ብሔራዊ የምክክር መድረክ ኮሚሽን፣ ጥያቄና ተስፋ
ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች)
Tilahungesses@gmail.com
የተሰበረ ግንኙነትን ለማደስ፣ ፍቅርን ለማንበር የሚደረግ ጥረት እጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ገለልተኛ፣በነጻ ህሊና የሚመሩ ሰዎች ያሉበት፣የሞራል የበላይነት ያላቸው ሰዎችን በአባልነት ያቀፈ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ውጤታማ ተግባራትን ይፈጽማል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የብሔራዊ የውይይት መድረክ ሁሉ ውጤታማ ነው ተብሎ አይገመትም፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ከተፈለገ የብሔራዊ የውይይት መድረኩ አላማ እና ዘዴው ለሰፊው ህዘብ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ በብሔራዊ የውይይት መድረኩ ላይ ሊነሱ የሚችሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች፣ ለአብነት ያህል በህዝቡ እዝነ ልቦና ውስጥ ለዘመናት የቆዩ መሰረታዊ ጥያቄዎች ለአብነት ያህል ህገመንግስቱ፣የጎሳ ፖለቲካ፣ የህግ የበላይነት.ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ወዘተ ወዘተ ጥያቄዎችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል ከወዲሁ ማሰላሰል የብሔራዊ ምክክር መድረኩ ኮሚሽን አባላቱ ከወዲሁ ማሰብ ማሰላሰል አለባቸው፡፡ ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ምሁራን የመፍትሔው አካል መሆን ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያሳስባሁ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኞችም ብትሆን የኮሚሽኑን ስራ በገለልተኝነትና በእውነት መሰረት ላይ ሆናችሁ በቅርብ መከታተል፣ ሃሳቦች በነጻነት እንዲንሸራሸሩ በታሪክ ፊት ቆማችኋል፡፡ ከዚህ ባሻግር የህብረተሰቡ እውነተኛ ፍላጎት ምን እንደሆነ ከወዲሁ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል ህዝቡ የሚያቀርበውን የጥያቄ ትርጉም ማቅረብብም ቢሆን የምክረሃሳቡ (የመፍትሔው) አንዱ አካል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አሊያ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወድያ ይሆናል፡፡
በነገራችን ላይ ከሂተለር ናዚ ዘመን በፊት በባሪያ ስርአት አሳዳሪ ዘመን የከፋ አሰቃቂ ወንጀል የተፈጸመ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ቀሪው አለም ክፉና ሰይጣናዊ ድርጊቶችን ለማመላከት ጣታችንን የምንጠቁመው በጀርመን ናዚዎች ላይ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እንዲህ አይነት አስከፊ ወንጀሎችን ማሳያ ወደ የሩቅ ምስራቅ፣አውሮፓ ወይም መሃከለኛውና ሌሎች የአፍሪካ ምድር መሄድ አያስፈልገንም፡፡ በቅርብ ግዜ ታሪካችንም ሆነ ባለንበት ዘመን የኢትዮጵያ መሬት ራሱ ከእብድ ውሻ የከፉ አረመኔዎችን ወይምጨካኞችንና አሜኬላዎችን አብቅሏል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ላይ የፋሺስቶችን ወይም ናዚዎችን ባህሪ የሚያሳዩ ወንጀሎች በቅርብ ግዜ ውስጥ እየተፈጸሙ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ደግሞ የወያኔ አሸባሪ እና ኦነግ አክራሪ ሸኔ ቡድን አባላት፣የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብረት አንጋቾች በመባል የሚጠሩ በንጹሃን ኢትዮጵያዊ ዜጎች ላይ የሚፈጽሙት ግፍ ማሳያ መሆኑ ለማንም ኢትዮጵያዊ ግልጽ ነው፡፡ የሰይጣናዊ ድርጊት ምንጩ ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ ( መልከ ብዙ ነው) በእርግጥ ምንም እንኳን ገለጻ ለማድረግ ብንሞክርም ዘዴው (the mechanism) የተወሳሰበ ነው፡፡
አንድ በአንድ፣የማሰብ ችሎታንና ስሜትን (Thinking (cognition) vs feeling (emotion) ፣ ምክንያትንና እምነትን (reason vs belief) ፣አይምሮን በመመርመር የአንድን ሰው( አንድ ጨካኝ ቡድን አባላትን) ክፉ ሃሳብ ወይም ሰይጣናዊ እቅድ ቀደም ብሎ ለማወቅ እጅጉን ይቸግራል፡፡
ጎሰኝነት በነገሰባት ኢትዮጵያ የእኛ እና የእነርሱ ፖለቲካ ሰይጣናዊ ድርጊቶች ሰርክ አዲስ እንዲፈጸሙ መሰረታዊ ምክንያት ከመሆኑ ባሻግር፡ የሀገሪቱን አንድነትና ህልውና አደጋ ላይ እየጣለው ይገኛል፡፡ እኛ እና እነርሱ መባባሉ እንኳን ለእኛ ድህነት ቤቱን በሰራባት ሀገር በምንኖር ግፉአን ዜጎች ቀርቶ ዩጎዝላቪያን የመሰለ አውሮፓዊት ሀገር ወደ የታሪክ ማህደርነት ቀይሯታል፡፡( In tribalized Ethiopia, Them and Us has become malignant )፣መለያየት ምን የመሰለ ዳቦ በነጻ ይታደላቸው ለነበሩ፣ግፋ ቢል ዳቦ በሳንቲም እየገዙ ይመገቡ ለነበሩ የቀድሞዋ ሶቬዬት ህብረት ሪፐብሊክ ዜጎችም ቢሆን ገነት አላመጣላቸውም፡፡ የዳቦን ነገር ያነሳሁት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዳቦ ጠግበን መመገብ ያቃተን አሳዛኞች ስለሆን ነው እንጂ አነርሱማ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የመጠቁ ናቸው፡፡ ዋናው ቁምነገሩ መለያየት፣መናቆር ለማንም አይበጅም የሚለው መልእክቴ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ጎሰኝነትና ብሔርተኝነት የሚያያዝቻው ቦንዴጅ ተመሳሳይነት ይበዛበታል፡፡ ምንአልባት ልዩነት አላቸው ከተባለ የቁጥር ሊሆን ይቻላቸዋል፡፡ ሁለቱም ጎሰኝነትና ብሔርተኝነት ከደም ጋር የተሳሰረ ግንኙነት ላይ ያተኩራሉ፡፡በአካባቢያዊ ማንነትና ውልደት ላይ ግንኙነታቸው የተመሰረተው፡፡ ከቆሙበት ማህበረሰብ ውጭ ላለው ሌላው ማህበረሰብ የሚደማ ልብ የላቸውም፡፡ ለብሔራዊ ስሜት ያላቸው ግንዛቤ አናሳ ነው ወይም እያወቁ እንዳላወቁ መሆን ሁነኛ መለያቸው ነው፡፡
በሌላ መልኩ ብሔራዊ ስሜት የሰውን ምንነትና የዜግነት ትርጉምን በቅጡ ማወቅ ግድ ይላል፡፡ከፍተኛ የሆነ የመንፈስ ልእልናን ይጠይቃል፡፡ በነገራችን ላይ የአንድ ሰው ማንነት መነሻው ቤተሰብ ለጥቆም ትልቅ ቤተሰብ (clan)፣ ከብዙ ቤተሰቦቸ (clans) የተሰራ (tribe)፣ስርወ መንግስት (kingdom)፣ሀገር( nation-state ) መጨረሻም የአለም ዜግነት (citizen of the world, globalism.) ላይ ይመሰረታል፡፡ የሰለጠነው አለም ማህበረሰብ ራሱን እንደ አንዱ የአለም ዜጋ መቁጠር ከጀመረ አመታቶች ነጎዱ፡፡ የእኛ፣ የሚለው ቀርቶ እኔና እነርሱ አባባል በነገሰበት ሀገር፣አለመተባበር፣እርስበርስ አለመከባበር ባለበት ሁኔታ አለም አቀፋዊ አስተሳሰብ አይታሰብም፡፡ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ምድር ጎሰኝነት ስር ሰዶ ማየቱ ልብን ያደማል፡፡ የኢትዮጵያን እድልም አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ በአንዳንድ አፍሪካ ሀገራት፣ ኢትዮጵያን ይጨምራል፡፡የስልጣን ጥማታሞች እና ሀብትን በብቸኝነት ለመቆጣጠር የሚሽቀዳደሙ አንዳንድ መንግስት ባለስልጠናት በሚሸርቡት ሴራ ምክንያት ጎሰኝነት እየተስፋፋ ስለመሆኑ የታወቀ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ጂኦግራፊና ድንበር የሰውን ማንነት ከመገደብ አኳያ እንቅፋት መሆናቸው እየቀረ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሆነው ስደትና ጋብቻ የአንድን ሰው መኖሪያ ሀገር የሚወሰኑ በመሆናቸው ምክንያት ነው፡፡ ይህም ማለት ለአብነት ያህል አንድ ኢትዮጵያዊ በስደት በሚኖርበት በሌላ ሀገር ከሌላ የውጭ ሀገር ዜጋ ከሆነች ግለሰብ ጋር ጋብቻ በመፈጸም የተለያዩ ማንነቶች ሊኖሩት ይቻለዋል፡፡ ( ከኢትዮጵያዊነት ማንነት ባሻግር ማለቴ ነው፡፡) ድንበር ሁል ግዜም ቢሆን በጦርነት፣በምጣኔ ሀብት ግንኙነት፣ ምክንያቶች ሊቀያየር ይቻለዋል፡፡ ለአብነት ያህል በአውሮፓና ኤሽ አህጉር የሚገኙ አንዳንድ ትንንሽ ሀገራትን መመለከት ይቻላል፡፡
እርግጥ ነው ይገባኛል በአንድ ዘመን በሰላም ተከባብረው፣ተዋልደው፣ተፋቅረውና በአንድነት ይኖሩ የነበሩ ጎረቤታሞች ወደ የመረረ ጥላቻ ውስጥ ገብተው ( አንደኛው ወገን ግዜ የሰጠው፣መሬቱ የኔ ነው፣እናንተ ከሌላ ስፍራ ነው የመጣችሁት በማለት በጎረቤቱ ላይ አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈጽመው በተወሳሰቡ ምክንያቶች ሊሆን ይቻለዋል፡፡) ሆኖም ግን ይሁንና ውስብስብ ምክንያቶች አንድ ጎረቤት የነበረ ማህበረሰብ በሌላው ወንድሙ ላይ ዝርፊያ ሲፈጽም አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ሲፈጽም፣የጎረቤቱን የቤት እንስሳት ሲገድል፣ ቤተ እምነቶችን ሲያቃጥል፣ ለደከመበትን የጎረቤቱን ሀብትና ንብረት ሲዘርፍ ወዘተ ወዘተ አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ ለምን ብሎ መጠየቅ የሰውነት ባሀሪ ነው ተብሎ ቢጻፍ ስህተት የሚል ይኖር ይሆን ? አይመስለኝም፡፡ በእኔ በኩል የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምክንያቶች ውስብስብ ቢሆኑም ለምን ብሎ መጠየቅ ግን ተፈጥሯዊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የጥላቻን መርዝ እንዴት ማርከስ ይቻላል ? አንድን የፖለቲካ ድርጅት ያለምንም አመክንዮ የሚደግፉ ጭፍኖችን እንዴት ደ ምክንያታዊ ደጋፊዎች እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል ? የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎች የሰብአዊ መብት አክባሪዎች እንዲሆኑ ማግባባት ይቻላልን ? እነኝህንና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎቹን ለመመለስ በሰውነት ደረጃ ላይ መቆም ይገባናል፡፡ ሰው ማለት ምን ማለት እንደሆነ ትርጉሙን ማወቁ ተገቢ እንደሆነ ማወቁ አይከፋም ለዚህ ደግሞ የሰውን ባህሪ የሚተነትኑ መጽሐፍትን ማንበብ ያስፈልጋል፡፡ እንደው ዘም ብሎ የሰውን ልጅ ክፉም ሆነ መልካም ባህሪ ለመረዳት አዳጋች ይመስለኛል፡፡
በተለይም ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎችን ባህሪ ለመረዳት እውቀት ይጠይቃል፡፡ በሌሎች ንጹሃን ዜጎች ላይ ወንጀል የሚፈጽሙ፣የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙ ግለሰቦችንም ሆነ ቡድኖችን ባህሪ ማጥናት ወንጀሎች ወይም የሰብአዊ መብት ጥሰት ከመፈጸማቸው በፊት መከላከል ያስችላል፡፡ በተለይም የአንድ ሀገር መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰት ከመፈጸሙ በፊት ለመከላከል ያስችለው ዘንድ በቅድሚያ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎችን ባህሪ በቅጡ መረዳት ያለበት ይመስለኛል፡፡ የት፣እነማን፣ለምን፣መቼ፣እንዴት፣ በእነማን ወዘተ ወዘተ የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በቅጡ የሚመልስ መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎችን አደብ ለማስገዛት አይቸግረውም፡፡
እንደ መደምደሚያ
አለም ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሁላችንም የተመቹ አይደሉም፡፡ በዚች ምድር ላይ በአብዛኛው የደላቸው ምእራባውያን የራሳቸውን የተደላደለ በማድረግ በተለያዩ የአለም ክፍሎች ጦርነት እንዲቀጣጠሉ በማድረግ ገሃነም እሳት ፈጥረዋል፡፡ ( በነገራችን ላይ ምእራባውያን ብቻ ሳይሆን አንዳንድ እንደ ሳኡዲ አረቢያ፣ቱርክ፣ኢራቅ፣ግብጽ፣ አረብ፣ኤሜሬትስ፣ሩሲያ የመሳሰሉት ሀገራት) በየመን፣ሶሪያ፣ኢራቅ ወዘተ ወዘተ የሚቀጣጥሉትን ጦርነት ልብ ይሏል፡፡) በኢትዮጵያም ቢሆን የራሳቸውን ልጆች በአውሮፓና አሜሪካን ሀገር በታወቁ ዩንቨርስቲዎች የሚያስተምሩ የድሃውን ልጆች ወደ ጦርነት የሚማግዱ ሞለተው ተርፈዋል፡፡ ጎበዝ ሰላም ለምን ይጠፋል በማለት እንደ ሰው ማሰብ አለብን፡፡ ሌላው አለም በተድላና ደስታ እየኖረ ለምን እኛ ቀኑ ጨለመብን ብለን መጠየቁ የሰውነት ባህሪ ነው፡፡ በቀሪው አለም በተለይም በሰለጠነው አለም የኑሮ እድገት እየተሻሻለ የመጣው፣ቁጭ ብሎ ለመነጋገር የተቻለው፣አንድነት፣ፍቅርና የሰላም አየር እየነፈሰ የመጣው በሰውነት ደረጃ ላይ ስለቆሙ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ሁሉ በመጪው የብሔራዊ እርቅና ውይይት መድረክ ላይ የሚቀመጡ የፖለቲካ ሀይሎች ተወካዮች ሁሉ በሰውነት ደረጃ ላይ እንዲወጠ፣ ከእኛና እናንተ የደካሞች ፖለቲካ እንዲወጡ፣ አንተ ትብስ፣አንቺ ትብሽ እንዲባባሉ ከወዲሁ በሰለጠነ መንገድ፣ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት መወትወት መማጸን አለብን፣ በነገራችን ላይ መጪው የውይይት መድረክ ከዳቦና ኬክ አንዱን ለመምረጥ የሚደረግ አይደለም፡፡ ብሔራዊ የውይይት መድረኩ የቆዩ የኢትዮጵያን መሰረታዊ የፖለቲካ ችግሮችን በግልጽ ውይይት አማሃኝነት ሰራሄ መፍትሔ የሚገኝበት መሆን ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡
እውን እኛ ኢትዮጵያውያን የተሳካ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ለማንበር ይሳካልን ይሆን እስቲ በየአካባቢችሁ ተወያዩበት፡፡ በእኔ በኩል በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ለመገዛት ከሆነልን የቀና ውይይት ለማድረግ ይቻለን ይሆን ብዬ አስባለሁ፡፡ ለማናቸውም ወደ ስምምነት ለመድረስ፡-
- የሚዋደዱ፣የሚፋቀሩ ሰዎች ባህሪ ሊኖረን ይገባል
- ለሌው ማዘን፣መቆርቆር፣
- ፈሪሃ እግዛብሔር ያደረብን ሰዎች፣
- በእውቀት የበለጸጉ ሰዎች በውይይት ላይ መካፈል አለባቸው
- ኢትዮጵያን በመዘንጋት የራሳቸውን ትንንሽ ጎጆ ለመቀለስ ያሰቡ ከዚህ ታሪክ ይቅር የማይለው ከባድ ስህተት ለመታረም መንፈሳ ወኔ መታጠቅ አለባቸው
- የተማሩ ሰዎች ፣ እውቀት ያላቸው ሰዎች እውቀታቸውን ከሀገራዊ ጥበብ ጋር ማጣመሩ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ
- …መከባበር፣አንተ ትብስ፤ አንቺ ትብሽ፤ ነግ በኔ፣ ወዘተ…የመሳሰሉት ጠቃሚ ብሂሎች ገቢራዊ ቢሆኑ መልካም ነው፤
በመጨረሻም የተከበሩ የብሔራዊ የውይይት መድረኩ ኮሚሽን አባላትም ሆኑ የብሔራዊ የውይይት መድረኩ ላይ የሚካፈሉ የፖለቲካ ሀይሎች የሰውን ባህሪ ለመረዳት በሺህ የሚቆጠሩ የመጽሐፍት ገጾችን ማንበብ እንደማይጠበቅባቸው ሳስታውስ በታላቅ አክብሮት ነው፡፡ ከእነርሱ የምንጠብቀው ራሳቸው በሰውነት ደረጃ ላይ ቆመው ውይይቱ የተቀና እንዲሆን ማመቻቸት፣ በውይይቱ ላይ የሚካፈሉት ደግሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅም ውጤት ለማምጣት መንፈሳዊ ወኔ እንዲታጠቁ በመማጸን እሰናበታለሁ፡፡
የካቲት 26 ቀን 2014