>

በአርምሞ የተጀመረው ተጋድሎ በአርምሞ ተፈጸመ....!!! (ብርሀኑ አድማስ)

በአርምሞ የተጀመረው ተጋድሎ በአርምሞ ተፈጸመ….!!!

ብርሀኑ አድማስ

 

*…. መርቆሬዎስ ተብለው በፕትርክና ከበሩ፣ የመርቆሬዎስ ዕለት ወደ ቅድስ ሀገር ኢትዮጵያ ገቡ፣ የመርቆሬዎስ ዕለት ወደዚያኛው ዐለም ገቡ…!
* … መርቆርዮስ ጻዲቅ እስኪታዘዝ ሎቱ
በአርምሞ ጸና እስከ እለተ ሞቱ 
መደናቆር በዝቶ አገር ተቃጠለ
መናገርን እንጂ ዝምታን ማን ቻለ?

በረከታቸው ይደርብን!!

ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከሀገር በስደት ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ አንድም ቀን ስለደረሰባቸው ስደትና መከራ ወይም ደግሞ በየትኛውም ዘመን በደል አድርሰውብኛል ስለሚሏቸው ሰዎች ተናግረው ሰምቼ አላውቅም። ከስደት በኋላ ከእርሳቸው በቅርበት ለሚኖሩ ሰዎችም እንኳ ተናግረው እንደማያውቁ ሰምቻለሁ። ይህን ከቅርብ ቤተሰቦቻቸውም አረጋግጫለሁ። እንደሰማሁት ክተሰደዱበት ጊዜ ጀምሮ ከቃለ እግዚአብሔር እና አልፎ አልፎ ሐሜትንና ብሶትን ለማስቆም ከተናገሯቸው ተግሣጾች እና ምልክቶች በቀር ሌላ ተናግረው አያውቁም። መከራና ስደታቸውን በብሶትና በመብሰክሰክ ሳይሆን በአርምሞና በትዕግሥት ተቀብለው ሀገራቸው ኢትዮጵያን ብቻ በመናፈቅ አሳልፈው በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ ለሀገራቸው በቅተው በመመለሳቸውም ሳይቦርቁ የአርምሞ ሱባኤያቸውንም ሳያቁርጡ እነሆ ለዕረፍታቸው በቅተዋል። በዚህም እንዲህ ያለ ነገር ከተፈጸመላቸው ጥቂት ቅዱሳንና ሊቃውንት በረከት ደርሰው ያለፉ ይመስለኛል። ይህን ሀሳቤን ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ የተመለሱበት አንደኛ ዐመት በተመለከተ በቤታቸው ውስጥ በአንድ ቅን ምእመን አዘጋጅነት በትንሹ ሲከበር በጊዜው በቦታው በነበሩት በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ትእዛዝ ያቀረብኩት ስለሆነ ዛሬም እርሱን ላስታውስ እና ነገሬን ላሳጥር።
በመጽሐፍ ቅዱስ በአማላጅነታቸው ብርታት በአንድ ላይ እግዚአብሔር የገለጻቸው ሦስት የዘመነ ብሉይ ቅዱሳን አሉ። እነርሱም ኖኅ ፣ ኢዮብና ዳንኤል ናቸው። እሥራኤልን የበደላቸውን  ጽናት ሲናገር እነዚህ ሦስቱ ቢኖሩ እንኳ ራሳቸውን ያድናሉ እንጂ ሌላውን አላድንም ሲል ይናገራል /ሕዝ 14 ፤ 14/። እነዚህን መርጦ ያነሣበትን ምክንያት ሊቃውንት በትርጓሜያቸው ሲያብራሩ ሦስቱም ተመሳሳይነት ያለው ነገር በተጋድሏቸው አይተዋል። ኖኅ ይህችን ዐለም በንፍር ውኃ ከመጥፋቷ በፊት ከተፈጠረች ጀምሮ የነበረውን ክብሯን ውበቷን አይቷል፣ በኋላ ደግሞ ጥፋቷን እልቂቷንና ውድመቷን አይቷል፣ በኋል ደግሞ ከጥፋት ውኃ በኋላ እንደገና ወደ ተፈጥሮዋ ስትመለስ ፍጥረታትም ሲባዙ አይቷል። ኢዮብም የቀደመ ክብሩን ጤንነቱን ሀብቱን ማዕረጉን ያውቃል፣ በኋላ ደግሞ ዐሥር  ልጆቹ በአንድ ቀን ሞተው፣ ሀብት ንብረቱ አልቆ ፣ እርሱም በጽኑ ደዌ ተመትቶ ተጎሳቁሎና ተዋርዶ ሰዎችም ንቀው ጠልተው መሳቂያ መሳለቂያ አድርገውት አይቷል። አሁንም እንደገና ከደዌው ተፈውሶ፣ እንደገና መልካም ልጆች ወልዶ፣ ሀብት ንብረቱ በእጥፍ ተመልሶለት የተሳለቁበትም አፍረው እንደገና ከብሮ ገንኖ አይቷል። ዳንኤልም የኢየሩሳሌምን የመጀመሪያውን ክብሯን፣ የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ ከእነ ሥርዐቱ፣ የእሥራኤልን ገናንነት ከእነ ሙሉ ክብሯ አይቷል። በኋላ ደግሞ በባቢሎን ምርኮ ቤተ መቀደሱ ፈርሶ፣ ሕዝቡ ተማርኮ ፋርስ ባቢሎን ወርዶ፣ እሥራኤል ተዋርደውን በአሕዛብ መሳቂያና መሳለቂያ ሆነው በመከራና በጭንቅ ውስጥ ሆነው አብሯቸው ተሰድዶ አይቷል። በመጨረሻ ደግሞ ከምርኮ ተመልሰው ቤተ መቅደሱ እንደገና ተሠርቶ መሥዋዕት ተሰውቶ የእሥራኤልም ክብራቸው ተመልሶ አይቷል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስም ተመሳሳይ ታሪክ የተፈጸመላቸው ይመስለኛል። መጀመሪያ በሲመት በክብር ሀገራቸው ላይ በፓትርያርክነት ክብራቸውን አይተዋል። በኋላ ደግሞ በስደት በመከራ፣ የነገሩን ምንነት እንኳ በአግባቡ ያልትረዱ ሰዎች በሌሉበትም እየሰደቧቸው እያዋረዷቸው መጀመሪያ በኬንያ በኋላም ምድረ ፋይድ ሊባል በሚችለው በአሜሪካ ለሪጂም ዐመታትን በመከራባ በተጋድሎ ቆዩ። የእግዚአብሔር ፈቃዱ ሲሆን ደግሞ እንደገና በግመል በበረሃ የተሰደዱት አባት የሀግሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር በሚበሩበት አውሮፕላን ተመልሰው በሁለት ቤተሰብ በድብቅ በበረሃ በተጓዙበት አንጻር በብዙ አጅብና በክብር ቀይ ምንጣፍ ተነጥፎላቸው ገቡ። ወደ መንበረ ፕትርክናቸው ተመልሰው በቀዳሚነት በጸሎት እየተጠሩ እንደገና ክብራቸው ተመልሶ አዩ። እንዲያውም የኋለኛው ክብራቸው ከቀደመ ክብራቸው ሳይበልጥ አይቀርም። አንደኛ እርሳቸው በአርምሞ ሆነው በትሕትና ፈጠሪያቸውን ብቻ በማነጋገር አገለገሉ፣ ሰውም በዝምታቸውና ምንም ምን ወቀሳ ከሰሳ ባሳደዷቸው ላይ ባለማምጣታቸው በእጂጉ አከበራቸው። ስለዚህም የኋለኛው ክብራቸው በልጦ በዐይናቸው አዩ። በፊተኛው ሲመታቸው በመፈራት ይከበሩ ነበር፣ በኋለኛው ግን በመወደድ ተከበሩ። በፊተኛው ጥቅም ፈላጊ ይከብባቸው ነበረ፣ በኋለኛው ግን በረከት ፈላጊዎች ብቻ ከበቧቸው። ስለዚህም ከቀደመው ክብር የሚበልጥ ክብር ለማየተ በቁ።
አሟሟታቸውም ለክብር ተሳታፊ መሆናቸውን የሚጠቁም ይመስለኛል። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ተብለው በገባሬ መንክራት ቅዱስ መርቆሬዎስ ስም ተጠርተው እንደከበሩ ከስደት ተመልሰው በክብር የተቀበልናቸውም የሐምሌ መርቆሬዎስ ነበረ። ዛሬ ደግሞ ዕለተ ቀኑን ሲጠብቁ የሰነበቱ ይመስል ልክ በዕለቱ የየካቲት መርቆሬዎስ ዐረፉ።
ዳግመኛም ከስደታቸው በኋላ በአርምሞ እንደኖሩና ግርግርና ፕሮቶኮልን እንደጠሉ እንደተጸየፉ አሁንም ቅዱሳን ሁሉ በበዐት ለሱባኤ በተከተቱበት፣ ከበሮ ጸናጽል በተሰቀሉበት፣ ግርግርና ጩኸት ረገብ ባሉበት በዐቢይ ጾም ማረፋቸው ዐለሙንና ጩኸቱን ምን ያህል እንደተጸየፉት የሚያሳይ ይመስለኛል። ለነገሩ ከዚህ በፊትም ዝምታ የሚወዱ ሰዎች በተመሳሳይ ጊዜ ዐርፈዋል። መናኙ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ እንዲሁ በሕማማት ሲያርፉ አምና ደግሞ ታላቁ ሊቅና መናኝ የኔታ ጥበቡ ታዬ እንዲሁ በሕማማት ዐርፈው መምህራቸው በተቀበሩበት ዕለት የስቅለት ተቀብረዋል። ዘንድሮም ቅዱስነታቸው አቡነ መርቆሬዎስ በአርምሞና በትዕግሥት የጀመሩትን ተጋድሎ በተሰየሙበት ሰማዕት መታሰቢያ ዕለት መርቆሬዎስን ይዘው በጽጥታውና በአርምሞው ወቅት በዐቢይ ጾም በማረፍ ወደ እውነተኛ ሰንበትና ዕረፍት ወደ ክርስቶስ ገብተዋል /ዕብ 4፤ 4 – 11/ ።  የቅዱስነታቸው በረከታቸው ይደርብን።
Filed in: Amharic