>

“ከፈተና ወደ ፍተላ” እና የአባ ጻፈው ብዕሮች...!!! (ኦሀድ ቢን አን)

“ከፈተና ወደ ፍተላ” እና የአባ ጻፈው ብዕሮች…!!!
 
ኦሀድ ቢን አን

ተመስገን ደሳለኝ ፊት ለፊቱ ያገኘውን ግድግዳ “ወይ አሳልፈኝ ወይ ጥሼህ አልፋለሁ፤” በማለት ብዕሩን ቀስሮ ከብዙ ግድግዳዎች ጋር እየተጋፈጠ የመጣ የብዕር አበጋዝ ነው፡፡ በአምባገነኖች፣ ሙሰኞችና የወያኔ ከሃዲዎች ላይ ግልፅ ጦርነት ከፍቶ ያለማሰለስ እየተዋጋና “ብዕር ከአፈሙዝ ይበልጣል፤” ብሎ ያመነና ያመነውን የኖረ ብርቱ ሰው፡፡ ብዕር ያበላሸውን ብዕር ማስተካከል ይችላል፡፡ በስናይፐር ያበላሹትን የንጹሃንን ህይወት ግን በስናይፐር የማያስተካክሉት እኩዮች አሁንም ማበላሸታቸውን መቀጠላቸው አሳሳቢ በሆነበት ፌርማታ ላይ የተመስገንን ስለታም ብዕሮች አለመፈለግ አይቻልም፡፡
ተመስገን ደሳለኝ በአሁኑ ጊዜ ወይም ከዘመነ-መለስ ጀምሮ ብዕሩን በድፍረት የሚቀስር ያመነበትን ከመናገር ወደኋላ የማይልና እስር ቤት ተጥሎ ከገዳዮቹ ጋር አብሮ መተኛት የለመደ፣ ከቀለም አፋሳሽ ተጋድሎው ፍንክች ያላለ፣ ደፋር መሆኑን ያስመሰከረ የወቅቱ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ነው ቢባል የሚቀየም የሙያ አቻው ያለ አይመስለኝም፡፡ “ራስን አሳልፎ ከመስጠት የበለጠ መስዋዕትነት” እንደሌለ መጽሓፉ ሲናገር ተመስገንም ለገበያ ባያውለውም ለአዳም የተከፋፈለውን ሸክም፣ ነገር ግን ሁሉም የማይችለውን አደራ ተቀብሎ ለሚወደው ሕዝብና አገር “ራሱን አሳልፎ የመሥጠት” ባህሪው ከፍተኛ መሆኑን የህይወቱ ዱካዎች በግልጽ ያመላክታሉ፡፡
ምን አልባትም ባለፉት 30 አመታት ከነሙሉጌታ ሉሌ ጀምሮ አምባገነንነት እየዋጣቸው “በመጥፋት ላይ ያሉ ጋዜጠኞቻችን” ትውልድ የመጨረሻው ፓንዳ ሳይሆን አይቀርም፤ (ጋዜጠኞቻችን ጨረሷቸው አደለ፤) እነዛ የቅዳሜ ማታ ቁርጥና ማወራረጃው ከአብራ-አዳሪዋ ጨረታ ጋር ሲናፍቃቸው፣ የተመስገን አንባቢዎች ደግሞ ቅዳሜ ጧትን ፍትሕን (መጽሔቷንና ራሷን ፍትሕንም) እየናፈቁ ለሚጠብቁት ወገኖቹ አንድ ከበድና ጠብደል ያለ አጀንዳ ሳይዝላቸው አያልፍም፡፡ ዲያስፖራዎቹም በዩቲዩብ የአባ ጻፈውን ጽሁፎች እስኪተረኩና “ስታርባክስ ቁጭ ብለው” በሰው አገር የአገራቸውን ቡናና የአገራቸውን ጉድ የሚያዋህዱበትን ቅዳሜ እስኪናፍቁ ድረስ “ፍትሕ” መጽሔትን ሌጀንድ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ አባ ጻፈውን የሚያደንቁትም የሚጠሉትም “ፍትሕ”ን በፊት-ለፊትም በቆረጣም በጨረፍታም ማየታቸው አይቀርም፡፡ ሥራዎች የሰዎች ታሪኮች ናቸው ከተባለ “ፍትሕ”ም የአባ ጻፈው ታሪክ ነች፤
በዛ ሰሞን ርዕሰ-ዜና የሚሆን ጉዳይ ያላቸው ባለሥልጣኖችን ድክመት፣ የአቋም መዋዠቅ፣ ሙሰኛነትና ቃል አባይነት በስፋት ለአክራሞት የዳሰሰባቸው ዘገባዎች ውስጥ የአንድ ብሔረሰብ ስብዕናዎችን የወጡባቸውን የ“ፍትሕ” ሽፋኖችን ብቻ መርጠውና ሰብስበው “የብሔራችን ጠላት ነው፤” በሚል እሳቤ ግልጽ ዘመቻ የከፈቱበት ሰዎችስ ነገር፤ ዘመቻው ከቃሊቲ ይጀምር ከኦሎምፒያ አካባቢ ለጊዜው የታወቀ ነገር ባይኖርም ፖለቲከኞቹ ለተጽዕኖ ተስፋፊነት ተቀናጅተው መስራት የጀመሩበትን ሁኔታ ያረዳ አጋጣሚ ነበር ይሆን የሚል ጥያቄ ማጫሩ አይቀርም፤ “የማይጠይቅ አእምሮ አይፈጠርና!”፤
ሆኖም ግን ዘመቻቸውም ሩቅ አልሄደም፤ ተመስገንም እየጻፈ እነሱም በአወዛቢ ህይወታቸው እየቀጠሉ ነው፡፡ የባለሥልጣናት ራስ-ምታቱ ጋዜጠኛ አሁንም ፋይል እየተሰበሰበበት እንደሆነ አለመገመት አይቻልም፤ ታምራት ነገራን የበላውና አልጮህ ያለው አዞ እሱንም እንደዘመኑ ፋሽን ሌላ ክልል ወስዶ ካልሰለቀጠው፤ መቼስ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚጸልዩት እናቶች ለሱም ከጸለዩለትና “የሚጠሏችሁን ውደዱ” የሚለው ቃል ወደ ልዕለ-ሥልጣናት ካረገ ተመስገንም፣ ፍትሕ መጽሔትም ዲሞክራሲም መሰንበታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ካልሆነ ግን ለ“ተመስገንን ፍቱት!” ዘመቻ ዜጎች መዘጋጀታቸው የሚቀር አይመስልም፤ ኖ ሞር (No More) የኮምፓሱን መርፌ አቅጣጫ ሊቀይር ይችላል፡፡
ፖለቲከኞች አቋራጭ መንገዶችን ለመጠቀምና በግል ፍላጎታቸው ሲታወሩ የማኅበረሰቡን የሕልውና ግብረ-መርሆችንና እሴቶችን ሲረሽኑ ስቅጥጥ አይላቸውም፤ ስንት ውሳኔዎቻቸው ስንቱን ግብረ-ሞራሎቻችንን እንደረሸኑብን እነዚህ አራት አመታት (የ27ቱ ይቆይና) አሳይተውናል፡፡ ቦዲጋርዶቹን ይዞ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናትን ለአስቸኳይ ጉዳይ በተሰበሰቡት ʻከነመሳሪያዬ ገብቼ ካላነጋገርኩʼ ሲል ʻተው ቆይʼ የተባለ ጉልቤ በጥበቃ ላይ ያለ መለዮ ለባሽ ላይ አጃቢው ተኩሶ እንዲገድል ትዕዛዝ የሰጠ (በተኩስ የጀመረ ነፍሰ-ገዳይ ወንጀለኛ ቢገባ ምን ሊፈጥር እንደነበረ የሰማዩ ይወቅ)  በነጻ ተለቆ፣ አገር ጠባቂው ወታደር ደመ-ከልብ ሆኖ ወንጀለኛው ያለምንም ፍርድና ያለምንም ሕጋዊ ሂደት ተፈትቶ ሲወጣና አፉን መክፈት ሲጀምር የሃገርን መጠበቅ ትርጉም ካላጠፋና ነገ ይሄው ሰውዬ ሌላ ጥበቃ ላይ ያለ ወታደር ፊት ሕገወጥ ትዕዛዝ ይዞ ቢመጣ “አትችልም፤” የማለት ድፍረት የሚኖረው ወታደር ማን ነው?
አንድ የነበረው ኢሕአዴግ ብልጽግና እና ህወሓት ሆኖ ችግሩን በሰላም መፍታት አቅቶት ቅራኔውን ሕዝብ ላይ ደፍቶት የደም ግብር ሲያስከፍልና በመቶ ሺዎች አጨራርሶ በሬሳቸው እና በታገቱት ሚሊዮኖች ዜጎቻችን መከራ ላይ ሊጨባበጥ እና እንደገና እንደ ደህና ፓርቲ ተስማምተናል ብሎ ሊቀጥል ሲያስብ የማይረሸኑትን ሞራላዊ እሴቶቻችንን ቆጥሮ የሚዘልቃቸው ማን ነው?
ያኔ ነው እንደነ አባ ጻፈው የብዕር አርበኞች እጅን ከወረቀት አንባቢን ከዕውቀት ጋር እንዲያገናኙና ድምጽና ደም አልባውን ሚናቸውን የሚወጡት፤ ደም አፋሳሾች ተለቅቀው ቀለም አፍሳሾች ሲሳደዱ ማየት የህብረተሰብ ሞራልን ከጀርባ በሜንጫ የመውጋት ክህደት መሆኑን የሚነግረውን ያጣ ኅብረተሰብ የሚከፍለው ድብቅ ዋጋ ትውልዶችን የሚሻገር ነው፤
አባ ጻፈው “ከፈተና ወደ ፍተላ፤” የሚለው ጽሁፉ እስካሁን ድረስ ካተማቸው በከፍተኛው ተገዳዳሪ ብዕሩ ከፍተኛውን ሰው የተዳፈረበት ታሪክ የሚሰንደው ከተራ የአመለካከት ውርጅብኝ ያለፈ ልዩ የጽሁፍ ድግስ ነው፡፡ ከንጉስ ዳዊት በስተቀር በአደባባይ የሰሩትን ስህተት በአደባባይ የሚነግራቸውን ሰው አፍሪካውያን ነገስታት አይወዱም፤ ንጉስ ዳዊት አንድ እብድ ከመሬት ተነስቶ ውርጅብኙን ሲያከናንበው ሊሰይፉት የተዘጋጁትን ጠባቂዎቹን “ተውት ምን አልባት እግዚአብሔር በሱ ሊናገረኝ የፈለገው ነገር ይኖር ይሆናል፤” ብሎ የማለፉንና ከእብድም ከጋማ ከብትም የመስማትን ጥበብ የአለም ነገስታት ብዙም ያዳበሩ አይመስልም፤ “ከሰደበኝ የነገረኝ፤” አሁንም አለች፡፡
ልክ ልካቸውን የሚነግራቸው ሚዲያ ያላቸው መሪዎች ብሩካን ናቸው፡፡ የዲሞክራሲ አንዱ መልካም ጎኑ መሪዎች ሰው መሆናቸውን አለማስረሳቱ ነው፡፡ እድለኞች ከሆኑ ከሕዝብ ጋር ማኪያቶ ለመጠጣት ካልሆኑ ደግሞ ሕግ እየተጠቀሰባቸውና የሚዲያው ውርጅብኝ እያሳደዳቸው ወይ ዘብጥያ ወይ ተምቤን መውረዳቸው አይቀሬ ነው፡፡ ወይም አገርን ለወያኔ አስረክበው በዚምባብዌ የሥልጣናት ገዳም እንደመነኮሱት ሰውዬ ገድላቸውን እየቆጠሩና ያጫረሱት ትውልድ መናፍስት እየጮኹባቸው ጥፋታቸውን ካድ ሽምምጥጥ አድርገው ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡ እሳቸው ቢክዱ በ17 አመታት ያጫረሱት ትውልድ ጥፋት አይካድ፤ (ግን በሳቸው ዘመን ይህን ያክል ሰው አልቆ ነበር እንዴ? ወቾ ጉድ፤ ደግሞስ “መለስ ማረኝ፤” የሚል ትውልድ ይነሳ ይሆን?) ረሃብ ከገደለብን እርስበርስ የተገዳልንበት ከበለጠ ወይ እኛ ወይ መሪዎቻችን ያልገባን ብዙ ነገር አለ፤
አገሪቷ ሁለቱንም ተቋማት የፕሬሱንም የጠ/ሚውንም ቢሮዎች ትፈልጋቸዋለች፤ ሆኖም ግን እነዚህ ተቋማት በግለሰቦች ሲወከሉና ሲገለጡ ድራማው ኮሜዲውና ትራጀዲው አይቀሬ ነው፡፡ ተልካሻ ምስጋና ፈላጊዎችና ውለታ አስቆጣሪዎች አባ ጻፈውን ሸብ አድርገው ሽልማታቸውን አፈፍ ለማድረግ መቋመጣቸውና “ዘራፍ አካኪ ዘራፍ የአቢቹ አሽከር የዛ ዘናጩ፤” ብለው መፎከራቸው እንደማይቀር ለብልህ አይነግሩም፡፡
ሕዝቡም እየሆነ ያለውን የማወቅ መብቱንና ፍላጎቱን የማሟላት ግዴታቸውን የሚወጡ ጋዜጠኞች ያስፈልጉታል፤ ሥልጣናትን የሚጠሉና የሚገዳደሩ፣ “ፍትሕ ያለችው የፍትሕ መጽሔት ገጾች ላይ ብቻ ነው፤” ብለው የሚያምኑና የጨቋኝ ብሔርና የጭቁን ብሔሮች መደብ እየተፈጠረ ነው ብለው የሚሰጉት ዜጎችም በነተመስገን ጽሁፎች አንጀታቸውን አርሰው ትራሳቸውን ይገናኛሉና:: ሲጠቃለል ከ“ፈተና ወደ ፍተላ” ላይ የተጻፈው ሁሉ እውነት ከሆነ አቢቹ ማርሽ መቀየርና ሱባኤ መግባት ያለባቸው እራሳቸው ናቸው ያስብላል፡፡
የትላንት ጓዶቻቸውን ጢም ባለውና የሰማያዊ ቀለም ሪፎርም የደረሰው የኢሠፓ ፓርቲ አዳራሽ ውስጥ በህዝብ ፊት ያን ያክል የመናገሩንና የራሳቸውን ፓርቲ ገበና አውጥቶ የመዘርገፍ ወስዋስ የሚፈታተናቸው ከሆነ ከባህሩ ወለል እይታ በታች ያለውን የበረዶ ቋጥኝ ግዝፈት ምን እንደሚያክል ገምቶ አቅጣጫ መቀየስ የሚችል ሰው ምንኛ አዋቂ ነው ሊያስብል ይችላል፡፡
መንግስት በመጽሔቱ ውስጥ ወደ ተነሱት ችግሮች ዞር ብሎ ራሱን ከማየት በላይ ወደ ተመስገን ደሳለኝ ዞሮ እንደነ ዘመነ-መለስ “የ…..  ጠላት ነው፤” ብሎና ፈርጆ የበለጠ ጊዜና ጉልበት በሱ ላይ የሚያጠፋ ከሆነ መስከረም ላይ ለብልጽግና ካርዳቸውን ያስገቡ ሁሉ ምንኛ እንደሚቆጩ ማሰቡ ሐዘን ይጨምራል፡፡ እንደነ አሜሪካ አይነት ዲሞክራሲ ቢሆን “ቆይ ብቻ የዛሬ አራት አመት ያገኛን፤” ተብሎ ይታለፍ ነበር፤ ዳሩ ግን አለመደብንምና እዛ ድረስስ ቆይተን ካርዳችንን የምንጠቀምበት መድረክ መኖሩንስ ማን ያውቃል?
ትግሉ መልኩን ከለወጠ ሪፎርሙ መስራቾቹንና አቀንቃኞቹን እየበላ ሲሄድ የአንቲ-ቴሲሱን ክፍተት ሚና የሚጫወት መፈጠሩ አይቀርም፤ አለምም ይህን መከልከል የቻለ መንግስት አይታ አታውቅም፤ “የኢትዮጵያ ሕዝብ መከራ አያልቅም፤” ብለው ለሚያዝኑ አልቃሾቿ የምስራችን፣ ለቆዘሙት ቀና ማለትን፣ ተስፋ ለቆረጡት ብርታትን፣ ላዘኑት መጽናናትን፣ ለተጠሙት ለውጥን ይዞ መዳን ከሌላ መምጣቱን ተስፋ ያደረገ ሁሉ የሚናፍቀው ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ታሪክም ደጋግሞ ሲጽፈው የኖረ ምዕራፍ ነው፡፡ ትግሉ ኢላማውንና አላማውን፣ መሪ ተዋናዮችንና ኮ-ስታሮችን ይቀይር እንደሆነ እንጂ መቀጠሉ አይቀርም፤
“አቦ ትግል ደስ ይላል እኮ፣ ትግል ናፈቀኝ፤” የሚሉ የትግል ባለተራዎች ከጥቅም ባለተራዎች ጋር ለመፋለም እጅጌያቸውን መሰብሰባቸውና መዳፋቸውን ማተሻሸታቸው ግድ ነው፡፡ አገራችን ከቀጣዩ የትግል ተረኝነትና የጥቅም ተረኝነት ግብግብ ነጻ እስክትወጣ ድረስ ቅራኔው ይቀጥላል፤ አይቀርም፤ ችግር ካለ ሁሌም ትግል አለ፡፡ ቅራኔ ካለ ነዳጅ አለ፤ ትግሉ ቀለም እንጂ ደም አፋሳሽ እንዳይሆን ግን የጸሎት ጓዶች ቢበረቱ መልካም ነው፡፡ ስንት ጊዜ መሪዎችን ማሳደደስ ይሆንብናል?
የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ አይቆርጥም፤ ተስፋ መቁረጥ ራሱ ተስፋ ቆርጦ እስኪሄድ ድረስ ግትር የሚል ሕዝብ ነው፡፡ ተረኝነት መልኳን ቀይራ፣ ጉራማይሌ ለብሳና ሽክ ብላ፣ ተኳኩላ ስትመጣም አረማመዷን ከሩቅ ያውቀዋል፤ “መጣች ደግሞ ይቺ መናጢ፤” ብሎ ዝግጅቱን ይጀምራል እንጂ የሚሸሽላት አይደለም፡፡ ትግሉ ከሷ ጋር መሆኑ ቀርቶ ከዋናዎቹ መሰረታዊ
ችግሮቻችንና እና ጉስቁልናችን ጋር ቢሆን መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን “በሱ ዘመን ምድሪቱም ከጦርነት አረፈች፤” የሚባልለት ሰውና ስርዓት እስኪመጣ ድረስ መፋተጉና መፈታተጉ አይቀርም፤ እነዚህ ጭቆናና ጭካኔ ያደነደናቸው መዳፎችስ ምን ምርጫ ይኖራቸዋል?
ነገስታት የናፖሊየን ቦናፓርቴን “ጠላትህ ሲሳሳት አትምከረው፤ ድልህን ታፈጥናለህ፤” ማለቱን ሰምተውና ተረድተውት ከሆነ የአባ ጻፈውን ትችቶች “ስታርባክስ ቁጭ ብለው” ፍትሕን ከሚያዳምጡት በላይ የሚናፍቁት እነሱ በሆኑ ነበር፤ ተመስገንም የማንም ግለሰብም ብሔርም ጠላት አለመሆኑን ተገንዝበው እሱም ሌሎች የሙያ አጋሮቹም የበለጠ እንዲነግሯቸው በቃተቱ ነበር፡፡ ገጾቹንም ጥርሳቸውን እያፋጩ ሳይሆን “ዛሬስ ምን እንማራለን?” ብለው በናፍቆት ይጠባበቁ ነበር፤ ነገር ግን ሌቦች የሚያመልጣቸው የጥቅም ቦታ ያለው የቦርድ አባልነትና ሌላ ሥልጣን እንጂ የነተመስገን ትችቶችን መቼ ከዕቁብ ቢቆጥሩ፤ በብዕር ካልተነጋገርንና በሃሳብ ካልተወቃቀስንና ካልተገነባባን በአፈሙዝ፣ በሜንጫና በእርግጫ መፈላለጋችን አይቀርም፤ እንዲያም ሲል ራሱ አባ ጻፈው እንዳለው “አልማዝን አይቼ አልማዝን ባያት፤”ን ስንሰማ በግርምት መስመጣችን አይቀርም፡፡
Filed in: Amharic