ታሪክን ወደኋላ
የመጀመሪያው የጉንደት ጦርነት በኢትዮጵያውያን አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ በግብፅ በኩል ሽንፈቱና የነ ኮሎኔል አለን ድሩፕ መሞት በካይሮ እንዳይሠማ በጥብቅ ተከለከለ። ግብፆች ዐፄ ዮሐንስን ድጋሚ በመውጋት በደንብ ትምህርት ሠጥቶ ለመቅጣትና ያለፈውን ሽንፈት ለመበቀል ከፍ ያለ የጦርነት ዝግጅት ያደርጉ ጀመር።
ስለዚህም ቁጥሩ እስከ 15,000 የሚሆን እጅግ ዘመናዊ ጦር ሠራዊት አደራጅተው ጦሩን እንዲመሩ የግብፅ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ አዛዥ መሐመድ ራቲብ ፓሻ በጠቅላይ አዛዥነት አሜሪካዊው ጄኔራል ዊ.ዊ . ሎሪን ቺፍ ኦፍ ስታፍ (ኤታማዦር) ሆኖ ከእነሱም ጋር ዊሊያም ማክ ዳይና ቻርለስ ፊልድ የሚባሉ ኮሎኔሎች ተጨመሩላቸው።
በጀርመን ሀገር የጦር ትምህርት ቤት የተማረው የተማረው ልዑል ሐሠን የሚባለው የኢስማኤል ፓሻ ልጅም አብሮ ተመደበ።
በዚህ አይነት ካይሮ ላይ ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀ የወታደሩ ቁጥር እንደ አስፈላጊነቱ እስከ 25,000 ከፍ ሊል እንደሚችል ተነግሮት ጠቅላይ አዛዡ ጉዞውን ወደ ምፅዋ ጀመረ።
ከምፅዋም ደርሶ በጥር ወር ላይ ወደ ደጋው ወደ አስመራ ወጥቶ ጉራዕ ደረሰ። አጤ ዮሐንስም ቀደም ብለው “አንተም ከአባቶችህ አትበልጥም! እኔም ከአባቶቼ አላንስምና በየአገራችን ረግተን እንደቀድሞው ወዳጅነታችንን እንቀጥል” እያሉ ለከዲቭ ኢስማኤል በደብዳቤ ያሳሰቡት ውጤት ሳያገኝ ቀረ።
የግብፅ ጦር ከቀድሞው በበለጠ ተዘጋጅቶ በራቲቭ ፓሻ እየተመራ ጉራዕ ላይ መስፈሩን ሲመለከቱ ከ 15, 000 እስከ 50,000 የሚሆን ሠራዊታቸውን ይዘው በራሳቸው ጠቅላይ አዛዥነትና ራስ ባርያውን ደግሞ ምክትል አዛዥ አድርገው ወደ ጉራዕ አመሩ።
በጉንደቱ ጦርነት የደረሠውን የመሸነፍ ውርደት ያውቃልና ራቲቭ ፓሻ ከነሠራዊቱ ደንበኛ ምሽግ አሠርቶ መድፉንና ጠመንጃውን ጠምዶ ከምሽጉ ተቀመጠ። ኢትዮጵያውያኑም ወደ ምሽጉ ሄደው መዋጋቱ አደጋ መሆኑ ስለገባቸው ሁለቱም በቅርብ ርቀት እየተያዩ ሳይዋጉ ብዙ ጊዜ አሳለፉ።
በመጨረሻ ግን የጦርነቱ ጊዜ መራዘም ለሁለቱም ተዋጊዎች ዘንድ በስንቅና በውሃ ረገድ ችግር የሚያመጣ በመሆኑ ግብፆቹ ከምሽግ ወጥተው የአጤ ዮሐንስም ጦር ከሠፈረበት ቦታ ተንቀሳቅሶ በመጋቢት 7 ቀን 1868 ዓ.ም ውጊያ ገጠሙ።
በጦርነቱም የኢትዮጵያ ሠራዊት በሜዳው ጦርነት ላይ ማጥቃት ሲጀምር ግብፆችም ተመልሰው ወደ ምሽጋቸው ገቡ። ኢትዮጵያውያኑም እስከ ምሽጉ ድረስ እየተከታተሉ ፈጇቸው። በዚህ አይነት በሜዳ የወጣው የግብፅ ጦር ቢሸነፍም በምሽግ ውስጥ ያሉት መመድፍና በጠመንጃ ብዙውን የኢትዮጵያ ሠራዊት ፈጅተውታል። ለተከታታይ ሁለት ቀናትም በምሽግ የቀረው የግብፅ ሠራዊት ጠንክሮ በመዋጋቱ ሊደመሰስ አልቻለም።
በዚህ ጉራዕ ጦርነት ላይ በሜዳ ላይ ከተደረገው ጦርነት ከ 3500 እስከ 4500 የሚሆን የግብፅ ጦር ሲደመሰስ እስከ ከ 2500 እስከ 3500 የሚሆነው ደግሞ ተማርኳል። በመሳሪያ ረገድ ከምሽግ ወጥቶ የተጠመደው 20 መድፍና 13000 ሬሚንግተን ጠመንጃ ከብዙ ሺህ ከሚቆጠር ጥይት ጋር በኢትዮጵያውያኑ ተማርኳል።
በኢትዮጵያውያን በኩል 5000 ሠራዊት የሞተና የቆሰለ ሲሆን ግማሹ ዘማች ብዙ የምርኮ መሳሪያና ዕቃ ስላገኘ ያለ ስንብት የማረከውን እየያዘ ወደሀገሩ ስለሄደ ከጦርነቱ በኋላ ንጉሡ አጠገብ የተገኘው ጦር 25,000 ብቻ ነበር።
ለሁለተኛ ጊዜ አጤ ዮሐንስን ሊቀጣ መጥቶ የነበረው ጦር ራሱ ተቀጣ። ከዲቭ ኢስማኤልም ለሶስተኛ ጊዜ ለመሳሳትም አልደፈረም።
ሁሉንም ነገር አመዛዝኖ “እንግዲህ በቃን” ብሎ ጦረኛ የነበረው መሪ ሠላማዊ ሆኖ በምሽግ ውስጥ ያሉትን የቀሩትን ሠራዊቶች ለማስለቀቅ የዕርቅ ደብዳቤ መፃፃፍ ጀመረ።
ይህ የጉራዕ ጦርነት በኢትዮጵያውያን አሸናፊነት የተመዘገበው ከ 146 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ዕለት መጋቢት 7 ቀን 1868 ዓ.ም ነበር።
ይህንን አፄ ዮሐንስ ሁለት ጊዜ በተከታታይ ግብፆች ላይ ያገኙትን ድል በማውሳት የአገራችን ገጣሚ እንዲህ አሞግሷቸዋል።
ከላይ የወረደው ከፅዮን መቅደስ
ባባቱ ሚካኤል በእናቱ ሥላስ
አጨደው ከመረው ያን ያሕዛብ ገብስ
ወቃው ደበደበው ሰጠው ለንፋስ
ዐሊሙ ነፍጠኛ ዐፄ ዮሐንስ
ክብርና ሞገስ ለጀግኖቹ