>

እንደ አይሁዳዊያን አገር አልባና በሚሊዮን እስክንፈጅ መጠበቅ አለብን? (ፊልጶስ)

እንደ አይሁዳዊያን አገር አልባና በሚሊዮን እስክንፈጅ መጠበቅ አለብን?

ፊልጶስ


አይሁዳዊያን በጥንት ዘመን ለውጭ ወረራና ብሎም፤  አገር አልባ  ለመሆን ከበቁበትን ምክንያት አንዱ በነገድ ተከፋፍለው በእንድነት  ለህልውናቸው ተደራጅተው  መታገልና በጋራ መቆም  አለመቻላቸው መሆኑ  ይነገራል። እንደ እኛ እንደ አሁን ዘመነኛ ትውልዶች፤ የውስጥ ችግራችውን መፍታት ስላልቻሉና ስለተናናቁ። 

 በኋላም  እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ እንደ ጨው ዘር ተበትነው ሲኖሩ ብዙ  ስቃይን አይተዋል። በየሄዱበት አገር በማህበረሰቡ  ዘንድ ብዙ ተቀባይነት አላገኙም። ስድብና ውርደት፣ መገለልና መሳደድን  አይሁድ በመሆናቸው ብቻ  ያስተናግዱ ነበር።  አንዳንዴም  ይገደላሉ፤ የእምነት መቅደሳቸውም ይቃጠል ነበር።   ታዲያ በዚህ ሁሉ ዘርፍ ብዙ ስቃያቸው በንግዱና በፍልስፍናውም ሆነ በጥበቡ ዓለም የተሳካላቸው ቢሆነም፤ እጅግ በጣም ጥቂቶቹ  ወደ ጥንት ምድራቸው ቢመለሱም አብዛኛዎቹ ግን ለሚደርስባቸውና ለሚፈጸምባቸው ሰባአዊነት ተጨባጭ መፍትሄ አልፈጠሩም። 

የጽዮናዊነትን ድርጅት ቢመሰረትም አይሁዳዊያን በዓለም ላይ ያላቸውን የንግድ  የበላይነት የሚያጡ ስለሚመስላቸው ብዙዎቹ  ወደተስፈዋ ምድርከመመለስ እየተናቁና እየተዋረዱ መኖርን መረጡ። 

ጽዮናዊነት በአይሁድ ዜጋ ቴዎዶር ሄርዝል (1860-1904 ( ፡አ፡አ))   1997 ሲመሰረት ዋና ዓላማው፤  በዓለም ላይ የተበተኑት አይሁዳዊያን ወደተስፈዋ ምድርእንዲመለሱና የሚሉት አገር እንዲኖራቸው ነው። ቴዎዶር ሄርዝል አገር እስከሌላቸው ድረስ፤  በየግዜው የሚደርሰው  በማንነት መገለለና  ጥላቻ  አንድ ቀን እልቂትን እንደሚያመጣባቸው  አስገንዝቦ ነበር።  

ነገር ግን ጽዮናዊነት እየተጠናከረና  በዓለም ዙሪያ ያሉ አይሁዶችን ቢያሳትፍም የተወሰኑት  ወደ አሁኗ እስራኤል  ቢመለሱም ብዙዎቹ  የዘመኑ አይሁዶች በየአሉበት አገር መኖርን መረጡ።   ቴዎዶር ሄርዝል  የፈራው አልቀረም የሁለተኛው ዓለም ጦርነት  ከስድስት ሚልዮን በላይ  አይሁድ በላ። አይሁዳዊያን ምን አልባትም ቀደም ብለው የጽዮናዊነትን  ዓላማ ቢተገብሩ ኖሮ የተጠበቀውን ያህል አይሁድ አያልቅም ነበር ይባላል። በሁለተኛው ዓለም ጦርነት የደረሰባቸው እልቂት  የዛሬዋን እስራኤል  እድትመሰረት አደረገ።  

ታዲያ ዛሬ እኛም በገዛ አገራችን  ያውም ከውጭ በመጣ ጠላት ሳይሆን በገዛ ወግኖቻችን  ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን  በመጠላት፤ ከአለፋት ሃማሳ ዓመታት  ጀምሮ   በኢትዮጵያዊነታችን ብቻ መሳደድ፣ መገደል፣ በማንነታችን እንድናፍርና እንደንሸማቀቅ፣ ብሎም  መገለጫችን የሆነው ሁሉ አየተወገዘ፤ መጠቀም ሆነ መያዝ እንዳንችል እየተደረገ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረን በየእስር ቤቱና በአሳዳጅዎቻችን ፍርድ ቤት እየተንከራተትን  ነው።  

የእኛን  ከአይሁዳዊያን የባሰና የተለየ  መራራ የሚያደርገው፤ ኢትዮጵያዊኖች የገዛ አገራቸውንና ለዘመናት አብሮ የኖረውን፤ እንደ ሸማ የተገመደውን፤ በክፋም በደጉም አብሮ የኖረውን  ወገናቸውን፤ በጎሳ ከፋፍለው  በጠላትነት ፈርጅው ለማጥፋት ሌትተቀን ሳይታክቱ ተደራጅተው መሥራታቸ ሳያንስ፤ የ’ነሱን እኩይ አመለካከትም  ለትውልድም ማስተላለፋቸው ነው።    

ሌላው  የእኛ አሳዛኝና  የግብዝነታችን ጥግ ያሚያሳየው ጨቋኝና ተጨቋኝ ፈጠረውና በጎሳ ከፋፍለው  ወገን በወገኑ ላይ ሰይፋ መዞ እንዲጫረስና አገር አልባ ለማደረግ የሚጥሩት ቡድኖችም ሆነ ግለሰቦች፤ እንወከለዋለን ከሚሉት ህዝብ ጋር የምግባርም ሆነ የፍላጎት እንድነት የሌላቸውና በስሙ ክብሩን የሰው ልጅ ደም የሚያፈሱ መሆናቸው ነው። 

ጥያቄው  በኢትዮጵያዊነታችን የሚደርስብን ጥቃትና ማሳደድ ከትላንቱ ዛሬ እየተጠናከረና  መንግሥታዊ  መዋቅርና ህግ ወጥቶለት እየተፈጸመብን  እያለ እኛ ምን እያደርግን ነውወይስ  እንደ እይህይዳዊያን አገር አልባና በሚሊዮን እስክንፈጅ መጠበቅ አለብን

አሁን ያለው ኢትዮጵያዊያንን የማጥላላት፣  የማሳደድ፡ የመግደልና  አገር አልባ የማድረግ ግብ፤  እንደ አይሁዳዊያን ሁሉ በእኛም በአንድ ጀምበር የመጣ አይደለም።    

ጸረኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን የራሳቸውን ማንነት ክደውና አስክድተው፤   እንድ ርምጃ ወደ ፊት ሲሄዱ እኛ ደግሞ እንድ ርምጃ ወደ ኋላ እንሄዳለን። 

በህገመንግሥት ደረጃ ብሔር፣ ብሔረስቦችና ህዝቦች ብለው በጎሳ ከልለው ሲገዙንና በማንነት ዜጋን ሲያሳድዱ ዝም ስለተባሉ   እኛ እንደምንፈልገው ካልገዛናችሁ ከፊሎቹ  እንገነጠላለን ሲሉ፤ ከፊሎቹ ደግሞኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን  እንደሚወርዱ ይደነፋሉ። አገርንና ህዝብን በጦርነት ያምስሉ።

አንድ ኢትዮጵያዊ በማንነቱ ሲገደል ምንም ባለማድረጋችን እነሱ በመቶዎች ይገላሉ፤ ያርዳሉ። 

በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች በማንነታቸው ብቻ ሲፈናቀሉ፤ ምንም ባለማድረጋችን አሁን በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ለማፈናቀልና ለማሳደድ በቁ።

– ሃይማኖት በገዥዎች ሲናቅና የእምነቱ ”ዶግማ” ተሽሮ ጳጳስ እንዲሰደድ ሲደረግ፤  የእምነቱ አባቶችም ሆኑ ምዕመናኑ ምንም ባለማድረጋቸው፤ ዛሬ ቤተክርስቲያን  በጎሳ ስብስብ  ከሚዘወረው ቤተ-መንግሥት  ትዕዛዝ ተቀባይ  ለመሆን በቅታ፤ የቤተክርስቲያን ቃጠሎም ሆነ የዜጎችን እልቂት እንዳልሰማች ሰምታ ታልፋለች።

ክቡርሰንደቅ ዓላማችን አረንጓዲ፣ ቢጫ፤ ቀይ  ረግጠው ሲያቃጥሉና ቀይረውት  የሰይጣን ይሁን የዓምልኮ ዓርማ ሲለጥፋበት ዝም ስላልናቸው፡ ዛሬ  ይዞ መገኘትም ሆነ   አሰፍቶ መልበስ እንደወንጀል ተቆጥሮ የሚያሳሰርና የሚያስገድል ሆነ። ጭራሽ ምን ታመጣልችሁ በማለት ‘’ዮኒቨርስቲ’’ የተባለው ትውልድ በእውቀት የሚታነጽበት፤ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ መያዝና የንጉስ ሚኒልክ  ምስል ያለው ልበስ ከለከለ። ጎሳን መስፈርት ያደረገው የትምህርት ተቋም በቀጥዩ ምን ሊያደርግ እንደሚችል መገመት አያዳግትም።  

መረሳት የለሌበት  የአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ  ከሰላሳ ዓመት በፊት ከአርባ አንድ የበለጡ እውቅ  ምሁራኖችን በማንነታቸውና በአመለካከትቻው ብቻ ሲያባርር፤  ተደራጅተው በመታገልና በማታገል ፋንታ፤  በየአገሩ ተበታትነው ምንም ለማደርግ ባለመቻላቸው ፤ በወቅቱ የነበሩት ገዥዎች  በአጥቃላይ በሚባል መልኩ የአገሪቱን የትምህርት ተቋም ገድለው፤ ጎሳን የሚያመልክ መንደረተኛ ትውልድ መፈለፈያ አድረገውት አሁን እንደሚታየው የኢትዮጵያዊነትን  መገለጫ  መጠቀም ወንጀል ሆኖ ህግ-ወጣ:: 

እንዲህእንዲህ እያለ  የመጣው የጎሰኝነት በሽታ  ከማንኛውም ግዜ በበለጠ ተጠናክሮ አገራችን፤ የድህነት፣ የስቃይ፣ የጦርነትና የሰው ልጅ  አይቶና ሰምቶ የማያውቀው  የጭካኔና የአረመኔነት ተግባር የሚፈጸምባት ለመሆን በቃች። 

እጅጉን የሚገርመው በጎሰኝነትና በኢትዮጵያ ጥላቻ ያበዱ ገዥዎቻችን ፤ የዘርን ፓለቲካ የሃብት ምንጫቸውና የስልጣናቸው ማሰጠብቂያ ስለአደረጉት፤ ያለፈውንም ሆነ አሁን ያለው የርስ በርስ እልቂት የሚፈልጉት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ፤ በተረ-መንግሥቱን ተቆጣጥረው አገርንና ህዝብን ይዘው ከመጥፋት ወደ ኋላ የማያሉና ለመመከርም ሆነ ቆም ብለው ለማሰብ ፍጹም ፍላጎት የሌላቸው መሆናቸው ነው። አሁንም ባለፈው የጥፋትና የልቂት  ምንጭ በሆነው የጎሳ- ህገ መንግሥትና የጎሳ ክልል እንደሚቀጥሉ  አስረግጠው ነግረውናል።

 ታዲያ በዚህ ሁሉ መሃል  እንዲጠፋ የተፈረደብት ኢትዮጵያዊ፤ ካለፈው ትምህርት ወስዶ፣  ራሱን ለመከላከልም ሆነ አገር ለማትረፍ የሚያደርገው ተጨባጭ ትግልና የሚመራበት ድርጅት አለመኖሩ፤ እንደ አይሁዳዊያን አገር አልባና በሚሊዮን እስክንፈጅ የምንጠብቅ ያስመስለዋል። ለዚህም ነውሰው የገዛ ጠላቱም ወዳጁምራሱ ነው። ”  የሚባለው።  

በዘመኑ ከነበሩት አይሁዳዊያን በተሻለ እኛ አሁንም አገር አለን።  በዓለም ላይ ተበትነው ከነበሩት አይሁዶች በተሻለ  እኛ  በቀላሉ ለመደራጀትም ሆነ ለመታገልና መጭውን ዘመን፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለመታደግና ኢትዮጵያን  የሁላችን  ለመድረግ እንችላለን። ለዚህ ግን  በጎስኝነት የምትታመሰውን አገራችን ያለችበትን ሃቅ መቀበልና ጄን ቻርፕከአምባገነን አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲበተሰኘው መጸሃፋ እንደሚመክረን፤  መራራ ቢሆንም አውነታውን መጋፈጥ  እንዳለብን ያስገነዝበናል። ይኽውም፤

1/ ጭቁን ህዝብ  ለትግል ያለውን  ቁርጠኝነት በራስ መተማመን፣ ሁኔታና ችግሮችን የመቋቋም ብቃቶችን ማጠናከር።

2/ ማህበራዊ ስብስቦችንና ተቋማትን ማቋቋምና ማጠናከር።

3/ ጠንካራ የሆኑ የአገር ውስጥ የተቃውሞ ኃይሎችን መፍጠር፡

4/ ነጻ ለማውጣት የሚያስችል ስልት የተሞላበት መረሃግብርና እቅድ መንደፍ፤ ይኽንም በዘዴ በተግባር መተርጎም።

ከዚህም በተጨማሪ  እንደ እኛ ላለ፤ ከህዝብ ፍላጎትና ጥቅም ውጭ፡ በጎሳ ቡድኖች በየቀኑ  በማንነቱ እየተገደልና እየተፈናቀለ የህልውና ጥያቄ ተደቅኖበት ለሚገዛና ለመተጋለ ለቆረጠ ህዝብ   የአይርላንዱ ተወላጁ ቻርልስ  ስትዋርት እንዲህ ይለናል፤

መንግሥት ላይ መተማመን ምንም ፋይዳ የለውም። በራሳችሁ ውሳኔና ቆራጥነት ላይ ብቻ ነው መተማመን ያለባችሁ። በአንድነት በመቆም ራሳችሁን እርዱ፤ በመካከላችሁ ደካሞች ካሉ አበረታቷቸው። ራሳችሁን አስተባብሩ፤ ራሳችሁን አደራጁ፤ ታሸንፋላችሁም። ይህ እንዲሆን እስከአልተነሳችሁ ድራስ፣ እስከዚያች ግዜ ድራስ የነጻነት ጥያቄው አይመለስም፤ አይሳካም።—–”

ስለዚህም  እንደ አይሁዳዊያን አገር አልባና በሚሊዮን  ከመፈጀታችን በፊት፤ በቆራጥነትና በራስ በመተማመን ተደራጅተን በመታገል፤ ራሳችንም  ሆነ  አገራችን  ከጎሰኞችና ከጸረኢትዮጵያዊያን ነጻ እናውጣ። በምድራችን ላይ በልመና ወይም በገዥዎች ፈቃድ የተገኘ ነጻነትም ሆነ እንድነት የለምና።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!!

E-mail: philiposmw@gmail.com    

Filed in: Amharic