>

የአብሮነትን ጥላ የሚዘረጋ ማኀደር ውስጥ የከረመ መጣጥፍ ነው ። አብሮነታችን _ ቀላል አቀራረብ (ደረጀ መላኩ)

የአብሮነትን ጥላ የሚዘረጋ ማኀደር ውስጥ የከረመ መጣጥፍ ነው ።

አብሮነታችን _ ቀላል አቀራረብ

ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com


” If you want to go fast, go alone. If you want to go far, go together.” – Ancient African proverb

ይህ ከላይ የተጠቀሰው የጥንት አፍሪካዊያን አባቶቻችንና እናቶቻችን ሥነ ቃል ማዕከል አድርጎ በዋናነት የሚያጠነጥነው ነገር ቢኖር ፤ አብሮነት የየትኛውም ማኀበረሰብ ጥንካሬ መሰረትና ረዥም እርቀት በአስተማማኝ በሆነ መልኩ መጓዝ እንደሚያስችል ነው። 

አብሮነት የወል ወይም የጋራችን ነው ብለን በምናስበው ሃሳቦቻችን ዙሪያ በኀብረት ከሰራንና ከተጓዝን ልዩ ልዩ የኑሯችን እንቅስቃሴዎች በፍሬያማነት እንደሚጠናቀቅ ያስገነዝበናል። 

ይህንን ንደንና አፍርሰን በተናጠል ጉዞ ከጀመርን ግን ከጭቅጭቅ፤ ከመነታረክ ፤ ከውዝግብና ከአተካራ ከፍ ሲልም የአለመግባባቶች ገመድ ይወጠርና ከችግር ውስጥ መውደቅ ነው።

በተፈጥሯችን ሰዎች ማኀበራዊ እንስሳ ነን። 

የአንዱ መኖር በሌላው ላይ የተደገፈ ነው ። 

ሰው ለብቻው የመኖር አቅምም ሆነ ችሎታም የለው ። 

አኗኗሩና የሕይወት ውጣ ውረዱ አስተሳስሮታልም አገናኝቶታልም ። ሰዎች ሁሉ የተለያየ ሙያና ክህሎት ሃብት ባለቤቶች ናቸው ። 

ሁሉም ለመኖር ሲል እንደየአቅሙ በተሰማራበት የሥራ ድርሻ ማኀበረሳባዊ ግዴታውን ለመወጣት ይጣደፋል ። 

በዚህም የቆመለትን ዓላማና ግብ ለውጤትና ለፍሬ ያደርሳል። 

በዚህ መልካም ምግባር ደግሞ በአግባቡ ከያዝነው ሁላችንም ተጠቃሚዎች ነን ። 

ይህ የሚሆነው ደግሞ በአብሮነት መንፈስ እንጂ በሌላ አስገዳጅ ሁኔታም አይደለም። 

በዚህ የምናምን ከሆነ ደግሞ ትኩረት ሰጥተን በጉዳዩ ላይ መሥራት ይጠበቅብናል። 

በአካልም በመንፈስም ርቀት መጓዝ የምንችለው በአብሮነት መንገድ እንጂ ሌላ መንገድ ያለው አይመስለኝም።

አብሮነት ማኀበረሰባዊ እንቅስቃሴ ነው ። 

እንቅስቃሴው ደግሞ ጥበብና ብልሃት የተሞላበት አስተዳደርም ጭምር ስለሚሆን ፍትሃዊነት ዝንባሌን ያገኛል ። 

ለአብሮነታችን መልካም ተምሳሌዎቹ የሦስት አፅቂዎቹ (insects ) ፍጡሮች ናቸው ። ለምሳሌ _ ንብ ፤ ጉንዳን ፤ ምስጥና ሌሎችንም ተመልከቱ ። እንቅስቃሴያቸውና ምግባራቸው እጅግ ቅብብሎሽ፤ ትብብር ፤ድጋፍ ያለበት ነው ።

አብሮነትን በትዕግሥት፤ በመቀራረብ ፤ በመፈላለግና በመሰባሰብ ማጎልበትና ማጠናከር ይቻላል። 

በአብሮ ነት የሚያድርብን የጋራ መንፈስ ነውና እንድንከባበር ፤ ሃሳብ ለሃሳብ እንድንደማመጥ ፤ እንድንተባበርም መንገድ ያመቻቻል ። 

አብሮነት ሰውን አያርቅም ፤ አያገልም ፤ አይነጥልም ከፍና ዝቅም አያደርግም ። 

ለአብሮነቱ መነሻው ቋንቋ ሰውነት ብቻ ነው ። 

ቋንቋው፤ ባህሉ ፤ አኗኗሩ ዓይነት፤ ቀለሙ፤ ፃታው፤ ዕድሜው፤ ዕምነትና ሃይማኖቱና ሌሎች ነገሮች ሊገድቡት አይገባም።

በአብሮነት የሚከሰቱ ችግሮችንና እክሎችንም መጋፈጥ ፤ መመከት ፤ መቋቋምና ማሸነፍም ይቻላል።

አብሮነት ወንዝ ፤ ባሕር፤ ጅረት ፤ ሽንተረር፤ ሜዳ፤ መስክ፤ ተራራ ፤ ጋራ ፤ ሸለቆ ፤ ጉድባ ፤ በረሃ ፤ ውቅያኖስ ፤ ቀዬ፤ መንደር፤ ከተማ ፤ አገርና አኀጉር የመሻገርና የመቆየት ጠባይም አለው ። 

አብሮነት እንደ ሙጫ አጣብቆ ይይዛል እንጂ አያለያይም ። በአብሮነት የሚዘለቅና የሚከርም ጥቅም እንጂ ጉዳት እምብዛም አይታየኝም።

አብሮነት ግን በፅንፈኝነት አስተሳሰብ ማምጣት አይቻልም ። 

ፅንፈኝነት አግላይና ነጣይ ነው። የተወሰኑ ቡድኖችን የፖለቲካ ፤ የኢኮኖሚና ልዩ ልዩ ባህላዊና ዕምነት እንቅስቃሴዎች ፍላጎት ብቻ የሚከተል አሰራር ነው ። የቆመውም እጅግ ለጥቂት ስሜታዊ ቡድኖች ስለሚሆን አደገኛ አዝማሚያ ነው ። 

ለአብሮነታችንም ጠንቅ ነው ። በማኀበረሰቡ መሃከል አፍራሽ ፤ ሁከትና ብጥብጥ የመፍጠር አቅም ስላለው በአብሮነታችን ቆይታ ላይ የተነጣጠረ አዝማሚያ ስለሚሆን ይወገዛል ።

Filed in: Amharic