>

በዛሬዋ ዕለት 1892 ዓ.ም ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ አረፉ...!!!! (ታሪክን ወደኋላ)

በዛሬዋ ዕለት 1892 ዓ.ም ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ አረፉ…!!!!
ታሪክን ወደኋላ

ከ 122 ዓመታት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን የታላቁ ንጉሥ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ አጎት የሆኑትና በጀግንነታቸው ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስን ጭምር ያስጨነቁት ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ ያረፉበት ዕለት ነበር።
ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ የስመጥሩ የሸዋው ንጉሥ የንጉሥ ሳህለሥላሴ ወሰን ሰገድ ልጅ ናቸው፡፡ እናታቸው ወይዘሮ ወሪጌ ይባላሉ፡፡ የደጃዝማች አስፋው፣ የደጃዝማች ደስታ፣ የፊታውራሪ ሸዋረገድ፣ የወይዘሮ ትሰሜ፣ የወይዘሮ አስካለ፣ የወይዘሮ ፀሐየወርቅ እና የልጅ ጉግሳ አባት ናቸው፡፡ [ወይዘሮ ትሰሜ ዳርጌ የልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ እናት ናቸው]
ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ የንጉሥ ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴ (የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ አባት) ወንድም ናቸው፡፡
በ1822 ዓ.ም ሸዋ ውስጥ የተወለዱት ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ፣ የልጅነት ጊዜያቸውን በአንኮበርና በአንጎለላ አሳልፈው ወደ ጎንደር ተጉዘው በነበሩበት ወቅት በሰላይነት ተጠርጥረው ታስረው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ራስ ዳርጌ ንፁህነታቸው ታውቆ ነፃ ከወጡ በኋላ በመልካም ጠባያቸውና በጦር ሜዳ ጀግንነታቸው  በንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ዘንድ ተወዳጅነትን አተረፉ፡፡ በዚህም ምክንያት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ራስ ዳርጌን ‹‹ዳሩ›› ፣ ‹‹ዳርዬ›› እያሉ ይጠሯቸው ነበር፡፡
የርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ ጀግንነት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስን ጭምር ያስጨነቀ ነበር፡፡ በንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ጊዜ ሸዋን ይገዙ የነበሩት መርዕድ አዝማች ኃይሌ ንጉሰ ነገሥቱን በመክዳት ተጠርጥረው ታስረው ነበር፡፡ ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስም አቤቶ ዳርጌን የሸዋ ገዢ አድርገው እንደሾሙ ተናገሩ፤ ነገር ግን ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ የራስ ዳርጌን የጦር ሰፈር ሲመለከቱት በጣም የደመቀና የተደራጀ ስለነበር በጣም ተጨነቁ፡፡
ንጉሰ ነገሥቱም አቤቶ ዳርጌን አስጠርተው ‹‹ዳርዬ ፈራሁህ! በጥንድ ጦር የሚስተውን ኃይሌን ሽሬ በነጠላ ጦር ደርበህ ሁለት ሰው የምትገድለውን አንተን በሸዋ ላይ አልሾምም›› ብለው በግልጽ ነገሯቸው፡፡ ራስ ዳርጌም የመከፋትና የቅሬታ ምልክት ሳያሳዩና ሳይከፉ ‹‹እሺ›› ብለው ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስን በትህትና እጅ ነሱ፡፡
ልጅ ምኒልክ (በኋላ ንጉሥ ምኒልክ፣ ከዚያም ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ) ከመቅደላ አምልጠው ሸዋ በገቡና በአባታቸው ዙፋን በተቀመጡ ጊዜም፣ ራስ ዳርጌ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ወደ ሸዋ ተመልሰው ከምኒልክ ጋር ተገናኙ፡፡
ምኒልክም ሸዋ ገብተው በአባቶቻቸው አልጋ ተተክተው የሸዋ ንጉሥ ሆነው ነበርና ራስ ዳርጌ እንደመጡ ‹‹እርስዎ ቀጥታ የንጉሥ ሳህለሥላሴ ልጅ ስለሆኑ ንጉሥነቴን ልተውልዎ›› ብለው ጠየቋቸው፡፡
ራስ ዳርጌም ‹‹የለም አባታችን ሳህለሥላሴ አልጋቸውን አውርሰው የሞቱት በቀጥታ ለአንተ አባት ለንጉሥ ኃይለመለኮት ነው፤ አሁንም የነጋሲነት መስመሩ በዚያው ባንተ በኩል ነው መቀጠል ያለበት›› ብለው እንቢ አሉ፡፡ ከዚያ በኋላም ራስ ዳርጌና ንጉሥ/ንጉሰ ነገሥት ምኒልክ እንደአባትና ልጅ ሆነው ከ30 ዓመታት በላይ ዓመታት ኖሩ፡፡
ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ የተለያዩ አካባቢዎችን በማቅናትና በማስተዳደር ስራ ውስጥ የላቀ ድርሻ ነበራቸው፡፡ ከነዚህ አካባቢዎች መካከል አርሲ እና ሰላሌና አካባቢው ይጠቀሳሉ፡፡
ንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛ እና ንጉሥ ምኒልክ በተቀያየሙ ጊዜም አስታራቂ ሽማግሌ ሆነው ያገለገሉት ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ ነበሩ፡፡ ንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛ እና ንጉሥ ምኒልክ ደብዳቤ የሚፃፃፉት በርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ በኩል ነበር፡፡ ደጃዝማች መሸሻ ሰይፉ በሸፈቱ ጊዜም ተቆጭው፣ አስማሚውና መካሪው ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ ነበሩ፡፡
በዓድዋ ጦርነት ወቅትም ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ለጦርነቱ ወደ ዓድዋ በተጓዙበት ወቅት የንጉሰ ነገሥቱን ቦታ ተክተው አገር ያስተዳደሩት ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ ነበሩ፡፡
በመጨረሻም በመልካም ጠባያቸው ፣ በበጎ አሳቢነታቸው እና በጦር ጀግንነታቸው የሚታወቁት ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ መጋቢት 15 ቀን 1892 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ስርዓተ ቀብራቸውም በደብረሊባኖስ ገዳም ተፈጽሟል፡፡
ምንጭ፡ አጤ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት
በአቶ ተክለፃዲቅ መኩሪያ (ገጽ 607-608)
(ልዑል ዓምደጽዮን ሠርፀድንግል)
Filed in: Amharic