>

አቶ ሃብተሥላሴ ታፈሰ  (የኢትዮጵያ የቱሪዝም አባት) - ታሪክ ን ወደኋላ

አቶ ሃብተሥላሴ ታፈሰ  (የኢትዮጵያ የቱሪዝም አባት)

ታሪክ ን ወደኋላ

አቶ ኃ/ሥላሴ በ 1918 ዓ.ም. ከአባታቸው ከፊታውራሪ ታፈሰ ሃብተሚካኤልና ከእናታቸው ከወ/ሮ ሙላቷ በላይነህ አዲስ አበባ ተወለዱ። ከሀገር ውጪ የልጅነት እድሜያቸውን ያሳለፉትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት አቶ ሃብተሥላሴ ታፈሰ ስምንት ያክል ቋንቋዎችን አቀላጥፈው መናገር ይችሉ ነበር። ይሁንና አማርኛን እነደ ሀገራቸው ቋንቋ አቀላጥፈው ለመናገር የረጅም ጊዜ ትግልን የጠየቃቸው ጉዳይ ነበር። ይህም የሆነበት ዋና ምክንያት የሃብተሥላሴ አባት የጠረፍ ሀገር አስተዳዳሪ ሆነው ሲመደቡ ልጃቸውን ጎረቤት ለሆኑ ለውጭ አገር ዜጎች በአደራ ሰጥተው ይሄዳሉ፣ እኝህም ባለ አደራ ወላጆች የፋሺስት ጣሊያን ወረራ ወሬ ከመሰማት አልፎ በእውን መታየት ሲጀምር የአብራካቸው ክፋ ይሆኑ ሁለት ልጆቻቸውንና ሃብተሥላሴን ይዘው ወደ ግሪክ አቀኑ። በዚህም ምክንያት ህጻኑ ሃብተሥላሴ በሰው ሀገር በሰው ቋንቋ ነበር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ግሪክ አቴና ውስጥ የተማሩት።
በዚህ መካከል በስደት አውሮፓ የነበሩት የሃብተሥላሴ አባት ልጃቸውን በቀይ መስቀል በኩል አፈላልገው በማግኘታቸው ወደ እናት ሀገራቸው ተመልሰው መጡ። ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱም ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብተው ለአንድ ዓመት አማርኛ ቋንቋን ተምረዋል። እስከዚ ጊዜ ሃብተሥላሴ መናገር የሚችሉት የግሪክና የራሺያን ቋንቋ ነበር። ቀጥሎም ግብፅ አገር ቪክቶሪያ ኮሌጅ ለሁለት ዓመታት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ በ1950 እ.ኤ.አ ወደ አሜሪካን ሀገር ሄደው ከካርልቶን ኮሌጅ ሚኔሶታ በኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ እና በስነ-መንግስት አስተዳደር መስክ ተመርቀው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡ ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ የመጀመሪያ ስራቸውን ሀ ብለው የጀመሩት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ነበር። በዚሁ ቢሮ እየሰሩ ሳለ ነበር የህይወት አቅጣጫቸውን የለወጡበትና ለኢትዮጵያም ትልቅ አስተዋጾ ያበረከቱበት አጋጣሚ የተፈጠረው። በወቅቱ የሥራ ሚኒስትር የነበሩት ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ከወጣቱ ሀብተሥላሴ ጋር ለስራ ጉብኝት ወደ አውሮፓ ተጓዙ። በአውሮፓ የቱሪዝም ዘርፍ እንቅስቃሴ የተደነቁት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በቱሪስቶች ዘንድ ተወዳጅ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት እንደሆነችና በዘርፉ ጠንክሮ ከተሰራ ብዙ ሀብት ማፍራት እንደሚቻል ለወጣቱ ሀብተሥላሴ ገለፁለት።
ከአውሮፓ እንደተመለሱም ሚኒስትሩ ልዑል ራስ መንገሻ ሃሳባቸውን ለንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በአጭር ማስታወሻ አቀረቡ። ንጉሠ ነገሥቱም ሃሳቡን ወዲያው ተቀብለው ለስራው የሚመጥን ሰው ሚኒስትሩ እንዲያቀርቡ ነገሯቸው። የሚኒስትሩ ምርጫ ሀብተሥላሴ በመሆኑ ወደ ቤተ መንግስት ተጠርቶ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንዲያቋቁም በንጉሰ ነገሥቱ ታዘዘ። ሀብተሥላሴ ግን በቱሪዝም ዘርፍ የትምህርትም ሆነ የሥራ ልምድና ዝግጅት እንደሌለው ለንጉሰ ነገሥቱ በትህትና አስረዳ። ሥራው ለወጣቱ ሀብተሥላሴ እንደማይሳነው የተገነዘቡት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ‹‹ … ግዴለም ትችላለህ! ስራው ቶሎ ይጀመር!›› በማለት አጭር መመሪያ ሰጡት። ስራውን ሲጀምሩ የነበረውን ሁኔታ በተመለከት አቶ ሃብተሥላሴ በአንድ ወቅት ሲናገሩ….”በዘርፉ ከመጀመሪያው (እ.ኤ.አ. ከ1954) ጀምሮ አገልግያለሁ። በወቅቱ ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣሁ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ እሠራ ነበር። ከዚያም በግድ ይህንን የቱሪዝም ሥራ እንድሠራ አዘዙኝ። ገባሁበት። ከባድ ሥራ ነው። ያን ጊዜ ካሜራ ወደ ኢትዮጵያ አይገባም ነበር። ሲገባም ጉምሩክ ይይዘዋል። ፈቃድ ከማስታወቂያ
ሚኒስቴር ማውጣትም ያስፈልግ ነበር። በዚህ ሰበብ ሁለት ጊዜ ታስሬያለሁ። ፎቶግራፍ ለምን ታነሳለህ ብለው ነው ያሰሩኝ። ያን ጊዜ ፎቶግራፍ የሚያነሳ ሰው ሰላይ ተደርጐ ይታሰብ ስለነበር ነው።” ይህን መሰሉ ፈተና ግን ሃብተሥላሴን የኢትዮጵያን የቱሪዝም ኢንደስትሪ እውን ከማድረግ የሚያግዳቸው አልነበርም። በጊዜው ቅርሶችንና ታሪካዊ ስፍራዎችን አስጎብኝቶ ገንዘብ ማግኘት እንደቀልድ ይታይ የነበረ ቢሆንም በጥረታቸው ያን ዘመን ተሻግረውታል። ከበጀትና ከቀረጥ ነጻ እቃዎችን ከማስገባት ጋር በተያያዘ የነበረው ቢሮክራሲ ለሃብተሥላሴ ቀላል ፈተና አልነበረም። ይህንንም ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር ሲናገሩ….
“ሁልጊዜም እየተጠራሁ ወቀሳ ይቀርብብኝ ነበር። ቤተ ክህነት ተጠርቼ ‹በቴሌቪዥን ለምን እንዲህ ተናገርክ?› እባላለሁ፤ የአገር ውስጥ ገቢ ይጠሩኝና እወቀሳለሁ። በዚያን ጊዜ ከቀረጥ ነፃ ሱቅ ከፍተን ነበር። የእኛ ቢሮ ከመንግሥት ቢሮዎች ሁሉ ሀብታም የሚባለው ነበር። በወቅቱ የቱሪዝም በጀት 220 ሺሕ ብር ስለነበር ‹በዚህ በጀት እንዴት አገርን ማሳደግ ይቻላል?› እያልኩ ከጃንሆይ ጋር እጨቃጨቅ ነበር። አንድ ጊዜ ቁልፉን ይዤ ሄድኩና ጃንሆይ ይህንን መሥሪያ ቤት ለሒሳብ ሹም ይስጡት፤ ደመወዝ ከመክፈል ውጪ ሌላ ሥራ መሥራት አልቻልኩም አልኳቸው። የቀረጥ ነፃ ፈቃድ ስጡኝ ብዬ ጃንሆይን ጠየቅሁ። በኋላ የገንዘብ ሚኒስትሩ መጡና ‹እኛ ኮንትሮባንድ መቆጣጠር አቅቶናል፤ ሀብተሥላሴ ደግሞ አናታችን ላይ ኮንትሮባንድ ለመፍጠር ይፈልጋል› አሉኝ። ንጉሡም ‹ሥራህ መቆጣጠር ነው እንጂ ሥራ አይሥራ ነው የምትለው ወይስ መቆጣጠር አልችልም ነው?› ብለው ጠየቋቸውና ተፈቀደልኝ።
……….ሥራው ሊጀመር ሲል ደግሞ ገንዘብ ስለጠፋ የአባቴን ካርታ ወስጄ አምስት ሺ ዶላር ተበደርኩ። በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ማግኘት ተቻለ። በአንድ ወቅት ከመላው ኢትዮጵያ የእኛ መሥሪያ ቤት ነበር ሀብታም የነበረው። አንድ ሚኒስትር ሲሾም በጊዜው እንዲነግድ አይፈቀድለትም ነበር። ለእኛ ተፈቅዶ ነበርና ብዙ ገንዘብ አስገብተናል። የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሕንፃ ተሠርቶ ሥራ ሲጀምር የእኛ መኪናዎች ነበሩ የሚያገለግሉት። 46 መኪናዎች ነበሩን። እኔ እንደ ሾፌር፣ እንደ አስጐብኚ፣ እንደ ፎቶግራፍ አንሺ እየሆንኩ ሠርቻለሁ። በኋላ ምቀኛ በዛና ‹የቀረጥ ነፃ ገንዘብ ወደ መንግሥት ይግባ› አሉ። ያ አሠራር በርካታ ሰዎች በዘርፉ መሰማራት እንዲችሉ የሚያደርግ ነው …›› በማለት ገልጸዋል።”
➻ የአስራ ሶስት ወር ጸጋ
እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ የቱሪዝም መለያ ሆኖ ያገለገለው ኢትዮጵያ፡ የ13 ወር ፀጋ / Ethiopia: Land of 13 Months of Sunshine የሃብተሥላሴ የምናብ ውጤት ነው። ስያሜውን እንዴት እንደመረጡት ሲያስረዱ እንዲህ ብለው ነበር።
‹‹ … እኔ ያደግሁት ውጭ አገር ነው። የትም ዓለም ላይ 13 ወር የለም። ፒራሚድ ሲታይ ግብፅ ነው። አይፈል ታወር ሲታይ ፈረንሣይ ነው። የነፃነት ሐውልት ሲታይ አሜሪካ አለ። እኛ የምንታወቅበት የለንም ነበር። ሁሉ ነገር ከዘር፣ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ነበር። ሳላውቀው አንድ ወቅት ላይ ‹የ13 ወር ደመወዝ ይሰጠን› ብዬ ጠየቅሁ። ወዲያው ይህንን ሐሳብ ወደ ቱሪስት መሳቢያነት መቀየር እንደሚቻል አሰብኩ። ሌላው ሁሉ ከዘር ከሃይማኖት ጋር የሚያያዝ ነበር። ላሊበላን ባደርግ ኢትዮጵያ በሙሉ ክርስቲያን ባለመሆኑ ችግር ነበረበት። የአሥራ ሦስት ወር ፀሐይ ግን ከምንም ነገር ጋር አይገናኝም። ምንም የፖለቲካና የሃይማኖት ንክኪ የለውም … ››
አቶ ሃብተሥላሴ ታፈሰ በውጪው ዓለም ኢትዮጵያን በማስተዋወቁ ረገድ በበርካታ የውጭ አገራት የንግድ ትርኢቶች ላይ በመሳተፍ አያሌ ስራዎችን ሰርተዋል። ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከነጋዴዎች ምክር ቤት ጋር በመተባበር ብዙ የሀገር ውስጥ ኤክስፖዎችና ኤግዚቢሽኖች እንዲዘጋጁ አድርገዋል። አቶ ሀብተሥላሴን የተለዩ የሥራ መሪ የሚያደርጋቸው የነበረን ወይም ያለን ተቋም ወይም ድርጅት ተቆጣጥሮ ማንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን ሥራ የመፍጠር ችሎታቸው ነው። የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብት ለውጭና ለሀገር ቤት ተመልካቾች ማሳወቅ (ፕሮሞሽን)ን መሰረታዊ ዓላማው አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው የቱሪዝም ድርጅት ሥራውን ለማከናወን አቅም ባነሰው ወቅት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚያስችለውን የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅትን አቋቋሙ። ዛሬ ይህ ድርጅት የአገሪቱን ቅርስና ባህል ከማስተዋወቁ በተጨማሪ ብዙ ትርፍ የሚያስገኝ ተቋም ሆኗል። በመቀጠልም ከፕሮሞሽኑ ሥራ ጋር ተደጋጋፊ የሆነውን የሀገር ባህል ዕቃዎች ማምረቻ ድርጅትን አቋቋሙ። የመኪና ኪራይ ድርጅት እንዲመሰረት ያደረጉትም እርሳቸው ናቸው። እነዚህ ድርጅቶች ገቢ ከማስገኘታቸው ባሻገር ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ናቸው።
ባንድ ወቅት ጃፓን ኦሳካ ላይ በተካሄደ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ለሻይ እና ለቡና ብዙም ግድ የላቸውም የሚባሉትን ጃፓናዊያን በተለየ የማስተዋወቅ ጥበባቸው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በፍቅር እንዲወድቁ ማድረግ ችለዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያልረገጡት መሬት እንደሌለ የሚናገሩት እኚህ ታላቅ ሰው ‹‹ … በእግር፣ በፈረስ፣ በግመል፣ በሄሊኮፕተር፣ በአውሮፕላን ሁሉ ተዘዋውሬ ከ100 በላይ ሰው ያልረገጣቸው የኤርትራ ደሴቶችን አይቻለሁ። ትልቅ ሀብት ናቸው። ቢያውቁበት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መሰብሰብ ይችሉ ነበር። በጋምቤላ በኩል ጂካው ድረስ ሄጃለሁ። የደቡብ ሱዳን ጠረፍ ነው። በኤርትራ በኩል ቤንአመር ድረስ ወዳለው የጠረፍ ቦታ ደርሻለሁ። ቤኒሻንጉልን በሙሉ እስከ ሱዳን ድረስ አዳርሻለሁ። መሥራት ካስፈለገ ማየትና ማወቅ ግድ ይሆናል። ካየንና ካወቅን በኋላ ማውራት ይቻላል … ›› በማለት ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።
የሳቸው አሻራ ካረፈባቸው ፕሮጀክቶች መካከል የሒልተን ሆቴል፣ የኢትዮጵያ ምግብ ኢንስቲትዩት፣ ለፕሮሞሽን ስራ የዋሉ አያሌ ዲዛይኖችና መጽሄቶች ተጠቃሽ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ‹‹የ13 ወር ፀጋ›› የሚለው የኢትዮጵያ የቱሪዝም መጠሪያ ‹‹ምድረ ቀደምት (Land of Origins)›› በሚል ስያሜ ተተክቷል። ‹‹ … ‹የ13 ወር ፀጋ› የሚለው የኢትዮጵያ የቱሪዝም መለያ ለብዙ ጊዜያት ያገለገለ ነው። አሁን መቀየር አለበት› የሚሉ ሰዎች አሉ። ይቀየር ቢባል ምን ይሰማዎታል?›› ተብለው ተጠይቀው አቶ ሀብተሥላሴ ‹‹ … ሁልጊዜ አንድ ነገር ሲፈጠርና የሚበልጠው ሲገኝ ያንን ማየቱ ተገቢ ነው። አሁን ከዚያ የበለጠ ከተገኘ ደግሞ ቶሎ መተካት ነው። ምንም ችግር የለውም›› ብለዋል።
አቶ ሃብተስላሴ ታፈሰ ከቱሪዝም ዘርፍ ስራቸው በተጨማሪ በርካታ ተግባራትን ያከናወኑ ሲሆን የአዲስ አበባ ሮተሪ ክለብ (Addis Ababa Rotary Club) መስራችና አመራር (ከ1958 እስከ 1959 ዓ.ም) ፕሬዝደንት ሆነውም አገልግለዋል። ለቱሪዝም እንጂ ለፖለቲካ ግድ የሌላቸው አቶ ሀብተሥላሴ ፖለቲካው ያመጣው ጣጣ ለእርሳቸውም ተርፎ ከ1974 እስከ 1982 ዓ.ም ድረስ ያለምክንያት በእስራት እንዲቆዩ አድርጓቸዋል።
በታታሪነታቸውና በውጤታማ ስራቸው በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ታዋቂነትን ያተረፉት አቶ ሀብተሥላሴ፣ የድካማቸውን ያህል ባይሆንም ላከናወኗቸው ወርቃማ ተግባራት ሽልማቶችን አግኝተዋል። ከነዚህም መካከል በ2009 ዓ.ም የዋንጫና የወርቅ የደረት አርማ (Pin) ሽልማት በወቅቱ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተበርክቶላቸዋል። የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በበኩሉ የገንዘብ ሽልማትና እውቅና ሰጥቷቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በቅርስና ባሕል ዘርፍ የ2007 ዓ.ም ‹‹የበጎ ሰው ሽልማት›› ተሸላሚ ሆነዋል። አቶ ሃብተሥላሴ ታፈሰ ከወይዘሮ ሙሉ መስፍን ጋር ትዳር መስርተው አንድ ሴትና ሁለት ወንዶች ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፤ አራት የልጅ ልጆችንም ለማየት በቅተዋል።
ስለኢትዮጵያ ቱሪዝም ሲነሳ የማይዘነጉት ታላቁ ‹‹የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ አባት›› አቶ ሀብተሥላሴ ታፈሰ ባደረባቸው ሕመም በሀገር ውስጥና በውጭ አገር የሕክምና ክትትል ሲያደርጉ ቆይተው ነሐሴ ሦስት ቀን 2009 ዓ.ም በተወለዱ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሥርዓተ ቀብራቸው ነሐሴ ሰባት ቀን 2009 ዓ.ም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።
#ታሪክን_ወደኋላ
©️
ቴሌግራም:https://t.me/TariknWedehuala
Filed in: Amharic