>

የካራማራ ድል 44ኛ ዓመት መታሰቢያ  - ዘመቻ ሐረር - (ሰለሞን ለማ ገመቹ)


የካራማራ ድል 44ኛ   ዓመት መታሰቢያ – ዘመቻ ሐረር
-!!
ሰለሞን ለማ ገመቹ
 ለየካቲት 26/1970 ዓ.ም

   ትረካ -፩-
ተኳሽ ደስ ይለኛል ሲታጠቅ ማለዳ
መራዥ ደስ ይለኛል ሲታጠቅ ማለዳ
የሚያበላ መስሎ የሚሸኝ ዕንግዳ… ”
           ማሪቱ ለገሰ-
ፓራ-ኮማንዶ በቆቃ የሚያደርገውን ስልጠና አላቋረጠም፡፡ የአሰልጣኝ ሰልጣኙ ጥምረት ልዩ መስህብ ነበረው፡፡ አሰልጣኙ ያለውን ዕውቀትና ችሎታ ሁሉ ተጠቅሞ፤ የሰልጣኙን ወታደራዊ ቁመና ከፍ ለማድረግ፤ የውጊያ ብቃቱን የሚያስተማምን ደረጃ ላይ ለማድረስና በግዳጅ አፈፃጸሙ ሀገሩንም ሆነ ወገኑን የሚያኮራ ሆኖ እንዲገኝ መታተሩን እንደቀጠለበት ነው፡፡ ሰልጣኙም ወደፊት ከእሱ የሚጠበቀውን ድርሻ በመገንዘብም ሆነ ለአሰልጣኞቹ ያለውን ፍቅርና አክብሮት ለመግለጽ፤ ብሎም በአሰልጣኞቹ ወታደራዊ ጥበብና ኢትዮጵያዊ ስሜት መንፈሳዊ ቅናት ያደረበት መሆኑን ለማስረዳት… የሚሰጠውን ትምህርት በትጋት በመከታተል ላይ ነው፡፡…
ይሁን እንጂ ኅዳር 4 ቀን 1970 ዓ.ም የነበሩትን የስልጠና ሂደቶችና ውበት የተላበሱ ሁኔታዎችን የሚለውጥ ነገር መጣ፡፡ “ስልጠና ይቁም! ሰልጣኞች ይሰብሰቡ…” ተባለ፡፡ ሥርዓቱንና ጠገጉን ጠብቆ የመጣው የዘመቻ ትዕዛዝ ነበረ፡፡ ይህንንም ቀጭን ትዕዛዝ የ32ኛ ሰልጣኝ ፓራ-ኮማንዶ አዛዥ ግልጽ አደረጉልን፡፡ በደቡባዊ አቅጣጫ በኩል የሶማሌ ጦር የሐረር ከተማን ለመቆጣጠር ጥቂት ምዕራፍ እንደቀረው፣ ከተማይቱ በጠላት ከባድ መሣሪያ ዒላማ ሥር እንደዋለች፣ በዚያ የሚገኘው ሕዝብ…ሐረርን ለመታደግ፣ አቅሙ በፈቀደለት ሁሉ የጠላትን ግስጋሴ ለመግታት… በመፋለም ላይ መሆኑን አዛዣችን ነገሩን፡፡ ቀጠሉናም፡- “እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ይህን በመሰለው አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ እየደማች ነው!… በስልጠናው መቀጠል ያስፈልጋል ወይስ ዛሬውኑ መዝመት አለብን?!” አሉ፡፡
የጥያቄያቸው አቀራረብ… ቃናው፤ ሀገርን ከውርደት፣ ሐረርን በጠላት ከመያዝ ለመታደግ ቁርጠኛ መንፈስ እንዲኖረን የሚያደርግ ነበረ፡፡ “እንዘምታለን! ሀገራችን እየደማችና እየቆሰለች ተጨማሪ ስልጠና አንሻም!… ስልጠናውን በጦርነት መሀል እንቀጥላለን፤ እናት ሀገር ወይም ሞት!…” የሚል ድምፅ በአንድ ላይ አሰማን፡፡ ታዳኙን ለመያዝ እንደሚያደባ ነብር፤ የ32ኛ ሻለቃ አባሎች ውጊያ ለመግጠም ተቅበጠበጥን፡፡ ወዲያው ወደ ሐረር የጦር ግንባር የምናደርገው የዘመቻ እንቅስቃሴ በጥድፊያ ተጀመረ፡፡
አሰልጣኞቻችን እንደ ቅጥርና እንደ ማዕረግ ደረጃቸው በመቶ መሪነት ተደለደሉ፡፡ የሻምበል አዛዦች በሐረር ይጠብቋችኋል ተባለ፡፡ በስልጠናው ጊዜ የሻለቃው አዛዥ የነበሩት መኮንን በቦታቸው ሆነው እንዲቀጥሉና በግንባርም የአዋጊነቱን ድርሻ እንዲወስዱ ከበላይ ተወስኗል፡፡ በስልጠናው ወቅት የጓድ መሪነትን ቦታ አግኝተው የነበሩት ሰልጣኞችም በዚያው እንዲጸኑ ሆነ፡፡ የኃላፊነቱ ቦታ ድልድልና ምደባ ከተጠናቀቀ በኋላ በቅድሚያ “ማኦ ሴቱንግ” የሚባለው ቀይ፣ ስስና ዘርፋፋ የቻይና ወታደራዊ ልብስ ከነመለዮው ታደለን፡፡ ተለዋጭ ይሁን ተብሎም ቅጠልያ ተሰጠን፡፡ ከዚያም “ቀሰ” ተብሎ የሚታወቀው የሩሲያ ጦር ዩኒፎርም ተጨመረልን፡፡ ከዋና አሰልጣኞቻችን አጠገብ በረዳት አሰልጣኝነት ተመድበን ስንሠራ ለነበርነው የሚሊሺያ ጦር ልብስ ተበረከተልን፡፡
“ድሬ-ዳዋ እስክትደርሱ ድረስ ያዙ!…” ተባልንና ዐመለኛዋንና ባለ አገልግሏን ፒ.ፒ. ኤስ.ኤች8 አውቶማቲክ የነፍስ-ወከፍ መሣሪያ ታጠቅን፡፡ እሷን ታጥቀን ሥለቱ ልዩ የሆነ ሳንጃ አገንድረን… የ32ኛ ፓራ-ኮማንዶ ሻለቃ አባሎች፤ ከቆቃ ወደ አዲስ አበባ ኅዳር 5 ቀን 1970 ዓ.ም ተነቃነቅን፡፡ ከቆቃ አዲስ አበባ እያካለበ ያመጣን አይፋ ቦሌ አየር ማረፊያ አራግፎን ተመለሰ፡፡ ከዚያ በቡድን በቡድን ሆነን 707 በተባለ አውሮፕላን ወደ ድሬ-ዳዋ በረርን፡፡
የሻለቃችን አባሎች በመሉ ድሬ ከገቡ በኋላ… ወደ ሐረር እንዲያደርሱን በተመደቡት ሎንቺናዎች ተሳፈርን፡፡ እነዛ ሎንቺናዎች መላ አካላቸውን ጭቃ እንዲቀቡና ሣር እንዲለብሱ ተደርገዋል፡፡ ሎንቺኖቹ እኛን እንዳሳፈሩ፤ ጉዞ ወደ ሐረር ሆነ፡፡ ድሬ-ዳዋ እንደደረስን የተጀመረው ፒ.ፒ.ኤስ.ኤችን በክላሽንኮቭ (በክላሽ) የመለወጥ ሂደት በየመንገዱም ቀጥሏል፡፡ ጊዜ የለም፡፡ ጥድፊያ ነው፡፡ ሎንቺኖቹ በተወሰነላቸው ፍጥነት ይሮጡና እንዲቆሙ በታዘዙበት ነጥብ ጣቢያ ይቆማሉ፡፡ የክላሽና የጥይት ዕደላው ይካሄዳል፡፡ እንደገና ጉዞ ይሆናል፡፡
በምናልፍበት ጎዳና ግራ ቀኝ፣ፊት ኋላ… የመድፍ ሼል፣ የሞርታር አረር ይወድቃል፡፡ “ጠመንጃ አለህ?… የተሟላ ጥይት ይዘሃል? ኮዳህ ሙሉ ነው ጎዶሎ?…” ብሎ የሚጠይቅ አዛዥ የለም፡፡ “ዕየዬ ሲደላ ነው” የምትባለው ተረት ትርጉም የታወቀችው ያኔ ነው፡፡ በየመንገዱ ወገን የሚያቀርበውን መሣሪያና ጥይት እየተቀበሉ ወደ ፊት መጣደፍ ብቻ፡፡  በዚህ ዓይነት ሁኔታ ተጉዘን ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ሐረር ደረስን፡፡ የከተማዋ መንደሮች አልፎ አልፎ በከባድ መሣሪያ እየተመቱ ነው፡፡ ነዋሪዋ እየተጯጯኸ ሕይወቱን ለማትረፍ ወደ ከፍተኛ ቦታዎች ይሮጣል፡፡ የቆረጠው ሲቪል ምሽግ ቆፍሮ ሊመጣ ያለውን አደጋ ለመጋፈጥ ተዘጋጅቷል፡፡
ሐረር እንደደረስን ለጥቂት ጊዜያትም ቢሆን እንደማረፍ…ያልነው በ”ሳንፊል” ሬዲዩ ጣቢያ ነው፡፡ ጣቢያው በድሬ-ዳዋ መስመር ሐረር ከተማ መግቢያ ላይ ይገኛል፡፡ ከጣቢያው በስተጀርባ ካለው ከፍታ ቦታ የወሬ ማሰራጫው ረዥም አንቴና ይታያል፡፡ ከሳንፊል በስተግርጌ በኩል ከወደ አናቱ ሲል… “ጋይንት” የምትባል አንድ ሆቴል ነበረች፡፡ በዚያች ሆቴል ለግዳጅ ከመንቀሳቀሳችን በፊት ጎራ ብዬ ለስላሳ መጎንጨቴ፤ ዛሬም ድረስ ሰው ከመሞቱ በፊት “ስንቅ ይሁነው…” ተብሎ እንደሚቀምሰው እህል-ውሃ ሆኖ ነው የሚሰማኝ፡፡
በጭጋጋማ የአየር ፀባይ ከነስጋቷ… የተቀበለችን ሐረር፤ በማግስቱ በነጭ ደመና ተጋርዳ ነበር፡፡ የዚያድ ባሬ ጦር ከተማይቱን ለመያዝ ወደ ሶፊትና ፈዲስ በመጠጋት ያሰፈሰፈው፤ ቆላማውን የሐረርጌ ክ/ሀገር በቅርብ በሚያዋስነው በሚዲ-ጋሎላ አቅጣጫ መጥቶ ነው፡፡ በቀላድ አምባ… በቢሲዲሞ በኩል ሐረር ለከባድ መሣሪያ ጥቃት ተጋልጣ የነበረችውም፤ የጠላት መድፍና ሞርታር አስተኳሽ በአቅራቢያው የነበረውን ሥፍራ የተቆጣጠረው በመሆኑ ነበር፡፡
ሐረር በዚያ ሁኔታ ውስጥ እያለች 3ኛ ፓራ-ኮማንዶዎች ስንደርስ ሳንፊል ሬዲዮ ጣቢያን ይጠብቁ የነበሩት፤ የከተማዋ ነዋሪዎች፣የአካባቢዋ ገበሬዎችና የሚሊሺያ ሠራዊት አባላት ናቸው፡፡ ከእነሱም መሀል ከፊሎቹ ወደ አቡ-ሸሪፍ እየሄዱ ነበረ፡፡ በዚያን ጊዜ ሐረር በጠላት እጅ ሳትያዝ የቀረችው፤ እንደ ንብ ትጉህ በነበሩት… የኢትዮጵያ አየር ኃይሎች ብርታት… ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ… የ32ኛ ሻለቃ አባላት በሳንፊል ሬዲዮ ጣቢያ መቀመጫችንን ስናደርግ የተቀረው የ3ኛ ፓራ-ኮማንዶ ብርጌድ ጦር ያረፈው፤ የሐረር ሕዝብ በሠራው ምሽግ ውስጥ ነበረ፡፡ …
Filed in: Amharic