻ በአዲስ አበባና በሐረር በሩሲያኖቹ ሃኪሞች የሕክምና አገልግሎት ያገኙ ቁስለኞችን ብዛት የሚያሳየው ሰነድ አንዱ ነው፦
በሐረር = 15 ሺ 955 ሰዎች፣
በአዲስ አበባ = 18 ሺ 919 ሰዎች
የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና ተደርጎላቸውና ምክር ተለግሷቸው ለቤታቸው እንደበቁ ተመዝግቦ እናገኛለን። በቋሚነት ተኝተው፣ እና በተመላላሽ የታከሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ፦
በሐረር  =  ለ7 ሺ 819፣
በአዲስ አበባ =  ለ5 ሺ 237፣
ሰዎች የቀዶ ህክምናና ብርቱ የህክምና አገልግሎቶች እንደተሰጣቸው በሩሲያኖቹ መዛግብት ላይ ሰፍሯል። ደግሞ ብሶባቸው ለተኙ፦
በሐረር = ለ151 ሰዎች፣
በአዲስ አበባ = ለ75 ሰዎች
ሙሉ ህክምና እንደተሰጣቸው የሃኪምቤቱ መዝገብ ያስረዳል፡፡
በወቅቱ ፔትሪ ቩሴፍ የሚባል የህክምና ተማሪ ዋና ዋና የበሽታ ዓይነቶችንና ጠንቃቸውን የሚገልጽ አጭር መጽሐፍ አዘጋጅቶ፣ የወቅቱ የምኒልክ አስተርጓሚ በዛብህ ኤልያስ ወደ አማርኛ እንዲመልሰው እንደተደረገና ለህዝብ ተሰራጭቶ ብዙዎች ስለጤና አጠባበቅ መሠረታዊ ግንዛቤን እንዳገኙበት ተጠቅሶ ስናይስ ምን እንል ይሆን?!
መገረማችን አይቀርም፡፡ የእውነት እምዬ ምኒልክ፣ ራስ መኮንን፣ እና ሌሎቹም ያገራችን ዘመናውያን አባቶች የ19ኛው ክፍለዘመን መሪዎች ሳይሆኑ፣ ዘመናቸውን ቀድመው የተሻገሩ የ21ኛው ክፍለዘመን ባለ ብሩህ አዕምሮና ራዕይ መሪዎች እንደነበሩ እንረዳለን፡፡
አጼ ምኒልክ ለቆሰለ ለታመመ ወገናቸው ይህን ሁሉ አድርገውም ግን “በቃኝ ሠራሁ” ብለው ረክተው ሲቀመጡ አናገኛቸውም፡፡
ደግሞ ሃኪምቤት መድረስ አቅቶት በየቤቱ ስለቀረው ሰው ሲጨነቁ፣ እና ሩሲያኖቹ ጥቂት ሰንብተው ለእነዚያም መምጣት ላልቻሉት ኢትዮጵያውያን ህክምና እንዲለግሱላቸው ሲማጸኑ እናገኛቸዋለን፡፡
በአንዱ ደብዳቤያቸው እምዬ ምኒልክ ገና እርዳታ ያላገኘ ብዙ ኢትዮጵያዊ በየአቅጣጫው እንዳለ ገልጸው ጥቂት ሀኪሞችን እንዲያስቀሩላቸው የሩሲያውን የሃኪሞች አዛዥ ጀኔራል ሸዊደውን ሲማጸኑ እናገኛለን፡፡ ታሪክ ዘግቦት እንደምናየው ተማፅኗቸው ውጤት አግኝቶ ለብዙ በመጓጓዣ ዕጥረት የተነሳ ዘግይተው አዲስ አበባ ለደረሱ ዜጎች ፈውስን ማዳረስ ተሳክቶላቸዋል፡፡
አንዱ የምኒልክ ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡-  
‹‹ይድረስ ከትልቁ የመስኮብ ቀይ መስቀል እንደራሴ
ኒኮላ ሸዊደው፡፡ ሰላምታየን እልካለሁ፡፡
ከአንተ ጋራ የመጡ ሐኪሞች ሥራቸውን እጅግ
ስላሳመሩ ብዙ ደስ አሰኙኝ፡፡ ነገር ግን ቁስለኛው
ሁሉ እስከ ዛሬ ድረስ ክረምቱን ፈርቶ ሳይገባልኝ
ስለቀረ ሦስት ሐኪሞች ወር ያህል ከኔ ጋር
እንዲቀሩ ማድረግ ቢመችህ እጅግ ደስ ይለኝ ነበር፡፡
የተቻለህን ሁሉ እንደምታደርግ አልጠራጠርም፡፡
የተመኘሁት እንዲሆንልኝ ብዬ ተስፋ አለኝ፡፡
መስከረም 24 ቀን አዲስ አበባ ከተማ ተጻፈ 1889 ዓ.ም.፡፡››
     (- የደብዳቤውን ኮፒ ለማየት ለፈለገ፣ ከፕ/ር ስርግው መፅሐፍ ፎቶው ሰፍሮ ይገኛል።)
የምኒልክ ዋና ዓላማ የቆሰለ ወገንን አሳክሞ እፎይ ማለት የመሠለው ካለ ምኒልክን በሚገባ አላወቃቸውም ማለት ነው። የእምዬ ዋና ጭንቀት የመስኮቦች ቀይ መስቀል ሥራውን ጨርሶ ወዳገሩ ሲሄድ፣ እርሱን የሚተካና ህዝቤን በቋሚነት የሚያክምልኝ ዘመናዊ ሃኪምቤት እንዴት ባደርግ አገኛለሁ የሚል ነበር፡፡
በመስኮቦቹ ቀይመስቀል ማህበር ሃኪምቤት ፈንታ፣ ተመሳሳዩን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል መታከሚያ አቋቁሞ የፈውስ አገልግሎቱን ለህዝቡ ማበርከቱን እንዲቀጥል ለማድረግ ነበረ ህልማቸው ሁሉ፡፡
በዚህም ሀሳብ ላይ ጀኔራል ሸዊደው ስለተስማማ አንድ ዋና ሀኪም፣ ሁለት ረዳት ሃኪሞች፣ አንድ አስታማሚና አንድ አስተርጓሚ ኢትዮጵያ ላይ እንዲቀሩ አድርጎላቸው ወዳገሩ ሄዶዋል፡፡
ይህን አጋጣሚ በመጠቀም አጼ ምኒልክ ለጄነራል ሸዊደው ከጻፉት ሰፋ ያለ የደብዳቤ መልዕክት፣ ምስጋናቸውንና በልባቸው ያሰቡትን ውጥን ያሰፈሩባትን የመግቢያ ክፍል ብቻ መርጬ አቅርቤ እሰናበታለሁ፡፡ እንዲህ ይላሉ እምዬ ምኒልክ፡-
‹‹ይድረስ ለክቡር ጀኔራል ኒኮላ ሻዊደው
የመስኮብ መንግሥት ቀይ መስቀል
ማኅበር አለቃ፡፡ ወዳጃችን ጀኔራል ሆይ!
ከብዙ ብልሃት ከሚያስደንቅ ብልሃት ጋር
የመስኮብ መንግሥት የቀይ መስቀል
ማኅበረተኞች ቁስለኞቻችንን በሽተኞቻችንን
አስታማችሁ ስለ አዳናችሁልን ከእርስዎም
ጋራ የመጡትን የቀይ መስቀል ማኅበረተኞች
ሐኪሞችና የሐኪም ረዳቶች በኔና በሠራዊቱ
ስም በብርቱ አመሰግናለሁ፡፡
‹‹እግዚአብሔር ያመስግናችሁ፡፡ ደግሞም
ለቀይ መስቀል ማኅበረተኞች የሚገባውን
ሁሉ መሣሪያ የሚያስፈልግ መድኃኒት ሁሉ
ትታችሁ መሔዳችሁን አይተን የተደነቀው
አሳባችሁን አስተውለን እናመሰግናችኋለን፡፡
አሁንም የኢትዮጵያ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ
የመስኮብን መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ ተክቶት
የቀይ መስቀል ማኅበር አጠገብ ስፍራውን
ስለያዘ የሁላችሁም ነገር በልባችን ታትሟል
እንጂ አልተለያችሁትም፡፡…››
ብቻ ይገርሙኛል እምዬ፡፡ ይገርሙኛል በዚያን ጊዜ የነበሩ አርበኞች አባቶቻችን፡፡ ምን ያህል ልባሞች ነበሩ፡፡ ምን ያህል አርቆ አስተዋዮች እንደሆኑ፡፡ ምን ያህል አርቆ አሳቢ፣ ለወገን ተቆርቋሪ፣ ደስታቸው በሕዝባቸው ደስታ ላይ ያረፈ! ግሩም ድንቆች፡፡
ምኒልክ ከአድዋ መልስ ጥቂት ሃኪሞች ቀርተው በኢትዮጵያ ምድር ህክምና እንዳይቋረጥ አደረጉ፡፡ ከዚያም ኢትዮጵያውያን ዘመናዊ የህክምና ጥበብን እንዲቀስሙላቸው አደረጉ፡፡ እነዚያ በሩሲያ በተለያየ የህክምና ሙያ ሠልጥነው መጡና ሕዝባቸውን ማገልገል ጀመሩ።
በወቅቱ በውጭ ሀገር ሰዎች ላይ ያለው የህዝቡ እምነት ገና ሥር ያልሰደደ ስለነበረ፣ በራሱ የሀበሻ ዘመናዊ ሀኪሞች እጅ የመታከሙን ብሥራት በደስታ ነበር የተቀበለው ህዝቡ፡፡
እምዬ ምኒልክ በ1903 ዓ.ም. በኢትዮጵያችን የመጀመሪያውን የህዝብ ሀኪም ቤት የሆነውን “ምኒልክ ሆስፒታል”ን አቋቋሙ። በዋና ሃኪምነትም ሆስፒታሉን ምራ ብለው፣ የራሳቸው ሃኪም የነበረውን የጉዋዳሉፕ ተወላጅ፣ የፈረንሳይ ዜጋ ጥቁር ሃኪም የነበረውን፣ ዶክቶር ቪታሊየን የሚባለውን ቀጠሩ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ዶክተር ጋርጊዮና ዶክተር ሄርሜኒየር የተባሉ ሁለት ሃኪሞችም ተቀጠሩ፡፡
እነዚህና፣ ሌሎች እምዬ ምኒልክ ሩሲያ ልከው ያስተማሯቸው ኢትዮጵያውያን ሀኪሞች ነበሩ ዘመናዊ ህክምናን ለሀገራችን ሕዝብ ያስፋፉት፡፡ ይህን ታሪክ ዶክተር ሜራብ ቪታሊየን ‹‹ሐኪሞችና ሕክምና በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ በፈረንሳይኛ ቋንቋ በጻፈው መጽሐፍ ላይ በዝርዝር አስቀምጦት እናገኛለን።
የሚያሳዝነው ግን በአድዋ ማግስት ሰለቸኝ ደከመኝ ብለው ሳይቀመጡ፣ ለሕዝባቸው የዘመናዊ ህክምና ፍላጎት መሟላት ቀን ተሌት የተጉት እምዬ ምኒልክ – በሚያሳዝን ሁኔታ የልጅ ልጃቸውን ወሰን ሰገድን በበቂ ህክምና እጦት አጡ፡፡
እምዬ ምኒልክ ግን በምንም የሚገቱ አልነበሩም። የመጀመሪያውን ኢትዮጵያዊ ሃኪምቤት በማቋቋም ብቻም ሳይወሰኑ፣ ከውጭ ያመጧቸውን ሃኪሞችና በአዲስ አበባ የሚገኙ ቆንሲሎችን በማግባባት፣ ፈዋሽ መድሃኒቶችን ከቀረጥ ነጻ በማድረግ፣ እና በተለያዩ ማትጊያዎች እንደ ምንም ብለው ሁለት ለኢትዮጵያችን የመጀመሪያ የሆኑትን ፋርማሲዎች (በዘመኑ አጠራር ‹‹የመድሃኒት መሸጫዎች››) እንዲከፈቱ አደረጉ። (አንዱ በአዲስ አበባ፣ ሌላኛው ደግሞ በሐረር)።
ለሁሉም ውለታቸውን ፈጣሪ ይመልስልን! ለእምዬ ምኒልክ፣ ለኢትዮጰያ እናት፣ ለአድዋ ጀግና፣ ለሁሉም ጀግኖች አርቆ አስተዋዮች ቀደምት አባቶቻችን፣ ስለህመማችን ለቆሰሉት፣ ስለቁስላችን ለተጨነቁት ለተጠበቡት ሩኅሩኅ አባቶቻችን፣ ነፍሳቸው ባረፈችበት የገነት ቅፅር ምሥጋናችን ይድረሳቸው!
ለትውልዳችን የአባቶቻችንን ብልሃት፣ ሩህሩህነት፣ ሀገር ወዳድነት፣ ጀግንነትና አርቆ አስተዋይ ልብ አብዝቶ ይስጥልን ፈጣሪ አምላክ!
ጽሑፌን በትዕግሥት ለዘለቃችሁ ወደጆቼ ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡
በበኩሌ እነዚህን ሁሉ ታሪካዊ መረጃዎች በአግባቡ አደራጅተውና ሰንደው ለትውልድ እንዲደርስ በመፅሐፍ አሳትመው ላለፉት ለታላቁ ኢትዮጵያዊ የታሪክና የቋንቋ ምሁር ለፕ/ር ስርግው ብለሥላሴ ከመቀመጫዬ ብድግ ብዬ አክብሮት የተሞላ ምሥጋናዬን አቅርቤ አበቃሁ፡፡
ይህ ፅሑፍ ለአድዋ ድል መታሰቢያ እንዲሆን የዛሬ ዓመት ካጋራሁት ፅሑፍ፣ ከጥቂት ለውጦች ጋር የቀረበ ነው።
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 
Filed in: Amharic