ግብ ጠባቂው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ ) …!!!
ታሪክን ወደኋላ
1978 ዓ.ም ለነበረ የኢትዮጵያ ሻምፒዎና፣ የእርስ በእርስ ግጥሚያ የነበራቸው ቅዱስ ጊዮርጊስና ሜታ ቢራ በአንድነት ካረፉበት ገነት ሆቴል ሃይሌ ካሴ የተባለ የጊዮርጊስ ተጫዋች ከአንድ የሜታ ቢራ ተከላካይ ጋር አፍ ላፍ ገጥሞ ያወራል። የሜታው ተጫዋች እነ ቤከም ባወርን እየጠቀሰ “ሊብሮ” ስለሚባለው የአጨዋወት መንገድ ለሃይሌ ካሴ በስሜት አስረድቶታል።
በማግስቱ…ለሃይሌ ገለፃ ሲያደርግ የነበረው የሜታ ቢራው ተከላካይ ከኋላ ተነስቶ፣ ግብ ጠባቂውን ጨምሮ አራት የጊዮርጊስ ተጫዋቾችን አልፎ ግብ ያስቆጥራል። ደስታውን ከቡድን አጋሮቹ ጋር ገልፆ ወደ ሜዳው ሲመለስ ሃይሌ ጠጋ ብሎ ጠየቀው “ሊብሮ ያልከኝ ይሄ ነው?” የሜታው ተጫዋች በፈገግታ ሁኖ መለሰለት “አዎ”። ከደስታው ሳይመለስ፣ ፈገግታውንም ሳይጨርስ አዲስ ስም ወጣለት፦ “ሊብሮ”። ይህ ስሙ የአያቱን ስም ተክቶ ባሳለፋቸው የሜዳም የሚዲያም ታሪኩ ውስጥ ከፍ ብሎ ተጠርቶበታል፦ ገነነ መኩሪያ ሊብሮ።
የታሪክ ፍቅሩ ከስቴዲየም ጫማ አሰቅሎ ስቲዲዮ ውስጥ ብዕር ሙጥኝ እንዲል ያደረገውን… ገናና የታሪክና የስፖርት ሰው ታሪክ መሰነድ ኩራትም ፍርሃትም አለው።
➻ ህፃኑ ገነነ
“ብዙም ትውስታ የለኝም” በሚላት ይርጋለም ነው ውልደቱ፤ መጋቢት 5 1957 ዓ.ም። የውልደት አመቱ ከሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪ ዥን ጣቢያ የምስረታ ዓመት ጋር መግጠሙን አስተውሎ ‘ይህ ልጅ የሚዲያ ሰው ይሆናል’ ያለ ባይኖርም፤ እርሱ ግን በኋለኛው ዘመኑ በህትመቱም በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ላይ ስፖርትና ታሪክን ይዞ መግነን ችሏል።
ከማያስታውሳት ይርጋለም ከተማ የበዛ የልጅነት ጊዜውን ወዳሳለፈባት ሻሸመኔ አቀና። በዚያ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል፤ የእግር ኳስና የጽሑፍ ችሎታውን ፈልጎ አግኝቷል። በአፄ ናዖድ ተማሪ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እየተከታተለ የቡና ነጋዴ አባቱ ገቢ ወጫቸውን ሲፅፉበት ከርመው የሞላ መዝገባቸውን ይሰጡታል፤ ህፃኑ ገነነ ተቀብሎ ከጋዜጦች የሚያገኘውን የስፖርተኞችን ፎቶ እየለጠፈ ለጓደኞቹ ያከራያል። ግማሹን የሚያዩ የቁልፍ (አዝራር) ፣ ሙሉውን የሚኮመኩሙ 5 ሳንቲም እንዲከፍሉ ግድ ይላቸው ነበር።
እዚያው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለ አዲስ ዘመንንና ሰለሞን ተሰማ ያዘጋጅ የነበረው “ስፖርት ፋና” ጋዜጦችን ያዞራል። 10 ጋዜጣ ለማዞሩ የሚከፈለውን 10 ሳንቲም ከመቀበል ይልቅ አንድ ጋዜጣ ተቀብሎ ይሄዳል። ከጋዜጦቹ ላይ የሚያገኛቸውን ስዕሎች ከአባቱ የሞላ መዝገብ ላይ እየለጠፈ፤ ዜናዎቹን በራሱ መንገድ ድጋሜ እየፃፈ ገቢውንም የጽሑፍ ችሎታውንም እኩል አሳደገ። ጋዜጣ ከማሳደድ ጎን ለጎን ኳስ ሊያድን “አረንቻታ” ለተባለ የሰፈሩ ቡድን በግብ ጠባቂነት ተሰለፈ። “ጎል ውስጥ መቀመጥ ስለማልወድ እየወጣሁ ብዙ ጎል ይገባብኝ ነበር” የሚለው ገነነ ከአረንቻታ ቀጥሎ “ነበልባል” ለተባለ ቡድንም በግብ ጠባቂነት ተጫውቷል።
7ኛ ክፍል ሲደርስ የወቅቱ መንግስት ከቀይ ሽብር በኋላ ወጣቱን በስፖርት ለመያዝ አልሞ በርካታ ውድድሮችን ያደርጋል። በቴኒስና በዝላይ ተሳትፎ ሳይቀናው የማታ ማታ አስር ሺ ሜትር ተወዳድሮ በወንድሙ እገዛ አንደኛ ወጥቶ ባልዲ እንደተሸለመ ያስታውሳል።
ይህ በሆነ በዓመቱ ከሰፈር ጓደኞቹ ጋር በመሆን “ቀዩ እምቡጥ” በሚባል የውትድርና ምልመላ ፕሮግራም ሰልጥሎ ለምደባ በዝግጅት ላይ እያለ የሻሸመኔ ቡድን የግብ ጠባቂ እጥረት ስላለበት የካምፑ ኃላፊና የወረዳው የስፖርት ሊቀመንበር “ገነነ ጥርሱ ቦንብ መንከስ አይችልም” ብሎ ሲያስቀረው ያለቀሰውን ለቅሶ ዛሬም አይረሳ።
እርሱ ብቻ ሳይሆን 5ቱም ወንድሞቹ እግር ኳስ ይጫወታሉ። አንድ ቡድን ውስጥ በዝተው ስላሉ የቀበሌያቸው ቡድን 09 ከመባል ይልቅ ‹የአቶ መኩሪያ ቡድን› ነበር የሚባለው። ገነነ ከሁሉም ወንድሞቹ በልዩነት ለሲ ቡድን አጥቂ፣ ለቢ ቡድን አማካኝ፣ ለኤ ቡድን ግብ ጠባቂ ሁኖ በመጫወቱ ሁለገብ ተጫዋች ተብሎ ብርሌ ተሸልሟል።
➻ የሸገር መንታ መንገዶች
1974 ዓ.ም ከግብ ጠባቂነቱ በመውጣት የሜዳ ተጫዋች በመሆን አውራ ጎዳና ለተባለ ቡድን ከፍተኛ ተከፋይ ሁኖ በ50 ብር ተቀጠረ። በአውራጃዎች ውድድር የሻሸመኔን መለያ ለብሷል፤ የሸዋ ውድድር ላይ ደግሞ ሃይቆችና ቡታጅራን ወክሎ ድንቅ ብቃቱን ናዝሬት ላይ አሳይቷል። ይህ ድንቅ ብቃቱ በ1975 ዓ.ም ገና የ12ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ለሜታ ቢራ እንዲፈርም አድርጎት ወደ ሸገር እንዲዘልቅ ሁኗል። ከሚከፈለው 183 ብር ላይ ቤት ተከራይቶ፣ የምግብ ኮንትራት ይዞ፣ ተግባረ- ዕድ ለትምህርት ከፍሎ የተረፈውን ቆጥቧል። 125 ብር በቆጠበበት ዓመት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “ምርጥ ቆጣቢ” ብሎ እንደሸለመው እያስታወሰ በቅርቡ መንገድ ላይ ያገኘው የባንኩ ወጣት ሰራተኛ “አካውንት ክፈት” ሲለው “አንተ ሳትወለድ የባንኩ ደንበኛ ነበርኩ” እንዳለው ይናገራል።
እግር ኳሱን እየተጫወተ፣ ከተግባረ ዕድ በጄነራል መካኒክነት ተመርቆ ለሜታ ቢራ እየሰራ ለአዲስ ዘመን ፅሑፍ መፃፍ ጀመረ። በእጁም በእግሩም የሚታትር ትጉህ ሆነ። በ1978 የነበረ ዓለም ዋንጫ ላይ ማራዶና በእጁ ጎል ሲያገባ የገነነ ጽሑፍ ደሞ ከእድሜ እኩያው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በፀጋ ቁምላቸው በኩል ገባ። ስሙ በቴሌቭዥን ሲጠራ የሰሙት አለቃው ስራውን አመቻችተውለት ቤተ መጽሐፍት እየገባ መፃፉን አበረታ። ለተለያዩ ጋዜጦችና ሚዲያዎች ቢፅፍም ከየካቲት መጽሔት በስተቀር አይከፍሉትም ነበር። እርሱ ግን ሁለት የሚወዳቸው ነገሮች ስለከፈሉት ደስተኛ ነው፦ እግር ኳስና የጽሑፍ ስራው።
የሜታ ቢራ ተጫዋች ሁኖ 3 ጊዜ የኢትዮጵያ ሻምፒዮን የነበረ ቢሆንም በ1978 ዓ.ም የብር ሜዳልያ ተሸላሚ የሆነበትን የፍፃሜ ጨዋታ ግን አይረሳም። ከህንፃ ኮንስትራክሽን ጋር በነበረ የፍፃሜ ግጥሚያ ገነነ ለአጋሩ ግብ ጠባቂ አቀብላለሁ ያላት ኳስ ራሱ መረብ ላይ አርፋ አንድ ለዜሮ በሆነ ውጤት ተሸንፈው ዋንጫውን አጥተዋል። ታሪክ ወዳጁ ገነነ ይሄን የራሱን ገጠመኝ እያሰበ “በታሪክ ብቸኛው ሰው ነኝ… አሸናፊው ቡድን የተጋጣሚው ተጫዋች አግብቶለት ዋንጫ ሲበላ የመጀመሪያው ነው” ይላል። ይሄኛውን ጎል ጨምሮ በዓመቱ ውስጥ አምስት ጊዜ ራሱ ላይ ማግባቱን በማስታወስ “ራሴ ላይ የማገባው የጎል ድርቅ ሲኖር ነው… እዚያ ማግባት ካልቻልክ እዚህ ታገባለህ” ይላል በቀልድ መልክ።
1980 ዓ.ም ላይ የገነነን ብቃት ያየ የወቅቱ የመብራት ሃይል አሰልጣን መንግስቱ ወርቁ ወደ መብራት ያዛውረዋል። ብዙም ሳይቆይ መንግስቱ ከክለቡ ለቆ አዲስ አሰልጣኝ ሲመጣ በአዲሱ አሰልጣኝ እቅድ ውስጥ ያልነበረው ገነነ ሳይመዘገብ ይቀርና ከልምምድና ከወዳጅነት ጨዋታዎች በዘለለ መሰለፍ ሳይችል ይቀራል። ለዋና ጨዋታ ካለመሰለፉ አጠገብ እየጣፈጠው ያለ የጽሑፍ ስራው አለ። እዚህች ጋ ወሰነ፤ ጫማውን ሰቅሎ እግሩን አሳረፈው። ያረፈው እግሩ ላይ የነበረ ብርታትን ከእጁ ላይ አክሎ በትጋት መፃፉን ቀጠለ።
➻ የእግሩን ብርታት ለእጁ ሰጠ
ገነነ አንድ ቢሮ ተገኝቶ እየፃፈ ሳለ እስኪርቢቶው አልፅፍ ይላል። ከቢሮው ኃላፊ ጋር ከምታወራ አንዲት የቢሮው ባልደረባ እስኪርቢቶ ተበድሮ ያሰበውን ፅፎ ካጠናቀቀ በኋላ የተበደረውን ሊመልስ ቀና ሲል አበዳሪውን ያጣታል። በቀጣዮቹም ቀናት አልተመለሰች። ቢሮው የመርሃ ስፖርት ጋዜጣ ቢሮ ነበር፤ እስኪርቢቶ አበዳሪዋ ደግሞ መዓዛ ብሩ። መዓዛ ይዛው የነበረ የጋዜጣውን የስፖርት ክፍል ከእርሷ መውጣት በኋላ እንዲረከብ ሲጠየቅ ያልታሰበ የእስኪርቢቶ ውሰቱን እንደ ስልጣን ርክክብ ቆጥሮ በግርምት ፈገግ ብሏል። “በጣም ያሳወቀኝ” ያለውን መርሃ ስፖርት ጋዜጣ እንዲህ ነበር የጀመረው።
ከመርሃ ስፖርት እኩል ገነነ መኩሪያ ሊብሮ የሚለው ስም እንዲታወቅ ያደረገው ብስራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ እንደነበር ያስታውሳል። በተለይ በ1981 ዓ.ም ተፈጥሮ የነበረውን መፈንቅለ- መንግስት ለመስማት 2 ሰዓት ላይ የሚጀምሩ ብሄራዊ የሬዲዮና የቴሌቭዥን ስርጭቶችን በጉጉት ሲጠብቁ የነበሩ ታዳሚዎች፤ በአንድ ሰዓት ብስራተ ወንጌል ላይ በወርቁ አለማየሁ ድምፅ የሚንቆረቆር የገነነን ፅሑፍ ልቅም አድርገው በመስማት አጣጥመዋል።
ከመንግስት ለውጥ በኋላ የግል ጋዜጣ ሲጀመር ገነነ ከአበበ ወልደ ጻድቅ፣ ወንደሰን ደምሴና ሁሴን አብዱልቀኒ ጋር በመሆን ሻምፒዮን የሚል ጋዜጣ ጀመረ። ተወዳጅ በነበረው ጋዜጣ ላይ ለወራት የሰራው የታሪክ ሰው “የምትሰጠኝ አንድ ከግማሽ ገፅ አነሰችኝ” በማለት ሌሎች አማራጮችን ማማተር ያዘ። ማማተሩ ሰምሮ በ1985 ዓ.ም ጥቅምት 23 ቀን ሊብሮ የተሰኘች የራሱን ጋዜጣ አሳተመ። ለዚህችኛዋ ጋዜጣ ህትመት የቦሌ ማተሚያ ቤት ስራ አስኪያጅ የነበረው አሰፋ ከበደ አስተዋፅኦ ከፍ ያለ መሆኑን ዛሬም ድረስ አልረሳም። የበዛ ትኩረቷን የሃገር ውስጥ ስፖርት ላይ ያደረገችው ሊብሮ ጋዜጣ ከዜና ይልቅ ለታሪክ ያደላች ነበረች። በ1973 ዓ.ም በጊኒ አድርገው ጠፍተው የነበሩ ተጨዋቾች ወደ ሃገር ቤት በተመለሱና ሞሮኮ የሄዱ ተጫዋጮች በጠፉ ሰሞን የመጀመሪያ ህትመቷ የሆነው ሊብሮ የፊት ገጿ ላይ ይዛው የወጣችው ርዕስ “ሞሮኮ ጠፉ፣ ጊኒ መጡ” የሚል ነበር። በወቅቱ አስር ሺ ቅጁ ተሽጦ ሁለተኛ እትም መታተሙን ያስታውሳል፡፡
➻ በድምፅ ሲገለጥ
ከጽሑፍ ስራው ሻገር ብሎ በራሱ ድምፅ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጠው 2000 ዓ.ም ላይ በዛሚ ኤፍ ኤም ነበር። ስፖርትና የቀድሞ ሙዚቃዎችን ታሪክ ለአድማጮች አሻግሯል። ከ2001 እስከ 2006 ዓ.ም በኤፍ ኤም አዲስ ከአዲስ ዜማዎች ጋር ሰርቷል። 2007 ዓ.ም ደግሞ በብስራት ኤፍ ኤም “መሴ ሪዞርት” እና ሌሎች ዝግጅቶች ላይ ታሪክና ስፖርትን አዋዶ ተገልጧል። የሀገር ውስጥ ስፖርት ላይ መበርታቱን ያየ ካፍ በ2009 ዓ.ም የ60 ዓመት ጎንደል ኦፍ ሜሪት ሸልሞታል። 6 ጋዜጠኞች ብቻ ያገኙትን ሽልማት በመውሰድ ገነነ ከምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው ነው። ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ከግሩም ዘነበ ጋር የቀረፀውን ዝግጅት በአሻም ቴሌቭዥን ላይ እያቀረበ ይገኛል፤ እስከ አሁን ከ150 በላይ የዚህ ተወዳጅ ዝግጅት ክፍሎች አየር ላይ ውለዋል። ከተመልካችም ጥሩ ምላሽ እንዳገኘ ይገልፃል።
➻ በመጽሐፍ ገነነ
ገነነ የሚዲያ ሰውነቱ፣ ዓለም ‹ዘመን የማይሽረው ሚዲያ› የሚለው መጽሐፍ ላይ ሲደርስ ይበረታ እንደሁ እንጂ ዝንፍ አይልም። ይህ ታሪኩ እስከተሰነደበት ጊዜ ድረስ ስምንት መጽሐፍትን ለንባብ አብቅቷል። ኢትዮጵያዊ ሥልጠና፣ የአሸናፊ ግርማ የህይወት ታሪክ፣ ኢሃፓና ስፖርት 1፣ 2፣ 3፣ የእግር ኳስ ወጎች፣ ፍትሃዊ የጠጅ ክፍፍል እና መኩሪያ። በ1994 ዓ.ም ለህትመት ያበቃው የመጀመሪያ መጽሐፉ ኢትዮጵያዊ የሆነ የእግር ኳስ አሰለጣጠንን በመፃፍ ቀዳሚም ብቼኛም እንደሚያደርገው ይናገራል።
አያይዞም ከተወዳጁ የስፖርት ጋዜጠኛ ሰዒድ ኪያር ጋር በመሆን GS and GK በሚል የስልጠና መንገድ ቡድን እንዳቋቋሙና በድረ ገፅም ተደራሽ እያደረጉት እንደሆነ ይናገራል። እንዳለ ጌታ ከበደ ጋር አንድ መድረክ ላይ ቆይታ ያደረገው ገነነ ኢሃፓና ስፖርት የሚል መጽሐፉ በአብርሃም ገዛኸኝ አማካኝነት “የነገን አልወልድም” በሚል ርዕስ ወደ ፊልም ቢቀየርም እስከአሁን አለማየቱን ሲናገር የዚህ ታሪክ ሰናጅ ተገርሟል።
➻ ሰነፉ ገነነ
‹‹በማህበራዊ ህይወቴ ደካማ ነኝ›› የሚለው ገነነ ጠንካራ ከሚላት ሚስቱ ጋር ሮማርዮ እንዳገናኘው ይናገራል። በአንድ አጋጣሚ የሮማርዮ ፎቶ በትልቁ የተለጠፈበት ምግብ ቤት ይገባና ምስሉን ወዶት ኖሮ ለጋዜጣ ይፈልገዋል። ወስዶ ኮፒ አድርጎ ለመመለስ ሲጠይቅ የምግብ ቤቱ አስተዳዳሪ ብር እንዲያሲዝ ትጠይቀዋለች። እንዳለችው አድርጎ ምስሉን ከመለሰ በኋላ ያዝያዘውን ብር ሳይቀበል ደጋግሞ ይመላለሳል። በመጨረሻም ምልልሱ ፍሬ አፍርቶ ብር አስይዝ ያለችው አስቴር አየለን አግብቶ የሁለት ልጆች አባት ሁኗል። ቃል በቃል “ከፈጣሪ በታች እርሷ ናት ያለች” ያለችኝ የሚላት ባለቤቱ ለእያንዳንዱ እርምጃው ድጋፍ እንደምታደርግለት በኩራት ይናገራል።
ሜዳም ሚዲያም ላይ እንደስሙ የገነነው ታሪክና ኳስ ወዳዱ ገነነ ተወዳጅ ሚዲያ የግለሰቦችን ታሪክ ለመሰነድ መነሳቱን ያደንቃል። በስራ አጋጣሚ የጊዮርጊስ፣ የመቻልና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መስራቾችን አግኝቶ ቃለመጠይቅ ማድረጉን እንደ እንድለኝነት የሚያየው ገነነ ዛሬ ታሪካቸው እንዲሰነድ ተጠይቀው ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች በኋላ እንደሚቆጫቸው ይናገራል። የማይደክመው የታሪክ ሰው አሻም ላይ ካለው ዝግጅቱ ጎን ለጎን በቅርቡ ኢሃፓና ስፖርት 4ን ጨምሮ በሌሎች ስራዎቹ ለመገለጥ ዱብ ዱብ እያለ መሆኑን ነግሮናል። የዚህ ታሪክ ሰናጅ ኩራት አንድ ነው… “የታሪክ ወዳዱን ሰው ታሪክ የሰነደ” መባል፤ ፍርሃቱም አንድ ነው “የታሪክ ወዳዱን ሰው ታሪክ ሲሰንደድ እንደመሻቱ ሰርቼለት ይሆን?” የሚል።
የመዝጊያ ሀሳብ ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
ገነነ መኩሪያ፣ ተንቀሳቃሽ ኢንሳይክሎፒዲያ ቢባል ይገባዋል፡፡ ስፖርትና ታሪክ አጣምሮ ይወዳል፡፡ ገነነ ለሚናገራቸውም ወይም ለሚያቀርባቸው የጽሁፍ ስራዎች በቂ ማስረጃ እና ሰነድ ይዞ ነው፡፡ በታላላቅ ቤተ-መጽሀፍቶች ጎራ ያለ ገነነን ሊያጣው አይችልም፡፡
ገነነ ሲያነብም ሆነ ሲመራመር አይደክመውም-ቢደክመው እንኳን ድካሙን ይረሳል፡፡ ገነነ ታሪክን ሲያቀርብ ማጣፈጡን ያውቅበታል፡፡ ለ45 ደቂቃ በዩኒቨርሲቲ የታሪክ ክፍለ ጊዜ ላይ ከመታደም የ12 ደቂቃዋ የገነነ ምጥን የታሪክ ጨዋታ ወደ አእምሮ ኩልል ብላ ትገባለች፡፡ ይህንን ለማድረግ ትልቅ ጥረትን ይጠይቃል፡፡ ማንበብን ይጠይቃል፡፡ ጥልቅ ምርምር ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ነገሮችን ወይም ያለፉ ታሪኮችን በሚገባ አዋዝቶ ማቅረብን ይጠይቃል፡፡ ማዋዛት የገነነ ልዩ ክህሎት በአድማጭ ፤ አንባቢ በተመልካች የተመሰከረለት ነው፡፡ገነነ ይጽፋል ያነባል የእግር ኳስ ቴክኒክን ያስተዋውቃል፡፡ ገነነ መጽሀፎቹን ሲጽፍ ከበቂ ጥናት ጋር ነው፡፡ ደግሞም መጽሀፎች ጥሩ የሽያጭ ሰንጠረዥ ውስጥ የገቡ ናቸው፡፡ ገነነ መኩሪያ በ 1970ዎቹ መጨረሻና በ 1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ በሀገራችን ብቅ ካሉ በሳል የሚድያ ሰዎች አንዱ ነው፡፡