>

ʺዓለምን ናቋት በዝምታም ቀጧት....!!!"  (በታርቆ ክንዴ)

ʺዓለምን ናቋት በዝምታም ቀጧት….!!!” 

በታርቆ ክንዴ

 በፈጣሪያቸው የተመረጡት፣ ለእርሱም የቀረቡት፣ ሳይሰለቹ ጸጋና በረከት በምድር ይሆን ዘንድ የሚጸልዩት፣ የበጎች እረኛ፣ መልካም መልእከተኛ፣ የሕይወት መምህር፣ የሀገር አድባር፣ በመንፈስ ሲደክሙ ማረፊያ፣ የጨነቀውን ጊዜ ማለፊያ፣ ምድርን የሚባርኳት፣ ክፉዋን ዘመን በጸሎታቸው የሚመልሷት አባት የናቋትን ዓለም ትተው ወደ ናፈቋት ሰማያዊ ዓለም አቀኑ፡፡  አላፊዋን ዓለም አብዝተው ናቋት፣ ዝም ብለውም ቀጧት፣ የማታልፈውን፣ ለእርሳቸውም የተገባችውን፣ ቅዱስ መንፈስ ያለባትን፣ ደጋጎችና ቅዱሳን የሚኖሩባትን፣ የእግዚአብሔር መላእክ የሚጠብቃትን ሰማያዊ ዓለም ናፈቋት፣ አብዝተውም ወደዷት፣ ከልጅነት ጀምረው አሰቧት::
መላእክት በሚጠብቋት፣ ቅዱስ መንፈስ በመላባት በዚያች ሰማያዊ ዓለም ውስጥ  የሰው እጅ ያልሠራው፣ የሰው አዕምሮ የማይመረምረው ታላቅ ነገር አለ፡፡ በዚያ የተቀደሰ ሥፍራም ይኖሩ ዘንድ ተጋድሏቸውን አበዙ፡፡  ከተሰጣቸው ጊዜ  ያስተረፉት አልተገኘም፡፡ ገና በለጋ እድሜያቸው ትክክለኛዋን መንገድ ፈለጓት፣ አገኟነት፣  በዚያችም ተጓዙባት፣ ምስጢርን አሰሱት፣ ፈለጉት፣ አመሰጤሩት፣ በምስጢሩ ረቂቅነትም ተመላለሱበት::
አላፊዋ ዓለም ትፈራቸዋለች፣ ጠፊዋ ዓለም ትደነግጥባቸዋለች፣ ለምን ካሉ እርሳቸው በእርሷ መንገድ አይራመዱም፣ ከእርሷም ባሕሪ ጋር አይዋደዱም እና፡፡ እርሳቸው አስቀድመው የፈለጉት፣ የተጓዙት፣ የተዘጋጁት ለማያለፍው  ዓለም እንጂ ለሚያልፈው ዓለም አይደለምና፡፡  የተጨነቁትን የሚያረጋጉት፣ በተኩላ መካከል ያሉትን በጎች የሚጠብቁት፣ ለጸሎት የሚተጉት አባት ከበጎቻቸው ጋር በስጋ  ተለዩ፡፡
ʺበእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ነገር ግን በስጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው።” እንዳለ መጽሐፍ ከሕዝብ ጋር መኖር እጅግ የሚያስፈልግ ቢሆንም ከክርስቶስ ጋር መኖር ደግሞ ይልቃል፡፡ በአፀደ ገነት ከክርስቶስ ጋር መኖር የናፈቁት፣ ትዕዛዛቱን የጠበቁት፣ በሕጉ የኖሩት ታላቁ አባት ወደ ማያልፈው ሰማያዊ ዓለም አቀኑ፡፡ ያን ዓለም አስቀድመው መርጠውታል፣ መልካሙን ገድል ተጋድለውታል፣ ሩጫውንም ጨርሰውታል፣ በቅድስና ኑረዋል፣ በትህትና ዘመናትን አሳልፈዋል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፡፡
ʺበአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ አልሁ።  ከዝምታ የተነሣ እንደ ዲዳ ሆንሁ፣ ለበጎ እንኳ ዝም አልሁ፤”   እንዳለ አንደበታቸውን ከንግግር ጠበቁት፣ ለበጎ ነገር ዝም አሉ፡፡ ዓለም በጬኸት ትናጣለች፣ ከመልካሙ ነገር ይልቅ ወደ ክፉው ነገር ታዘነብላለች፡፡ እርሳቸው ግን ጩኸት በበዛባት ዓለም፣ ሀሜትና ምቀኝት በተጠናወጣት ምድር ላይ አንደበታቸውን ዘጉ፣ ከአንደበታቸው ቃል ማውጣት ረሱ፡፡ የዝምታቸው ነገር ለሰዓታት ይኾን ሲባል፣ ለቀናት ዘለቀ፣ ለቀናት ይኾን ሲባል ለሳምንታት ዘለቀ፣ ለሳምንታት ይኾን ሲባል ለወራት፣ ለወራት ይኾን ሲባል ለዓመታት ዝም አሉ፡፡ ቃል ሳይሰጡ፣ ከአንደበታቸው ንግግር  ሳያወጡ ዝም ብለው፣ በዝምታ ታዝበው፣ በዝምታ  ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ፡፡ ማረፋቸው በስጋ እንጂ በመንፈስ አይደለም፡፡
ለምን ዝም እንዳሉ፣ በዝምታቸው ዘመንስ ምን እንደታዘቡ አይጠየቁ ነገር አይናገሩም፣ ንግግር ትተዋል፣ ዓለምን ንቀዋል፡፡ ድንቅ ነገር፣ ጩኸት በበዛባት ዓለም ዝምታን መረጡ፡፡
ዘመኑ ወራሪዋ ኢጣልያ በኢትዮጵያ ምድር ወረራ የፈጸመችበት ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ጀግኖችም ከጠላት ጋር በዱር በገደሉ እየተዋደቁ ነበር፡፡ ጠላትን አልመው እየመቱ፣ በጋራና ሸንተረሩ  ይጥሉት ነበር፡፡  በዚህ ዘመን በስሜን በጌ ምድር ጠቅላይ ግዛት  በደብረታቦር አውራጃ ብላታ ፈንታ ተሰማና ወይዘሮ ለምለም ገሠሠ የሚባሉ ደጋግ ባልና ሚስቶች ነበሩ፡፡
እነዚህ ደጋግ ሰዎች ፈጣሪያቸውን የሚፈሩ በበጎ ምግባር የጸኑ ነበሩ፡፡ ፈጣሪም ደግነታቸውን አይቶ፣ መልካምነታቸውን ተመልክቶ፣ ለቤቱ አገልጋይ አስቀድመው የተመረጡ ልጅ ከአብራካቸው ባርኮ ሰጣቸው፡፡ ያም ጊዜ 1930 ዓ.ም ነበር፡፡ በጥበብ አደጉ፣ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ቀለም ይቆጥሩ፣ ዳዊት ይደግሙ፣ መጻሕፍትን ይመረምሩ ዘንድ ወደ መምህር ተላኩ፡፡ ለታላቅ ነገር አስቀድመው የተመረጡት አባት ከመምህራቸው እግር ሥር ተቀምጠው ቀለም ቆጠሩ፡፡ ዳዊትም ደገሙ፡፡  ቅኔ ተቀኙ፣ ምዕራፍ ተማሩ፣ አቋቋም ዘለቁ፣  በድጓም አስመሰከሩ፡፡  አስቀድመው የተዘጋጁት፣ በጥበብ የሚጓዙት አባት ሊቅ ኾኑ፡፡
ሊቁ ትምህርታቸውን በደንብ ከተማሩ፣ ጥበብን ከመረመሩ በኋላ ከተማሪነት ወደ መምህርነት ተሸጋግረው ወንበር ተክለው ማስተማር ጀመሩ፡፡ ጥበብን የሚሹ ሁሉ ከእግራቸው ሥር እየተቀመጡ ይማሩ ጀመር፡፡ ታላቁ አባት መንኩሰው መኖር ምኞታቸው፣ ፍላጎታቸው እውን ይሆን ዘንድ ጸሎታቸው ነበርና ነብሴን ለሥላሴ ስጋዬን ለመነኩሴ ሲሉ መመንኮስን መረጡ፡፡  ገዳማትና አድባራት ወደሚበዙበት፣ ቅዱስ መንፈስ ወደ መላበት ወደ ጣና ሐይቅም አቀኑ፡፡ በሐይቁ ውስጥ ባሉት ገዳማትና አድባራት፣ በገዳማቱ በሚኖሩ መነኮሳት፣ በሁሉም ይደነቁ ነበር፡፡ በገዳመ ዳጋ እስጢፋኖስም ሥርዓተ ምንኵስናን ተቀበሉ፡፡  ያም ጊዜ 1961 ዓ.ም ነበር፡፡
ዲቁና፣ ቅስና፣ ምንኵስና፣ ቁምስና በየፈርጁ ከጥበብ ጋር የያዙት አባት መማር በቃኝ አይሉምና ሐዲሳትን፣ አቡሻኽሩን ተማሩ፡፡ ለከፍተኛ ማዕረግ የተመረጡበት ዘመን እየቀረበ መጣ፡፡ በመንፈሳዊ ተጋድሏቸው ቀጠሉ፡፡ የንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ተጠናቆ የደርግ ዘመን መጥቷል፡፡ ታላቁ አባትም በተጋድሏቸው እንደ ጸኑ ነው፡፡
ታላቁ አባት ለታላቁ ክብር ታጩ፡፡ በ1971 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ኤጵስ ቆጶስ ኾነው ከተሾሙት ሊቃነ ጳጳሳት መካከል አንደኛው ኾነው ተሾሙ፡፡ የጵጵስና ስማቸውም  ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ ኾነ፡፡ የምንኵስና ስማቸው አባ ዘ ሊባኖስ ነበር፡፡ ከዲቁና፣ ቅስና፣ ምንኵስና፣ ቁምስና ከዚያም ጵጵስና ላይ የደረሱት፣ በመልካሙ መንገድ የሚጓዙት አባት በጎዴ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው ተሾሙ፡፡ በዚያ በረሃ በበዛበት ሥፍራም በትጋት አገለገሉ፡፡ ወደ ጎንደር ሀገረ ስብከትም ተዛወሩ፡፡ አያሌ መንፈሳዊ ተጋድሎዎችን አደረጉ፡፡ አብያተ ክርስቲያናትን አሠሩ፣ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያናቸው የተጎዳውን አሳደሱ፣ መንፈሳዊና ታሪካዊ ቅርሶች እንዲጠበቁ አደረጉ፡፡
የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ልዩ ሹም የነበሩትና አብረው የተሰደዱት  መላእከ መእዊ ቀሲስ ልሳነ ወርቅ ውቤ እንደነገሩኝ በመንፈሳዊ ተጋድሎና በልማት ውጤታማነት ለአምስት ዓመታት አንደኛ እየወጡ መሸለማቸውን አስታውሳለሁ ነው ያሉኝ፡፡
ሌላ ዘመን መጣ፣ ታላቁ አባት ለሌላ ክብር ታጩ፡፡ አስቀድሞ ፈጣሪ መርጦ አዘጋጅቷቸው ነበርና በነሐሴ 29/1980 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ተብለው ፓትርያርክ ኾነው ተሾሙ፡፡ ይህም ኢትዮጵያዊ ኾነው በኢትዮጵያ መንበር ላይ በፓትርያርክነት ሲሾሙ አራተኛው ያደርጋቸዋል፡፡
እሳቸው ፓትርያርክ ኾነው በተሾሙበት በዚያ ዘመን ነጻ አውጭ ነን ባዮች በዘመኑ መንግሥት ከነበረው ከደርግ ጋር ይዋጉ ነበር፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ገዳማትና አድባራት ይጎዱ ነበር፡፡ እኒያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ታዲያ ስለ ሚጎዱት አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት ዝም ማለት አይቻላቸውምና ጉዳት የሚያደርሱትን ተው አሉ፡፡  ጦርነት በሚካሄድበትና ካሕናቱ ለተቸገሩባት ለታላቋ አክሱም ጽዮን ካህናት የሚሆን ድጋፍ ያደርጉ ነበር፡፡ በዚያ አካባቢ ላሉ አድባራትና ገዳማት ካህናትም ድጋፍ አደረጉ፡፡
በዚህ ጊዜ ታዲያ የደርግ መንግሥት ታጣቂዎችን ይደግፋሉ ሲል አማቸው፣ ነጻ አውጭ ነኝ ብሎ የተነሳው ወያኔ  ደግሞ ከቀኝ ሽብር ጋር እጃቸው አለ እያለ ለሰማይና ለምድር የከበዱትን አባት ስማቸውን ያጠፋ ነበር፡፡ እሳቸው ግን ለሰው ልጅ መዳን ይጸልያሉ፣ ይሠራሉ እንጂ ይህንስ አስቀድመው የተፀየፉት ነበር፡፡ ያም ዘመን ለእሳቸው ፈታኝ ዘመን እንደነበር መላእከ መእዊ ቀሲስ ልሳነ ወርቅ ነግረውኛል፡፡ ጠቢብ አባት ናቸውና ሁሉንም በጥበብ መሩት፡፡  ታጣቂ ቡድኑ ቅዱስ ሲኖዶስን ይቃወም ነበር፡፡
የደርግ ዘመን ተፈፀመ፡፡ ኢህአዴግ ስልጣነ መንበሩን ያዘ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱን ሲቃዎም የነበረው አዲሱ መንግሥትም ተቃውሞውን በቅዱስ ፓትርያሪኩ ላይ አበረታ፡፡ ቅዱስነታቸውን አጥላላ፣ ባልዋሉበት አዋላቸው፣ ባልሰሩት ሥራ ከሰሳቸው፡፡ ከእርሳቸው ጋርም አብሮ እንደማይሠራ ተናገረ፡፡ በቅዱስነታቸው የተነሳው ጫና በረከተ፡፡ የተቀደሰውን መንበራቸውን ለቀው እንዲወጡ ተገደዱ፡፡  በቅድስና የተቀመጡበትን መንበር ለቅቀው ወጡ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም በአንድ ቤት ተቀመጡ፡፡ ቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ እያለ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም አለች፡፡ ዳሩ አልተቻለም፡፡ አቃቢ መንበር ተሾመ፡፡ ቅዱስነታቸው ተመለከቱ፡፡ ሐምሌ 6/1984 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ኾነው ተሾሙ፡፡ በፈጣሪ ከተመረጡበት፣ በቅድስና ከተቀመጡበት መንበር በግፍ የወጡት አባት የሚሆነውን ሁሉ ተመለከቱ፡፡
ከመንበራቸው ከመውጣታቸውም በላይ በሀገራቸው እንዳይኖሩ ዛቻና ማስፈራሪያ ይደርሳቸው ጀመር፡፡ እሳቸው ግን ለእውነትና ለጸናች ሃይማኖቴ ስል ሰማእታቱ እንደ ተቀበሉት ሞት፣ ሞትን እቀበላሁ፣ እንደ አፈሰሱት ደም ደሜን አፈስሳለሁ፣ የሚመጣውንም ለመቀበል እጠብቃለሁ፣ ተዘጋጅቻለሁ፣ ሞትን በጸጋ እሞተዋለሁ፣ በሞት ውስጥ ማሸነፍን ከጌታዬ ተምሬያለሁና ሞት አያስፈራኝም፣ መከራ አያስበረግገኝም አሉ፡፡ አበው ግን ቅዱስነታቸው ከሀገር እንዲወጡ ተማጸኗቸው፡፡ በሚቀርቧቸው ሰዎችም አስጠየቋቸው፡፡  እሳቸው ግን እምብኝ አሉ፡፡  ከብዙ ድካም በኋላም እየበረታ በመጣው ጫናና እንግልት ከሀገር ለመውጣት ተገደዱ፡፡
መላእከ መእዊ ቀሲስ ልሳነ ወርቅ ወደ ሞያሌ ሄደው ቅዱስነታቸው ስለሚወጡበት መንገድ አመቻችተው ተመለሱ፡፡ በዚያ ዘመን የምናማክረውም የምናምነው ሰውም አልነበረም ሲሉ የነበረውን ጭንቅ መላእከ መእዊ ቀሲስ ልሳነ ወርቅ ያስታውሳሉ፡፡ አንድ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሾፌር ከነበረ  ታማኝ ሹፌር ጋር መላእከ መእዊ ቀሲስ ልሳነ ወርቅ  ተነጋገሩ፡፡  ስሙም መሃሪ ይባላል፡፡ 35 ቁጥር ማርቸዲስ መኪና ያሽከረክር ነበር፡፡ ይህቺም መኪና የእርዳታ እህል ማመላለሻ ነበረች፡፡ ሹፌሩም ይህ ታሪክ ነውና እስከ ሞት ድረስ ቃል እገባለሁ፣ የምታዘዘውን ሁሉ እፈጽማለሁ አለ፡፡ ማርቼዲሷ የተመረጠችበት ምክንያት የእርዳታ ማመላለሻ ስለ ነበረች ፍተሻው ቀለል እንዲል ነበር፡፡
ቅዱስነታቸው ሀገራቸውን እና መንበራቸውን በሀዘን ተሰናብተው ከሀገር ሊወጡ ጊዜው ደረሰ፡፡ ዕለተ እሁድ  መስከረም 30/1985 ዓ.ም በሌሊት በማርቼዲስ መኪና ከአዲስ አበባ ተነሱ፡፡   ከአዲስ አበባ እስከ ሞያሌ ድረስ 14 የፍተሻ ጣብያዎች ነበሩ፡፡ ቅዱስነታቸው የጵጵስና ተክህኗቸውን አውልቀው እንደ አንድ የደብር መሪጌታ ለብሰው በዚያች መኪና ተጓዙ፡፡ በፈጣሪ ረዳትነት የፍተሻ ጣብያዎች ሁሉ አለፉ፡፡
በእልልታና በምስጋና፣ በድባብ የሚሄዱት፣ ሕዝቡን የሚባርኩት፣ ያዘነውን የሚያጽናኑት፣ እጅግ የተዋበ ልብሰ ተክህኖ የሚለብሱት፣ የሚያበራ መስቀል የሚጨብጡት፣ የሚያስደነግጥ በትረ ሙሴ የሚይዙት፣ በፊትና በኋላቸው በካህናትና በዲያቆናት የሚታጀቡት፣ ከፍ ተደርገው የሚከበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ተገፍተው ያለ አጀብ፣ ከሀገራቸው ወጡ፡፡ እረኛው በጎቻቸውን እንዳይጠብቁ ተሳደዱ፣ በጎቻቸውን ጥለው በግዞት ሄዱ፡፡ ወዮላቸው ለእነዚያ በጎች በተኩላዎች መካከል ለሚኖሩት፣ ወዮላቸው ለእነዚያ በጎች ጠባቂ አልባ ለቀሩት፡፡
የኢትዮጵያን ምድር እንደ ጨረሱ ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ዞረው ʺ አይ ኢትዮጵያ” ብለው ማዘናቸውን ቀሲስ ያስታውሳሉ፡፡ የሄዱባትን መኪና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እንደሆነች የሚገልጽ ጽሑፍ ጽፈው፣  በኢትዮጵያ ምድር አቁመው፣ ቆልፈው ቁልፉን ብቻ ይዘው ተሰደዱ፡፡ ሾፌሩም የታሪክ አካል ነኝና ሲል አብሯቸው ተሰደደ፡፡ ዳሩ በኬኒያ ምድር ላይመለስ አሸለበ፡፡
ከሞያሌ፣ ኢቲኦሎ፣ ከኢቲኦሎ ናይሮቢ ገብተው በዚያም ለዓመታት ተቀመጡ፡፡ የተቀመጡትም ከናይሮቢ ወጣ ባለ ጫካ የበዛበት ሥፍራ ነበር፡፡ ከአምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ አሜሪካ አቀኑ፡፡ በኢትዮጵያ የተገፉት ቅዱስ አባት በዓለም ላይ ላለው ኢትዮጵያዊ ጥላ ኾኑ፡፡ አብያተ ክርስቲያናትን አስፋፉ፡፡ ምዕምናንን ባረኩ፡፡ ዓመታት እየተተካኩ ቀጠሉ፡፡ እሳቸውም በሚወዷት ሀገራቸው ናፍቆት እየተቀጡ ተቀመጡ፡፡
ይህ ሁሉ ዘመን ሲሄድ አሳዳጆቻቸውን አይከሱም፣ አይወቅሱም ይሏቸዋል ቀሲስ፡፡ በጸሎታቸው ይበረታሉ እንጂ ንግግሩን አይወዱትም ነበር፡፡ ስለ እውነት ተናገሩ፣ ስለ እውነት ሠሩ ነገር ግን  ባለ ጊዜዎች እውነታቸውን አጣጣሏት፡፡ ሃቃቸውን ገፏት፡፡
በውሸት አደባባይ እውነት መናገር ፋይዳ እንደሌለው ተረዱ፡፡ ለስልጣን የሚደረገው ሽኩቻ፣ መከፋፋልና ፍቅር ማጣት አሳዘናቸው፡፡ እውነት ቦታ ስታጣ ተመለከቱ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በውስጣቸው መገናኘትን ብቻ መረጡ፡፡ እውነት ቦታ በሌለባት ዓለም ከምናገር ዝም ብል ይሻላል ሲሉ አንደበታቸውን ቆለፉ፡፡ ፍትሕ በሌለበት ዓለም ከመናገር ፍትሕ የሚሰጠውን አምላክ በዝምታ ማሰብና መጠበቅ ይሻላል አሉ፡፡ መናገር ትርጉም እንደሌላት አወቁ፣ እውነት ስትገፋ አዩ፣ ንግግር ከለከሉ፡፡
ዘመን ዘመንን ተካ፣ ያሳደዷቸው ተሳደዱ፣ በቤተ መንግሥት የነበሩት ወደ ዋሻ ወረዱ፡፡ የመመለሻቸው ዘመንም ደረሰ፡፡ ወደ ሀገራቸው ሲመጡ ነብሳቸው ሃሴትን አድርጋለች፣ በተቀደሰችው ምድር በተከበረውና በሚያስፈራው መንበራቸው ተቀምጠው የናፈቃቸውን ሕዝብ ባርከዋል፣ በረከት ለሚሻው በረከትን ሰጥተዋል፡፡ ይቅርታና ምህረት ይሆን ዘንድ ያለ መቋረጥ ጸልየዋል፡፡
በሰማእቱ መርቆሬዎስ ስም ጳጳስ የሆኑት፣ በባዕለ መርቆሬዎስ ቀን ከስደት ወደ ቅድስት ሀገራቸው የተመለሱት፣ በባዕለ መርቆሬዎስ ቀን ከአላፊዋ ዓለም ድካም ያረፉት  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በዝምታ ኖረው፣ በዝምታቸው ውስጥ ከፈጣሪያቸው ጋር በልባቸው ተገናኝተው በዝምታ አልፈዋል፡፡ ወደሚወዷት ሀገራቸውና ወደ ተከበረው መንበራቸው  ተመልሰው በሚወዷት ሀገራቸው ነብሳቸው ከስጋቸው ተለየች፡፡ ስጋቸውም በሚወዷት ሀገራቸው ታርፋለች፡፡
በአካለ ስጋ ኾነው መባረክን ያልታደለች ምድር በረከትዎን ትሻለች፡፡ በረከትዎ ይደርባት፣ ምልጃና ጸሎትዎ አይለያት፣ ባሉበት ኾነው አይርሷት፡፡ በረከትዎ ሁሉ በምድር ይሁን፡፡ 
Filed in: Amharic