>
5:18 pm - Tuesday June 15, 8055

ቁጭ ብለን የሰቀልናቸውን ቆመን ለማውረድ እንዳንቸገር   (ደረጀ መላኩ - የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

ቁጭ ብለን የሰቀልናቸውን ቆመን ለማውረድ እንዳንቸገር  

 

ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

 

 Tilahungesses@gmail.com 

 እንደ መግቢያ

ከሃበሻ ወግ መጽሔትም ሆነ ከሌሎች ሀገር ውስጥ ለህትመት ከበቁ ጋዜጦችም ሆኑ መጽሔቶች በተለይም ከዝነኛዋ የፍትሕ መጽሔት አምደኞች ብዙ ትምህርት አግኝቼበታለሁና ምስጋናዬ የላቀ ነው፡፡ ለሃሳብ ልእልናም ለምትተጉ ኢትዮጵያዊ ወንድሞች እና እህቶች አክብሮቴ የላቀ ነው፡፡ መወለድ ቋንቋ ነው ይላሉ እነኛ የጥንት አባቶች ፡፡ 

አዎን የኢትዮጵያን ጉዳይ ጥቁርና ነጭ አድርገን ከመመልከት መቆጠብ አይከፋም፡፡ ገና ከጅምሩ ዲጂታል ወያኔዎችና መሰል አላማ ያላቸው የኢትዮጵያ መንግስትን ይቃወሙ የነበሩት ለየግል ጥቅማቸውና አጀንዳቸው እንጂ ሁሉም ለሀገራችን ጥቅም አስበው አንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ በተለይ በትክክለና ስማቸው ሳይሆን በብእር ስም በፌስ ቡክ አንድ ሰው አስር አካውንት አውጥቶ የፌስ ቡክ ሠራዊት በማደራጀት የውይይትን አቅጣጫ ለማሳትና ልዩነት አያራገቡ እርስ በእርስ እንድንናቆር ይጥሩ የነበሩትና ያሉት ሳይዘነጉ………፡፡ እኔ ከእነኚህ ተርታ ውስጥ የለሁበትም፡፡ ጸሃፊው የማናቸውም ፖለቲካ ድርጅቶች፣መንግስትንም ይጨምራል አሸርጋጅ፣ወይም ተቃዋሚ አይደለም፡፡ የእኔ ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ነው፡፡ በየግዜው የምሰጣቸው አስተያየቶች ለኢትዮጵያ ህዝብና ኢትዮጵያ የሚበጅ ሃሳብ ለማቅረብ እንደሆነ አንባቢውን አስታውሳለሁ፡፡

መንግስት  ጥሩ ነገር ሲሰራ መደገፍና የተሳሳተ አቅጣጫ ሲወስድ እርምት እንዲወስድ መጮህ፣እሪ ኡኡታ ማሰማት፣የመፍትሔ ሃሳብ መሰንዘር ትላንትም፣ዛሬም ነገም ትክክለኛ መንገድ ነው፡፡ መርሳት የማይገባን ሦስተኛው መንገድ እየተቃወምነው እንኳን የሀገር ጉዳይ አደጋ በሚያንዣብበት ወቅት የእርስ በርስን ትግል ወደ ሁለተኛ ደረጃ አውርዶ ክፍተትን በመዝጋት ሀገርን ከባሰ አደጋ መከላከል በኔ ዕምነት ምንግዜም ልክ ነው፡፡ ብዙዎች እንደምትሉት ሀገር ሲኖረን ነውና ጸቡም ፍቅሩም የሚቻለው፡፡ ልክ ያልሆነው ጭፍን ድጋፍና ጭፍን ተቃውሞ ነው፡፡ ይህ ማለት ሦስተኛ የተሻለ አማራጭ ካለ አለመቀበል ማለት አይደለም፡፡ ሁላችንም እንደምናስታውሰው ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሚሊዮኖች ድጋፍ ሰጥተውት ነበር፡፡ ዛሬ ላይ የማንክዳቸው ብዙ በጎ እቅዶችና እንቅስቃሴዎችን አሳይቷል፡፡ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ያለገኘነውን ብዙ ነገሮች አሰምቶ የብዙ ኢትዮጵያውያንን  ልብ ወስዶ ነበር፡፡ ያን ሁሉ ያደረገው ለምን ነበር ? እስቲ በየአካባቢያችሁ ተወያዩበት ፡፡ ለማናቸውም በእኔ በኩል ኢትዮጵያዊነትንና አክራሪ ብሔርተኝነትን ‹‹ አስታርቆና አቻችሎ ›› ለመሄድ የቆረጠ ይመስለኛል፡፡

 ‹‹ መንግስት አላማረኝም ›› ይሄ እንደሚሆን እንጠብቅ ነበር ብለው ምንም ሳይሰሩ ቁጭ ብለው ከርመው ስህተት ሲከሰት ‹‹ ትከሻዬ ነግሮኝ ነው ያልደገፍኩት ›› ይሄ እንደሚከሰት ቀድመን እናውቅ ነበር ›› እያሉ መንግስትን መቃወም እንደ ተራማጅነትና የትግል ዘዴ አድርገው የሚያዩትና፣ እንደ መደገፍ ጀምረው እንደ ‹‹ በቁርባን ጋብቻ›› ቃል የተገባቡ እስከሚያስመስሉት ‹‹ ፍቅር እስከመቃብሮች ›› መሃል ብዙ ልዩነት ስላለ ውይይቱን ‹‹ እናንተ ልክ አልነበራችሁም፣ እኛ ልክ ነበርን ›› ወደሚል ዝቅ ወዳለ ክርክር አለመውሰዱና ነገሮችን በየወቅቱ ከሚወስዱ አቋሞች ተነስተን መቀወምም ሆነ መደገፍ ይሻላል፡፡

ስንደግፍም ሆነ ስንቃወም ከራሳችን ጠባብ የድርጅት ፍቅርና፣ ‹‹ የኛ›› ብለን መርጠን ከቆምንበት ጥግ እራሳችንን ነጻ ሳናወጣ ? የምንሰጠው ድጋፍ ፣ እንደ የእግርኳሱ ሆሊጋኖች አካሄድ ነው የሚሆነው፡፡ ሆሊጋኖች የሚደግፉት ክለብ ለማሸነፍ ጥሩ ጨዋታ ብቻ ማሳየት የለበትም፡፡ ዓላማው ማሸነፍ ስለሆነ እግር ሰብሮም ሆነ አጭበርብሮ የገባበትን ጎል ክዶም ቢሆን ማሸነፍ አለበት፡፡ ተጫዋቾቹ የሚችሉትን ሞክረው ከተሸነፉ በተናደዱ፣ በራሳቸው ቡድን ደጋፊዎች የሚገደሉ ተጫዋቾች እንዳሉ ከወደ ብራዚል ተሰምቷል፡፡ መንግስትን ትንሽ መደገፍ ሲጀምሩ  ውርጅብኝ እንደሚወርድባቸው የተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎች ፣ በደቦ ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም ምክንያታዊ መሆን አይጠበቅም፡፡ ውይይት፣ ድምጽ ብልጫ፣አማራጭ ማቅረብ ሳይሆን  መሪውን በጭፍን መከተል ነው፡፡ ይህ የእውር ድምብር ጉዞ ደግሞ ለሀገር አይበጅም፡፡ 

ሆሊጋኖች ስሜታቸው ከአዕምሯዋቸው በላይ ስለጠነከረ ‹‹ አብሮ ›› በደመ – ነብስ በስሜት ብቻ ተነሳስተው ከመደገፍ፣ከማበድና ከማውደም ውጭ፣ ምን እያጠፉ እንደሆነ የሚያደርሱትን ጥፋት አያስተውሉም፡፡ ዋናው ቁመነገር ቡድናቸው ውስጥ አንዱ ለሌላው ገደብ የለሽ ድጋፍ እንደሚሰጥ ማስመስከሩና መተጋገዙ ነው፡፡ ማን የበለጠ ጨካኝና ደፋር እንደሆነ ማሳየቱ እንጂ፣ተጋግዘው ሰው ሲደበድቡ፣ መስታወት ሲሰብሩ፣ ንብረት ሲዘርፉ፣መኪና ሲያቅጥሉ፣አንዱ ሌላውን ይረደዋል እንጂ ተው የሚል ከልካይ መሃከላቸው የለም፡፡ስሜት ጣራ ሲነካ በምክንያት ማሰብ ባፍጢሙ ይደፋል፡፡ ይህ ነው መራሩ ሀቅ፡፡

 ጥቂት የማይባሉ የሀገራችን ‹‹የዜግነትም ይሁኑ የብሔር ድርጅት አባላትና ደጋዎቻቸው ልክ እንደ የእግርኳሱ ሆሊጋኖች፣ መያዣና መጨበጫ የሌላው፣ቅጥ አንባሩ የጠፋባቸው እስከሚመስሉ ድረስ፣ የሚደግፉትንም ሆነ የሚቃወሙትን ድርጅት ዋሽተውም ሆነ ቀጥፈው በማንኛውም መንገድ ትክክለኛ እንደሆነ ማስመስከር እንደሚጠበቅባቸው አድርገው እራሳቸውን አሳምነው ሌሎችንም ሊያሳምኑ ሲሰባበሩ ማየት እለመድነው ሄደናል፡፡ ሌላው ዘውትር የሚያስጨንቀኝና የሚያሳስበኝ ጉዳይ አለ፡፡ ይሄውም አንድ መንግስት በስልጣን ዘመኑ ላይ ላደረገው መልካም ተግባር ማመስገን፣ላጠፋው ጥፋትም ሆነ ወንጀል መውቀስ ወይም እንዲየሻሽል ሃሳብ መሰንዘር በብዙ ዜጎች አለመለዱ ነው፡፡ ብዙዎቻችን ዝምታን መርጠን መንግስት ድንገት ስልጣኑ መናድ ሲጀምር እርግማናችን አይጣል ነው፡፡ እምባችን እንደ ጎርፍ ይጎርፋል፡፡ ወይም እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አባባል ‹‹ አድፋጮች  ›› ነን፡፡ ይህ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያዘነበለ መሰለኝ፡፡ ሰርክ አዲስ በግልገል አምባገነኖች አስቀጠቀጠን እንጂ ኑሮአችንን አላሻሻለውም፡፡ ዘውተር ከል እንደለበስን አለን፡፡ ይሁንና ይህ መልእክቴ፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከልብ ለሚያሳስባቸው እንጂ ፣ ዲጂታል ወያኔና መሰሎቻቸውን ጨምሮ ፖለቲካን መተዳደሪያ፣ መደበሪያ፣ ስንፍና መደበቂያ፣ማህበራዊ ኑሮን ማሞቂያ፣ የሚጠሉትን ሰው ማጥቂያ፣ ላደረጉ ግጭት ጠማቂዎችና ደካሞች አይደለም፡፡

በነገራችን ላይ መልእክቱ የሚያተኩረው  በኢትዮጵያ መሰረታዊ የፖለቲካ ችግር ላይ የራሴን የግል አስተያየት ላይ ነው። የዛሬው መልእክቴ የቡዙሃን ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ላያ ያተኮረ መሆኑን አንባቢው ሊገነዘበው ይገባል  ይገባል ባይ ነኝ። የማናቸውንም የፖለቲካ ድርጅት አላማ የሚደግፍ ወይም የሚነቅፍ አይደለም፡፡ የችግራችን ምንጭ ምን እንደሆነ መጠቆም ግን የጽሁፉ ዋነኛ አላማም ነው፡፡

አያሌ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ሰዎችና እውቅ ጋዜጠኞች በጥናት እንደደረሱበት ከሆነ የችግራችን ዋናው ምንጭ ህገ መንግሥቱ መሆኑን የታወቀ ነው፡፡ እርግጥ ነው ይገባኛል፣ ይህ ህገመንግስት እንዲነካ የማይፈልጉ፣ወይም መሻሻል የለበትም የሚሉ የብሔር ድርጅቶችና የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች ሞልተው ተርፈዋል፡፡ 

ለማናቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና ፓርቲቸው ባላቸው ክፍተኛ ድጋፍ ቀደም ብለው ለኢትዮጵያ ህዝብ የጉቡትን ቃልኪዳን መፈጸሚያዎ ግዜው አሁን ነዉና  በየትኛውም መገናኛ ብዙሃን ወይም የህትመት ውጤቶች ላይ ሀገር ወዳድ እና  በህሊና ሚዛን ላይ የተቀመጡ ሰዎች የሚሰጥቱን አስተያየት ደጋግመው ቢመለከቱ ለሀገርችን እና ለህዝባችን ጠቃሚ መፍትሄ እንደሚያገኙበት አልጠራጠርም ።

ቲያትሩ

“የብልጽግና የመጀመርያ ጉባኤ፣ በቲያትር መልክ ቢቀርብ ግሩም ቲያትር ነበር ይሆን ነበር ብዬ  አስባለሁ፡፡!”

በስእል ዓለም ውስጥ የተለያዩ ቀለማትን በማውሃድ፣ የጠቆረውን በብርሃን፣ ዳመናውን በጭጋግ፣ ፀሐይን በግርዶሽ ተፈጥሮያዊ ይዘቱን ለተፈለገው መንገድ አሳምሮ የስነ ጥበብ ክህሎትን ማሳየት የሚቻለው በስእል፣ በሙዚቃና በቲያትር…ብቻ ሳይሆን፣ በንግግርም እንደሚቻል በብልጽግና ስብሰባ ላይ፣ ዶክተር አቢይ ሕገ-መንግስቱን በተመለከተ በሰጡት አገላለጽ ላይ ተረድቻለሁ፣ ጭብጥ ሃሶቦቹን መቀበል ብቸገርም……

ጥቂት ከዘረዘሯቸው ውስጥ በ ሀ እና ለ በሁለት ተከፍሎ ባጭሩ ቢታይ….. 

ሀ/ –ብልጽግና ፓርቲ “ሕገ መንግስቱ እንደ መጽሃፍ ቅዱስና ቁራን መነካት የለበትም የሚለውን አይቀበልም፡፡” –“ሕገመንግስቱ ተቀዶ መጣል አለበት የሚሉትም ሆኑ፣ መነካት የለበትም የሚሉት፣ ሁለቱንም ዋልታ ረገጥ አቋም አይቀበልም፡፡” –“ሕገ መንግስቱ አዲስ ፓርቲዎች በመጡ ቁጥር፣ ልክ እንደ ትህነግ ሕገ መንግስቱንና ሠራዊቱን አፍርሶ የበተነው ስህተት ነበር፡፡” –“እኛ ተሰብስበን ስለ ሕገ መንግስት መወሰን አንችልም ….ወዘተ” ያልሉትና 

እንደ መፍትሄ በተደጋጋሚ ያቀረቡት ሌላው አስተያየት ለ/ –“ሕገመንግስቱ ለመቀየር ሕዝብን ባሳተፈ ሕግና ስርዓትን በተከተለ አግባብ ብልጽግና ያምናል፡፡” –“ሕጋዊ መንገድ መከተል አለበት፡፡” –“ሕዝብን ባማከለና ሕግና ደንብን በተከተለ መንገድ ሕዝብን አሳትፈን አወያይተን ነው የሚቀየረው” –“እኛ ስንቀየርና ስናድግና ለመቀየር ክፍት ነን” ..ወዘተ የሚለው ይገኝበታል፡፡ 

ሀ እና ለ በመርህ ደረጃ ለየብቻ ተነጣጥለው ሲታዩ ለኔ ሁሉም ልክ ናቸው፡፡ 

ነገር ግን ሀ እና ለን ሕዝብ እየተጠየቀና እያቀረበ ካለው አውድ ውጭ ይዘቱን ቀይሮ በማቅረብ የተሰጡት መልሶች፣ እንደ ስእሉ ወይም ሰአሊው፣ ሁሉም ሊያይ በሚመቸው መንገድ ለራሱ እየተረጎመ እንዲጽናናበት የቀረበ መከላከያ እንጂ በትክክል ከየአቅጣጫው ይተላለፍ የነበረው ጥያቄም ሆነ ከአራት ዓመታት በኋላ እንጠብቃቸው የነበሩት መልሶች እነኚህ ሊሆኑ አይገቡም ነበር፡፡ 

እንደነዚህ አይነት አሻሚ መልሶችም ነበሩ ብዙዎቻችን፣ “ከምርጫ ቦኋላ፣ ሕጋዊ መንግስት ሲመሠረት፣ ጦርነቱ ሲገባደድ፣ ጠላት እንዳይጠቀምበት ውጥረቱ ሲበርድ..ወዘተ” እያልን ተስፋ ሰንቀን ለአጣዳፊ ችግሮች ቅድሚያ የተሰጠው፡፡ ግፊት ለማሳደር ወቅቱም ጥሩ አልነበረምና፡፡ 

“እኔ አሻግራችኋለሁ” አይነት ወሳኝ አጀንዳዎች ከራሳቸው ውጭ ለማንም ዕድል መስጠት ስላፈለጉ ነው የአስመራጩን ቦታ ተቆጣጥረው አስመራጭ፣ መራጭና ተመራጭ የሆኑት፡፡ 

በተጨማሪም በወርሃ መጋቢት 2014 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ በተካሄደው የመጀመርያ የድርጅታቸው ስብሰባ የዶክተር አቢይን አቀራረብ ሳስተውል ወዴት እየሄድን እንደሆነ እያስፈራኝ፣ አዳራሽ ውስጥ ተቀምጠው ማስጠንቀቂያ ይዘንብባቸው የነበሩት አባላትን ሳስተውል አሳዘኑኝ፡፡ የከፋ ችግር ጓዙን ጠቅልሎ እየመጣ እንደሆን አቀራረባቸውን ሳስተውል ደነገጥኩኝ፡፡ በተለይ “ትላንት ከኛ ጋር የነበሩ ዛሬ እዚህ የሉም፡፡ ነገ እናንተም “እኔም” ….የነሱ እጣ ነው የሚጠብቃችሁ እያሉ፣ በአርጩሜ ሕፃንን ልጅ እንድሚያስፈራሩትና፣ ሲያለቅስ “በል ዋጥ አድርጋት”ተብሎ እያመመው አፉን እንደሚቀጠቀጥ ልጅ ነው ያን የሚያህል አዳራሽ ጸጥ ያለው፡፡ 

በአንድ በኩል በውይይቱ ሁሉንም ማህበረሰብ ያላሳተፈ ሕገመንግስት እንደሆነ ሊቀመንበሩ ያመኑበት የሚመስል አቋም “በአራዳ ሽወዳ” በተደጋጋሚ፣ “የብሄር ፖለቲካ ይቀይሩልናል” ብለን እንድናስብ በገደምዳሜ እየተናገሩ፣ በሌላ ጎኑ “ሕዝብ ተወያይቶ መክሮበት ነው የሚሻሻለው…” የሚሉት እርስ በራሱ ይቃረናል፡፡ 

ያም ቢሆን እንኳን፣ ሁሉም ሕዝብ አንድ ቦታ ተገናኝቶ መወያየትና መወሰን ስለማይችል፣ ሕዝብ “እኔን ይወክሉኛል” “ድምጼን ያሰሙልኛል” “ፍላጎቴን ያንጸባርቁልኛል” ብሎ የመረጣቸው የፓርላማ አባላት በዚህ አጀንዳ ላይ ለመወያየት ምን ያንሳቸዋል?፡፡ የገዢው ፓርቲ ሚኒስቴሮች ይህን አጀንዳ ወደ ፓርላማ መምራት ለምን አልፈለጉም?፡፡ የትኛው አካል ነው መንገዱን የዘጋው?፡፡ እንደዚህ አይነት ትልቅ ሀገርን አደጋ ላይ ሊጥል ከሚችል አጣዳፊ ጉዳይ በላይ ፓርላማው ሊመለከተው የሚችል ምን ጉዳይ አለ?

ከዚህ አካሄድ እንደምንረዳው የብሔር ፌደራሊዝም ገዥው ፓርቲ ተመችቶት በዛው መንገድ መቀጠል እንጂ፣ በዚህ አቀራረብ እንኳን መቀየር ማሻሻል ይፈልጋል ወይ?፡፡ ብልጽግና በዚህ አጀንዳ “አይነኬ እና ይፍረስ” የሚሉ ሁለት ጽንፍ የቆሙ አቋሞች መሃል ወይም ውጭ ሊያደርጋቸው የሚችለው መመዘኛ ምንድነው?፡፡ 

በዚህ አይነት የመንግስት ግፊትና ጫና፣ የምክክር ኮሚሽኑስ ቢሆን እንዴት በነጻነት ሊሠራ ይችላል?፡፡ ዋናውን የሕዝብ አማካሪዎችን የፓርላማውን ስራ ተክቶ ነው ወይስ እንደ አጋዥ የሚሠራው?፡፡ ይህ ኮሚሽን የፓርላማውን ስራ እንዲወርስ የተፈቀደለት፣ ምናልባት ዶክተር አቢይ ከሚፈልጉት አቅጣጫ ውጪ ካፈነገጠ ለማፍረስ ስለማያስቸግር?

እስከዛሬ ሕዝብን እያፈናቀለና እርስ በርስ እያጋጨ ያለው የክልል አስተዳደር በገዢው ፓርቲ እንደ ችግር ካልታየ? ከትህነግ ጋር ጸቡ የስልጣን ነበር ማለት ነው? ያ ሁሉ ሕዝብ ያለቀውና ንብረት የወደመው ከላይ የተወሰኑ ቁንጮዎቹን ብቻ አስወግዶ በነበረው መንገድ በተራ ለመቀጠል? ….. 

መልሱን ህሊና ላላቸው እየተውኩኝ፣ ተገዳዳሪ የሆነ ጠንካራ የተቃዋሚዎች ህብረት መኖር እንዲህ አይነት አካሄዶችን በጊዜ እያየ የተሻለ አቅጣጫ ማሳየት ብቻ ሳይሆን፣ ለአገዛዙም እራሱን የሚያይበት መስታወት ስለሆነ፣ ፖለቲከኞቻችን ይህ ሕዝብን እያጫረሰ ያለው ብሔርንና ቋንቋን መሠረት ያደረገውን “የፌደራል አስተዳደር” እንዲወገድ የሚፈልጉ ድርጅቶች ወደ አንድ አቅጣጫ ተሰባስበውና ለዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው ታግለው እያታገሉ አቅጣጫ የሚያመላክቱበት ወሳኝ ወቅት ላይ ያለን ይመስለኛል ብዬ እንደ አንድ ተራ ሀገር ወዳድ በኔ እይታ የታዘብኩትን ሳካፍል፣ ያላየሁትንና የተሳሳትክት ካለ ለመታረም ዝግጁ ነኝ ለማናቸውም ቁጭ ብለን የሰቀልናቸውን ቆመን ለማውረድ እንዳንቸገር በሰከነ መንፈስ ተነጋግረን ለመሰረታዊ የፖለቲካ ችግሮቻችን መፍትሔ እንድንፈለግ በማሳሰብ እሰናበታለሁ፡፡ ሰላም፡፡

 

Filed in: Amharic