>

ከምርጫ 97 በፊት በአዲስ አበባ ፖሊስ እንዴት ይመለመላል? ፓሊስ እንዴት በማህበረሰቡ ተጠያቂ ይሆናል? (ኤርሚያስ ለገሰ)

ከምርጫ 97 በፊት በአዲስ አበባ ፖሊስ እንዴት ይመለመላል? ፓሊስ እንዴት በማህበረሰቡ ተጠያቂ ይሆናል?
ኤርሚያስ ለገሰ

*…እስከ ዛሬም ድረስ የአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን በጀት (የፓሊስ አባላትን ደሞዝ ጨምሮ) የሚሸፈነው አዲስአበቤ ከሚከፍለው ግብር ነው። የአዲስ አበባ ወጣት በስራ አጥነት እየተሰቃየ 50ሺህ የፓሊስ አባላትን ከሌላ ቦታ መልምሎ በማምጣት አዲስአበቤ ከሚከፍለው ግብር መቅጠር ከሕግም፣ ከሞራልም አንፃር ወንጀል ነው።
*… እንዴት ነው ነገሩ?
፩. የትግራይ ክልል ፓሊስ ለመሆን ከትግራይ ውጭ ተመልምሎ ያውቃል?
 
፪. የአማራ ክልል ፓሊስ ለመሆን ከአማራ ክልል ውጭ ተመልምሎ ያውቃል?
 
፫. የአፋር ክልል ፖሊስ ለመሆን ከአፋር ክልል ውጭ ተመልምሎ ያውቃል?
 
፬. የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ለመሆን ከኦሮሚያ ክልል ውጭ ተመልምሎ ያውቃል?
 
፭. የአዲሲቷ ሲዳማ ክልል ፓሊስ ለመሆን ከሲዳማ ክልል ውጭ እየተመለመለ ነው?
 
፮. የሶማሌ ክልል ፓሊስ ለመሆን ከሶማሌ ክልል ውጭ ምልመላ ይካሄዳል?
 
… ለአዲስ አበባ ከክልሎች…??? ምን ማለት ነው
ከምርጫ 97 በፊት በአዲስ አበባ የፓሊስ ምልመላ የአፈፃፀም ችግሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ጥሩ የሚባል አሰራር ነበረው። ከአፈጻጸም ችግሮቹ መካከል ከመመሪያው ውጭ በድብቅ የገዥው ፓርቲ ወይም የፎረም አሊያም የወጣቶች ማህበር አባል መሆንን ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑ ነበር። አልፎ አልፎ በዘመድ አዝማድ እና ፒቲ ኮራፕሽን ምልመላ ይካሄድ ነበር። የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ቤተሰብ የሆነም የመመልመል እድሉ እጅግ በጣም ጠባብ ነበር።
ከላይ ከተጠቀሰው የአፈጻጸም ችግር ውጪ አካሄዱ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነበር። በዚህ አጋጣሚ እኔም ከአዲስ አበባ ዞኖች የአንዱ አስተዳዳሪ በነበርኩ ሰዓት በቅርበት ስከታተለው የነበረ ዘርፍ ነው።
እስቲ ምልመላው እንዴት እንደሚካሄድና ማህበረሰባዊ ተጠያቂነት ለማምጣት ምን ጥረት ሲደረግ እንደነበር ላንሳ፣
፩ኛ፡ በሁሉም ቀበሌዎች በተለያዩ አደባባዮችና የማስታወቂያ ቦርዶች ላይ ወጣቶች ወደ ፖሊስ እንዲገቡ ግልጽ መስፈርቶቹን የያዘ ማስታወቃያ ይለጠፋል። ከመስፈርቶቹ መካከል የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀቀ እና በህብረተሰቡ ዘንድ በመልካም ስነ ምግባሩ የሚታወቅ የሚሉ ይገኝበታል።
፪ኛ፡ ወጣቶቹ የተጠየቁትን ማስረጃ ይዘው ወደ ቀበሌ ይመጣሉ። ምዝገባው የሚካሄደው በቀበሌው የፓሊስ ተወካይ፣ የመስተዳድሩ ተወካይ፣ የአካባቢ መካሪ ሽማግሌ ተወካይ፣ የእድር አመራር ተወካይና የሐይማኖት አባት ተወካይ ባሉበት ኮሚቴ ይፈፀማል።
፫ኛ፡ ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኋላ ኮሚቴው በድብቅ የተመዘገበው ወጣት ጎረቤቶች ጋር ሄዶ ስለ ተመልማዩ ማንነትና ፀባይ መረጃ ያሰባስባሉ። ተጨባጭ ችግር አገኘንበት የሚሉትን ውድቅ አድርገው ለሚቀጥለው ምዕራፍ ያዘጋጃሉ።
፬ኛ፡ የሰንበት ቀናት ተጠብቆ ህዝቡ በአዳራሽ እንዲሰበሰብ በማይክራፎንና የእድር ጡሩንባ ጥሪ ይተላለፋል። እያንዳንዱ የፓሊስ ተመልማይ ፕሮፋይል ቀርቦ ግምገማ ይካሄዳል። ሕዝቡ ነገን በማሰብ የራሱን ልጆች ያለ ይሉንታ አብጠጥሮ ይመረምራል። ለቀጣዩ መድረክ ያስተላልፋል።
፭ኛ፡ ከቀበሌው መድረክ ቀጥሎ በወረዳው የሚገኝ ሕዝብ ጥሪ ቀርቦለት ተመልማዮችን ይመረምራል። ይህም የሕዝብ መድረክ ፍፃሜ ይሆናል።
በዚህ መልኩ የተለዩ ወጣቶች ወደ ፖሊስ ማሰልጠኛ ማዕከል ገብተው ይሰለጥናሉ። ስልጠናውን ሲጨርሱ በየአካባቢያቸው በመመደብ ቤተሰቦቻቸውን ያገለግላሉ። በዚህም ሳይወሰን የአካባቢው ሕዝብ በየአመቱ ክረምት ላይ በየአዳራሹ በመሰብሰብ በወረዳ ደረጃ አፈፃፀማቸውን ይገመግማል። ጎበዞቹን፣ ጠንካሮቹን፣ መልካም ስነ ምግባር ያላቸውን ይሸልማል። መታረም ያለባቸውን እንዲታረም ይመክራል። መታረም ያልቻሉትን እንዲሰናበቱ ምክረ ሃሳብ ያቀርባል።
(በምስጋና ፕሮግራም ላይ ታዋቂ የኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ዝግጅታቸውን በነጻ ያቀርባሉ። ከዚህ አንጻር ድምጻዊ ሀመልማል አባተ በቀድሞ ወረዳ 23 ሳርቤት ለሶስት ተከታታይ አመታት በነጻ ዝግጅቷን ስታቀርብ በእንግድነት ተገኝቼ ነበር ።)
ከዚህ ሁሉ ሀተታ በኃላ አንዳንዶች “ምንድነው የምታወራው?” ሊሉ ይችላሉ። ተገቢ ጥያቄ ነው ። አዎ እጅግ ተገቢ ጥያቄ ነው ።
ዛሬ አዲስ አበባ 50ሺህ ምስለኔ ፓሊሶች ከሌላ ቦታ እየተመለመለላት እንደሆነ መረጃ ወጥቷል። እነዚህ 50ሺህ ምልምል ፓሊሶች ለአዲስአበቤ እየመጡበት እንጂ እየመጡለት አይደለም። እየመጡ ያሉት ሊያስፈራሩትና ሊቀጡት ነው።  አዲስአበቤ አያውቃቸውም። እነሱም አያውቁትም። የማያውቁትን ደግሞ ነገ ከነገ ወዲያ ተጠያቂ ሊያደርጉት አይችሉም። ከሁሉም በላይ እነዚህ ኃይሎች በበታችነት እና ከተሜ ጠልነት የሚሰቃዩ እንደመሆናቸው መጠን ግብራቸው እንደ እንስሳት አብዮቱ “የናፓሊዮን ተናካሽ ውሾች!” ይሆናል። በረባው ባልረባው እየነከሱ የሚገድሉ!
እናም አዲስአበቤ በሰላማዊ ሕዝባዊ ተቃውሞ ድርጊቱን በማውገዝ በአስቸኳይ እንዲቆም አድርግ። አለበለዚያ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ይሆንብሃል።
Filed in: Amharic