>

ማመንና የሳይንስ እውቀት ለየቅል! ማጥላላት አላዋቂነትን አይሸፍንም። ( ክፍል 2 ታላቁ ፍንዳታ - በ አኒሳ አብዱላሂ )

ማመንና የሳይንስ እውቀት ለየቅል!

ማጥላላት አላዋቂነትን አይሸፍንም።

ክፍል 2

ታላቁ ፍንዳታ

ካለፈው የቀጠለ

በ አኒሳ አብዱላሂ

“ የሂሳብን ፅንሰ ሃሳብ የማዝገባው አለምን ሊረዳ አይቻለውም! !”

ጋሊሌዮ ጋሊሌ

 

ምንም አይነት ደመና በሌለበት ወቅት ወደ ሰማይ ቀና ብለን ብንመለከት በእጅጉ የሚያብረቀርቁ ከዋክብቶችን ማየት እንችላለን። ከነዚህ ከዋክብቶች የሚወነጨፍ የብርሃናቸው ጨረርና በአይናችን መካከል፣ ጨረሮችን የሚውጥ ወይንም ደግሞ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲወነጨፉ የሚያደርግ ሁኔታ እንደሌለ የሚያመላክት ነው። ባጭሩ በሕዋ ውስጥ አብዛኛው አካባቢ ባዶ ነው ማለት ነው። ይህን ሁናቴ መገረምና መደነቅ ብቻ ሳይሆን ኮከቦቹ እንዴትስ ሊፈጠሩ ቻሉ? ከየት መጡ? ምንጫቸውስ ምንድን ነው? እኛንስ ማን ፈጠርን? በሰው ፍጡርና በከዋክብቶቹ መካከል የለው ግንኙነት ምን ይመስላል? የሚሉትን ጥያቄዎች በሰው ጭንቅላት ውስጥ የሚያጭር ነው። በውነትም ደግሞ የሰው ፍጡር ማሰብና ማሰላሰል ከጀመረበት ወቅት አንስቶ በተከታታይ ትውልድ አባላት አማካኝነት ጥያቂዎቹ እየተጠየቁ በወቅቱ የእውቀት ደረጃ ላይ የተመረኮዙ የመላ ምቶች መልስ ሲሰጥባቸው እንደነበሩ የታሪክ መረጃዎች የሚያመላክቱት ናቸው።  

በጊዜ ሂደት የሰው ፍጡር የእውቀት አድማሱ እየሰፋ፣ የመመርመሪያ ቴክኒኮችም እንዲሁ እያደጉና እየተሻሻሉ በመጡ ቁጥርም በዛው መጠንም የግለሰቦችና የሕብረተሰቡ ግንዛቤ እየጨመረ ሲሄድ በከዋክብቶቹ አፈጣጠርና ሰለሚያደርጉት እንቅስቃሴም ባካበታቸው ግንዛቤዎቹ የበለጠ ለማወቅ ረግረግ ማመቻችቱን በከፍተኛ ግለት ያስፋፍል።  በዚህ ብቻ አልተወሰነም። በ 30ኛውን በ40 ኛው መቶኛ አመተ ምህረት ለመጀመሪያ ጊዜ ቁስ አካላት በጥቃቅንነታቸው በሚታወቁ ንጥረ ነገሮች የተመሰረቱ መሆናቸው ጋር ተያይዞ በሩሲያዊው ሊቃውንት በሜንዴሌቭ ሥም የሚጠራው (Periodic Table of Elements) የተለያዩ የቁስ አካላትን ዝርዝር ሁኔታና በውስጣቸው ያቀፏቸውና የየግል ጠባዮቻቸውንና ተመሳሳይም ሆነ ተቃርኗቸውን ያጣመረ ሰንጠረዥ ለመደበኛ የእውቀት መገኛ ጥርጊያ መንገዱ በሚያስደንቅ ሁናቴ ተበርግዶ ተከፈተ። ቀስ በቀስም የነዚህ ቁስ አካላት ስረ መሰረታቸው ከዋክብቱ መሆናቸው፣ ከዋክብቶቹም በበኩላቸው ከታላቁ ፍንዳታ መፀነሳቸው ከግንዛቤ እየተወሰደ ይመጣል። በመሆኑም በዚህ ግንዛቤ ላይ የተመሰረቱ በአለማችን በተለያዩ አካባቢዎችና ከፍተኛ የዩኒቨርሲቲ ተቋማት በሚገኙ ቤተሙከራዎች የተገኙ የተለያዩ ምሁራዊ ጥናቶች ከመቼውም ግዜ በበለጠ ይህንኑ ሁናቴ ከጥያቄ ሊገቡ በማይችሉበት ደረጃ እየተረጋገጡ ይበልጡኑ ደግሞ ለቀጣዩ ምርምር ረግረጉን ማመቻችት ሊችሉ በቁ። በዚህም የተነሳ በሰው ፍጡርና በአፅናፈ አለም ውስጥ በሚገኙ ከዋክብቶች መካከል አንዳች አይነት የዝምድና ግንኙነት ያላቸው መሆናቸው በየቦታው ለሕትመት በበቁ መጣጥፎችና መፅሀፍቶች ለሕዝብ ይፋ እየተደረጉ ይመጣሉ። 

በዚህም ብቻ አልተወሰነም። የሰው ፍጡር በቤተሙከራዎች ባገኛቸው የጥናታዊ ምርምር ውጤቶች ላይ በመመስረት ስለ አፅናፈ አለም ባጠቃላይ ከፅንሱ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ስለተከሰቱ ሁናቴዎች፣ ወደፊት ሊያጋጥሟቸው ስለሚችሉት ክስተቶች ሁላ ሳይቀር መተንበየና ምርመራ በማድረግ መረዳት ይቻላል የሚለውን ከቦምብ ፍንዳታ የማይተናነስስ ዜናና በርካታ ምሁራንን ያስደሰተ፣ ያስገረመ፣ ያስደነቀ ባጠቃላይ ጉድ አስኝቶ ያስሳፈነጠዘ ዜና በአለም አቀፍ ደረጃ ተበሰረ።  ለተፈጥሮ ሳይንስ ቀናና ብሩህ አመለካከት ያላቸው በርካታዎችም በያሉበት ይህንን ፈለግ በመከተል ጥናታዊ ምርምሮቻቸውን አጧጧፉት። 

ለዚህም ነው ስነ ፈለክ (ኮስሞሎጂ) ተፀንሶ መዳበር የጀመረው ኮፐርኒከስ የተባለ ሊቃውንት የሰው ፍጡርና አንስሳት የሚኖሩባት ምድራችን የአለማችን እምብርት በምንም አይነት ልትሆን አትችልም በማለት በምርምር ላይ የተመረኮዘ ሃሳቡን ለንባብ ይፋ ካደረገበት ጊዜ አንስቶ ነው ተብሎ አፅንኦት በተሞላበት ሁናቴ እየተነገረ የሚገኘው። ይህ እጅግ ድፍረት የተሞላበት አስተያየት አፅናፈ አለም ስፋቱ በጣም ትልቅ የሆነ፣ መሬት በዚህ አፅናፈ አለም ውስጥ ልዩ ቦታ የማትይዝ መሆኗ ለሰው ፍጡር በእውቀት ለታጀበ ጉዞው የመጀመሪያው ዳዴ ሆኖ ሊከሰት የቻለበት ክስተት ነው ተብሎ በበርካታዎች የሚገመት እንደሆነም የተለያዩ ፅሁፎች ያመላክታሉ።

ይህ ሁናቴ ከተከሰተ ከ 200 አመት በኋላ አይሳክ ኒውቶን የተባለው ብልህ ሊቃውንት ያቀረባቸው የእንቅስቃሴ ሕጎችና የስበት (ግራቪቲ) ፅንሰ ሃሳቡን ማብሰሩ፣ የአፅናፈ አለምን ፅንሰ ሃሳብን መጎልበትና መዳበርን ቅርፅ ሊያሲዘው መብቃቱ የሚነገርለት ነው። የሰው ፍጡር  በወቅቱ ስለ አፅናፈ አለም የነበረውን ግንዛቤ ይበልጥ ሊያዳብረበት ያስቻለው ደግሞ በ 20ኛው መቶኛ አመት አልበርት አንሽታይን የኖቬል ሽልማት ለማግኘት የበቃበት ልዩና አጠቃላይ የአንፃራዊነት ጽንሰ ሃሳብን  (General and Special Relativity Theorie) በማፍለቁ ላይ የተመሰረተ ነበር። በምሳሌነት ከሚጠቀሱት ውስጥ 1. ማንኛውም ቁስ አካል ከአንድ ቦታ ተንቀሳቅሶ ወደሌላ ቦታ ለመድረስ የሚያስፈልገው ፍጥነት ሁሌም ከብርሃን ጨረር ለምን አናሳ እንደሚሆን፣ 

2- በቁስ አክልና በኃይል መካከል ያለውን ግንኙነት የሚገልፀው (E = mc2) ቀመሩ ውስጣዊ ይዘቱ ምን እንደሆነ ለመረዳት በመቻሉ የሰው እውቀት ከህጻንነት ወደ ልጅነት ማደጉን አበሰረ።

በመቀጠልም የስነ ፈለክ አባት ለመባል የበቃው ኤድዊን ሐብል (1925 ዓ.ም.) (Milch Street) የወተት መንገድ ተብሎ በሚታወቀው ጋላክሲ የከዋክብቶች ስብስብ ፀሃይንና ስርአቷን አሽቀንጥሮ ወደ ዳር መግፋት ብቻ ሳይሆን እንደዚሁ ጋላክሲ የመሰሉ ሌሎች በርካታዎች እንዳሉ፣ ያመነጫቸው ሕጎች፣ ጋላክሲዎቹ መሬት ከምትገኝበት አንፃር ሲታዩ እጅግ ፈጣን በሆነ ሁናቴ እየራቁ መሄዳቸው፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ አፈጣጠራቸው ከአንድ የቁስ አካል ከሆኑ ጥቃቅን ንጥረ ነገሮች በከፍተኛ እፍግታ(እምቅታ) (Density) የመጨረሻ ትንሽ ከሆነና  መነሻው በፍንዳታ ሊሆን እንደሚችል መተንበዩና ይህም እያደር በሌሎች ተመራማሪዎች መደገፍና የየበኩላቸውን ማረጋገጫ ይፋ ማድረጋቸው (የአልበርት አንሽታይን ፅንሰ ሃሳብ ታክሎበት) የሰው ፍጡር የእውቀት አድማስ ከመቼውም በበለጠ ለመጎለበት አስቻለው። 

ሌላው አፅናፈ አለምን ለመገንዘብ መሰረት የሆነው ከጥቃቅን ንጥረ ነገሮች ውስጥ ከሚመደበው አቶም ጋር የሚገናኙትን  አቅፎ የያዟቸው ምን አይነት ጠባይ እንዳላቸው ለመገንዘብ መቻሉ በአስተዋፅዖ አበርካትነታቸው የሚመደቡ ናቸው። ጠለቅ አድርገን ስንመለከታቸው አቶም በዙሪያው አቅፎ የያዛቸው ሴቴ(ኔጋቲቭ) የኤሌክትርክ ኃይል ያለው ኤሌክትሮን፣(electron) ወንዴነት(ፖሲቲቭ)/ ጠባይ ያለው ፕሮቶንና(Proton) ገለልተኝነት ጠባይ ያለው ኒውትሮን(Newtron)  የተሰኙት ንጥረ ነገሮች ናቸው። ፕሮቶንና ኒውትሮን በየበኩላቸው ኩዋርክ (Quark) በተሰኙ በበለጠ ጥቃቅን ነገሮች የተመሰረቱ ስለሆነ በጥቃቅንነት ሳይሆን በተለየ የሚታዩና የሚጠቀሱ ናቸው። ባጠቃላይ ስድስት አፕ፣ ዳውን፣ ስትሬንጅ፣ ቻርም፣ ቦቶምና ቶፕ (up, down, strange, Charme, Bottom and Top) የተሰኙ እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ክብደትና የኤሌክትሪክ ጠባይ (charge) ያላቸው ሲሆኑ ፕሮቶን ከኤሌክትሮን ጋር ያለው ክብደት ሲነፃፀር ደግሞ ወደ 2000 ገደማ እጅግ ከፍ ያለ ነው። ፕሮቶን ከሁለት አፕ ዎችና (up) አንድ ኩዋርክ (Quark) በውስጡ አቅፎ የተዋቀረ  ሲሆን ኒውትሮን በበኩሉ አንድ አፕና (Up) ሁለት ኩዋርኮችን (Quark) በውስጡ ያቀፈ ነው። በአሁኑ ወቅት ከነዚህ ጥቃቅን ንጥር ነገሮች ሌላ ወደ 200 የሚጠጉ ተገኝተዋል።

  • ፕሮቶንና ነውትሮን የአቶም እምብርት በመሆናቸው ደግሞ በነሱ ዙሪያ የኤሌክትሪክ ጠባይ ያለው ኤሌክትሮን እንዳሻው የሚንፈራገጥበት ምህዋር (Orbit) ይኖረዋል። አቶምን በውስጡ ከያዛቸው ጥቃቅን ነገሮች ጋር አያይዘን ስንመለከተው ስፋቱ 0-0000000001 ሜትር እርዝማኔ ሲኖረው እምብርቱ እንዲያውም አንድ ሚሊዮን ጊዜ በጣም አናሳ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህም ሆኖ ሊቃውንቶች በጥናት እንዳረጋገጡት 99 ከመቶ የሚሆነው የአቶም ክብደት በእምብርቱ ተከማችቶ ይገኛል። ኤሌክትሮንና በምህዋር ውስጥ ይሽከርከር እንጂ በሱንስ በፕሮቶን መካከል የለው ቦታ ፈፅሞ ባዶ ነው። በመሆኑም የወንዴነት (positive) ጠባይ ያላቸው ፕሮቶኖች ለምሳሌ የሕይወት መስረት ከሆነው አንድኛው  ካርቦንን ብንመለከት  ስድስት ፕሮቶንና ስድስት ኒውትሮን በውስጥ በማቀፉ መፈረካከስ ሲገባው ምንድነው በአንድ ቦታ አቆራኝቶ የያዛቸው ስንል መሰረታዊ ከሆኑ የተፈጥሮ ኃይሎች ውስጥ በሁለተኛነት የተመደበው ጠንካሪው  የኒውክለር ሀይል እርስ በርሳቸው ከሚገፋፉበትና ንጥረ ነገሩን ከሚያርከሰክሱት በላይ ኃይለኛ በመሆኑ እንደሆነ እንገነዘባለን። ይህ ኃይል ደግሞ ከሁሉም ኃይሎች በተለይም ከኤሌክትሮ ማግኔቲክ ኃይል ሲነፃፀር ማለት ነው። ጠንካራው የኒውክለር ኃይል ለቁስ አካላት በማጣበቂያነት የሚያገለግል ነው። በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት ከግንዛቤያችን ገብተው የምናገኛቸው የቁስ አክላት ቅርፅ ምንጮቻቸው ከላይ የተጠቀሱት ኃይሎች በመሆናቸው ስለ ታላቁ ፍንዳታ ሊኖረን የሚችለውን አረዳድ በበለጠ በማጎልበታቸው የሰው ፍጡር የእውቀት አድማሱ ወደ ጎልማሳነት ማደጉ የሚመዘንበት አንድኛው ነጥብ ሊሆን በቅቷል።

ሌላው ለግንዛቤያችን ተጨማሪ መደላድል ሆኖ የምናገኘው ደግሞ ከአራቱ የተፈጥሮ ኃይሎች አንዱ የሆነው ደካማው የኒውክለር ኃይል ነው። ምስጋና ይግባትና ፀሃይ በየቀኑ በምንኖርበት መሬት ለኑሯችን እጅግ ተስማሚ የሆነ ሙቀት የምትለግሰን ብቻ ሳትሆን ራሷ መሬትም ሆነች እንደኛ የመሰለ የሰው ፍጡር በዚችው መሬት ላይ ለመኖራችን በዋና ምክንያትነት የምትጠቀስ ነች። ነገር ግን ለብዙ ጊዜያት ፀሃይ ከላይ የተጠቀሰውን ሁናቴ አስመልክቶ አልበርት አይንሽታይን የተባለ ሊቃውንት በምርምር ያገኛቸውን ውጤትና ቀመር (E = mc2) አፍታቶ እስከሚያቀርብልን ድረስ ኃይሏን ከየት እንደምታገኝ ግልፅ አልነበረም። የአይንሽታይን ቀመር በቁስ አካልና በኢነርጂ(ኃይል) መካከል ተመጣጣኝነት፣ ተመሳሳይነት ተመዛዛኝነት ያላቸው ሲሆኑ በሁለቱ መካከል ያለው በሴኮንድ 300 000 ኪሎ ሜትር የሚወነጨፍ የብርሃን ጨረር የፍጥነቱ ምንነትን የሚገልፀው ብቻ ነው። ይህንን የብርሃን የፍጥነት ልክ በራሱ ስናባዛው ደግሞ እጅግ በጣም ከፍተኛ አሃዝ ያለው ቁጥር የሚሰጠን ነው። ይህም በጣም ትንንሽ ክብደት ያላቸው እንደ አቶም የመሰሉ ጥቃቅን  ቁስ አካላቶች ከፍተኛ የኃይል ጉልበት ማቀፍና በውስጣቸው መያዝ የሚያስችላቸው ጠባይ እንዳላቸው የሚያመላክት ነው። 

ይህንን ሁናቴ እንደገና ጠለቅ አድርገን ስናጤነው ደግሞ ከዋክብቶች ያላቸው እምቅ ኃይል ከሌላ ከውጭ ሳይሆን በራሳቸው ውስጥ ከሚገኘው ከአቶም እምብርት ውስጥ እንደሆነ እንገነዘባለን። የፀሃያችንን ሁናቴ  ስናጤንም በውስጧ እጅግ መጠነ ሰፊ ክብደት ያለው የኒውክለር መወሃድ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። እሱም  ሁለት ኃይድሮጅን አቶሞች አንድ ፕሮቶንና አንድ ኒውትሮንን ያቀፈና ትንሽ ከበድ ወዳለው ዶይቶሪየም ይቀየራል። ይህም በበኩሉ እንደገና ከሌላ ፕሮቶን ጋር በመዋሃድ ወደ ሄሊየም ይቀየራል። በዚህ ሂደት ውስጥ በውጤትነት የሚገኘው ከዋክብቱን ብርሃናማ እንዲሆን የሚያደርግ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ ኃይል መፍለቁ ነው። በርግጥም ይህ ደካማ የኒውክለር ኃይል ፀሃያችን በአፅናፈ አለም የምታሰራጨውን የብርሃን ኃይል በማምረት ሂደት ውስጥ በረዳትነት መንቀሳቀሱ የሰው ፍጡር ብቻ ሳይሆን እፅዋትና ሌሎችም ተጠቃሚዎች የመሆን ሁናቴ አጋጥሟቸዋል። ይህ ደካማ የኒውክለር ኃይል ደካማና ጥንካሬነት በሌላቸው የአቶም እምብርቶች ላይም ኃይልን በውስጣቸው በመጨመር ጥንካሬነት ወዳላቸው እንዲቀየሩ እርዳታውን ይለግሳቸዋል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ በተለይም በአውሮፓና በአሜሪካ የሚገኙ የኒውክለር ኃይል ማመንጫ ተቋማት የዚህ ቴክኒክ ተጠቃሚ ናቸው። ይህ ሁናቴ ስለ ታላቁ ፍንዳታ ሊኖረን የሚገባውን የእውቀት አድማስ ለማስፋት የረዳ ሌላው የትምህርት ዘርፍ ነው። 

ስለ አፅናፈ አለም አፈጣጠር የተለያዩ ፅንሰ ሃሳቦች ይገኛሉ። ከነዚህም ውስጥ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በኃይማኖት ተቋማት፣ በፍልስፍና፣ በሌሎችም አማካኝነት የሚቀነቀኑት በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው። የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ ከሌሎች ጋር ሙግት ለማድረግ ምንም አይነት ፍላጎት ስለሌለው የነሱን ጉዳይ ለአንባቢያን በመተው ግን ትኩረት ሰጥቶ ለማቅረብ የሚሞክረው በተፈጥሮ ሳይንስ የሚቀርበውን አስተያየት ብቻ ነው። በተፈጥሮ ሳይንስ አካባቢም ቢሆን የተለያዩ አመለካከቶች ያሉ መሆናቸው ጠፍቶት ሳይሆን በአሁኑ ወቅት ትኩረቱ በአብዛኛው የተፈጥሮ ሳይንስ ሊቃውንቶች ተቀባይነት ያገኘውን በታላቁ ድንፋታ ሥም በሚጠራው ፅንሰ ሃሳብ ላይ ነው። 

ታዲያ የዚህ ፁሁፍ አቅራቢ ለምንድን ነው በተፈጥሮ ሳይንስ ላይ ብቻ እምነቱን የመሰርተው? የሚል ጥያቄ ቢቀርቡለት የሚከተሉትን ነጥቦች በዋና ምክንያትነት ያቀርባል። አንባቢያንም ይህንን ጎዳና እንዲከተሉ አጥብቆም ያሳስባል።

  1. ሳይንስ ለእውነትና ለእውቀት ከፍተኛ ግምት የሚሰጥ በመሆኑ ነው። እንዲያውም በአሁኑ ወቅት ውሸታሞችና አታላዮች እንደ አሸን በፈሉበት ዘመን ከነዚህ የተሳሳተ መረጃ አቅራቢዎችና ስህተቶቻቸው ለመዳን የሚቻለው በተፈጥሮ ሳይንስ የተደረጉ ጥናታዊ መረጃዎችን ለ እውቀት ማግኛ  በዋነኛ ምንጭ ለመጠቀም በመቻሉ ብቻ ነው። ለዚህም  ነው በተቻለ መጠን እውቀት እንዲገኝና እንዲዳብር የተለያዩ መመዘኛዎችን እያነጠረ የሚያወጣቸው። በመሰረቱ የሳይንስ አላማና የሁል ግዜም ጥረቱ ስርአትን የተከተለ ምክንያታዊና የተረጋገጠ፣ ለእውነታ የሚቀርቡ መረጃዎች ላይ የተመሮከዘ  እውቀትን ማስገኘት እንደሆነ ያለፉ ተመክሮዎች የሚያመካቱ ስለመሆናቸው በርግጠኝነት መመስከር የሚቻል ነው።
  2. ለሳይንሳዊ ጥበብ መገኘት በመመዘኛዎች የሚያገለግሉ መረጃዎች ትክክለኛነታቸው፣ እውነትነታቸው እንዲሁም ካለፉት ጊዜያት የተገኙ ተመክሮዎች እንደሚያመላክቱት ተአሚነታቸውን ለመገመት ብዙም አይቸግረንም። በዚህ ጎዳና የማይሰማሩ ጨርሶውኑ ምንም አይነት ሙከራ የማያደርጉ አፅናፈ አለምን ለማወቅና ውስጣዊ ይዘቱን ለመረዳት በምናደርገው ጥረት መረጃዎቻቸውን ተአሚነት ያላቸው ምንጮች አድርገን ለመውሰድ አስቸጋሪ መሆናቸው ከመቼውም በበለጠ ግልፅ እየሆነ ያለ ክስተት ነው። ለዚህም ነው ጨው ለራስህ ብለህ ጣፍጥ ነውና ከፍተኛ ጥንቃቄ ማደረግ አግባብነት ይኖረዋል ተብሎ አፅንዖት በተሞላበት ሁናቴ ምክር እየተለገሰ የሚገኘው። ለመሆኑ ከዚህ አንፃር የሳይንስ መለያዎች ምንድን ናቸው።

Picture ሀ.  ሳይንስ ስነ ስርአትን በመላበስ ስለሚያደርገው ምርምር በጥሞና የሚታሰብበት፣ የሚታቀድበት፣ የሚነደፍበት ሂደት ያለው ነው።

ለ. በስይንስ ምርምር የሚገኙ ውጤቶች ከጅምሩ አንስቶ እስከመጨረሻው ውጤት መገኝት ድረስ ለበርካታ ሰዎች የሚገለፁና ለፈተናም የሚቀርቡ መሆን እንዳለባቸው ለተፈጥሮ ሳይንስ የእምነቱ እምብርት ናቸው። 

ሐ. የሳይንስ መመሪያዎች አስተዋይነትን፣ ምዛኔነትን የተላበሱ ተግባራት ናቸው። በተፈጥሮ ሳይንስ የሚሰማሩ ሊቃውንቶች የምርምራቸው አላማና የነሱም ፍላጎት ሁሌም ከግምት የሚገቡ መሆናቸውን የሚቀበሉ ናቸው።

መ. አለመግባባትን ለማስወገድ ይቻል ዘንድም ማምጣት ስለሚፈለገው የምርምር ውጤት ውስጣዊ ይዘታቸው፣ ማሳረጊያዎቹ ጭምር አስቀድሞዉኑ የሚገለፁ ናቸው።

ሰ. የተፈጥሮ ሳይንስ የምርምር ውጤቶች ግልፅነት ያላቸው በመሆናቸው  ለመፈተን ዝግጁነትን የተላበሱ፣ ሥራቸው ለእርምት  ግልፅ መሆናቸው፣ ለምርምሩ መሰረት የሆኑ ማጠየቂያዎች ግልፅ መሆንን ሁሌም የሚጠይቁ መሆናቸው ለቀን ተቀን ተግባራቸው በመመሪያነት የሚገለገሉባቸው ናቸው።

ረ. ከሁሉም በላይ ደግሞ ከእሴቶች ነፃ  በመሆን ጥናታዊ ምርምርን ለማድረግ ዝግጁነትን የተላበሰ  ነው።

ከዚህ አንፃር የታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሀሳቦች በነዚህ መመሪያዎች ላይ የተመረኮዙ በመሆናቸው ከፅንሱ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የተለያዩ ከቀላል እስከ እልህ አስጨራሽ እስከሆኑት ድረስ ቢቀርብበትም መሰረቱ ሊናጋ ቀርቶ ይበልጡኑ እየዳበረ በመሄድ  ላይ የሚገኝ ብቸኛ ፅንሰ ሃሳብ ለመሆን የበቃ ነው። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢም ይህንን አስተሳሰብ በፅኑ የሚጋራው ነው። ይህ ማለት ተፎካካሪ ፅንሰ ሃሳቦች የሉም ማለት አይደለም። እምብዛም አልራቁም እንጂ። 

ይህ በንዲህ እንዳለ ወደ ፅሁፋችን ከመግባታችን በፊት ለአንባቢያን ግልፅ ሊሆን የሚገባው በዚህ ክፍል 2 ውስጥ ስለታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሃሳብ ለግንዛቤ ይረዳል በሚል መነሻ የቀረበ ሲሆን ፈጣሪን በአሉታዊ ገፅታ ለመቀባት የሚደረግ ሙከራ ተብሎ ለመውሰድ የሚቃጣው ካለ ችግሩ ከአንባቢው እንጂ ከመጣጥፉ ከቶም ሊሆን አይችልም። የዚህ መጣጣፍ አቅራቢም ሃሳቡን በመግለፅ ለመማርና ለማሳወቅ እንጂ ሌላ ምንም አይነት የተደበቀ ፍላጎት ያለው አይደለም።

ስለሆነም ለእውቀት መገኘት ልቦናውንና ሕሊናውን ክፍት በማድረግ መጣጥፉን የሚያነብ ማንኛውም አንባቢ  ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳውም። በመሆኑም ወደ መጣጥፉ ይዘት እንግባ። 

የታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሃሳብ የሚመሰረተው በሁለት ምክንያታዊ ማጠየቂያዎች ላይ ነው።

እነዚህም፥-

1ኛ. በምድራችን ላይ በምርምር ሊታወቁ የተቻሉት የተፈጥሮ ሕጎች በአፅናፈ አለም ላይም ተግባራዊ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ሲሆን ለዚህ የቀረበው ማጠየቂያ የአፅናፈ አለም መፈጠር መስረት የሆነው መላ ምት (Hypothesis) በነዚህ ሕጎች ተመስርቶ ጥናታዊ ምርምር ማድረጉ አግባብነት ያለው መሆኑን በመገንዘብ ነው።

2ኛ. አፅናፈ አለም በየትኛውም ቦታ በሁሉም አቅጣጫ በስነ ፈለክ መርህ ተብሎ በሚታወቀው ፅንሰ ሃሳብ መሰረት በአንድ አይነት መልክ ለመታየት በመቻሉ ቀደም ብሎ እንደተገለፀው የአፅናፈ አለም እድገትና ክስተት በአዳዲስ ፅንሰሃሳቦች  (በኳንተንፈልድና  በአጠቃላዩ አንፃራዊ ጽንሰ ሃሳብ) በመመስረት ሊጠኑና ሊገለፁ የሚችሉ መሆናቸውን ከግምት በማስገባት ነው።                                                            

ታላቁ ፍንዳታ በዘመናዊ ስነፈለክ ፅንሰ ሃሳብ መሰረት የአፅናፈ አለም የመጀመሪያ ክስተት ተብሎ የሚወሰድ እንደሆነ ሊቃውንቶቹ የሚገልፁት ነው። በመሆኑም በስነፈለኩ መደበኛ ሥእላዊ ሞዴል አገላለፅ አፅናፈ አለም የተፈጠረው ከ 13,8 ሚሊያርድ አመት በፊት እንደሆነ ሊቃውንቶቹ ይገልፃሉ። ፍንዳታው የተካሄደው አስቀድሞውኑ ባለ ህዋ ውስጥ ሳይሆን ቁስ አካል፣ ህዋና ጊዜ (Matter, Time and Room) በአንድ ላይ ከአንድ እጅግ በጣም እጅግ (በሊቃውንቶቹ አጠራር Singularity) የመጨረሻ አናሳና በልዩ ሊተረጎም ከሚቻል እፍግታነት(Density) ካለው ስረምንጭ/መነሾ ተጣምረው የተከሰቱበትን ሁናቴንና እድገታቸውን ነው። ከዚህ ድምዳሜ ለመድረስ የተቻለው ደግሞ ሊቃውንቶች የአፅናፈ አለምን እየሰፋ መሄድ በምርምራቸው ካረጋገጡ በኋላ ሲሆን እየሰፋ የሚሄድ ደግሞ የግዴታ ከአንድ የሥረምንጭ/መነሾ  ቦታ መጀመር አለበት በማለት ያቀረቡት የመላ ምት ግምታቸው በተጨባጭ እውነት ሆኖ በበርካታ ተመራማሪዎች በመረጋገጡ የተነሳ ነው። ከዚህ ግንዛቤ በመመስረት ሶስት የአሜሪካ ሊቃውንቶች ከላይ የተጠቀሰውን መላ ግምት በመውሰድ እጅግ በጣም አስደናቂ፣ አስገራሚ፣ እንኳን በዚያን ጊዜ አሁንም ድረስ በርካታዎች ለማመን የሚቸግራቸው አስተያየት በመሰነቅ ምርምራቸውን በጥልቀት ማካሄድ ይጀምራሉ። ከዚህ በኋላ የሰው ፍጡር ባገኛቸው የተፈጥሮ ሕግጋትና እውቀት ላይ በመመስረት እንኳን በጥቃቅን ቁስ አካላት ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው አፅናፈ አለም ስላለው ሁናቴ ለመርመርና ለማወቅ ይቻላል በማለት ፍፁም ድፍረት በተሞላበትና ለብዥታ ክፍት ቦታ በማይሰጥበት መልኩ ትንቢታቸውን ይፋ አደረጉ። (ድርብ ድርብርብ መስመር ይሰመርበት)። አንባቢ እዚች ላይ ቆም ብሎ በጥሞና ደጋግሞ እንደገና ደጋግሞ እንዲያሰላስለው የሚፈለገው አንድ ቁም ነገር ይህንን አስተያየት የሰጠው ሌላ ሳይሆን የሰው ፍጡር ራሱ መሆኑን ነው።  የታላቁ ፍንዳታ እውነትነት በጥናታዊ ምርምር መረጋገጥ ይህንን አስተሳሰብ በሁለት እግሩ እያቆመው መሆኑ እየታየ ነው። 

እንግዲህ እስካሁን ከላይ በተገለጹት ፅንሰ ሃሳቦች የአረዳድ ግንዛቤዎች ላይ በመመስረት አፅናፈ አለምን መረዳት የምንችል ከሆን አፅናፈ አለምን በምናባችን እያሰብን ወደኋሊት መሄድ እስከምንችለው እስከመጨርሻዋ ትንሿ መነሻ ነጥብ ድረስ ብንጓዝ የተፈጥሮ ሕግ የሚፈቅድልን ምን ያህል ድረስ ነው የሚለውን ጥያቄ በቅድሚያ መመለስ የግዴታ ያሻል ማለት ነው። ለዚህ መልስ ልናገኝ የምንችለው ደግሞ ሀይዘንበርግ የተባለው ሊቃውንት ባቀረበልን (Uncertainty Principle) የተሰኘውን መርህ በመጠቀም ይሆናል። ይህም መርህ ደግሞ ተግባራዊ የሚሆነው  እንደ ኤሌክትሮን የመሳሰሉ እጅግ በጣም ጥቃቅን ቁስ አካላት በሚገኙበት አካባቢ ወይም ሰፈር ነው። በመሆኑም እነዚህ ጥቃቅን ቁስ አካላት ባሉበት አካባቢ እያንዳንዱን በተናጠል የሚንቀሳቀሱበትን የጊዜ ፍጥነትና ቦታ ለመለካት ብንሞክር የምንለካበት መሳሪያ የቱንም ያህል ዘመናዊና የመለኪያው ትክክለኛነት እጅግ በጣም ከፍታ ያለው ቢሆንም ፈፅሞ የማይሳካልን መሆኑን በተደጋጋሚ የተደረገው  ጥረት የሚያመላክተው ነው። 

ማክስ ፕላንክ የተባለ ሊቃውንት በበኩሉ በ1900 ዓ.ም. ገደማ እንደ ብርሃን ፍጥነት (c = 300 000 m/s ሜትር በሰከንድ) (ሊቃውንቱን በዘላለማዊነት እንዲታወስና እንዲከበር ይቻል ዘንድ በስሙ እንዲጠራ የተደረገ) አዲስ አይነት የተፈጥሮ ሕግ ፕላንክ („h“ = Planck’s constant h = 6.626 070 15 x 10–34 J s (J s = kg m2/s))  አገኘ። ይህንን በዋናነት ከብርሃን ፍጥነትና (c) ከስበት(ግራቪቲ)(G) ጋር በማጣመር በምናባችን እያሰላሰልን ያለውን ለመጓዝ የምንችልበት እርዝማኔ፣ ግዜንና ክብደቱንም ሆነ ስፋቱን  እንዲሁም እፍግታውን ያስገኝልናል።

    1/2

                                    እርዝማኔ   lP          =    G/c3      1,616199· 10-33 [m]

    1/2  

                                     ጊዜ         tP       =     G/c5        5,39106· 10-44 [s]

                                                                            1/2

                                    ክብደት     mP      =       c/G           2,17645· 10-8 [kg]

በማስከተልም የሙቀቱ ልክ TP  =  EPk = 1k·c5G 1,41679· 1032 [K]

 ስፋቱ AP  =  LP2  = Gc3 2,61223· 10-70 [m2]

እንዲሁም እፍግታው (Density) PP   =  mPLP3 = c5G2 5,15500· 1096 [kgm-3]

አንባቢያን ከላይ የተቀመጡትን አሃዞች ከታች ካለው ስዕል ጋር ሲያነፃፅር  ሊገነዘበው የሚችለው አንድ ቁም ነገር ለአፅናፈ አለም መፈጠር ለፍንዳታው አግባብነት ያለው የመጨረሻዪቱ እጅግ ትንሿ በእንግፍታ የተሞላችውና ከፍተኛ ሙቀት ይኖራታል ተብላ የምትጠቀሰው የፕራንክ ሥረ ምንጭ/መነሾ  ምን ያህል ከአንድ አቶም እጅግ አናሳ እንደሆነች የሚያሳይ ነው። 

ስዕሎቹ በሙሉ አንባቢያን  ለማነፃፀር እንዲመቸው ተብሎ የቀረቡ ናቸው።

የተገኙት ከድረ ገፆች ነው።

እነዚህ በፕላንክ ሥም የተጠቀሱት ቁጥሮች በፍንዳታው ጊዜ መሰረታዊ ሚና እንደነበራቸው ና ለታላቁ ፍንዳታ ማረጋገጫ ተብለው ስለሚጠቀሱት ነጥቦችን በተከታዩ መጣጥፍ የሚብራሩ ይሆናል። እስከዛው መልካም ንባብ ከመልካም ግንዛቤ ጋር።

Filed in: Amharic