የከንቱ ሰዎች ወረራና የእልም ዛፎች ተጋድሎ አንድነት ይበጀናል ዛሬ
ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች)
እንደ መግቢያ
ሰው በዚች ምድር ላይ የሚኖረው አንድ ግዜ ብቻ ነው፡፡ እንደ ልእለስራው እስከመጨረሻው ስሙን እያስጠራ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል፡፡ በኖረበት ዘመንና ከዚያም ውጭ ዝንታለም ሲነሳና ሲወደስ የሚኖር ሥራ ሰርቶ ማለፍ ከታላቅ የስራ ክንውኖች ሁሉ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ከእያንዳንዱ ሰው የሚጠበቅ ተግባር ቢሆንም ከእጣት እጣት ይበልጣልና ሁሉ ሰው ዕኩል ይዘልቃል ማለት አይደለም፡፡ ከተራው ሰው በአያሌው የላቀ ተግባርና ምግባር ይዘው የሚገኙ አሉ፡
የኢትዮጵያ አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ መቆም እንዳለበት በህይወት ዘመናቸው አስተምረው ያለፉ እና ስማቸውን በወርቅ ቀለም አጽፈው ካለፉ ጎምቱ እና ለበሙሉ ኢትዮጵያዊ ምሁራን መሃከል አቶ ተክለጻቅ መኩሪያ፣አቶ ሀዲስ አለማየሁ፣ ክቡር አቶ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ፣ጋሼ ሙሉጌታ ሉሌ፣ጋሼ አሰፋ ጫቦ፣የኤደንብራው ምሩቅ ክቡር ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ የአለም ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን፣ አምባሳደር ዮዲት እምሩ፣ አንገፋዎቹ ጋዜጠኞች አሃዱ ሳቡሬ ( አሃዱ ሳቡሬ አጠገበኝ ወሬ በሚል ይታወቁ የነበሩ ትንታግ ጋዜጠኛ)፣ ደራሲ በአሉ ግርማ፣ጋሼ ክበበው ገበየሁ ፣በህይወት ካሉት ደግሞ ዶክተር ታዬ ወልደሰማያት፣ዶክተር ሀይሉ አርአያ፣ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልክያስ፣ ወዘተ ወዘተ ምንግዜም ቢሆን ከማይዘነጉ የኢትዮጵያ ልጆች መሃከል ግንባር ቀደሞች ናቸው፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም፡፡
የኢትዮጵያ የአንድነት ታሪክ የመቶ አመት ነው የሚለው አስተሳሰብ እጅግ በጣም የዋህ የሆነ አለመካከት ብቻ ሳይሆን ሸፍጥ የተሞላበት መርዛማ አስተሳሰብም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የአንድነት ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን ለማረጋገጥ ብዙም የሚያስቸግር ጉዳይ አይደለም ብዬ አስባለሁ፡፡ የአክሱምን ሀውልት መመልከቱ ብቻ በቂ ነው፡፡
አንደ ዛሬው ሳይሆን እንደ ጥንቱ ኢትዮጵያውያን የጎሳ፣ሃይማኖት እና ቋንቋ ማንነት አጥር ሳይገድባቸው አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው የሀገራቸውን ዳርድንበር ( የግዛት አንድነት) ለአሁኑ ትውልድ አስረክበው በክብር አልፈዋል፡፡ ጥንታዊ አባቶቻችን፣እናቶቻችን፣ቅድመ አያቶቻችን የህብረት ችቦ በመለኮሳቸው ምክንያት የቱርክ ወራሪዎችን፣ የግብጽን ወረራ፣የፋሺስት ጣሊያንን ወረራ በመመለስ ኢትዮጵያ በነጻነቷ ኮርታ እንድትኖር ያደረጉም ናቸው፡፡
አንድነት ይበጀናል ዛሬ
ፓኪስታንና ህንድ፣ፓኪስታንና ባንግላዴሽ የቅኝ ገዢ ታላቋ ብሪታንያ በቀመመችው የከፋፍለህ ግዛ መርዝ ተመርዘው ርስበርስ በመከፋፈል ጦርነት ቢገጥሙም ለችግራቸው መፍትሔ አላገኙም፡፡ በመጨረሻው እጣ ፈንታቸው መለያያት ነበር፡፡ ፍቺው ግን ዛሬም እያመረቀዘ ሁለቱን ሀገራት በተለይም ፓኪስታንና ህንድን የቃላት ጦርነት፣ አንዳንዴም ጥይት የሚያማዝዝ ግጭት ውስጥ ሲዘፈቁ ይስተዋላል፡፡ በተለይም በካሽሚር ግዛት ጥያቄ ላይ ዛሬም አይንና ናጫ ሆነዋል፡፡በነገራችን ላይ ሁለቱም ሀገራት ለሶስት ግዜያት ያህል አሸናፊና ተሸናፊ ባልነበረበት አውድ የለየለት ጦርነት ገጥመው እንደነበር ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ደግነቱ ሁለቱም ሀገራት የበለጸጉና የኒኩሊዬር ባለቤትና ታጣቂዎች በመሆናቸው፣ እንዲሁም አያሌ ዜጎቻቸው በእውቀት እየመጠቁ በመምጣታቸው የሚከባበሩ መሆናቸው እንጂ ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት ለመግባት የሚያስችሉ ቀዳዳዎች ገና አልተደፈኑም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በካሽሚር ግዛት ለዘመናት ተጋብተውና ተዋልደው ይኖሩ ከነበሩ ሰዎች መሃከል በሚሊዮን የሚቆጠሩ የእስልምና ተከታዮች ወደ ፓኪስታን ግዛት እንዲጠቃለሉ ሲደረግ፣የሂንዱና ሌሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሃይማኖት ተከታዮች ደግሞ ወደ ህንድ ግዛት ውስጥ እንዲኖሩ ተደርገዋል፡፡ በአጭሩ ቤተሰብ የነበሩ ሰዎች ተለያይተው ቀርተዋል፡፡ እኛና እነርሱ የሚለው የፋሺስቶች ብሂል መጨረሻው አያምርም፡፡ እክቂት ኋላም ተለያይቶ መቅረትን ይጋብዛል፡፡ በሌላ በኩል ከ60 አመት በፊት ፓኪስታን በእብሪት ተነሳስታ የራሷ ግዛት ለማድረግ የከፈተችባትን ጦርነት ድል የነሳችው ባንግላዴሽ ዛሬ በእድገት ጎዳና ላይ ትገኛለች፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በወያኔ የጎሳ አገዛዝ ከዛሬ 30 አመት በፊት የጎሳ መርዝ የተዘራባት ኢትዮጵያ ሀገራችን በታሪክ ፈተና ላይ የወደቀች ትመስለኛለች፡፡ በተለይም በወልቃይት፣ጸገዴ፣ሁመራ ፣በሰሜን ወሎ ጫፍ ላይ ያሉ እንደ ራያ ያሉ አካባቢዎች እና በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚነሱ የድንበር ወይም የግዛት ይገባኛል ጥያቄዎችን ለመፍታት ጥበብ፣የሰከነ መንፈስና ቁጭ ብሎ መነጋገርን ግድ ይላል፡፡ ከዚህ ባሻግር ታሪክን በእውነት መሰረት ላይ ሆኖ ማጥናት፣መከባበር፣መዋደድ፣አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ መባባሉ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በቅድሚያና በዋነኝነት ግን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት እና አንድነት ማጽናት ተገቢ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እደግመዋለሁ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ማክበርና ማስከበር የኢትዮጵያውያን ሁሉ ሃላፊነት ነው፡፡ ሌላው ይደረስበታል፡፡ በኢትዮጵያ ሌላ የካሽሚር አይነት ግዛት እንዲቆም መፍቀድ የለብንም፡፡ በቅድሚያና በዋነኝነት የኢትዮጵያን አንድነት ማስከበር ከተቻለ የተጠቀሱት ግዛቶች በነበሩበት ግዛት ውስጥ ቢጠቃለሉ እዳው ገብስ ነው፡፡ ማናቸውም ኢትዮጵያዊ( የትግራይ ወንድሞቻችንን ይጨምራል) ዜጋ በማናቸውም የሀገሪቱ ግዛት ተንቀሳቅሶ የመስራት መብቱ ከተከበረለት ወልቃይትም ሆነ ጸገዴ ወይም ሌሎች አካባቢዎች ወደነበሩበት ክልል ተመልሰው በአካበቢው ተወካይ ሰዎች አመሃኝነት ቢተዳደሩ ክፋት ያለው አይመስለኝም፡፡( በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች እንደሆነው ሁሉ የወልቃያት አካባቢ ሰዎች ራሳቸው በወከሏቸው ሰዎች ቢተዳደሩ ለማለት ነው) ምክንያቱም አንዲት ሉአላዊት በሆነች ሀገር ውስጥ ማናቸውም ኢትዮጵያዊ ወደ አካባቢው ተንቀሳቅሶ የመስራት መብቱ ስለሚከበርለት ነው፡፡ የወልቃይት ተወላጆችም ከፈለጉ ተከዜን ተሻግረው ወደ ትግራይ በመጓዝ ከአልሆነላቸው ደግሞ ወደ መሃል ሀገር ወይም ደቡብ ኢትዮጵያ በማቅናት ህይወታቸውን ይመራሉ ማለት ነው፡፡ ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ወደ ተጠቀሰው አካበቢ ተንቀሳቅሰው ይሰራሉ ማለት ነው፡፡ ይህ የጸሃፊው እምነትና አስተያየት እንጂ በመሬት ላይ ያለው እውነት ለየቅል ነው፡፡ በተለይም በዚህ አካባቢ ያለው አደገኛ እና አስፈሪ ሁኔታ፣ አንዲሁም በሌሎችም የኢትዮጵያ ግዛቶች የሚገኙ የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎች የሚፈቱት የህገመንግስት ማሻሻዮች ሲደረጉ ብቻ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እኛና እነርሱ በማለት ሰዎች እንዲታበዩ የሚያደርገው የጎሳ ፖለቲካ መርዝ ሰንኮፍ ከኢትዮጵያ መነቀል አለበት የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በተለይም በቅርቡ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው የብሔራዊ እርቅ ውይይት ላይ የሚሳተፉ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣(የሐገር ሽማግሌዎቸ፣የሃይማኖት መሪዎችና የሲቪል ማህበራት ተወካዮች በውይይቱ ላይ የሚካፈሉ ከሆነ) ይህን መሰረታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ለመፍታት መንፈሳዊ ወኔ እንዲታጠቁ መልእክቴን ሳቀርብ በታላቅ አክብሮት ነው፡፡ ለማናቸውም ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከእኛ እና እነርሱ የደካሞች የፖለቲካ አስተምህሮ ወጥተን በሰውነት ደረጃ ላይ መቆም አለብን፡፡ ውድ ኢትዮጵያውያን በአለም ላይ ካሉት ሀገራት ሁሉ በድህነት ከሚታወቁት አምስትና ስድስት ሀገራት አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ የምንኖር መሆናችንን መዘንጋት የለብንም፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ሀገራችን በተፈጥሮ ሀብት እጅግ የታደለች እና ተስማሚ የአየር ንብረት ያላት ሀገር ብትሆንም በእድገት ጎዳና ላይ መራመድ ቀርቶ ህዝቧን በቅጡ መመገብ ያልቻለች ናት፡፡ ይሄን ጽሁፍ በምጽፍበት ግዜ ( ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም.) በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እና ቦረና አካባቢዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ርሃብተኞች እንዳሉ ከአለም መገናኛ ብዙሃን ሰምቻለሁ፡፡ አብዝሃው በከተማ ነዋሪ የሆነው በአኗኗሩ የተመቸው አይደለም፡፡ ድህነት ቤቱን ሰርቶበታል፡፡ ድህነቱ እንዳለ ሆኖ ታሪካዊ ጠላታችን ግብጽና ውድቀታችንን በሚመኙ ሌሎች ሀገራት በቀመሙልን የጎሳ መርዝ ሰክረው ያዙኝ ልቀቁኝ ባይ የጎሳ አምበል መብዛቱ ሲስተዋል በእውነቱ ለመናገር የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ ማሳዘን ብቻ አይደለም፡፡ ህሊናን ያደማል፡፡ ሆድንም ይበጠብጣል፡፡ የቆዳ ስፋቷ የምእራብ አውሮፓን የምታህለው የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ እጅግ ውድ ከሆነው ዩራኒዬምን ጨምሮ የማእድን ሀብቷ የአለምን ቱጃሮች አይን የሳበና ሰከረ ነው፡፡ ይህቺ አፍሪካዊት ሀገር ሰላሟን እንዳታገኝ የአለም ሀብታም ሀገራት ሁሉ እንደ ግሪሳ ወረዋት ፍዳዋን ማስቆጠር ከጀመሩ ብዙ አመታት ነጎዱ፡፡ የዚች ሀገር ፍዳ መቁጠር ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ አንድነቷን ሊያስከብር የሚችል ጠንካራ መንግስት ባለመነሳቱ እንደሆነ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ልብ ልንል ይገባል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ሁሉ አንተም ተው፣አንቺም ተይ በመባባል አንድነታችንን ማጥበቅ ይገባናል ባይ ነኝ፡፡ ይህም ሲባል ግን የአጠፋ አይከሰስ፣የተበደለም አይካስ ማለቴ አይደለም፡፡ ባለፉት ሰላሳ አመታት፣ ከዛም በፊት ሃምሳና ስልሳ አመታት በፊት ለተፈጸሙ አስከፊ ወንጀሎች እውነቱ መነገር አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ለተፈጸሙ አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት በተመለከተ እንዴት እንደተፈጸመ፣ በእነማን፣እነማን የሰብአዊ መብት ጥሰት እድተፈጸመባቸው፣ለምን፣መቼ፣የት ወዘተ ወዘተ ለመሳሰሉት ጥያቄዎች መልስ ይገኝላቸዋል፡፡ ይህን ለማድረግ መንፈሳዊ ወኔ ከታጠቅን እውነቱ ይወጣል ማለት ነው፡፡ እውነት ከተደበቀችበት ከወጣች ደግሞ ፍትሕ ፍንትው ብላ ትታያለች፡፡ ወንጀለኞች ሁሉ በፍትህ አደባባይ ተገኝተው የህግ ተጠያቂ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ፍትህ ገቢራዊ ከሆነች በኋላ ደግሞ ለተጎዱት የካሳ ክፍያ፣ በመጨረሻም በዛች ሀገር ላይ ብሔራዊ እርቅ ይሆናል፡፡ የደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክን ጉዳይ ለግዜው ትተን ሩዋንዳ ከዛ ከባድ ሀዝን እና መከራ ወጥታ ዛሬ ሰላሟ የሰፈነ፣አንደነቷ የተጠበቀ፣ በእድገት ጎዳና ላይ ለመራመድ የበቃችው መሪዎቿ በተለይም ፕሬዜዴንት ፖልካጋሚና የትግል አጋሮቻቸው የእውነታና እርቅ አፈላለጊ ኮሚቴ በሩዋንዳ ምድር ለማቆም መንፈሳዊ ወኔ በመታጠቃቸው ነው፡፡ ዛሬ ያቺ ሀገር ለአፍሪካ ሀገራት ሁሉ ምሳሌ ለመሆን በቃች ሀገር በመሆኗ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከሩዋንዳውያን ወድቆ መነሳት እንማር፡፡ ራሳችንን ባናታልል መልካም ነው፡፡ በስም ብሔራዊ እርቅና ውይይት መድረክ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን በተለይም የስም ፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎቻቸውና አባላቶቻቸው ረሳቸውን አታለዋል፡፡ ይሄ መራር ቀልድ የሚበቃን ይመስለኛል፡፡ አሁን ግዜ የለም፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ሀገሬ የገጠማት ፈተና ከበፊቶቹ ከገጠማት ፈተናዎች በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ ያለምንም ማገነንና ውሸት ኢትዮጵያ የህልውና ፈተና ገጥሟታል፡፡ በተለይም በኢትዮጰያ አንድነት ጽኑ እምነት ያላችሁ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪል ማህበረሰብ አባላት፣የሃይማኖት አባቶች፣ኢትዮጵያዊ ምሁራንና ኢትዮጵያ ህዝብ በቅርቡ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው የውይይት መድረክ እውነተኛ ብሔራዊ እርቅ እንዲሰፍን በትኩረት መከታተል ያለባችሁና የራሳችሁን አበርክቶ ለማቅረብ በታሪክ ፊት ቆማችኋል፡፡ በድጋሚ ራሳችንን እንዳናታልል ሳስታውስ በአክብሮት ይሆናል፡፡ በቅድሚያ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት መቅደም አለበት፡፡ ሌላው ይደርሳል፡፡
የድንጋይ ዘመን
በድንጋይ ዘመን ‹‹እልም››የምትባል የዛፎች አገር ነበረች፡፡ ይህቺን የዛፎች አገር በተለያየ ጊዜ የቅዠት ሰዎች ሊደፍሯት ቢሞክሩም ጥቅጥቅ ደኗ ስለሚያስፈራ፤ አንበሶችና ነብሮችም ስለሚኖሩባት ሳትደፈር ትኖር ነበር፡፡ የቅዠት ሰዎች ዕልምን በእሳት ሊያቃጥሉ ደጋግመው ቢሞክሩም የዕልም ምድር ደረቅ ስላልነበረና ዝናብም ስለማይጠፋ የማቃጠሉ ተንኮል ሳይሳካ ቀረ፡፡ የድንጋይ ዘመን ሲገባደድና ባልጩት በብረት መሳሪያ ሲተካ የቅዠት ሰዎች ዕልምን በምሳር ለመድፈር የስለላ ጉንጉን መጎንጎንና መረብ መዘርጋት ጀመሩ፡፡
የከንቱ ሰዎች የስለላ መረብ በይበልጥ የተዘረጋው ከጠማማ ዛፎች ዙሪያ ነበር፡፡ ጠማማ ዛፎች ቀጥ ብለው መውጣትና መቆም ስለማይችሉ ቀጥ ያሉት ዛፎች “ጎባጦች፣አጎብዳጆችና አጎንባሾች” እያሉ ይንቋቸው ነበር፡፡ ጠማማ ዛፎች በፈንታቸው ቀጥ ያሉ ዛፎችን እንደ ረጅሟ የአለቃ ገብረሃና ሚስት ወይዘሮ ማዘንጊያ ሽቅብ እያዩ “ሥራቸውን ቢቦድሱት ማየትና መስማት የማይችሉ ቀውላሎች!” እያሉ ይሰድቧቸው ነበር፡፡ ይህንን በጠማማና በቀጥተኛ ዛፎች መካከል ያለውን ቅራኔ የከንቱ ሰዎች በዘረጉት የሥለላ መረባቸው አጠኑ፡፡ በጥናታቸውም የዕልም አገር ሳትደፈር የኖረቸው በዛፎች ትብብር፤ በተለይም ደግሞ በቀጥተኛ ዛፎች ቀጥ ያለ አቋቋም፣ አስፈሪነትና ግርማ ሞገስ መሆኑን ተገነዘቡ፡፡
በዚህ ግንዛቤም ጠማሞችን ከቀጥተኞች አጣልተው ጠማማዎቹን ከጎናቸው የሚያሰልፉበትንና ቀጥተኞችን የሚያጠፉበትን ሰነድ አረቀቁ፡፡ “ቀጥ ያሉ ዛፎች እናንተን ጠማሞችን እንኳን እንደ ዛፍ እንደ ደን አካልም አይቆጥሯችሁም፤ እንደ ደን አካል ስለማይቆጥሯችሁም አፈሩን፣ አየሩንና ፀሐዩንም ተቆጣጥረው በአካል እንድትጣመሙና እንድትቀጭጩ አደረጉ፤ በዚህም ምክንያት ዓይን ለዓይን ሳይሆን ቁልቁል እያዩአችሁ ይኖራሉ፡። መንፈሳችሁንም እንደ ጥጥ አሳስተውና በራስ የመተማመን ሥነ-ልቡናችሁን እንደ ሙክት ፍሬ ሰልበው እንደ ኩምቢ አቀርቅራችሁ ምድርን ብቻ ስታዩ እንድትኖሩ አስገደዷችሁ” እያሉ ያለመታከት ሰበኳቸው፡፡
የከንቱ ከንቱ ሰዎችን ስብከት የሰሙ እድሜ ጠገብ ጠማማ ዛፎች “ይህንን ዛፍን እርስ በርሱ የሚያጋጭ መሰሪ የባዕድ ስብከት አትስሙ! ቀጥተኛ ዛፎች የበለጠ የከንቱ ሰዎች ዘመድና ወዳጅ ሊሆኑን አይችሉም፤ በመካከላችን ያለውን ችግር ራሳችን እንፈታዋለን” ብለው ለግላጋ ዛፎችን እያስተማሩ ለብዙ ዓመታት የከንቱ ሰዎች ተንኮል አከሸፉ፡፡ ዳሩ ግን ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ የከንቱ ሰዎች ያላሰለሰ ስብከት የጠማማ ዛፎችን ልብ እንደ ልጃገረድ ማሽኮርመምና ማማለል ቻሉ፡፡ አሽኮርማሚዎቹ የከንቱከንቱ ሰዎች “ከጠማማ ዛፎች የምንፈልገው ትንሽ እርዳታ ነው፡፡ ከጎበጡት ቅርንጫፎቻችሁ የተወሰኑትን ብትለግሱን ቀጥ ያሉ ዛፎችን አጥፍተን የዕልምን ምድር የጠማማ ዛፎች ምድር እናደርጋታለን፤ ሥሟንም ከዕልም ዛፎች አገር ወደ ጠማማ ዛፎች አገር እንቀይረዋለን” ብለው ሲሰብኳቸው ጠማሞች ቀጥ ያሉ ዛፎች እንደ ዳይኖሰር ጠፍተው የዕልም ምድር በጠማማ ዛፎች ስትሸፈንና ሥሟም የጠማማ ዛፎች አገር ሲሆን ታያቸውና ጎባጣ ቅርንጫፎቻቸውን ለቅዠት ሰዎች ለማበርከት እንደ አዲስ አባባ የስኳርና የዘይት ሰልፈኞች ተራ ለማያዝ ተሽቀዳደሙ፡፡ ይኸንን የጠማማ ዛፎች እሽቅድድም የተመለከቱ የከንቱ ሰዎችም ከጎባጣ ቅርንጫፎች የሚጠርቡትን እጀታ ከምሳር አጋብተው የዕልም ዛፎችን ሲከተክቱ፤ በዚህ ክትከታ ምክንያትም ቀጥተኛና ጠማማ ዛፎች ተጣልተው እርስ በርሳቸው ሲተላለቁ፤ በዚህ የመተላለቅ ግርግርም የደኑ አውሬዎች ደንብረው ሲጠፉና አውሬዎች ሲጠፉም የዕልምን ምድር እንደልባቸው ሲጠቀሙ ታያቸውና ተደሰቱ፡፡
የከንቱ ሰዎች ጎባጣ ቅርንጫፎችን ከጠማማ ዛፎች ተረከቡና “የተደበቀው ውበታችሁ እንዲወጣና እንድታምሩ ጠርበን ቅቤ እንቀባችሁ” በሚል ማታለያ እየጠረቡና ቅቤ እየቀቡ እጀታ ሰሯቸው፤ እጀታ ከሰሯቸው በኋላም “የበለጠ ለማስጌጥና ዘመናዊ ለማድረግ” በሚል መሸንገያ ምሳሮችን እንደ ሎቲ ሰኩባቸው፡፡ እጀታዎች ምሳሮች እንደ ሎቲ ሲሰኩባቸው ከዛፎች ባህል እጅግ ራቁና እንደ አካላቸው ሁሉ የመንፈስ ጉብጥናም ተጠናወታቸው፤ የመንፈስ ጉብጥና ስለ ተጠናወታቸውም የሚያብረቀርቁትን የምሳር ሎቲዎች ስላንጠለጠሉ ከጥንታዊ ዛፍነት ወደ ዘመናዊ ብረትነት የተቀየሩ መሰላቸው። የቅዠት ሰዎች ዛፎችን ለመቁረጥ ሲሄዱ በትከሻቸው ሲሸከሟቸው ያከበሯቸው መሰላቸው፡፡… እንደ እጀታዎች ጠማማ ዛፎችም እጀታዎችን ከቅዠት ሰዎች ትከሻ ሲመለከቱ “እውነትም የቅዠት ሰዎች ለጠማማ ዛፎች ክብር ያላቸው፤ ለፍትህ የቆሙና ጠማማ ዛፎችን ከቀጥተኛ ዛፎች ጭቆና ለማላቀቅ ከሰማይ የወረዱ መላእክት” አሉና ሰገዱላቸው፡፡
የከንቱከንቱ ሰዎች በጠማማ ዛፎች መሪነት ከእጀታ በተሰካ ምሳር ቀጥ ያሉ ዛፎችን እየገነደሱ የመርካቶ ዘራፊ ጂዶ እንደመታው ነጋዴ መዘንደብ ሲጀምሩ በዕልም ምድር ድንጋጤና ውዥምበር ተፈጠረ፡፡ ውዥንብሩ እየጠራ ሲሄድ ዛፎች በተናጥል በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ከቅዠት ሰዎች እየወደቁ ወገባቸውን ሰበሩ፣ ከፊሎቹም የምሳርን ጥርስ አዶለዶሙ፣ ሌሎችም እጀታዎችን እየታገሉ ሰንበር በሰንበር አደረጉ፡፡ …በዚህ ትንቅንቅ ልባቸው እንደ ቅቤ የቀለጡና ውሀ ሲመጡና ኦክሲጂን ሲፀዳዱ ኖረው አፈር ለመሆን የወሰኑ መሐል ሰፋሪ ዛፎች ደሞ “ጊዜ እስኪያልፍ ያባትህ ባርያ ይግዛህ!” በሚል የጡርቂዎች ፈሊጥ ከጠማማ ዛፎች ተመሳስለው መከራን ለማለፍ ማንነታቸውን ለመቀየር መጉበጥ ጀመሩ፤ በአደባባይ ቀጥተኛ ዛፎች እንደሆኑ ለመናገር ተቸገሩ፡፡
ከብዙ እልቂት በኋላ ቀጥተኛ ዛፎች በምስጢር ተሰባሰቡና “በምን ምክንያት ለእልቂት በቃን፣ ማንስ ፈጀን? እንዴትስ ራሳችንን መከላከል አቃተን” እያሉ መወያየት ጀመሩ፤ ከፊሎቹ “ያስፈጁን ከራሳችን የወጡ ጠማማ ዛፎች ናቸው!” እያሉ ሲቆጩ ከፊሎቹ ደግሞ “አህያውን ቢፈራ ዳውላውን! እኛን የፈጁን የከንቱ ሰዎች ጠፍጥፈው የሰሯቸው ምሳሮች ናቸው!” እያሉ ተከራከሩ፡፡ የቀሩትም “ቀንደኛ ጠላቶቻችን የከንቱ ሰዎች ናቸው!” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጡ፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ ጉንጭ አልፋ ክርክር ቀጥ ያሉ ዛፎች መግባባት ስላልቻሉ ግጭት ተፈጠረና በአንድነት መቆም ተሳናቸው፡፡ ይኸንን የቀጥተኛ ዛፎችን የአቋም መፈረካከስ የተመለከቱ ጠማማ ዛፎችም “ቀጥ ብለው መሄድ የማይችሉ ጠማሞች እያሉ ሲተርቱብንና ሲሰድቡን ኖረው ዛሬ እነሱ ቀጥ ብሎ መሄድ አቃታቸው፡፡ እንደ ወልካፋ እየተወላከፉና እንደማገር እየተወናገሩ ገመናቸውን ማሳየት ጀመሩ ኪ..ኪኪ..ኪኪኪ..” እያሉ ሳቁ፤ተሳለቁ፡፡
የከንቱ ሰዎችም ይህንን የዛፎችን ትርምስና ብጥብጥ ተጠቅመው አንበሶችና ነብሮችን አቅፈው በመያዝ የዕልምን ምድር አስከብረዋት የኖሩት ዛሬ ቀን ጥሏቸው በአንድነት መቆም ያቃታቸውን ዛፎች መጨፍጨፉን ቀጠሉ፡፡ የሚጨፈጨፉት ዛፎችም “እኔ አለቃ ልሁን፤ እኔ ልምራ” በሚሉ ፉክክሮችና “ጊዜ ያመጣውን ጊዜ ይመልሰዋል” በሚል አጉል ተስፋ ተተብትበው በተናጠል ማለቁን ቀጠሉ፡፡ አንዱ ቡድን “የኔ ትግል ስልት ፍፁም ነው!” ሲልና ሌላው የዚህን ቡድን ሥልት አጣጥሎ የራሱን ሥልት ፍፁምነት ሲሰብክ ብዙ የዛፍ ልጆች ተጨፈጨፉ፡፡ አንዱ ዛፍ ከሩቅ ተገንድሶ ሲወድቅ ሌላው “ከእኔ እስኪደርሱ አምላክ መፍትሔ ያመጣል” ሌላውም “እኔን እስኪያገኙኝ አንበሶችና ነብሮች የከንቱን ሰዎች ይለቅሟቸዋል” እያለ እንደ ፀጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ የማይነጋ ህልም ሲያልም በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ዛፎች አለቁ፡፡ በዛፍ ቡድኖች አለመግባባት፣ በመሐል ሰፋሪው ብዛትና ራስን የመከላከል ድክመት የዕልም ምድር እንደ በደኖ ገደል፣ እንደ ጋንቤላ ሜዳ እና ሰሜን ኢትዮጵያ ተራሮች በሬሳ ተሸፈነች፡፡ ሌላው ቀርቶ አንዳንድ እጀታዎችም በጭፍጨፋው ብዛት አንገቶቻቸው እየተቀሉ ከምድጃ ተማገዱ፡፡ አያሌ ምሳሮችም ጥርሳቸው ረግፎ አዷማ እየተሰሩ አፈር መብላት ጀመሩ፡፡
አንገቶቻቸው የተቀሉ እጀታዎች ከእሳት መጣላቸውን የሰሙ ጠማማ ዛፎች “አገልግሎታችን ሲያልቅ መጨረሻችን ገሀነመ እሳት መሆኑን መች አወቅን” እያሉ ማጉረምረም ጀመሩ፡፡ የከንቱ ሰዎች ግን “አንድም እጀታ ከእሳት አልተጣለም!” ሲሉ ሙልጭ አርገው ካዱ፡፡ በከንቱ ሰዎች አጭበርባሪነት፣ አረመኔነትና በጠማማ ዛፎች ክህደት የበገኑ ቀጥተኛ ዛፎች የአልሞት ባይ ተጋዳይ ተጋድሎ ቀጠሉ፡፡ እንደ ዋንዛ ያሉ ጠንካራ ዛፎች የእጄታን ጭንቅላት መተርከክና አንገቱን መቅላት ጀመሩ፡፡ እንደ ቁጥቋጦ ያሉ ዘዴኛ ዛፎችም ድንጋዮችን በቅጠሎቻቸው ሸፍነው ካጠገባቸው የበቀለን ቀጥ ያለ ዛፍ የሚጨፈጭፍ ምሳር ጥርስ መሰባበር ጀመሩ፡፡ እንደ አጋምና ቀጋ ያሉ ተናዳፊዎችም የከንቱ ሰዎችን ቆዳ በመገሽለጥና አይናቸውን በማፍሰስ ታገሉ፤ዳሩ ግን እነዚህ ዛፎች የሚያደርጉት ተጋድሎ የተናጥል ስለነበር አንዱ እጀታ ሲቀጭ ሌላው እየተተካ፣ አንዱ ምሳር ጥርሱ ሲረግፍ ሌላው ጥርሳም እየተተካ፣ አንዱ የከንቱ ሰው ዓይኑ ሲፈስ ሌላው ስስታም ዓይኑን ይዞ ከች እያለ ዛፎች ለድል አልበቃ አሉ፡፡
ለድል አልበቃ ያሉበትን ምክንያት ለመመርመርና የትግል ስልት ለመቀየስ አስተዋይ ዛፎች መጀመርያ ምስጢራዊ ውይይት አደረጉና ቀጥለው ጠቅላላ ስብሰባ ጠሩ፡፡ በስብሰባው ወቅትም የተለመደው ጭቅጭቅ ተጀመረ፡፡ ሰብሳቢው ሾላ “አለም ከተፈጠረች ጀምሮ ታፍረንና ተከብረን ተኖርንበት ምድር እንዴት ልንጨፈጨፍ ቻልን?” ብሎ ጥያቄውን ሳይጨርስ ..“ምን ጥያቄ አለው! ያስጨፈጨፈን የራሳችን ጠማማ ነው?” አለ ዋንዛ በንዴት!.. የተናደደውን ዋንዛ የጎሪጥ እያዬ ኮባ የተባለው ተክል “አህያውን ቢፈራ ዳውላውን! የከንቱ ሰዎች እኛን እንዲያጠፋ የጠፈጠፉት ምሳር ተቀምጦ የራሱን ወገን ይወቅሳል” አለ፡፡ ..ዋንዛም ኮባን በንቀት እያዬ “ተናግረህ ሞተኻል! ጥርሳሙ ምሳር ወገን ከምትለው ጠማማ ዛፍ ወሲብ ባይፈጽም አቅሙን ከየት ያመጣው ነበር! ” ሲል ወጠረ፤ “አቅሙን የሚያገኘውማ ከጠማማው ዛፍ ሳይሆን ከቅዠት ሰዎች ነው” አለ ኮባን የደገፈው እንሰት፤ በኮባና በእንሰት ክርክር ያልረካው የስብሰባው መሪ ሾላ “ኮባና እንሰት የምታስቡት በቅጠላችሁ ይመስለኛል! የእኛው ጠማማ የቅዠት ሰዎችን እጆችና የምሳርን ቀለበቶች ባያገናኝ የከንቱ ሰው አቅም በምን ታምር ወደ ምሳር ተላልፎ ምሳር እኛን እንዲከትፍ ያበቃው ነበር?” እያለ እንደ ፊዚክስ ሳይንቲስት ጉልበት ወይም ኃይልን ከአንዱ ቁስ ወደ ሌላው የመፍሰስን ሂደት አስረዳ፡፡ ..ይህ የጉልበት ወይም ኃይል ፍሰት አገላለጽ ቀለም በደም ሥርም ሆነ በአፍ ቢሰጣቸው ከማይገባቸው እንደ ብሳና ካሉት ዛፎች በቀር ሁሉንም ቀጥ ያሉ ዛፎችን ልቦና አረካ፡፡.. ልቦናቸው በመርካቱም የጠማማ እንጨት ክህደትና አስፈጅነት እንደ መስተዋት ቁልጭ ብሎ ታያቸውና ቅርንጫፎቻቸውን እያፋጩ “ጠማማ ይሰበር! ባንዳ ይቀልጠም! ከሀዲ ይቃጠል!” እያሉ መፈክር አሰሙ፡፡
በጠማማ ዛፍ ክህደት፣ አስፈጅነትና ቀንደኛ ጠላትነት በተደረሰው ስምምነት ያልተደሰተ የገዴ ማደርያ ዛፍ “ጦርነት ውስጥ ከምንገባ የተወሰነውን የዕልም ክፍል አስረክበን በእርቅ ብንፈታውና ሰላም ቢሰፍን ይሻላል” ብሎ ሳይጨርስ “አንተን ብሎ ገዴ! ገድህ ይጥፋ! የምታስረክበው አካባቢ ያሉት ዛፎች ወንድሞችህ አይደሉም? ወንድሞችህን በጎባጣ እንጨት፣ በምሳርና በቅዠት ሰዎች አስፈጅተህ አንተ በሰላም ልትኖር ታስባለህ.. በወንድሞችህ መቃብር የሰላም ሐውልት ልትገነባ ታቅዳለህ፤ ሆዳም! ስንት ዘመን ለመኖር ይኸንን ያህል ለከርስህ ትገዛለህ? ወንድሙን በክህደት የሚያስበላ ከፈጣሪ፣ ከፍትህና ከታሪክ የተጣላ እርጉም ነው!” አለ ዋንዛ ቅርፊቱ በላብ ወርዝቶ፤… በዋንዛ አቋም የረካው ዘንባባ “አንዱ በይ ሌላው ተበይ ሆኖ ሰላም የለም!” ብሎ ለዋንዛ ያለውን ድጋፍ ተናግሮ ሳይጨርስ በዘንባባ ንግግር የተገረመው በለስ “አንተም ዘንባባ… አንተም ሰላምን በመስበክ ፋንታ ለጦርነት ድጋፍ ሰጠህ?… ስምንተኛው ሺ የደረሰ መሰለኝ.. የሰላም ምልክትነትህ የት ደረሰ?” አለ፡፡ ..ዘንባባም በለስን ቁልቁል በትዝብት እያዬ “ዕፀ- በለስ! እንደ ልማድህ ለማሳሳት ታልሆነ ያልኩትን አጥተኸው አይመስለኝም፤ ቀበሮ በግ መብላቱን ታላቆመ፤ ዓለም ከተፈጠረች ጀምሮ ለበላው በግ ካሳ ካልከፈለና ንሰሐ ካልገባ፤ በግን ከቀበሮ ተስማማና ሰላም ፍጠር ብትለው እንዴት ሊሰማህ ይችላል? …የምታውቀው እባብ ሲውጥህ እግርህን ዘረጋግተህ ስጠው የሚል ቃል ከየትኛው መፅሀፍ ተፅፏል?..፣ ሰይጣን ቀኝ ፊትህን ሲመታህ ግራህን ስጠው የሚል ትዕዛዝስ የትኛው አምላክ አስተላልፏል?” በሚሉ ጥያቄዎች አፋጠጠው፡፡
በዚህ ጠንከር ያለ ክርክር ግራ የተጋባው ብሳና “አምላክ ሆይ! ደብቀን የያዝናቸውን አንቦሶችና ነበሮች አስነስተህ የቅዠትን ሰዎች አጥፍተህ እኛንም እርስ በራሳችን ተመናከስ አድነህ በሰላም አኑረን” ብሎ ወዠብ እንደ ገፋው ቅርንጫፎቹን ዘቅዝቆ ለእግዞታ ከምድር ተደፋ፡፡ ብሳናን ለእግዞታ ሲደፋ ያየው ዋንዛ “ድፍት ያርግህ ብስናታም! አንበሳ ነፃ ያውጣን እያልክ ነጋ ጠባ ትደፋለህ! ዛፍን ነፃ ማውጣት ያለበት ራሱ ዛፍ ነው! በሞግዚት ነፃነቱን ያገኘ ፍጡር ባለም የለም! በሞግዚት ነፃ አውጣኝ ብትለውም እግዜር አይረዳህም! ሲያምርህ ይቅር!” ሲል ተቆጣ፡፡ ዋርካ ስብሰባው ወደ መፍትሔ ሳይሆን ወደ ቡድን ውዝግብ መሄዱን ተረዳና ‹‹ጎበዝ.. ወደ ቁም ነገሩ እንግባ! ለመሆኑ ከፊታችን የተደቀነብን ትግል የመኖርና ያለመኖር የህልውና ትግል መሆኑን ስንቶቻችን ተረድተናል? … የህልውናችን ትግል ከዳር እሚደርሰው በተግባር የሚተረጎም የረቀቀ የጋራ የትግልና ስልት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ይህ የጋራ የትግል ሥልትም የሚተለመው ሁላችንም የየራሳችን ተሰጥኦና ሙያ ማበርከት ስንችል ነው፡፡ የጥፋት አዋጅ ታውጆብን መጓተቱና መጋጨቱ መጥፋታችንን ያፋጥናል እንጅ መፍትሔ አይሆንም›› በማለት ሀሳቡን አስቀመጠ፡፡
በውይይቱ ቅርፅ መያዝ የተደሰቱ አንድ የእጣን ሊቀ ጠበብት “እሽዋ…እሽዋ..” እያሰኘ እንደ እጣን ማጨሻ ቅርንጫፎቹን እርግፍ እርግፍ አርጎ አካባቢውን አጠነና “አንድም ሁለትም ሆናችሁ ተገኙ፤በመካከላችሁ እገኛለሁ ብሏል” ብለው ንግግራቸውን ጀመሩ፤ በመቀጠልም “እንደዚህ ዓይነት የመደማመጥና የመረዳዳት መንፈስ በመካከላችን ሲፈጠርና እኛም ስንረዳው እርሱም ይረዳናል፤ ፈጣሪ ግፈኞችን ያንበረክካልና እኛም ስንጥርና ስንረዳው ሳንደርስባቸው የደረሱብንን የቅዠት ሰዎች ያንበረክክልናል፡፡.. ስናጎርሳቸው የነከሱንን ጠላቶች ያመነዥክልናል፤ እኛን ለማጥፋት የተጠፈጠፈውን የምሳርን ጥርስ ይሰርብርናል፤ የከሀዲዎችን ክንድም ያዝልልናል፡፡ በእነኚህ መረን በለቀቁ አረመኔዎችም አንበሶችና ነብሮችን ሊለቅባቸው ይችላል፤ ሳንሄድባቸው ለመጡብን፣ ሳንነካቸው ለነኩን፣ ሳንወስድባቸው ለወሰዱብን፣ ባበላናቸው ላስታወኩብንና ባጠጣናቸው ለሸኑብን ማዕበልና ጎርፍ ሊያወርድ ይችላል…” ብለው ሀላፊነትን ሲወስዱ ጭብጨባው ቀለጠ፡፡
ተረኛው አባ እጣን የተጨማደደ ቅርፊታቸውን እንደ ካባ ደርበው አስተያየታቸውን ቀጠሉ ‹‹..እግዚአብሔር ሁለት ልብ አይፈልግም፤ ለእግዚአብሔርና ለሳጥናኤል መገዛት አይቻልም፤ እግዚአብሔርና ሳጥናኤል ዘወትር ጦርነት ላይ ናቸው፡፡ የጦርነት ሜዳቸውም የሰው ልብ ነው፡፡ ሰው ልቡን ለሳጥናኤል ሰጥቶ እየካደ፣ የሰውን ሐብት እየተመኘ፣ እየሰረቀ፣ እየተስገበገበ፣ እርስ በርስ እያጋጨ፣ እያመነዘረ፣ እየመቀነ፣ እየገደለና እያሰቃየ እጁን ለፈጣሪ ቢዘረጋ ከየትኛው ሰማይ እሚኖር እግዚአብሔር ይሰማዋል?… በዘረፈውና አጭበርብሮ ባካበተው ገንዘብ የአምልኮት ሥፍራ ቢሰራ የትኛውን አምላክ ሊያታልል ይችላል? አምላክ ቀናተኛ መሆኑን አበክሮ ነግሮናል፤ ከእርሱ በቀር ሳጥናኤልንም ሆነ የሳጥናኤልን ጣኦቶች ገንዘብና ስልጣንን እንዳናመልክ አስጠንቅቆናል፤ ስለዚህ ሙሉ ልባችንን ለእግዚአብሔር ሰጥተን፤ ትስስራችን አጠንክረን፣ በሙያችን ተሰልፈን፤ ከሀዲና ባንዳን ከጉያችን እንደ መዥገር ነቅለን ለፍትህና ለነፃነት ከታገልን እግዚአብሔርም እንደ ዛሬው አብሮን በውይይታችን መሀል ይቆማል… ከማመንታትና ሁለት ልብ ከመሆን አውጥቶ ለድል ያበቃን እግዚአብሔር ይመስገን፤ እርስ በርሳችን አጋጭቶ ሊያጠፋን ከሚነሳ ጠላት ይጠብቀን፤ የሰማእታትን ነፍስ ይማር” ብለው ንግግራቸውን ሲጨርሱ ሁሉም ዛፎች “አሜን፤ አሜን፤ አሜን፡፡” እያሉና የተጨፈጨፉት ወገኖቻቸውን እያሰቡ በቅርንጫፎቻቸው ተቃቅፈው እንባቸውን ከቅጠሎቻቸው እንደ ነሐሴ ዝናብ አወረዱ፡፡
አገር ብርሌ ነው አንዴ ከወደቀ፣
የሚሰማ ይስማ አለቀ ደቀቀ፡፡